በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ የጎርፍ መጥለቅለቅን እያስከተለ በመሆኑ በሰዎች ሕይወት በንብረትና በኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳደረ ነው። በጎፋ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት አልፏል። ንብረት ወድሟል። ዜጎች በክረምት በዚህ ጭንቅ ሰዓት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የመሬት መንሸራተቱ እንዲሁ በወላይታና በሌሎች አካባቢዎች ተከስቶ ሰዎች ሞተዋል። ንብረት ወድሟል። ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እንበለው የከባቢ አየር ሙቀት ሰደድ እሳት፣ ከባድ ዝናብና ጎርፍ፣ ድርቅ እያስከተለ የበለጸጉ ሀገራትን ሳይቀር እየተፈታተነ ይገኛል። በአሜሪካ ግዛቶች፣ በአውሮፓ በግሪክ፣ በስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በእስያ በቻይና፣ በአፍሪካ ሀገራችንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት፣ በላቲን አሜሪካ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የሰደድ እሳትና የሱናሚ አደጋ ዜጎችን እያፈናቀለ፣ ሕይወት እየቀጠፈ፣ በአንዳንድ ሀገራት ላይ ደግሞ የህልውና ስጋት እየደቀነ ይገኛል።
የበለጸጉ ሀገራት ሳይቀር ዜጎቻቸውን ከዚህ አደጋ ለመታደግ ሲቸገሩ እየታዘብን ነው። ይህን የታዘቡት የቬኒዞላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝ አሜሪካ በኤልኒኒዮ ክፉኛ መፈተኗን፤ ኩባ እንደ ኤልኒኒዮ ወይም እንደ ሱናሚ ያለ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥማት ውሻና ዶሮ ሳይቀር ከአደጋ ቀጣና አካባቢ ስታወጣ አሜሪካ ግን ዜጎቿን በቅጡ መታደግ ይቸግራታል ሲሉ መተቸታቸው ይታወሳል። ይህ የተደራጀ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ላላቸው ሀገራት እንኳ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ያሳያል።
አደጋው የሚደርሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጥናቶች ዛሬም የማይተካ ሚና እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች Early Warning Systems (EWS) በድርቅ፣ በጎርፍ እና በሌሎች አደጋዎች በተደጋጋሚ የምትጎዳ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተፅእኖ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ከቅድመ ማስጠንቀቂያ የሥርዓቶች ዋና ዋናዎችን እንመልከት፦
1.ወቅታዊ መረጃን ማሰራጨት፦ስለሚመጡ አደጋዎች ወቅታዊ ማንቂያዎችን ያቀርባል፣ ይህም ማህበረሰቦች እንዲዘጋጁ እና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ይህ የአየር ሁኔታዎችን፣ ሊኖሩ ስለሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችና የመሬት መንሸራተት ወይም የድርቅ ሁኔታዎች መረጃን ያካትታል።
2.የአደጋ ምዘና እና ካርታ ሥራ፦ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች አደጋዎችን እና ተጋላጭነቶችን መገምገም፣ አደጋ የተጋለጡ አካባቢዎችን ለመለየት ይረዳል። ይህ መረጃ ለውጤታማ እቅድ ማውጣት እና ሀብትን ለማከፋፈል አስፈላጊ ነው።
3.የማህበረሰብ ተሳትፎ፦ የአካባቢ ማህበረሰቦችን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ልማት እና አተገባበር ውስጥ ማሳተፍ ማንቂያዎች ተገቢ መሆናቸውን እና ማህበረሰቦች እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ እንደሚያውቁ ያረጋግጣል። የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች የአካባቢ አቅምን ሊያሳድጉ ይችላሉ።
4.ከአካባቢያዊ እና ሀገራዊ ሥርዓቶች ጋር ውህደት፦ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች በአካባቢም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ሰፊ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ማዕቀፎች መካተት አለበት። ይህ የተቀናጀ ምላሽ እና ቀልጣፋ የሀብት ማሰባሰብን ያረጋግጣል።
5.ቴክኖሎጂ እና ዳታ መጠቀም፦ የሳተላይት ምስሎችን፣ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን እና የርቀት ዳሳሾችን መጠቀም የቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ትክክለኛነት ያሻሽላል። የሞባይል ቴክኖሎጂም ለርቀት ማህበረሰቦች የማንቂያዎችን ፈጣን ግንኙነት ያመቻቻል።
6.የፖሊሲ ልማት፦ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ለፖሊሲ አውጪዎች እንደ መሠረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እና ለአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ልማዶችን የመሳሰሉ ቀዳሚ ርምጃዎችን አስፈላጊነት ማሳወቅ ይችላሉ።
7.የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ዕቅዶች፦ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና ምላሽ ዕቅዶችን እንዲያዘጋጁ እና እንዲተገብሩ ያግዛሉ፣ ይህም አደጋ ሲከሰት ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል።
- ክትትልና ግምገማ፦ የአደጋዎችን ቀጣይነት ያለው ክትትል እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ውጤታማነት መገምገም በጊዜ ሂደት ትክክለኛነታቸውን እና አስተማማኝነታቸውን ሊያሻሽል ይችላል ይህም ለአደጋ ዝግጁነት የተሻለ አቅም ይፈጥራል።
9.መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ትብብርን መፍጠር፦ መንግሥታዊ ካልሆኑት ድርጅቶች እና ከዓለም አቀፍ አካላት ጋር ያለው ትብብር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን አቅም በእውቀት መጋራት፣ በቴክኒክ መደገፍ እና በገንዘብ ለማገዝ ያስችላል።
10.የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ፦ በመጨረሻም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፤ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ለመቋቋም ልምዶቻቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያግዝ መረጃ በማቅረብ በአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ስልቶች ውስጥ ሚና መጫወት ይችላል። ሀገራችን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና በማጠናከር የተፈጥሮ አደጋዎችን የመቋቋም አቅሟን ማሳደግ፣ በመጨረሻም ሕይወትን ማዳን፣ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎችን መቀነስ እና አጠቃላይ የማህበረሰብ ደህንነትን ማሻሻል ትችላለች።
ኢትዮጵያ ለተፈጥሮና ለሰው ሠራሽ አደጋዎች ተጋላጭ ሀገር ናት። ለረጅም ዘመናት ድርቅ ቶሎ ቶሎ የሚጎበኛት፣ በጎርፍ በተደጋጋሚ ጉዳት የሚደርስባት፣ አልፎ አልፎ በመሬት መንሸራተት የምትጠቃ፣ በጣም በተደጋጋሚ በመለስተኛና በከፍተኛ ግጭቶችና በአውዳሚ ጦርነቶች መከራዋን የምታይ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ሳቢያ፣ ቢያንስ ከ260 በላይ ወገኖች ሕይወታቸውን ከማጣታቸውም በላይ በአደጋው ምክንያት የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች ፍለጋ እየተደረገ ነው። ከሟቾችና የደረሱበት ካልታወቀ ሰዎች በተጨማሪ፣ በበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ መጠኑ ያልታወቀ ንብረት ወድሟል። በጣም ብዙዎቹ ለሕልፈትና ለአካላዊ ጉዳት የተዳረጉት፣ ከነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር በናዳው ምክንያት የአፈር ክምር ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማትረፍ ሲረባረቡ እንደሆነ ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተቋም እንዲኖር የተደረገው በ1965 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ነበር። በወቅቱ ‹‹ድብቁ ረሃብ›› ተብሎ በውጭ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ያገኘው ድርቅ ለ1966 ዓ.ም. አብዮት መፈንዳት አንደኛው ምክንያት ሲሆን፣ በተበታተነ መንገድ ይከናወን የነበረውን የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራ በተቋማዊ መንገድ ለማካሄድ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ) በዘመነ ደርግ መጀመሪያ ላይ ተመሠረተ።
በኮሚሽኑ አማካይነት ከሀገር ውስጥና በብዛት ከውጭ ከፍተኛ ዕርዳታ በማሰባሰብ ድርቁን ለመቋቋም ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ ሲሆን፣ በሒደት ኮሚሽኑ ራሱን እያሰፋና እያጠናከረ በአፍሪካ ትልቁ ተቋም ለመሆን በቅቶ ነበር። ምንም እንኳ በተለያዩ ምክንያቶች ድርቁ እየደጋገመ ቢከሰትም፣ ኮሚሽኑ ግን ትልልቅ መጋዘኖችን ከበርካታ ተሽከርካሪዎችና ከአውሮፕላኖች ጭምር ባለቤት መሆን ችሎ ነበር።
በዘመነ ኢሕአዴግ ስሙ ተቀይሮ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን (አመዝኮ) ተብሎ ለተወሰነ ጊዜ ከሠራ በኋላ፣ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ እንደ አንድ መምሪያ ሆኖ ተዋቅሮ ያን የነበረውን ቁመና አጥቶ ነበር። የተለመደው ድርቅና ሌሎች ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደጋገሙ ደግሞ፣ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ተብሎ ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።
በዚህ ሁሉ ጊዜና ቅብብሎሽ ውስጥ ድርቅ ወይም አደጋ ሲያጋጥም መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች የውጭ አጋር አካላት በትብብርና በተናጠል ድጋፍ ቢያደርጉም፣ የኢትዮጵያን አደጋ የመከላከልና የዝግጁነት አቅም ለመገንባት ጥረት ባለመደረጉ ችግር ባጋጠመ ቁጥር ወደ ውጭ ማንጋጠጥ የተለመደ ተግባር ነው። የሰሞኑ የጎፋ ዞን የመሬት ናዳ አደጋ ቢቻል በወረዳው ካልተቻለ በዞኑ፣ ካልሆነ ደግሞ በክልሉ ፈጣን ምላሽ ማግኘት ነበረበት።
አካባቢው ከዚህ ቀደም በመሬት መንሸራተት አደጋ ይጠቃ እንደነበር ይታወቃል። በመሬት ጥበት ምክንያት ሰዎች ለም አፈር ፈልገው ከእነ ሥጋቱ በአካባቢው ሰፍረው ቢያርሱም፣ ባልታሰበ ሰዓት ሊከሰት የሚችለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ዝግጅት ያስፈልገው ነበር። ለዚህም ሲባል በፌዴራል፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ በመናበብ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም መገንባት ነበረበት።
ከዚህ ቀደም የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች በጎርፍ ምክንያት ሲደርስባቸው የነበረው አደጋ በአንፃራዊነት የቀነሰው፣ ለበርካታ ዓመታት በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ላይ ሕይወት ማጣትን ጨምሮ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው። አሁንም ቢሆን ጎርፉ ሙሉ በሙሉ ሊገታ ባለመቻሉ ከፍተኛ ሥጋት አለ። ሊያጋጥሙ ለሚችሉ አደጋዎች ልዩ ትኩረት ሲሰጥ የመከላከልና የዝግጁነት አቅም ስለሚገነባ ጉዳቱ በጣም ዝቅተኛ ነው የሚሆነው።
ከግጭቶችና ከአውዳሚ ጦርነቶች በተጨማሪ በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱባት ሀገር ውስጥ፣ ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ልዩ ትኩረት መስጠት የግድ ይላል። በክረምት ወቅት ከሚያጋጥሙ እንደ መሬት ናዳና ጎርፍ ከመሳሰሉ አደጋዎች ባሻገር፣ በበጋ ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በደኖች ላይ ቃጠሎ እየደረሰ በርካታ ሀብት ወድሟል። ደኖች ላይ በሚደርስ የሰደድ እሳት ምክንያት ከዕፅዋት በተጨማሪ በዱር እንስሳትና በአዕዋፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያጋጥማል።
ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት የሚደረገው ባሕላዊ ርብርብ ከአደጋው ጋር ስለማይመጣጠን ውድመቱ ከፍተኛ ነው። በዘመናዊ የአደጋ መከላከል ዘዴዎች ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሀብትና የሰው ኃይል ሥልጠና የሚያስፈልግ ሲሆን፣ መንግሥት ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም ግንባታ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል። ለዚህ የሚውል ኢንቨስትመንት ከጥፋት ይታደጋል።
ክረምትና በጋ ሲፈራረቁ እንደ አየሩ ጠባይ ወይም ሁኔታ የሚያጋጥሙ የተፈጥሮ ክስተቶች ይኖራሉ። እነዚህ ክስተቶች በአብዛኛው ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትሉ ስለሆኑ ልዩ ትኩረት ይሻሉ። በደኖች ላይ ከሚደርሱ የሰደድ እሳት አደጋዎች በተጨማሪ በአነስተኛና በከፍተኛ የእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎች፣ በኃይል ማመንጫዎች፣ በቴሌኮምና በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች፣ በጤና ማዕከላት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በምርት ማከማቻ መጋዘኖች፣ በመኖሪያ መንደሮችና በተለያዩ ተቋማት ላይ ሰደድ እሳት ሊነሳ ይችላል።
ጎርፍ ደግሞ አሁን ከተፋሰሶች ባሻገር በከተሞች ውስጥ በስፋት እየተከሰተ ጉዳት እያደረሰ ነው። እነዚህና ሌሎች ክስተቶች ሲያጋጥሙ አደጋን በብቃት የመመከት አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ሕይወትን ለመታደግ ሁሌም ዝግጁ መሆን የግድ መሆን አለበት። አደጋን ቀድሞ ለመከላከል ዝግጁ አለመሆን በሕይወትም ሆነ በንብረት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ከጎፋ ዞን የመሬት ናዳ ዕልቂትና ውድመት በመማር አቅም መገንባት ተገቢ ነው።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም