የሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር እአአ 1988 በሴዑል ኦሊምፒክ መድረኩን ሲቀላቀል፤ በቀጣዩ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ደግሞ ጀግናዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በታሪክ የመጀመሪያውን ድል በማስመዝገብ ለሃገሯና ለአፍሪካ ኩራት ለመሆን ቻለች። ይህቺ አትሌት በመድረኩ 2 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ እስካሁንም ቀዳሚ ስትሆን፤ የአክስቷን ፈለግ የተከተለችው ሌላኛዋ ጀግና አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም በተመሳሳይ የሜዳሊያ ቁጥር ትከተላታለች። አትሌት ጌጤ ዋሚ እና እጅጋየሁ ዲባባም ተጨማሪ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘትም ይጠቀሳሉ።
በጥሩነሽ እግር የተተካችው አልማዝ አያና ደግሞ እአአ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያውን የዓለምን ክብረወሰን በመስበር ጭምር ማጥለቋ የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱ ርቀቱን 29:17.45 በሆነ ሰዓት ያሸፈነችው አትሌቷ ያሻሻለችው ሰዓት 23 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑም አድናቆት አትርፎላት ነበር። ከአራት ዓመት በፊት ደግሞ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በለተሰንበት ግደይ የነሐስ ሜዳሊያው ተገኝቷል። በአጠቃላይ በዚህ ርቀት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ብልጫውን የያዘች ሃገር ስትሆን፤ በ5 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሰፊ ልዩነት ትመራለች።
በረጅም ርቀት ሩጫ ስኬታማ ሃገር እንደመሆኗም እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ለሜዳሊያ ከሚጠበቁ ሃገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት። ዛሬ ምሽት 3ሰዓት ከ55 ደቂቃ ላይ በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያን በመወከል አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ ፎቴን ተስፋዬ እና ጽጌ ገብረሰላማ የሚካፈሉ ሲሆን፤ አትሌት አይናዲስ መብራቱ ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዛለች። ጉዳፍ አትሳተፍም ቢባልም በይፋ አልተረጋገጠም።
በኢትዮጵያ የርቀቱ ታሪክ በ8 ኦሊምፒክ ተሳትፎዎቿ ሜዳሊያ ያላገኘችበት ኦሊምፒክ ባለመኖሩ በዛሬው ሩጫም የስፖርት ቤተሰቡ ውጤት ይጠብቃል። በእርግጥም ይህ ቡድን ካለው ጥንካሬ አንጻር ለሜዳሊያ ተጠባቂ ይሁን እንጂ እጅግ ጠንካራ ፉክክር ሊገጥመው እንደሚችልም ግልጽ ነው።
ዘንድሮ በሦስት ርቀቶች በኦሊምፒኩ የምትሳተፈው የዓለም ሻምፒዮናዋ ጉዳፍ በ5ሺ ሜትር እንደታሰበው ባይሳካላት በዚህ ውድድር ግን ጠንካራ ፉክክር እንደምታደርግ ትጠበቃለች። በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የ10ሺ ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያውን የግሏ ማድረጓ የሚታወስ ነው። ከጥቂት ወራት በፊትም በኦሪጎን ከተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ጎን ለጎን በተደረገው የ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ መሳተፏ ይታወሳል። እጅግ ፈጣን በነበረውና የዓለም ክብረወሰንም በተሰበረበት በዚህ ውድድር ላይም ጉዳፍ ኬንያዊቷን አትሌት ተከትላ ስትገባ ያስመዘገበችው 29:05.92 የሆነ ሰዓት የግሏ ፈጣን በሚል ተይዞላታል። በዚህም ምክንያት አትሌቷ በርቀቱ ሦስተኛዋ ፈጣን አትሌት ልትሆንና በዚህ ኦሊምፒክም ለሜዳሊያ እንድትጠበቅ አስችሏታል።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፎቴን ተስፋዬ ደግሞ በስፔን በተካሄደው የሴቶች 10ሺ ሜትር ማጣሪያውን በቀዳሚነት በማጠናቀቋ በኦሊምፒኩ ሃገሯን ትወክላለች። የ26 ዓመቷ አትሌት የገባችበት 29:47.71 የሆነ ሰዓት በርቀቱ የግሏ ፈጣን እንዲሁም ከጉዳፍ ተቀራራቢ የሆነ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቷ በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለሦስት ዓመታት ከስፖርቱ ርቃ ብትቆይም በድጋሚ ራሷን በማጠናከርና ወደ ቀደመ ብቃቷ በመመለስ ለኦሊምፒክ ተሳትፎ የበቃች ጠንካራ አትሌት ናት። በመሆኑም ከቡድን አጋሮቿ ጋር ለተቀናቃኝ አትሌቶች ፈተና እንዲሁም የሜዳሊያ ተፋላሚ እንደምትሆን ይገመታል።
ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በኦሊምፒክ የመወከል ዕድል የገጠማት ሌላኛዋ አትሌት ደግሞ ወጣቷ ጽጌ ገብረሰላማ ናት። እአአ በ2018 በወጣቶች ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ የውጤታማነት መንገዷን የጀመረችው አትሌቷ በሁለት የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች 1 የወርቅ፣ 2የብር እና 1 የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች። በቶኪዮ ኦሊምፒክ በዚህ ርቀት ተሳታፊ የነበረችው ጽጌ፤ ልምድ ያላት አትሌት ስትሆን 29:48.34 የሆነ ምርጥ ሰዓት ባለቤትም ናት። በርቀቱ ከዓለም 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለች ምርጥ አትሌት እንደመሆኗም በምሽቱ ውድድር ኢትዮጵያ ሜዳሊያ እንድታገኝ የሚኖራት ሚና ቀላል አይሆንም።
በኢትዮጵያ በኩል የሚሰለፉት ጠንካራ አትሌቶች ይሁኑ እንጂ በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ እንዲሁም የቶኪዮ ኦሊምፒክ አሸናፊዋ አትሌቶች መሳተፋቸው ፍልሚያውን እንደሚያከብደው አያጠያይቅም። ሁለቱ አትሌቶች በተለይም ከጉዳፍ ጋር የሚኖራቸው የሜዳሊያ ትንቅንቅ ደግሞ የዕለቱ ትኩረት ማዕከል ነው። ከቀናት በፊት የ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያውን የግሏ ያደረገችው ኬንያዊቷ አትሌት ባትሪስ ቼቤት በተያዘው ዓመት 28:54.14 በመሮጥ በአትሌት ለተሰንበት ግደይ እጅ የቆየውን ክብረወሰን ስትረከብ በሴቶች ከ29 ደቂቃ በታች ርቀቱን በመፈጸምም ቀዳሚዋ አትሌት ናት። አትሌቷ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የተዘጋጀች ሲሆን፤ ኔዘርላንድን የምትወክለው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፈን ሃሰንም የቡዳፔስት ቁጭቷን ለመወጣት ሌላኛዋ የውድድሩ ከባድ ተፎካካሪ መሆኗ አያጠራጥርም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም