መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል። አዲሱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ዘላቂነትን በሚደገፍ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለመመሥረት የሚያስችል ነው።
ማሻሻያው ፈጠራን የሚያበረታታና ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል። የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን የሚያጠናክርና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደጊያ እንደሚሆንም ይጠበቃል ።
ማሻሻያው ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽል ታምኖበታል።
ማሻሻያው ቀጣዩን የኢትዮጵያን የዕድገት ደረጃና ከቀረው የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን እና እያደገ የመጣውን ትስስር ለማጠናከር የሚረዳ ነው። የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና ለነዋሪዎችና ለአምራች ዘርፎች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ይረዳል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። በኢንዱስትሪና በፍጆታ ዕቃዎች ምርት ዘርፎች የተሠማሩ ተኪ ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በተሰኘው ዕቅድ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ኢንዱስትሪዎች፣ ከማሻሻያው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል።
ሆኖም ሁለንተናዊ ለውጥ ያረጋግጣል የተባለለት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ጎን ለጎን ሊሠሩ የሚገባቸው ተግባራት አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው በማሻሻያው ምክንያት ሊፈጠር በሚችል የዋጋ ግሽበት ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊጠብቁ የሚችሉ ስልቶችን በማያቋርጥ መልኩ መተግበር ነው።
በብዙ ሀገራት እንደታየው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲደረግ እና የገንዘብ ማስተካከያ ፖሊሲ ሲሻሻል አብረው ከሚከሰቱ ችግሮች ቀዳሚው የዋጋ ግሽበት ነው። ይህ ደግሞ በመጀመሪያ የሚጎዳው ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ነው። ስለዚህም ይህን የኅብረተሰብ ክፍል ሊታደግ የሚችል አቅጣጫ ማስቀመጥና በአግባቡ መተግበርም ይገባል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተተገበረበት ወቅት እንደተገለጸው በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት እንደሚደጉም መንግሥት ይፋ አድርጓል።
በዚህም ነዳጅን፣ ማዳበሪያን፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይትን የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ የአራት መሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ጫና በአንድ ጊዜ ወደ ሸማቹ እንዳይተላለፍ መወሰኑ አንድ እርምጃ ነው። ያለውን የገንዘብ ምንጭ በመጠቀምና የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በማያባብስ መልኩ ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ውድነት መደጎሚያ ደሞዝ ለመጨመር መታሰቡና በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የሚደረገው የሴፍቲኔት እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ መደረጉ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው።
ሆኖም እነዚህ እርምጃዎች ውጤት እንዲያመጡ የመንግሥት ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል። በተለይም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች መበራከታቸው የመንግሥት ቁጥጥርና እርምጃ ወሳኝ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።
መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ማድረጉን ባስታወቀበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሸቀጦችን በመደበቅ፤ በማከማችትና ከልካቸው በላይ ዋጋ በመቆለል የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር እና ኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ለማድረግ ሲሞክሩ ታይተዋል። ስለዚህም የድሃው ኑሮ በእነዚህ ስግብግቦች እንዳይነጠቅ መንግሥት ቆንጠጥ ያለ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡ መሬት እንዲነካ እና የታሰበው የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር ያስችላል። የትኛውም አይነት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ሲያድግ ብቻ ነው።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በተለይም በግብርናው ዘርፍ የታየው ምርታማነት አበረታች ነው። የሀገሪቱን መልክዓ ምድርና የአየር ፀባይን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች በመሠራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪኳ አምርታቸው የማታቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችለዋል።
ጤፍን ብንመለከት የለውጡ መንግሥት እውን እስከሆነበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም። ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በክላስተር ማረስ በመቻሉ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል። ዘንድሮም ከ800 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ጥረቶች ተጀምረዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአዲስ የልማት ጎዳና እንድትራመድ ካደረጓት የግብርና እንቅስቃሴ አንዱ የስንዴ ልማት ነው። ቀደም ሲል በጥቂት መጠን፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፤ በክረምት ብቻ ይመረት የነበረውን የስንዴ ልማት ወደ በጋም በማሸጋገር የስንዴ ምርትን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም ላይ ተደርሷል።
ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመሥራት ላይ ትገኛለች። ዘንድሮም 80ሚሊዮን ኩንታል በማምረት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። አበረታች ውጤቶችም መ ታየት ጀምረዋል።
የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል። 500ሺ የነበረው ዓመታዊ ምርትን ወደ 800ሺ ማሳደግ ተችሏል። በዚህም 700ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ገቢ ወደ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ችሏል። የሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለሀገሪቱ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የማምጣት አቅም ላይ ደርሷል።
ከዚህ በሻገርም በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል። በማር፤ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋፅዖ፣ በጓሮ አትክልትና በፍራፍሬ ምርት ላይ የጎላ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ዜጎች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ብሎም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏል።
በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ያለው መሻሻል ስንዴን፤ ሩዝንና አቦካዶን የመሳሰሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም እንዲቀርብ ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ በውጭ ታዛቢዎች ጭምር የተመሰከረለትና ኢትዮጵያም በግብርናው ዘርፍ እምርታ እያሳየች መምጣቷን ያሳየ ነው። እነዚህ የምርታማነት ጥረቶች ተጠናክረው ከቀጠሉ የታሰበው የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው የሚፈለገውን ውጤት ይዞ እንደሚመጣ ማሳያዎች ናቸው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍም ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል። በአሁኑ ወቅት በግብዓትና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንዱስትሪዎች ካላቸው አቅም እያመረቱ ያሉት ከ50 በመቶ ብዙም የዘለለ አይደለም። በሌላ በኩልም ከውጭ የሚገባውን ምርትም በመተካት ረገድ ከ40 በመቶ የዘለለ ድርሻ የላቸውም። ስለዚህም ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን የውጭ ምንዛሪ እና የግብዓት እጥረት በመቅረፍ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማበረታታት ያስፈልጋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ 70 በመቶ ማሳደግ ይገባል። ይህ ሲሆን ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን አልፈው የውጭ ምንዛሪንም ማስገኘት ይችላሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የቢሮክራሲ ማነቆዎችን መፍታትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን ሠላም እንዲሰፍን መሥራት እና ግጭትን ማስወገድ የሁሉም ዜጋ ትኩረት ሊሆን ይገባል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም