የሱስ መዘዝ

በ1977 ዓ.ም የተወለደችዋ ለይላ ሰዒድ፤ ስታድግ መልኳ የሚያጓጓ እና እጅግ የሚያምር፤ ተክለ ሰውነቷም ሁሉን የሚያሸብር፤ ያያት ሁሉ የሚመኛት ዓይነት ውብ ልጃገረድ ነበረች። ሊያገባት የማይፈልግ በአካባቢዋ የማያንዣብብ ወንድ አልነበረም። ለይላ ሰዒድ ግን ይህን ሁሉ ችላ ብላ በትምህርቷ ገፋች። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ጨርሳ ኮሌጅ ገብታ እስከ ዲፕሎማ ተምራለች።

ከልጅነቷ ጀምሮ ታታሪ ናት። ሠርታ ሀብት በማግኘት የተንደላቀቀ ኑሮን ለመምራት ትመኛለች። ነገር ግን ይህንን የምትፈልገውን ኑሮ ለማግኘት ተቀጥሮ በመሥራት ፍፁም ሊሳካ እንደማይችል አረጋግጣለች። ሃብታም ማግባትም አዋጭ አይሆንም ብላ ገምታለች። ነገር ግን ለመነገድም በቂ የመነሻ ገንዘብ የላትም። ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀጣሪ ሆኖ መሥራትም የተሻለ ሕይወትን ለመምራት የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህ የተሻለ ያለችውን አማራጭ ወሰደች። በሠራችው ልክ ማግኘት ትፈልጋለችና ወደ የመን አቀናች።

በየመን ቆይታዋም ሥራ አገኘች። ሥራ ወዳድ በመሆኗ ገንዘብ መሰብሰብ ቻለች። በአጋጣሚ ከሀገሯ ልጅ ከመሐመድ ፈረጃ ምራ ጋር በ1997 ዓ.ም በፍቅር ወደቀች። የኑሮ ዕድገት ከትዳር ጋር ሲጣመር ምርጥ ይሆናል ብላ፤ ከመሐመድ ጋር ብዙም ሳይቆዩ በዛው ዓመት ጋብቻ ፈፀሙ። ‹‹ በሰው ሀገር ከመኖር ይልቅ በደንብ ከሰራን ኢትዮጵያም ቢሆን ተረዳድተን እናድጋለን። ›› ብለው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ። እንደተመለሱም በልጅ ተባረኩ።

ወይዘሮ ለይላ እንደተናገረችው፤ የመጀመሪያ ልጇን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ ግን የመሐመድ ፀባይ ተቀየረ። ምግብ እንዲበላ የእጅ ውሃ ሲቀርብ ውሃው ቀዘቀዘኝ ብሎ ሰው ካልገደልኩ ማለት ጀመረ። ከቤት ሠራተኛ አልፎ ለይላን መስደብ እና ማዋረድ ጀመረ። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ልጅ ብትወልድም ፀባዩ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት በጣም ተቆጪ እየሆነ ቀጠለ።

የተቀየረው አባወራ

ሰርቶ ከማምጣት ይልቅ ቀኑን ሙሉ በቤት ውስጥ ተኝቶ መዋል ወይም የተለያዩ መቃሚያ ቤቶች በመሔድ ጫት መቃም የሕይወቱ ዋነኛ ተግባር አደረገው። ቆሞ የሚሔደውም፣ የሚኖረውም፣ የሚያስበውም ስለጫት ብቻ ሆነ። ወይዘሮ ለይላ ‹‹ከቀን ወደ ቀን ሕይወቱ ይቀይራል፤ ወደ ራሱ ይመለሳል። ›› ብላ ብትጠብቅም አልሆነም። ለመፋታት ብትፈልግም፤ በተደጋጋሚ ሽማግሌ ተሰብስቦ ቢመከርም ራሱን ለማሻሻል ምሎ ተገዝቶ ተመልሶ ለቤተሰቦቹ የማይመች ለትዳሩ መሆን የማይችል የማይረባ ሰው ሆነባት። ወይዘሮ ለይላ ቆርጣ ልትተው እና ልትፈታው ፈለገች። ነገር ግን ቤተሰቦቿም አልፈቀዱላትም።

ከቤተሰቧቿ ውጭ ከመሆን ብላ መሐመድን ራሷ እያበላች፣ እየተሰደበች፣ እየተደበደበች ቻለችው። ሲከፋት እያለቀሰች ልጆቿን ስታይ ደግሞ እየተደሰተች እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ አምስት ሴት ልጆችን ወለደች። የእርሷ ብቻ ሳይሆን የልጆቿም ሕይወት አስጨናቂ ሆነባት። በተደጋጋሚ ስድብ እና ዛቻ አልፎ ተርፎ ዱላም የአባወራነት ግዴታው አስመስሎ ሕይወቷን በምሬት እንድትገፋ አስገደዳት።

ልጆቻቸው የአባታቸው ዛቻም ሆነ ስድብ ተመልካች ከመሆን ባለፈ፤ እነርሱም በአባታቸው መሰደብ እና መደብደብ የየዕለት ግዴታ ሆነባቸው። ገና በልጅነት ዕድሜያቸው አባታቸው እናታቸውን አፀያፊ ስድብ እየሰደበ ሲደበድብ ማየት፤ በተደጋጋሚ አንቆ ሊገድላት እንደሚፈልግ ሲናገር፤ ልጆች እየሰሙ ከመፍራት አልፈው በስጋት ውስጥ እየተሸማቀቁ ለመኖር ተገደዱ።

መሐመድ ሲፈልግ ተኝቶ ፤ ካልሆነም ሲዞር ውሎ መኪናውን አሽከርክሮ ቤቱ ገብቶ በሠራተኛ እጁን ታጥቦ የፈለገውን የላመ እና ያማረ ተመግቦ ቢኖርም፤ ደስታ ከእርሱ ዘንድ አልነበረም። አልፎ ተርፎ አንዳንድ ጊዜ እቃ እስከ መስበር የደረሰ ብስጭት ውስጥ ይገባል። የቤት ሠራተኛዋ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ላይ እንደሰፈረው፤ ‹‹መሐመድ ቀኑን ሙሉ ተኝቶ የሚውል ሲሆን፤ ሲመሽ ጫት ይቅማል። ሌሊቱንም ሺሻ እያጨሰ ያድራል። ››

የቤት ሠራተኛዋ፤ በየቀኑ ለይላን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቿንም ጭምር የሚነኩ ስድቦችን ከመስደብ አልፎ ይዝትባት እንደነበር አንዳንዴም እንደሚደበድባት ተናግራለች። የቤት ሠራተኛዋ ስትገለፅ፤ በዛ ቤት በሰላም ውሎ ማደር ከባድ ነው። አንዳንድ ቀን ማታ አንዳንድ ቀን ደግሞ ጠዋት መሐመድ ይረብሻል። አንዳንዴ የቤት እቃ የሚሰብር ሲሆን፤ አንድ ቀን ጠዋት ተነስቶ 55 ኢንች ቲቪ እና ሙሉ የብፌ ዕቃውን በሙሉ ሰባብሮ መኪናውን አስነስቶ እንደወጣ ታስታውሳለች።

ምንም እንኳ በዛ አጋጣሚ ከወጣ በኋላ ተጣልተው ሌላ ቦታ መኖር መጀመሩን አስታውሳ፤ በመጨረሻም ክረምት አልፎ ልጆች ትምህርት ሲጀምሩ ‹‹ልጆች ትምህርት ቤት ላድረስ›› ብሎ መመላለስ ጀምሮ በድጋሚ ወደ ቤት እንደተመለሰ ተናግራለች። ልጆቹ አባታቸውን በጣም እንደሚፈሩ እና በተደጋጋሚ ስለሚቆጣቸው ምግብ እንኳ እርሱ እያየ እንደማትሰጣቸው ገልፃለች።

የልጅ ምስክርነት

በመዝገቡ ሠፍሮ እንዳገኘነው ሕፃን ዘቢባ መሐመድ በመጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በሥነ ልቦና ባለሙያ ታግዛ በሰጠችው የምስክርነት ቃል አባቷ እናቷን በተደጋጋሚ ከመደብደብ አልፎ እነርሱም ላይ ጥቃት ይሰነዝር እንደነበር ተናግራለች። የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላት ዘቢባ እንደተናገረችው፤ በተደጋጋሚ የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለምሳሌ ለምን ቁርሃን አልቀራሽም እና ሌሎችንም ሰበቦች እየፈለገ ሽንት መሽኛዋን ይቆነጥጣት ነበር። በተደጋጋሚ ሲነካካትም ያመኛል ስትለው፤ ‹‹ለእናትሽ ትነግሪና እገልሻለሁ›› ይላት እንደነበር ገልፃለች።

ስቃዩ ሲበረታባት ግን ለመንትያ እህቷ አለውያ ነግራት እንደነበር ገልፃለች። እህቷም ‹‹ለእናታችን መናገር አለብን›› ብላ እህቷ ብትፈራም እርሷ መናገሯ እና እናቷ ስትጠይቃት አባቷ ምን ያደርጋት እንደነበር መዘርዘሯን ገልፃለች።

የ38 ዓመት ሙሉ ሴት የሆነችዋ ለይላ፤ ቤተል አደባባይ አካባቢ የሞቀ የምንጣፍ ሱቅ ከፍታ ታዋቂነትን ብታተርፍም፤ የሥራዋን ስኬት ያህል ልጆቿን በቤት ውስጥ የሚደርስባቸውን ግፍ ለማየት ዓይኗን አልገለፀችም። እናም ልጆቿ ብዙ ዋጋ ከፈሉ። ወይዘሮ ለይላ በሰጠችው ቃል ላይ ልጇ አባቷ መሐመድ በሽማግሌ ታርቆ ሊገባ እንደሆነ ለእናቷ ትጠይቃለች። ሊይላ ለልጇ ‹‹አይ አይመለስም›› ስትላት፤ እርሷም እንዲመለስ እንደማትፈልግ እና ለይላ ቀድማ ተረድታ ባትጠይቃቸውም ሁለቱም ልጆቿ አባታቸው በተደጋጋሚ ሲፈፅም የነበረውን በደል እህትማማቾቹ ለእናታቸው አስረዱ።

የትዳር መጨረሻ

ወይዘሮ ለይላ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ወይራ ሰፈር አርሴማ ቤተክርስቲያን አካባቢ ወደሚገኘው ቤቷ ከመምጣቷ በፊት፤ የቤት ሠራተኛዋ አስቤዛ ገዝታ እንድትመጣ በስልክ ደውላ ነገረቻት። ወይዘሮ ለይላ ለልጆቿ እና ለባለቤቷ ለመላው ቤተሰቡ ያስፈልጋል ያለችውን ሸምታ ቤት ስትደርስ ሠራተኛዋ የመኪና በር ከፈተች። ወይዘሮ ለይላ መኪናውን አሽከርክራ ስታስገባ፤ ከኋላዋ መሐመድም የራሱን መኪና ይዞ ተከትሎ ገባ። ሠራተኛዋ ሁለቱም ከገቡ በኋላ የከፈተችውን በር ዘግታ ወደ ለይላ ስትጠጋ ፤ ዕቃውን ከማውረድሽ በፊት የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ አለቻት። የቤት ሠራተኛዋ ወደ ቤት ስትገባ መሐመድ የመኪናውን በር ከፍቶ በመውረድ ወደ ለይላ መኪና ሄደ። የቤት ሠራተኛዋ ይዛላት የመጣችውን ውሃ አስቀድሞ ነጥቆ እርሱ ጠጣው።

ተንደርድሮ ወደ ቤት በመግባት ልጆቹ ክፍል ገብቶ ከመደርደሪያ ላይ ከተር ይዞ ወረደ። ያ ሁሉ ሲሆን፤ ለይላ ከመኪናው አልወረደችም ነበር። ስለት ነገር ይዞ መምጣቱን ያየችው የቤት ሠራተኛ ሮጣ ወደ ቤት በመግባት ልጆቹን ይዛ የቤቱን የውስጥ ደረጃውን በመጠቀም የፎቁ አናት ላይ ሆና ወደ ታች መመልከት ጀመረች። ለይላ እዛው መኪናዋ ላይ እያለች መሐመድ ለይላን ፊቷ ላይ ወጋት፤ እንዳትጮህ በግራ እጁ አፏን አፍኖ በቀኝ እጁ መውጋቱን ቀጠለ።

ፊቷን እና ትከሻዋን እየደጋገመ ከወጋት በኋላ ራሷን ለማዳን በሩን ከፍታ ልትወጣ ስትል፤ በሩን ከፍቶ ፀጉሯን እየጎተተ ከመኪና ላይ አወረዳት። በእግሩ ጭንቅላቷን ደጋግሞ ከመርገጥ አልፎ በተደጋጋሚ በያዘው ከተር ጀርባዋን ሲወጋት እንደነበር የቤት ሠራተኛዋ የሰጠችው የምስክርነት ቃል ያመለክታል።

‹‹ለእከሌ ገንዘብ ሰጥተሻል እመኚ›› እያለ ይደበድባት እንደነበር የተናገረችዋ የቤት ሠራተኛ፤ ሌላ ሰው ልታገቢ ነው ብሎ፤ ሲናገር እንደነበርም ገልፃለች። በመጨረሻም የለይላ ደም መሬት ላይ ሲፈስ መኪናውን አስነስቶ ጠፋ ብላለች። ይህ ሁሉ በደል ሲፈፀምባት የቆየችው ወይዘሮ ለይላ፤ በዛው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከምትኖርበት ቤት ሳትወጣ ግፉ ሲያንገሸገሻት ክስ መሠረተች።

የተመሠረተውን ክስ ተከትሎ በተካሔደው ምርመራ አቶ መሐመድ ድርጊቱን ሲፈፅም እንደቆየ፤ ሚስቱ ወይዘሮ ለይላ ላይ የግድያ ሙከራ አድርጓል ለማለት የሚያስችል መረጃ በመገኘቱ ድርጊቱን መፈፀሙ ተረጋገጠ። ከምስክሮች ቃል ባለፈ የሐኪም ማስረጃም ቀረበበት። ልጆቹም በሥነ ልቦና ባለሞያ በመመርመር እና የሐኪም ማስረጃም በማቅረብ በልጆቹም ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈፅም እንደነበር ታወቀ። አቶ መሐመድ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ ተረጋገጠ።

አቶ መሐመድ ድርጊቱን ፈፅሞ ቢጠፋም በፖሊስ ብርቱ ክትትል የተያዘ ሲሆን፤ ‹‹ድርጊቱን ፈፅመሃል ወይስ አልፈፀምክም?›› በማለት ከመርማሪ ፖሊስ የእምነት ክህደት ቃል እንዲስጥ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ የፖሊስ የምርመራ ቡድን ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ያለውን መረጃ አቀረበ። የፌዴራል ዐቃቤ ሕግም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ተከሳሽ መሐመድ ፈረጃ ጥፋተኛ ነው ብሎ ብይን እንዲሰጥ እና የፍርድ ውሳኔም እንዲተላለፍበት ጠየቀ። የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ ተከትሎ በዳኞች ፊት ፍርድ ቤት የተለያዩ ማስረጃዎች ቀርበው ክርክር ተካሔደ።

                                                                                                      – ውሳኔ

በመጨረሻም በከሳሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ መሐመድ ፈረጃ ምራ መካከል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር በመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት መቋጫ አገኘ። ተከሳሽ የተከሰሰበትን ሰው የመግደል ሙከራ ወንጀል መፈፀሙን ማስረጃዎች ተስምተው በበቂ ያስረዱ በመሆናቸው፤ ፍርድ ቤቱ መሐመድ ፈረጃ ላይ የቀረበው ሰው የመግደል ሙከራ ወንጀል ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ወንጀል ፈፃሚውን ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት በ11 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You