ወረርሽኞችን የመከላከልና የመቆጣጠር ጥረት

ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተከስተዋል። በኢትዮጵያም በሰው ሠራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች በተለይም በግጭቶች፣ በድርቅ፣ በጎርፍና ሌሎችም ምክንያቶች በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ወርሽኞች በሀገሪቱ ተቀስቀሰዋል። ከነዚህ ወረርሽኞች ውስጥ ደግሞ ወባ፣ ኮሌራና ኩፍኝ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

እነዚህን ወረርሽኞች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጤና ሚንስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም በወረርሽኞቹ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የሞት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ችሏል። ወረርሽኞች ሲከሰቱ በፍጥነት ምላሽ በመስጠት፣ መልሶ በማቋቋምና ፈጣን የቅኝት ስራዎች በመስራት ወረርሽኞቹ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ተችሏል።

የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደሚናገሩት፣ ባለፉት አመታት አለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ታይቷል። ይህንኑ ተከትሎ በተለይ በአፍካ አህጉር የወረርሽኞች ተጋላጭነት ጨምሯል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የወባ ወረርሽኝ ነው። የወባ ወረርሽኝ እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2023 ድረስ ባሉት አመታት አፍሪካ ለብቻዋ ከ90 ከመቶ በላይ በበሽታው ተጋላጭነትና በሞት ቁጥር ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው አህጉሮች ውስጥ ቀዳሚዋ አድርጓታል። ባለፉት ሶስት አመታት ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ተፈጥሯዊና ተፍጥሯዊ ካልሆኑ ተጋላጭነቶች በተለይ ኮቪድ ካመጣቸው ጫናዎች አንፃር እ.ኤ.አ በ2021 እና 2022 ወደ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ አዲስ ህሙማን መገኘታቸውን አለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለወባ ህሙማን መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ። ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። በኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጡ እንዳለ ሆኖ ሀገሪቱ ያላት መልከዓ ምድር በተለይ ደግም 69 ከመቶ ያህሉ ህዝብ ለወባ አጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሚገኝ መሆኑ ለወባ ስርጭት ከፍ ማለት አስተዋፅኦ አድርጓል። በባለፉት የዝናብ ወራት ከበፊቱ በተለየ መልኩ የወባ ተጋላጭነትን ጨምረዋል።

ብዙ ግዜ የመጀመሪያው የክረምት ወር አልፎ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት ውስጥ ነው ጫናውም ቁጥሩም ይጨምራል ተብሎ የሚጠበቀው። ከዛ በኋላ ደግሞ የበልግ ዝናብን ተከትሎ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ድረስ የወባ በሽታ ስርጭት የመጨመር አዝማሚያ ያሳያል። ስለዚህ በነዚህ የዝናብ ወቅት ብዙ የቁጥጥር ስራዎች ካልተሰሩና የበሽታ መከላከል አቅምን ማጎልበት ካልተቻለ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥርና ለሞት ተጋላጭ የሚሆኑ ወገኖች ቁጥር ይጨምራል። ከዚህ አኳያም ነው ጤና ሚንስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከክልል ጤና ቢሮዎች እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየው።

ጤና ሚንስትሯ እንደሚሉት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የቁጥጥርና መከላከል ስራው ጠንካራ በመሆኑ በኢትዮጵያ የወባ ስርጭት ዝቅተኛ ነበር። ይሁንና የማህበረሰብ የመከላከል ስራው ላይ መዘናጋት በተለይ ለወባ መከላከል ስራ የሚያግዙ ግብአቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ከአየር ንበርት ለውጥ ቀጥሎ ለወባ ስርጭት በድጋሚ ማገርሸት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በተለይ በዚህ አንድ አመት ውስጥ የወባ ጫና ከፍ ብሎ ታይቷል። በነዚሁ መነሻነት ለወባ ተጋላጭ የሆኑ 220 ወረዳዎች ተለይተው በ10 ክልሎች ውስጥ ጠንካራ የምልከታ፣ ክትትልና ቅኝት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ይኸው ስራ በባለፉት ሳምንታትና በአሁን ሳምንት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከእያንዳንዱ ለድንገተኛ ምላሽ ከሚያገለግሉ ተቋማት ውስጥ በመሆን ምልከተታዎችን፣ ቅኝቶችንና ቁጥሮችን መለየት ላይ ስራዎች በስፋትና በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰሩ ነው። ከእያንዳንዱ ወረዳዎች በመነሳት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ከጤና ጣቢያ አንስቶ እስከሆስፒታሎች ድረስ ቅኝቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በየሳምንቱ ከክልል አመራሮች በተለይ ከክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎችና በቅኝት ስራ ላይ እገዛ ከሚያደርጉ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ምን ያህል ታካሚዎችን ማስተናገድ እንደተቻለ፣ ምን አይነት የመከላከል ስራዎች እንደተሰሩና ህብረተሰቡ ግብአቶችን በአግባቡ እየተጠቀሙ እንደሆነ ቅኝት ማድረግ፣ የማስተማርና የማነቃቃት፣ የአጎበሮች ስርጭትና የኬሚካል መድሃኒት ርጭቶች ምልከታዎች ተደርገዋል።

ለክልል አመራሮችም በጉዳዩ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲያገኙ ተደርጓል። የክልል ሃላፊዎች በሙሉ ስራውን በሃላፊነት እንዲገመግሙና እንዲያዩ እንዲሁም የሚያዩትን ክፍተት በትብብር እንዲሞሉ ስራዎች ተሰርተዋል። ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰበ ክፍሎችን አክሞ ማዳን ዋነኛ ሀላፊነት በመሆኑ በተለይ ከመድሃኒት አቅርቦት አገልግሎትና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን አስፈላጊ የወባ መከላከል ግብአቶች ወደ ህብረተሰቡ፣ መድሃኒት ቤቶችና ሆስፒታሎች የማድረስ ስራዎች ተከናውነዋል።

ሚንስትሯ እንደሚያብራሩት የወባ በሽታን ጫና ለማወቅ በርካታ ምልከታዎች ተደርገዋል። ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከ700 ሺ በላይ ህሙማን ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። የቅኝት ስራውን እለታዊ በማድረግ ምን ያህል ታካሚዎች የህክምና መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጋቸው በመለየት የመድሃኒት አቅርቦቱን ለመጨመር ብዙ ስራ ተሰርቷል። ለዛም ነው ከባለፈው ቁጥር በበለጠ የወባ መድሃኒቶች ተገዝተው ለእያንዳንዱ ክልሎች እንዲሰራጭ ተደርጓል። ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህሙማንን ማከም የሚያስችል የፀረ ወባ መድሃኒቶች ወደሃገር ገብተዋል። ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፈጣን የመመርመሪያ ቋቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። ከህክምና ግበአቶችና መድሃኒት አቅርቦት በተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም በስፋት ተከናውነዋል።

በ2015 ዓ.ም ብቻ ከ19 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አጎበሮች እንዲሰራጩ ተደርጓል። ይህም አንድ አጎበር እስከ ሶስት አመት ድረስ እንደሚያገለግል ታሳቢ በማድረግ ነው። ባጠቃላይ ባለፉት ሶስት አመታት 30 ሚሊዮን የሚሆኑ አጎበሮች ተሰራጭተዋል። ባለፈው ሳምንት ብቻ 551 ሺ የሚሆኑ አጎበሮች እንዲሰራጩ ተደርጓል። ተጨማሪ አጎበሮችን ማምጣት ብቻውን አገልግሎት መሆን አይችልም። ስለዚህ ህብረተሰቡ የመከላከል ስራውን አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል። ማህበረሰቡ አጎበሮችን ለምን አላማና እንዴት እየተጠቀመባቸው እንደሆነ መፈተሽ ያስፈልጋል። በዚሁ መነሻነት በተሰራ ጥናት የህብረተሰቡ አጎበሮችን በአግባቡ የመጠቀም ዝንባሌ ከ50 በመቶ በታች ሆኖ ተገኝቷል።

የአካባቢ ቁጥጥሮች ላይ የሚካሄዱ የኬሚካል ርጭቶችም ዋነኛ ስራዎች ናቸው። በዚህም ባለፉት ሳምንታት ብቻ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቤቶችን በኬሚካል እንዲረጩ ተደርጓል። ለርጭት የሚያግዙ ግብአቶችም ለክልልሎች እንዲደርሱ ሆኗል። ለዚህ ስራ ደግሞ የክልል ሃላፊዎች ትልቅ ትብብር አድርገዋል። በርካታ ህሙማንን ማከም የሚያስችሉ መድሃኒቶችም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል። ካለፈው ስደስት ወር ወዲህ ደግሞ ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ የወባ መድሃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ለወረርሽኙ ጠንካራ የሆነ ምላሽ ለመስጠት በሚያስፈልጉ ቦታዎች ላይ ተሰራጭተዋል።

ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ግዚያት ሊደርሱ የሚችሉትን ችግሮች ለመከላከልና ጠንክሮ ስራዎችን ለማከናወን ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ማዳፈንና ማጥፋት ያስፈልጋል። በዚሁ ዙሪያ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ስራዎችን መስራት ተጀምሯል። የበለጠ ግን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ስራው የአንድ ወቅት ብቻ መሆን የለበትም። በተለይ የጤና ኤክስተንሽን ሰራተኞችና የጤና ባለሞያዎች ተባብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ጤና ተቋማትም ከሳምንት እስከ ሳምንት ለሀያ አራት ሰአታት ለማህረሰቡ ክፍት ሆነው አገከልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል።

ሚንስትሯ እንደሚገልፁት የኮሌራ ወረርሽኝ ምላሽን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብዙ ግዜ ከንፅህና አጠባበቅ ችግር ጋር በተያያዘ የኮሌራ በሽታ ተጋላጭነት ወቅቶች አሉ። ከነዚህ ወቅቶች ደግሞ አንዱ የክረምት ወቅት ነው። በዚህ ክረምት ወቅት ኮሌራን ለመከላከል ጠንካራ ስራ መስራት ያስገፈልጋል። በተለይ በ2016 ዓ.ም በወረርሽኝ መልክ ኮሌራ ከተከሰተ በኋላ 152 ወረዳዎችን ተለይተው በሶማለየ ክልል በመገኘት የኮሌራ ወረርሽኝን መግታትና መቆጣጠር እንደ ዋና ስራ ተደርጎ ንቅናቄ ተጀምሯል። ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላ ባለፉት ሰባት ወራት ከ152 ወረዳዎች ውስጥ በ5 ክልልሎችና በ109 ወረዳዎች ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝ ሙለ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል። አሁን ካሉ አምስት ክልሎች ውስጥ በ43 ወረዳዎች ላይ ክትትሉ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህ ዙሪያ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ ዋነኛው ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ግዜ የሚሰሩት ጊዚያዊ የማከሚያ ማእከላት ናቸው። በነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ባለፉት ወራቶች ወደ 904 የሚሆኑ ጊዚያዊ የማከሚያ ማእከላት ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ማእከላቱ ቶሎ ምላሽ ለመስተትም አግዘዋል። በተለይ ደግሞ የውሃ ጋኖችን በኬሚካል የማከም ስራ ከአጋር ድርጅቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተሰርቷል። ይህንን ስራ ግን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የመፀዳጃ ቤቶችንና እጅ መታጠቢያዎችን ማዘጋጀት ይገባል። በንጽህና አያያዝና አጠባበቅ እንዲሁም በምግብ አበሳሰል ዘሪያ ለማህረሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል።

በተለይ ወረርሽኞች አሉ ከሚባሉበት ቦታዎች በተጨማሪ ሌሎችም ቦታዎች ላይ ፅዳትን መጠበቅ፣ ጥሬ ምግቦችንና ፍራፍሬዎችን በጥንቃቄ መመገብ ላይ ይበልጥ መስራት ያስፈልጋል። ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት ይሰራቸው የነበሩ ነገሮችን አጠናክሮ ከቀጠለ አሁንም ቢሆን ይህን ታሪክ ማድረግ ይቻላል።

የኩፍኝ በሽታን በሚመለከት በተለያዩ ግዚያት መግለጫዎች ተሰጥተዋል። በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ ወደ 442 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቷል ከተባለ በኋላ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ዘመቻ ተደርጓል። ዘመቻው ተደርጎ ቁጥጥር ከተደረገ በኋላ 422 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ተችሏል። በተለይ ከጥር ወር ወዲህ ለኩፍኝ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ያሉ ህፃናት እንዴት አድርጎ መያዝና መከተብ እንደሚቻልና ያልተከተቡ ህፃናትን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ዋናው ስራ ስለነበረ በ ‹‹big catch up›› ዘመቻ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችና ንቅናቄዎች ተደርገዋል። ክልሎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዚህ ላይ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል።

በዚህም ከመደበኛ ክትባት በተጨማሪ ለዚህ የሚያግዙ በዘመቻ የሚሰሩ የክትባት ስራዎች ተካሂደዋል። በዚህ የማካካሻ ክትባት ዘመቻ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ምንም አይነት ክትባት ያልወሰዱ 600 ሺ የሚሆኑ ህፃናትን መከተብ ተችሏል። ይህ ትልቅ ስራ ነው፤ ምክንያቱም የኩፍኝ በሽታት መከላከል ብቻ ሳይሆን ሌሎች በክትባት መኪላከል የሚቻሉ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ ግብአት በመሆኑ ነው።

በ22 ወረዳዎች ላይ የኩፍኝ ቅኝት አሁንም ቀጥሏል። መረጃዎችም እየተሰባሰቡ ነው። ህፃናት መድሃኒቶችን እንዲያገኝና ታክሞ መዳን እንዲችሉ ስረአቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ተደርገዋል። በኩፍኝ የተያዙ ህፃናት ደግሞ አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ የህክምና ግብአቶችን ማስባሰብ ስራዎች ተከናውነዋል። በሽታውንም ለመግታት እንዲያግዙ ባጠቃላይ በ8 ክልሎችና በ58 ወረዳዎች ላይ ከስደስት ወር አስከ አስር አመት ያሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የኩፍኝ ክትባት ተሰጥቷቸዋል። ወደ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ከስደስት ወር አስከ አስር አመት የሚደርሱ ህፃናት በክትባት ዘመቻ ውስጥ በማድረግ እንዲከተቡ ተደርጓል። አሁን ደግሞ ተጨማሪ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህፃናትን ለመከተብ እየተሰራ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You