ከጉንጭ አልፋ ሙግት ይልቅ መፍትሔ ላይ ቢተኮር

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ መወሰኑ የምጣኔ ሀብት ሊቃውንትን ለሁለት ከፍሏል። አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጨምሮ እነ ቴዎድሮስ መኮነን (ዶ/ር) ውሳኔውን ደግፈው ሲቆሙ እነ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ እና አቶ ክቡር ገና ደግሞ በሒደት ሊሆን ሲገባ በአንድ ጊዜ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ተገቢ አይደለም ይላሉ። የእነሱን እሰጥ አገባ ከተለያዩ ምንጮች ቀራርሜ የምመለስበት ሲሆን፤ አሁን ግን ውሳኔው ትክክል ነው አይደለም የሚለው ላይ ጉንጭ አልፋ ሙግት ከማድረግ ይልቅ ውሳኔው ሊያስከትለው የሚችለውን ዳፋ እንዴት መቀነስና ውጤታማ እንዲሆን፤ ምን መደረግ አለበት በሚል አቅጣጫ ማመላከት ላይ ቢተኮር ይበጃል።

ተንሳፋፊ የምንዛሪ ዋጋን ማስተዳደር በተለይ በማደግ ላይ ላሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የሚከተሉትን ስትራቴጂዎችን በመተግበር እንደ ሀገር የሚገጥሙ ፈተናዎችን ቀለል ማድረግ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ውጭ ውሳኔው ትክክል ነው አይደለም የሚለው ክርክር የረፈደበት ስለሆነ እሱ ላይ ችክ ማለቱ ሀገርም ሕዝብም አይጠቅምም።

1.የገንዘብ ፖሊሲ ተለዋዋጭነት፦ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ተመኖችን በማስተካከል የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እና ገንዘቡን ማረጋጋት ይችላል። የዋጋ ግሽበትን በማስተዳደር፣ ማዕከላዊ ባንክ የምንዛሪ ተመን ላይ ያለውን ተለዋዋጭነት ለመቀነስ ይረዳል።

2.የውጭ ምንዛሪ ክምችት፦ የውጭ ምንዛሪ ክምችቶችን መገንባት ከምንዛሪ ውጣ ውረድ አንፃር ቋት ሊፈጥር ይችላል። መጠባበቂያዎች ገንዘቡን ለማረጋጋት በውጭ ምንዛሪ ገበያ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

3.የኤክስፖርት ብዝኃነት፦ በተወሰኑ የወጪ ንግድ ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ ኢኮኖሚውን ከውጭ ድንጋጤ ለማረጋጋት ያስችላል። ሰፋ ያለ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማስተዋወቅ የምንዛሪ ውጣ ውረድ በገቢ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ሊቀንስ ይችላል።

4.የተሻሻለ የንግድ ግንኙነት፦ ከበርካታ ሃገሮች ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ማጠናከር የምንዛሪ ልውውጥ ተጋላጭነትን ይቀንሳል። የንግድ ስምምነቶች የበለጠ የተረጋጋ የኤክስፖርት ገበያ ማቅረብ ይችላሉ።

5.የፊስካል ፖሊሲ ማስተባበሪያ፦ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎችን ማስተባበር የምንዛሪ ተመን ተለዋዋጭነትን ለመቀነስ ይረዳል። ለምሳሌ፣ አስተዋይ የፊስካል አስተዳደር ማዕከላዊ ባንክ ምንዛሪውን ለማረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት ሊደግፍ ይችላል።

6.የፋይናንስ ገበያ ልማት፦ የሀገር ውስጥ የፋይናንሺያል ገበያን ማዳበር የምንዛሪ ዋጋን ለመከላከል ብዙ መሣሪያዎችን ማቅረብ ይችላል። ይህ ንግዶች የምንዛሪ ተጋላጭነትን ለመቆጣጠር ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ አማራጮችን እና የወደፊት ውሎችን ያካትታል።

7.የሕዝብ ግንዛቤ እና ትምህርት፦ የንግድ ድርጅቶችን እና ኅብረተሰቡን ስለ ተንሳፋፊ የምንዛሪ ዋጋ አንድምታ ማስተማር እንደ መከላከያ መሣሪያዎችን መጠቀም ወይም የዋጋ አወጣጥ ስልቶችን ማስተካከል ያሉ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

8.በመሠረተ ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት፦ መሠረተ ልማትን ማሻሻል ምርታማነትን እና ተወዳዳሪነትን ሊያጎለብት የሚችል ሲሆን ይህም የወጪ ንግድን በማሳደግ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ገንዘቡን ለማረጋጋት ያስችላል።

9.ክትትልና ምርምር፦ የምንዛሪ ተመን እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት እና ጥናትና ምርምር ማድረግ ፖሊሲ አውጪዎች ተንሳፋፊ ዋጋ ያለውን አንድምታ እንዲገነዘቡ እና ምላሽ ሰጪ ስልቶችን እንዲያዘጋጁ ያግዛል።

10.ለተጎዱ ዘርፎች የሚደረግ ድጋፍ፦ በምንዛሪ ተመን ተለዋዋጭነት በጣም ለተጎዱት ዘርፎች ማለትም ግብርና ወይም ማኑፋክቸሪንግ ላሉ ዘርፎች የታለመ ድጋፎችን መተግበር በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሱትን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቀነስ ያስችላል። እነዚህን ስልቶች በማጣመር ሀገራችን በተንሳፋፊ የምንዛሪ ተመን ሠርዓት የሚገጥሟትን ተግዳሮቶችና ዕድሎች በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠር ትችላለች።

በሀገር ደረጃ ታሪካዊ የሚባል የመንግሥት ውሳኔዎች ካረፈባቸው ሃገራዊ ጉዳዮች መካከል ከሰሞኑ ሥራ ላይ የዋለው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓትን የሚያቋቁመው ውሳኔን ሊስተካከል የሚችል አለ ለማለት ይቸግራል ይለናል “የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በሁለት አቋም የከፈለው የመንግሥት ውሳኔ” በሚል በሪፖርተር ላይ ባስነበበን መጣጥፉ ዳዊት ታዬ።

በዚህ ውሳኔ ዙሪያ አስተያየታቸውን ካጋሩን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሉ ኢኮኖሚስቶችና የፋይናንስ ባለሙያዎች በአብዛኛው ይህንን ሃሳብ በመጋራት ውሳኔውን በታሪካዊነት ይፈርጁታል። መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መወሰኑን ሲሰሙ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ ትልቁንና አስፈላጊውን ውሳኔ እንደወሰነች ተሰምቶኛል›› ያሉት የፋይናንስ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረመድኅን ናቸው። አቶ አሰግድ፣ ይህ እንዲመጣ ብዙ ታግለው የነበረ መሆኑን በመግለጽ ውሳኔው ትልቅ ዕርምጃ ብለውታል።

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ገበያን በነፃ ገበያ ሥርዓት እንዲገበያይ ያሳለፈው ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ አምስት ቀን ቀደም ብሎ የኅብረት ባንክ 25ኛ ዓመቱ ክብረ በዓል አስመልክቶ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይም ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለችው የገንዘብ ፖሊሲ ለውጥ የውጭ ምንዛሪን በአንድ ጊዜ በገበያ ዋጋ የምትወስን ከሆነ አደጋ ይኖረዋል ብለው ነበር። የውጭ ምንዛሪ ለውጡን ቀስ በቀስ እያሳደገች መምጣት አለባት እንጂ በአንዴ ገበያውን መክፈቷ ተገቢ ያለመሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል።

ይህንን ከተናገሩ ከቀናት በኋላ መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት መወሰኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ፕሮፌሰሩም ውሳኔውን በመቃወም አቋማቸውን በተለያዩ መገናኛ መንገዶች ሲገልጹ ተስተውለዋል፣ ተደምጠዋል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር ይህ ውሳኔ ሊያስከትል ይችላል ያሉትንም ችግር የተለያዩ ጥናቶችን በማጣቀስ አስረድተዋል።

በዚሁ የኅብረት ባንክ መድረክ ላይ የተገኙት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የውጭ ምንዛሪ ገበያውን በነፃ ገበያ ማካሄድ የተሻለው አማራጭ መሆኑን በመግለጽ ከቀድሞ አስተማሪያቸው ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ለየት ያለ ምልከታቸውን አንፀባርቀዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፤ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከችግሯ ለመውጣት የምትወስዳቸው ማናቸውም ዕርምጃዎች ሕመም ያላቸው መሆኑን ነው። ‹‹ሕመም የሌለው መውጫ የለንም። የሚሉት ቴዎድሮስ ሁሉም መውጫዎች ሕመም አላቸው። ነገር ግን አነስተኛ ሕመም የሚያስከትለው አማራጭ መወሰድ አለበት ብለዋል። አሁን መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃም የተሻለ ነው ብለውታል።

‹‹ከዚህ ቀደም ብዙ ብር አትመን ብራችንን አርክሰነዋል። በጦርነቱ መንግሥት ብዙ ብር ነው ያተመው። ብር ብዙ ሲታተም ደግሞ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ብርህ ይረክሳል። ስለዚህ ዶላር መወደዱን ልናስቀረው አንችልም። ትክክለኛው ዋጋ 57 ብር አይደለም። ብር ብዙ ስላተምነው ረክሷል። ጥፋት ነበር ማለት ነው። ጥፋት ካጠፋህ የዚያ ነገር ኮንስኪዌንስ ይኖረዋል። አሁን ኮንስኪዌንሱን ዘሊስት መንገድ የትኛው ነው ብሎ መወሰንን ስለሚጠይቅ አነስተኛ ሕመም ያለውን መርጧል። ስለዚህ መንግሥት ችግሩን አምኖ አሁን የወሰደው ዕርምጃ አነስተኛ ሕመም ያለውና መደረግ የነበረበት ነው›› ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

ኢኮኖሚውን የማያነቃቃ ውሳኔ ቢሆንም፣ በምንዛሪ ለውጥ ነገሮች ሁሉ ይስተካከላሉ ማለት እንዳልሆነ፣ ጎን ለጎን ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ውሳኔው ሕመም ቢኖረውም መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ትልቅ ዕርምጃ ነው ብለዋል። ነገሮች እስኪስተካከሉ እየተባለ እስካሁን መዘግየቱ የበለጠ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሰሞኑን የመንግሥት ውሳኔ እንደሚደግፉት የገለጹት የፋይናንስ ባለሙያ አቶ አሰግድ ገብረመድኅን፣ ይህ የመንግሥት ውሳኔ አስደንጋጭ ሊሆን አይችልም ይላሉ። አቶ አሰግድ አክለውም ‹‹የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ይወሰን በሚል ስንጮህና ስንታገል የነበረ በመሆኑ፣ ዛሬ ይህ ዕውን ሲሆን በመልካም ልንቀበለው የሚገባና በአግባቡ ሥራ ላይ የሚውል ከሆነ ጠቃሚ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።

ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓትን በሚከተል ሀገር ውስጥ እንቅስቃሴዎች በነፃነት መካሄድ እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት አቶ አሰግድ፣ የምርት እንቅስቃሴ መስተጓጎል እንደሌለበት፣ ምርት ማደግ እንዳለበት ነገር ግን ይህ እንዳይሆን እንቅፋቶች በየቦታው መኖራቸውን ጠቁመዋል። ‹‹ግጭቶች አሉ፣ ጦርነቶች አሉ። ስለዚህ የሠላም ማጣታችን ችግር ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ በዚህ ሰዓት ከዶላር የምታገኘውን ጥቅም ይዛ እንዲህ ያለውን ነገር ማስተካከል እንደሚኖርባት መታመን አለበት፤›› ብለዋል።

እንደ ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ያሉ ኢኮኖሚስቶች ሥጋት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በቂ ምርትና አቅርቦት የለም፣ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም ተሸርሽሯል፣ በዚህም ምክንያት ማኅበረሰቡ ገንዘብ ባንክ ከማስቀመጥ ይቆጠባል የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ ቁጠባም ስለማይኖር ባንኮች ሊያበድሩ አይችሉም፣ ይህ ከሆነ ደግሞ ባንኮችም አይኖሩም የሚለውና የመሳሰሉትን ይዘረዝራሉ። በተጨማሪም፣ ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይጠቀሳሉ። አሁንም ባለው ሁኔታ የመንግሥት ውሳኔ ከሥጋቱ ይልቅ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ይህ ሊሆን ይችላል በሚል ሥጋት ውሳኔውን መቃወም ተገቢ አለመሆኑንም አቶ አሰግድ ጠቁመዋል።

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ከወሰዳቸው ትልልቅ ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች መካከል በውጭ ምንዛሪ አሠራር ላይ የወሰደው ውሳኔ ድፍረት የተሞላበት ስለመሆኑ የገለጹት የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ግርማ ደግሞ ውሳኔው ለአምራች ዘርፉ ይጠቅማል ይላሉ። እርሳቸውም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ በነፃ ገበያ መወሰን እንደሚኖርበት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሲገልጹ እንደነበር ገልጸዋል። በተለይ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንጻር ሊኖረው የሚችለው ጠቀሜታ ቀላል እንደማይሆንም እርግጠኛ ነኝ ብለዋል። እሳቸው በሚመሩት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ በመግለጽ የሰሞኑ ውሳኔ ግን ከዚያ ችግር ሊያላቅቃቸው የሚችልበት ዕድል ስለመኖሩ ጠቅሰዋል።

ለምሳሌ አንድ ፋብሪካ ለምርቱ ከሚያስፈልገው ጥሬ ዕቃ አብዛኛውን አግኝቶ አምስት በመቶ የምትሆነዋን ጥሬ ዕቃ ለመሙላት የሚያስፈልግ ጥሬ ዕቃ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ በማጣት ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት አንዳንዴም ከዚያ በላይ ወረፋ የሚጠብቅበት ሁኔታ አለ። ምርቱን ለማምረት የምትጎለዋን ጥቂት ጥሬ ዕቃ ለመግዛት የሚፈለገው የውጭ ምንዛሪ እስኪገኝ ፋብሪካዎች ለወራት የሚቆሙበት አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ይከሰት እንደነበር የገለጹት አቶ አበባየሁ፤ ይህ ችግር ሁሉ ይፈጠር የነበረው የውጭ ገበያ በነፃ ገበያ ሥርዓት ሲመራ ስላልነበር ነው ይላሉ።

ከውጭ ምንዛሪ አሠራር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም የተለየች ስለመሆኗ በሥራቸው አጋጣሚ በተለያዩ አገሮች ባደጉት ጉብኝት መታዘባቸውን ያስታወሱት አቶ አበባየሁ የውጭ ምንዛሪ በትንንሽ ኪዎስኮች ጭምር ሲመነዘርና በእነዚያ ሃገሮች የውጭ ምንዛሪ እንደ ችግር አይታይም። ይህም የሆነበት አንዱና ትልቁ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲገበያይ ወስነው መሥራታቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ። ስለዚህ በየሃገሩ እናይና እንመኝ የነበረውን ነገር እዚህ ለመተግበር መንግሥት የወሰነው ውሳኔ ለእርሳቸውና ለመሰሎቻቸው መልካም ዕድል ይዞ የመጣ ሃገራዊ ኢኮኖሚው ላይም ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ጭምር ገልጸዋል። እንዲህ ያለው የመንግሥት ውሳኔ ጥቅሙ የላቀ ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ አሰግድ ደግሞ፤ የዚህ ውሳኔ አንዱ ማሳያ ሊብራላይዝድ የሆነ ኢኮኖሚ መፈጠሩን በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑ ነው ይላሉ።

በተለይ የውጭ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከመግባታቸው በፊት መንግሥት ይህንን ዕርምጃ መውሰዱ ተገቢና ትክክልም ብለው ያምናሉ። እሳቸውም ይህ እንዲሆን ለዓመታት መታገላቸውን የገለጹት አቶ አሰግድ ዕርምጃው የኢትዮጵያን የንግድ ባሕሪ የሚቀይርና የሚያሳልጥ ነው። በአካባቢው የሚኖራትን የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲይዝ የሚያደርግ ነው፤ በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በ2030 ሪጅናል ኢንተግሬሽን የጋራ ገበያ የሚፈጥሩ በመሆኑ በዚህ ገበያ የማይተካ ሚና የሚኖረው አንዱ መግዣ ዶላር ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ይፋ ማድረጓ በዚህ ቀጣና ያለውን ገበያ ለመምራት ጭምር ያግዛታል። ከዚህም ሌላ የጠነከረ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ ጠንካራ ከረንሲዎችን መጠቀም በመሆኑ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪን ፍላጎትና አቅርቦት ላይ በተመሠረተ የገበያ ሥርዓት መመራት ተወዳዳሪ ገበያ እንዲፈጠር የሚያግዝና በተሻለ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You