ቀታሪ ግጥም

በዚህ ምጥን ሥነ-ጽሑፋዊ ዳሰሳ ጽሑፍ ሁለት ጉምቱ የኪነጥበብ ሰው የሆኑት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በ‹‹ውስጠት›› እና አሰፋ ጉያ በ‹‹የከንፈር ወዳጅ›› የግጥም መድብሎቻቸው ያካተቷቸውን ‹‹ሰው እና ሚዛን የለሽ ሚዛን›› ግጥሞችን እንቃኛለን። መቃኛችን ቃል ነው።

ጉድ እኮ ነው!

ከላይ ጎባባውን ሰማይ፣ ከታች ደግሞ ከእግሩ ስር የወደቀችው መሬት ታኮም ሆነ ድሆ የሚኖረው፣ የራሱ ባለዕዳ የሆነውን ሰው ቀጥለው በቀረቡ ሁለት የተለያዩ ግን የሰውን(የግለሰብን) ኃያልነት የሚያሰናኙ ግጥሞች ውስጥ ኃይሉን አጮልቀን እንመለከታለን። ምልከታው ምናባዊ ነው። በዚህም በእኔ እና ከእኔ በቅርብና በሩቅ (ከቦታና ከዘመን አንፃር) ያለ አንባቢ የጋራ የኪነት ቤት የምንሠራበት ነው። ጉዳዩ ቀታሪ ነው። በቀላሉ የሚጨበጥ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ አንድም የቋንቋ፣ ሌላም የሕይወት ልምድ ማነስ ምናባችንን ይቧጥጣል።

ያም ሆኖ ጥረታችን ከንቱ እንዳይቀር ቀታሪ የሚለውን ቃል በማፍታታት እንጀምር።

[ቀታሪ፡- ስሩ ቀተረ ነው። ቀተረ፡- እኩል ለመሆን ተከታተለ፡- ተቀታተረ፡- ተመለካከተ፡- ተወዳደረ፡-ተተካከለ፡-ተመዛዘነ፡-ተፎካከረ፡-ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር። (ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷የአማርኛ መዝገበ ቃላት÷ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷2008 ዓ.ም) ግጥም ምንጬ ሕይወት ነውና (ቋንቋው(መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብን እና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል። ) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው። መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል። ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም። አይታኘክም-የተመጠጠ ነውና። ]

. . .

ሰው

የሴሎች ሴሎች ክምችት

የቃላት ርችት፦–

ጭንቅላታም፣

በባሰ ይባስ ዓይነቱ ነገር ያዢ

ፍጥረትን ገዢ

ሳያሠልስ

እሱው አንጋሽ እሱው ንጉሥ።

(ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ውስጠት፣1981 ፣ገፅ 78)በግጥሙ፣ ሰው የነገሮች ቅጥልጥላት ውጤት ነው። ይህም ‹‹የሴሎች ሴሎች ክምችት›› በሚለው አሰነኛኘት ተገልጿል። ‹‹የሴሎች ሴሎች…›› የሚለው አገላለፅ ብዛት ያላቸው ነገሮች የተከማቹበት መሆኑን አመላካች ሲሆን ሰው የብዙ ሰዋዊ ጉዳዮች ውጤት መሆኑን ለማመልከት የገባ ነው። ይህን አጠቃቀም በመደብ ብንወስደው የበርካታ መደቦች ክምችት መሆኑን የሚገልፅ ነው። ሴሎቹ ምንድን ናቸው? ስሜት፣ ድምፅ፣ ቃላት፣ ሃሳብ፣ እሳቦት፣ እሳቤ፣ እውቀት፣ሥርዓት፣ እምነት፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣… ከረቂቅ ወደ ተጨባጭ ወይም ከጥቃቅን ወደ ግዙፍ ነገር እያደገ የሚሄድ ‹‹የሴሎች›› ድምር ውጤት ነው። ግጥሙ ላይ ሂደቱ በየስንኞቹ ተገልጿል። ከጥቃቅን ነገር የጀመረው ማንነት እያደገ ሄዶ የፍጥረት አለቃ እስከመሆን ያድግና አንጋሽና ንጉሥ ማዕረግ ባለቤት ይሆናል።

የግጥሙ አሰነኛኘት ሰው በቋንቋ አማካኝነት የሠራውን ዓለም አጠቃላይ ምስል የሚያሳይ ነው። የመጀመሪያው ስንኝ ስለ ድምፆች ክምችት በየፈርጁ ያለውን የክምችት አቅም ወይም ብቃት ገላጭ ነው። ሁለተኛው ስንኝ ደግሞ የድምፆች ክምችት ውጤት የሆነው ቃል በርችት መልክ በአንደበት ለአደባባይ ሲበቃ ያለውን ሰዋዊ ባሕሪ እና ተግባር የወከለ አሰነኛኘት ነው። በዚህም የሰው ልጅ የልሳን ባለቤት መሆኑን እና በዚህ ብቃቱ የሚከናወነውን ርችታዊ ተግባር (በፍንዳታ የተወከለው አብሳሪ፣ ትርጉም) ያለው መሆኑን ለማመልከት ነው።

ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ጭንቅላታም›› በሚል የተገለፀው ሰዋዊ ተግባር አሰላሳይ፣ ንቁ፣ በአዕምሮው የሚመራ መሆኑን ለማመልከት የገባ ነው። ይህም ተግባር በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው።

‹‹በባሰ ይባስ ዐይነቱ ነገር ያዢ›› ደግሞ ነገር እና ተግባር መራጭ፣ የላቀ(የባሰ) ጉዳይ ባለቤት መሆኑን ወካይ ሆኖ የገባ ነው። በዚህም ‹‹በባሰው ይባስ ባይ›› በመሆኑ ክልከላን የሚጥስ፣ ኃላፊነት ወስዶ ነገሮችን የሚፈፅምና የሚመጣውን መከራ ወይም ኃላፊነት ለመወጣት ወሳኝ ተደርጎ ተገልጿል። እዚህ ላይ ‹‹ነገር ያዢ›› የሚለው ሐረግ ወግ፣ ሕግ አዋቂ የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን አንድም የቋንቋን ሥርዓት ሠሪ፣ አንድም ደግሞ የኑሮውን ወግ፣ ባሕል አጥብቆ ያዥ መሆኑን ገላጭ ሆኖ ተሰናኝቷል። ስለሆነም መራጭና የሚስማማውን ነገር የሚተገብር (ያዢ) ነው።

‹‹ፍጥረትን ገዢ›› የሚለው አምስተኛ መስመር ላይ ያለው አሰነኛኘት ደግሞ ሰው በዘረጋው ወግ፣ ሥርዓት ወይም ሕግ አማካኝነት በዙሪያው ያሉ ፍጥረታትን የሚያስተዳድርበት አቅም የተላበሰ መሆኑን ጠቋሚ ነው። በዚህም ሰው በራሱ መፍጨርጨር የኃይል የበላይነቱን የያዘ፣ ገዢ ማንነት ያለው ነው። ይህ ሚናው ደግሞ ‹‹ሳያሠልስ›› የሚተገበር ነው። ይህም ሰውን ከምንም ነገር ተፅዕኖ የሚያላቅቅና ከራሱ ሥርዓት ውጪ ከምንም ነገር ነፃ የሆነ መሆኑን ማሳያ ነው። አሰነኛኘቱ የአረጋጋጭነት ሚና ያለው ነው። በዚህም ምክንያት ‹‹ሳያሰልስ›› የሚገዛ ነው።

በመጨረሻም ሰው ‹‹እሱው አንጋሽ እሱው ንጉሥ›› መሆኑን በመግለፅ ግጥሙ ይቋጫል። በዚህም የሁሉም ሰዋዊ ተግባር ምንጩም አመንጪም እሱ ሆኖ ተበስሯል። ይህም ሰው ከራሱ ውጭ በሆነ ሥርዓትም ሆነ ሕግ የማይመራ፣ ማንነቱም ያልተቀረፀ መሆኑን አረጋጋጭ በሆነ አገላለፅ የተሰናኘ ነው። በዚህም ምክንያት የሰውን ማንነት የሚገልፁ ነገሮች በሙሉ በራሱ በሰው የተሠሩ፣ የተዘረጉ የማንነቱ ድር ናቸው። ስለሆነም በግጥሙ ውስጥ ዙፋኑም ዳኛውም ራሱ ሰው በመሆኑ ሕልውናውን በራሱ ዐሻራ የሚቀርፅ ሆኖ ተስሏል።

በመቀጠል ‹‹ሚዛን የለሽ ሚዛን››ን እንቃኝ፡-

ሚዛን የለሽ ሚዛን

ርዝመትስ በእጥረት ተመተረ

ፈሳሽስ በጠጣር ተሰፈረ

ውፍረት – በቅጥነት…

ክብደትም በቅለት… ተመዘኑ፤

ልስላሴ በሻካራ…

ሙቀትም በቅዝቃዜ… ተወሰኑ፤

መደመር በመቀነስ ተጨመረ

ድልም በሽንፈት ተበሠረ፤

ሚዛኑስ በምን ሚዛን ተከወነ?

ውጤቱስ በማን ተበየነ???

መስከረም 1982

(አሰፋ ጉያ፣ የከንፈር ወዳጅ፣ 1984፣ ገፅ 36)

‹‹ሚዛን የለሽ ሚዛን›› የሕይወት ተቃራኒ መልኮች ያላቸውን እርስ በርስ ግንኙነት እና አንዱ ለሌላው ስፍር ወይም ልክ ማሳያ ሆነው የገቡበት ግጥም ነው። ለአብነትም ድል እና ሽንፈት፣ መደመር እና መቀነስ፣ ውፍረት እና ቅጥነት፣ ክብደት እና ቅለት፣ ልስላሴ እና ሻካራ፣ ሙቀት እና ቅዝቃዜ፣ ፈሳሽ እና ጠጣር እንዲሁም ረጅም እና አጭር በግጥሙ የልክ ማሳያ ተደርገው የቀረቡ ናቸው። ስለሆነም በየራሳቸው የቆሙ ጉዳዮች ቢሆኑም አንዱ ለሌላው ሕልውና እውን መሆን ያለውን አስተዋፅዖ ነጋሪ አሰነኛኘት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የእነዚህን ጥምረት እና እውን መሆን የሚከውነው አካል የተጠየቀበት አሰነኛኘት ነው።

ግጥሙ ስለ ሚዛን ወይም ልኬት የሚያትት ቢሆንም መስፈርቱ እውን እንዲሆን ያደረገውን አካል ማንነት ይጠይቃል። ሚዛኑን ሚዛን ያደረገው ምንድን እንደሆነ ይጠይቃል። የግጥሙ የመጨረሻ አሰነኛኘት በመስፈርት የማይሰፈር ሚዛን መኖሩን ጠቋሚ ነው። ይህም የሰውን ልጅ እምቅ አቅም አመላካች ከመሆኑም ባሻገር ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ያፀደቃቸው፣ የፈጠራቸው፣ የሚጠቀምባቸው እራሱ ሰው መሆኑን ገላጭ ነው። ይህም ሰው ጥልቅ እና ነፃ ማንነት ያለው መሆኑን አብሳሪም ነው። የሚራቀቀው፣ የሚመረምረው የራሱን ማንነት ፍለጋ እንደመሆኑ መጠን እይታው በሰፋ ቁጥር መዳረሻውና በዙሪያው ያሉትን ተጨባጭና ረቂቅ ነገሮችን የሚመዝንበት ወይም የሚመለከትበት መንገድም እየተለጠጠ መሄዱን ነጋሪ አሰነኛኘት ነው።

ሰው ተግባር ላይ የተመሠረተ ሕይወት ስለሚመራ እና ድርጊቱ ደግሞ በምርጫ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሚያስገኘው ውጤት ወደ መርሕ እየተለወጠ ማንነቱን ያፀናል። ይቀርፃል። ሁኔታው በነፃነት ላይ የተመሠረተ ነው። በግጥሙ የመጨረሻ ሁለት ስንኞች ላይ በጥያቄ መልክ የቀረበውም ይኸው ጉዳይ ነው። ‹‹ሚዛኑስ በምን ሚዛን ተከወነ?

ውጤቱስ በማን ተበየነ???››

በማለት የሰፈረው የአመፅ ድምፅ ነው። እንቢተኝነቱ ተግባራቱን ከዘረዘረ በኋላ የሚያሽሟጥጥ መሆኑ ላይ ነው። ሽሙጡ አድጎ በንቅት ድምፀት ‹‹ይህን ሁሉ ዝባዝንኬ ሚዛን አድርጎ የወሰነውና ውጤቱን የሚለካው ማን ነው?›› በሚል ይተካል። ይህ የአመፅ ድርጊት ስለሆነ ከማንም ምንም ዓይነት ምላሽ አይጠብቅም። ዓላማውም ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ እና ሰው ነፃነቱን አሳልፎ እንዳይሰጥ ለአንክሮ የቀረበ በመሆኑ ነው።

በአጠቃላይ ሁለቱ ግጥሞች በጥቅሉ የሰው ልጅ ወይም እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ ባለዕዳ መሆኑን አስረግጠው የሚገልፁ ናቸው። ይህም ሰው መሆንን አፅዳቂ አገላለፅ ነው። ኃላፊነቶቹ የመነጩት ከውስጡ ሲሆን ድርጊቱ የሚያስከትለው ውጤት ዞሮ የሚያርፈው ራሱ ሰው ላይ ነው። የሚራቀቀውም ሆነ ሕግ የሚያወጣው በራሱ ላይ ነው። ሁኔታው የሰውን ላብ ወይም የዘመናት ድካም ዋጋ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

በአንለይ ጥላሁን ምትኩ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You