የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያሳየን ያለውን ቁርጠኛ ፍላጎትና ጥረት ተከትሎ አሉታዊ አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች ተፈጥረው ተመልክተናል። ከእነዚህ ውስጥ ታሪካዊ ባላንበጣዎቻችን ይገኙበታል። ብሄራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅልን ይህንን አጀንዳ የአንድ ሰሞን ወሬ አድርገው የተመለከቱት አካላት አትዮጵያ ለእቅዱ መሬት መንካት እየሰራች ያለውን ተግባራዊ ስራ ወደ እውነታው እየቀረበ መሄድ ሲረዱ ሂደቱን ለማክሸፍ አያሌ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን እየተመለከትንና እያደመጥን የምንገኘውም ይህንኑ ነው። የባህር በር የማግኘት ፍላጎታችን የመጀመሪያው ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መሆኑን የተረዱ አይመስሉም። የትኛውም ሀገር ብሄራዊ ጥቅሙን በሚያስከብር መልኩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የራሱን አቋም ሊይዝ እንደሚችልም አልተገነዘቡም። በኢትዮጵያ በኩል የተያዘው አቋም ግን ይህንኑ የብሄራዊ ጥቅም መርህ የሚያመለክት ነው። በዓለም ላይ የተከሰቱ ምሳሌዎችን ብንመለከት የምናገኘው ሀቅም ይሄው ነው።
ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ የባህር በር (መተንፈሻ) ብታገኝ እድገትና ልማት ከማፋጠን የተለየ አጀንዳ እንደሌላት እያወቁ አሳሳች ፕሮፓጋንዳን ከማሰራጨት በጥቅማችን ደጃፍ ላይ ጋሬጣ ሆኖ ከመቆም አላገዳቸውም። ኢትዮጵያ በገልፍ ኦፍ ኤደንና በቀይ ባህር ላይ ያላትን ሚና ማስፋትና የንግድ ሰንሰለቱን ያለስጋት መቀላቀል አንደምትሻ ተደጋጋሚ በሆነ መልኩ ግልፅ አድርጋለች።
የአንዳንድ ሀገራት በጉዳዩ ላይ እያሳዩት ያለው ፀባይም ሆነ አቋም ‹‹ከፍየሏ›› በላይ እንደሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል። የዚህ አላማ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም መፃረርና እድገቷን የመግታት ድብቅ ፍላጎት ማሳያ ነው። ይህንን ጉዳይ መግታትና በተመሳሳይ ግልፅ የኢትዮጵያን አቋም ማሳየት ይገባል።
‹‹ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል›› እንደሚለው ብሂል ኢትዮጵያም በባህር በር ዙሪያ አማራጭ መንገዶችን የመፈለግ ሚና እንደቀጠለ ነው። ከሁሉ በላይ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩን የሚመለከትበት እይታ ማስተካከል ስለሚገባና ከሚነዛው ውዥንብር መከላከል ስለሚያስፈልግ፤ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ጥረት የምናደርግበትን ዋና ዋና ምክንያቶች ማመላከት ያስፈልጋል። የዛሬውን የነፃ ሃሳብ ምልከታዬን በባህር በር እና በወደብ አስፈላጊነት ላይ ለማድረግ የወደድኩትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ከግንዛቤ እንዲገባ እሻለሁ።
የባህር በር በአንድ ሀገር ላይ ከሉአላዊነት እኩል የሚታይ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው። የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የንግድ፣ የዲፕሎማሲ፣ የደህንነት ደም ስር ሆኖ አንዱን ከአንዱ የሚያስተሳስር የስልጣኔ ገመድ ነው። ከሕዝብ ቁጥር ጋር ሲጣመር ደግሞ የሚሰጠው ጥቅምና የሚያጎድለው ጉድለት የዛኑ ያክል ነው። ሀገራችን ከቀጣናው አልፋ አፍሪካን ተሻግራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆን ላይ ነች። ይሄ ግስጋሴ ከህዝብና ከመንግሥት ቁርጠኝነት እኩል የባህር በር ያስፈልገዋል። አንድ ሀገር የራሷ የሆነ ወደብ ሲኖራት የኢኮኖሚ ደረጃዋን በ20 ከመቶ ማሳደግ ትችላለች። በሌላ ቋንቋ ወደብ የአንድን ሀገር 20 ከመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ ይይዛል ማለት ነው።
የባህር በር አልባ በመሆን ለሰላሳ ዓመታት የከፈልነው መስዋዕትነት ከዚህ አንጻር ቢቃኝ ቁጭቱ ሁላችንንም የሚነካ እንደሆነ አምናለሁ። አሁን ላይ የወደብ አስፈላጊነትን ማብራራት ለቀባሪ የማርዳት ያክል ነው። እንደግዝፈታችን ወደብ ያስፈልገናል። እንደታሪካችን፣ እንደ ሕዝብ ቁጥራችን፣ እንደፍላጎታችን የባህር በር የግድ ይለናል። እንደእድገታችን፣ እንደኢኮኖሚያችን ከሌላው ዓለም ጋር በነጻነት የምንተሳሰርበት፣ ሉዓላዊነታችንን የምናስጠብቅበት፣ በስማችን የሚጠራ ወደብ የትውልዱ መሻት ነው። ወደብ ለአንድ ሀገር ከኢኮኖሚ በረከቱ ባለፈ የደህንነት ማስጠበቂያም ነው። አንድ ሀገር ወደብ ሲኖራትና የሌሎችን ወደብ በኪራይ ስትጠቀም ጥቅሙ እኩል አይደለም።
የባህር በር ሲኖረን ባለቤትና የበላይ ጠባቂዎች እኛ ነን። ምንም ነገር ስጋት የሚሆንብን ነገር አይኖርም። ከሌሎች ወደእኛ የሚገቡ ማናቸውም ነገሮች በእኛ ይሁንታና ፍቃድ በኩል ስለሚሆኑ አስተማማኝነታቸው የበረታ ነው። በሌሎች ወደብ ስንጠቀም ግን እንደዛ አይደለም የጸጥታ ስጋት፣ የደህንነት ጉዳዮች ሁልጊዜ አስተማማኝ ላይሆኑ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል ብለን ስንነሳ ኢኮኖሚውንና በየቀኑ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግና ለደህንነት ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ነው።
ካለ ባህር በር ለሦስት አስርት ዓመታት የ20 ከመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ ሳይኖረን ነው የቆየነው። በየትኛውም ሁኔታ ቢቃኝ ጉዳቱ በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚንጸባረቅ ነው። መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመሰለፍ ለምትታትር ሀገር ይሄ ትርጉሙ ብዙ ነው። መጪውን የተሻለ ለማድረግ ስለሀገሩ ግድ የሚለው፣ የሚቆጭና የሚታትር የለውጥ ሐዋርያ የሆነ ትውልድ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነት የሀገርን ጥቅም መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በትውልዱ ንቃት ነው። የወደብ ጥያቄ ከመሻት ባለፈ የሁሉም ጥያቄ ሊሆን ይገባል። የምናድገው እንደሀገር ነው፤ የምንከሽፈውም አንድ ላይ ነው። አብረን ለመሻገር አብረን መጠየቅ አለብን።
የባህር በር የአዲሱ ትውልድ የበኩር ጥያቄው ነው። አዲስ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ስለሀገሩ የሚቆጭ፣ በሀሳብ የዳበረ ትውልድ ነው። አስፈላጊ የሆኑ ነገሮቻችንን ዋጋ በመስጠት፣ በመቀናጀትና ዋጋ በመክፈል ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም የሚሰጡ እንዲሆኑ ማድረግ ከሁላችን የሚጠበቅ ነው። የወደብ ጉዳይም በአሁኑ ሰዓት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ብሄራዊ ጥያቄዎች መሀል አንዱ ነው። ለማደግና ለመለወጥ ለያዝነው እቅድ የአንበሳውን ድርሻ የሚያግዘን ነው። ከጥያቄ ወደመልስ፣ ከምኞት ወደመሆን እንድንሸጋገር በበረታ የህብረብሄራዊ ሃሳብ ስር መቧደን አለብን።
በኢኮኖሚና በንግድ በሌሎችም ዘርፎች መጪውን የተሻለ ለማድረግ በበላይነት የምንጠቀመው ወደብ የማስፈለጉ ነገር አጠያያቂ አይደለም። እየሄድንበት ላለው የእድገት ግስጋሴ ገፊና አንቂ ሆኖ ተጨማሪ ኃይል በመሆን ተስፋችንን በማለምለም የማይተካ ሚና አለው። ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ኖሮት በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህር በር የሌለው ሀገር የለም። የሕዝብ ቁጥር አብሮ ይዞት የሚመጣው ብዙ ነገር አለ። መሰረታዊ ፍላጎት አለ፣ የሕዝብ ጥያቄ አለ፣ የተሻለ ህይወት፣ ሰርቶ መለወጥ፣ ወልዶ መሳም አለ እኚህ ሁሉ መሻቶች መልስ ይፈልጋሉ። እንዲህ አይነቱ ሀገራዊ ጥያቄ መልስ ከሚያገኝባቸው አጋጣሚዎች መሀል ቀዳሚው ደግሞ የባህር በር ነው።
የባህር በር ያስፈልገናል ብለን ለጎረቤት ሀገሮች ጥያቄ ስናቀርብ እንዲህ ባለው ተጨባጭ ምክንያት ነው። የሕዝብ ቁጥራቸው ዓመት ከዓመት ከሚጨምር ሀገራት መሀል ነን። ይሄ መሆኑ ችግር ባይኖረውም በዛው ልክ ለሕዝቡ ቁጥር፣ ለሚነሳው ጥያቄና፣ እለት በእለት ለሚንረው ፍላጎት መልስ የሚሰጥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳር ያስፈልጋል። ችግሮቻችንን በወቅቱ ካልፈታን ሌላ ችግር እየፈጠረ ነው የሚሄደው።
አሁናዊ የባህር በር ጥያቄ ነባር ችግሮችን በመፍታት መጪውን የተሻለ ለማድረግ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ተመልሶ ቢሆን አሁናዊ ጥያቄዎቻችን ባልነበሩ ነበር። ታሪካችን ከቀይ ባህር ጋር የተሳሰረ ነው። ጥንት ስልጣኔያችን የቀይ ባህርን ወደብ ተንተርሶ ነፍስ የዘራ ነው። በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ ሀገራት መሀል አንዱን ሆነን በመፈራት ያሳለፍነው ጊዜ በዚህ ትውልድ ላይ ተደግሞ ሀገራችንን ከወደብ ኪራይና ተያይዞ ከሚመጣው የደህንነት ስጋት መጠበቅ ይኖርብናል።
‹‹ዓለም አንድ መንደር ናት›› ስንል ከእኛ ወደሌላው ከሌላው ወደእኛ በሚሸጋገር ቴክኖሎጂ፣ ስልጣኔ፣ ሳይንስ፣ እውቀት፣ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ፣ ባህል፣ ሥርዓት ወዘተ በኩል ነው። ይሄ መስተጋብር ደግሞ በወደብ በኩል የሚሳለጥ ነው። ወደብ ከሌለን ለመስተጋብሩ ሦስተኛ ወገን ነው የምንሆነው። የባህር በር ያስፈልገናል ስንል ለዚህ አይነቱ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ሚና ነው። ያለመጠራጠር የእድገትና የዘመናዊነት ግስጋሴ የባህር በር ያስፈልገዋል። ከወቅታዊ ሀገራዊ መነቃቃት ጋር በማያያዝ አስፈላጊነቱን ብንቃኝ በርካታ ዘርፎችን መንካት ግዴታችን ይሆናል።
ሀገራዊው ኢኮኖሚው በተለይም የወጪና የገቢ ንግዱ የወደብ ነጻነትን መሰረት ያደረገ ነው። እንደምሳሌ ይሄን እናንሳ እንጂ የወደብ አስፈላጊነት ግድ የሚሆንበት ብዙ ምክንያት አለ። ከአፍሪካ ቀድሞ ከዓለም በሚከተል የሕዝብ ቁጥርና የትውልድ ፍላጎት መሀል የወደብ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ንቃትን ከብስለት ጋር ባነገበ የእርስ በርስ ትስስር ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲያገኙ በተያያዘ እጅ እስከ ጥግ መጓዝ ይጠበቅብናል። በሴራና በሸፍጥ ከታሪክ ተገምሰን ከሙላታችን የጎደልነው፣ ከበትረ ብኩርናችን ወደተረጂነት የዞርነው እድገታችንን በማይፈልጉ የውጪ ኃይሎች ቢሆንም ትውልዱ የጀመረውን በማስቀጠል ወደነበርንበት የምንመለስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ባይ ነኝ።
‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ ለምን የባህር በር አጣች›› ለሚለውን ጥያቄ እንደዋና ምክንያት የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ሲነሳ ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ደግሞ ተከታይ በመሆን ለክስተቱ ግብዓት በመሆን ይከተላሉ። ሆኖም ግን የታሪክ ምሁራኑ በሚከተለው ምክንያት ላይ የጋራ መስማማት አላቸው ‹አፍሪካን ነጻ ያወጣችና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የኩራት ምንጭ የሆችው ሀገራችን በቅኝ ካለመገዛቷ ጎን ለጎን ስለሌሎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ ክብር ግድ የሚሰጣትና ተቆርቋሪ መሆኗ በጊዜው ለነበሩ ቅኝ ገዢዎች ያልተዋጠ ነገር ነበር። ጽናት እና ብርታቷ፣ አንድነቷና ልዕልናዋ አፍሪካን ለተቀራመቱ አውሮፓውያን እንቅልፍ የነሳቸው ጉዳይ ነበር።
በዚህ ከቀጠለች አፍሪካን አንድ በማድረግና በማንቃት ለእኛም ለቅኝ ገዢዎች አስቸጋሪ ስለምትሆን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር ባጠቃላይ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚኖራት ወዳጅነት የምትዳከምበትን መላ መፍጠር እንዳለባቸው ሲያስቡ ቀይ ባህር መጣላቸው። ቀጥለውም ከቀይ ባህር ጋር የነበራትንና የሚኖራትን ታሪካዊ ዳራ ማጥፋት እንዳለባቸው መከሩ። ከዚህ ሂደት በኋላ ነው ከይዞታችን ተፈናቅለን ወደብ የሌላት ወደሚል ማንነት የተመለስነው። በዓለም ላይ ከ40 በላይ የባህር በር አልባ ሀገራት አሉ። በአፍሪካም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ከአስራ አምስት የሚልቁ ወደብ አልባ ሉአላዊ ሀገራት አሉ። እንደእኛ ሀገር በሕዝብ ቁጥሩ ጫፍ ነክቶ ወደብ የሌለው ሀገር ግን የለም። የባህር በር አልባ ከሆኑት ሀገራት አንድ ሦስተኛውን የሕዝብ ቁጥር የምንይዝ ነን።
የባህር በር የአንድ ሀገር የህልውና መልክ ነው። ስልጣኔና ዘመናዊነት ሀገር አቋርጠው ወዳለንበት የሚመጡት በወደብ ተሳፍረው ነው። ስናወራው ቀልድ ሊመስል ይችላል፤ ግን አይደለም። ወደብ ባላቸውና በሌላቸው ሀገራት መካከል የገዘፈ ልዩነት አለ። ለጉዳዩ አትኩሮት መስጠት ህልማችንን እውን የምናደርግበት የመጀመሪያ ርምጃ ነው። ለሩብ ዓመት የቀረበ የኢኮኖሚ መነቃቃት በዚህ የወደብ የገበያ ልውውጥ በኩል የሚመጣ ነው። ይሄንን የመሻትና የወደብ ባለቤት የመሆን ምኞት እውን ለማድረግ ስለጥቅሙ በሚገባ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው።
መንግሥት እንደመንግሥት፣ ሕዝብም እንደሕዝብ ኃላፊነት ወስዶ የአስፈላጊነቱን ጉዳይ በሚገባ ሊረዳው ይገባል። የጋራ ድምጽ ከተናጠል ጩኸት በላይ የሚሰማ ነው። አብረን እየጮህን አብረን ለመስማት መዘጋጀት አለብን። ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ሊያሻሽሉን ለሚችሉ ነገሮች እንደሀገር ዋጋ መክፈል ይኖርብናል። ዓድዋን በጋራ ድምጽ አቁመናል። የህዳሴ ግድብን በአብሮነት ገድበናል። የሚቀረን የወደብ ባለቤትነት ነው። በነገራችን ላይ የህዳሴ ግድብና የወደብ ባለቤትነት ተለያየተው የማይታዩ ናቸው። የአንዱ መኖር ለአንዱ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በብዙ ነገር ላይ ተግተን ውጤት አምጥተናል። ትጋቶቻችን ወደነገ ተላልፈው የባህር በር ባለቤት እንደሚያደርጉን አምናለሁ። ትጋት ከአብሮነት ጋር የላቀ ውጤት መገኛ ነው። በምንም ነገር ላይ ከተጋን ውጤት እንዳለን ማመን አለብን። በዓድዋ ላይ ተግተናል፣ በህዳሴ ግድብ ላይ ተግተናል፣ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ተግተናል እየተጋንም እንገኛለን። ትጋቶቻችን ወንዝ ተሻግረው ዓለም አቀፋዊነትን ተላብሰዋል። ከፍላጎቶቻችን እስክንደርስ ድረስ ትጋቶቻችን መቀጠል አለባቸው። የባህር በር እንድናገኝ፣ በወደብ ባለቤትነት ታሪካችንን ለማደስ ከትጋታችን ጋር አብረን መሄድ ግዴታችን ይሆናል። ከሕዝብ ቁጥራችን ጋር የሚጣጣም፣ ከፍላጎቶቻችን ጋር አብሮ የሚሄድ ኢኮኖሚ ለመገንባት የባህር በር መኖር አስተዋጽኦ የላቀ ነው። አበቃሁ!!
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም