መንግሥት ከሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡የውሳኔውን ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች እንዲሁም ፋይዳ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫም፣የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከልና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፣ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስና የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግና ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር የሚችሉ ግቦች እንዳሉት አሳውቋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ ጠንካራ፣ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባትም ተጨማሪ ግቦቹ መሆናቸው አመላክቷል፡፡
የፖሊሲ እርምጃዎቹ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶቻችን ጋር ተጣጥመው እንደሚከወኑና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበሩም ከፍተኛ የክትትልና የድጋፍ ማዕቀፎችን እንደሚዘረጋ እወቁልኝ ብሏል፡፡
‹‹ለዚህም በሁሉም በሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥታዊ ተቋማት በኩል አስፈላጊ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል፤ በሁሉም በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል የፖሊሲ ትግበራ አፈጻጸም ወጥነት እንዲኖር መንግሥት ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያ አመራር መኖሩን ያረጋግጣል›› ብሏል፡፡ መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን አስታውቋል።
አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና ኢ-መደበኛ አሠራር በማስቀረት ተወዳዳሪ፣ ግልጽና አመቺ ወደሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መግባትን የሚያበረታታ እንደሆነ ነው የገለጸው። ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳም አመላክቷል።
ለፖሊሲው ስኬታማነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሰፊና በቂ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገም በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎምና እንዲሁም የገንዘብ ድጎማ ለመስጠትም መወሰኑን ገልጿል፡፡
ይሁንና በተለይ የማሻሻያው አካል የሆነውን የውጭ መገበያያ ገንዘቦችን (Foreign currency) በገበያው እንዲወሰን የማድረግ ውሳኔ በራሱ ይዞት የሚመጣው ጥሩ ነገርም ቢኖርም፤ሊያመጣ የሚችላቸው ችግሮች ስለመኖራቸው ለክርክር የሚያስቀምጥ አይሆንም። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የዜጎች የምግብ ዋስትና ባልተረጋገጠባቸው ሀገሮች የገበያ ሥርዓቱ እስኪለመድና እስከሚረጋጋ ድረስ ለጊዜው የኑሮ ውድነት ማስከተሉ አይቀርም። በሀገራችን ገና ከጅምሩ የኑሮ ውድነቱን የማባባስ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡
አሁን ላይም ወትሮም በቋፍ ያለው የግብይት ሥርዓት ለከፍተኛ ግመታ (Speculation) ተጋልጧል። በዚህም ምክንያት ምርቶችን መሰወር፣ የግብይት ሰንሰለቱን እንዲበጣጠስ ማድረግ ፣ የሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ማናር እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱን የማተረማመስ አዝማሚያዎች በመታየት ላይ ናቸው፡፡ የፖሊሲ ማሻሻያ በተደረገ ማግስት ፣ አዲስ ምርት ከውጭ ሳያስገቡ ዶላር ጨምሯል በሚል የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉም እየታዘብን ነው፡፡
በሕዝብ ላይ መቆመር የማይሰለቻቸው ስግብግብ ነጋዴዎች በምድርም በሰማይም ቅቡል ያልሆነውን ድርጊት ለመፈጸም ጊዜ አላባከኑም። ይህም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያክማል የተባለውን መድኃኒት በጎሪጥ ወደ መመልከት እና ‘አሁንም የዋጋ ንረት ይከሰታል’ ወደሚል የስጋት ቆፈን ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።
በእርግጥ መንግሥትም የፖሊሲ ማሻሻያው በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫናውን ለማቃለል የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ማቀዱን ግልጽ አድርጓል። መንግሥት ከዘራዘራቸው የማሻሻያ እርምጃዎች መካከል ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ውድነት መደጎሚያ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ይጠቀሳል። የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎም መወሰኑን እንዲሁም በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የሚደረገው የሴፍቲኔት እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ የሚደረግ መሆኑ ገልጿል።
ይሁንና ፖሊሲው ገና ተግባራዊ ከመሆኑ በስመ ነጻ ገበያ የሚደረገውን የዋጋ ንረት ሕዝቡን እንደ ሰደድ እሳት እየለበለበው ይገኛል። የፖሊሲ ትግበራውን መንግሥት በብልሃት እንዲጓዝ በማድረግ ሊፈጠር የሚችለውን የኑሮ ውድነት ከወዲሁ መቆጣጠር ካልተቻለ ውጤቱ ከዚህም የተሻገረ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው የገበያው ዘዋሪዎች ሥልጣን፣ ጉልበት፣ ሀብትና ኔትወርክ ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹም በተደራጀ መንገድ ድጋፍና ከለላ አላቸው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ጤነኛ መስተጋብር ሊኖራቸው የሚገቡ ሦስቱ ተዋንያን ማለትም መንግሥት፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ሸማቾች መሆን ሲገባቸው ኮንትሮባንድ ከሚነግዱና ከሚያስነግዱ እስከ ጥቁር ገበያ ዘዋሪዎችና ደላሎች ድረስ ከባድ ተግዳሮት አለ ፡፡
ፖሊሲውን ያመጣዋል የተባለው ውጤት እንዲመጣ ከታሰበ ታዲያ በትግበራ ሂደት በተለይ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል በጥናት ላይ የተመሠረተ ጠንከር ያለ ሪፎርም አስፈላጊ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሕዝቡን ከስግብግብ ነጋዴዎች ዝርፊያ መታደግ የግድ ነው፡፡ በነጻ ገበያ ስም ሕዝብ መዘረፍ የለበትም፡፡ የመንግሥት በዘመቻና በግርግር መደብሮችን በማሸግና ውክቢያ በመፍጠር ገበያው የበለጠ እንዳይተራመስ፣ ምክንያት አልባ የዋጋ ንረትን ለመከላከል የሚያስችል አሠራር መተግበርና ለዚህም ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ ጥራት ያለው አፈጻጸም ማሳየት አለበት፡፡
በፌዴራልም ሆነ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ለታይታ ሳይሆን፣ ሕግና ሥርዓት የተከተለ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወትሮም በጥቁር ገበያ ቁጥጥር ሥር ውሎ ሸማቾች ለብዝበዛ የተጋለጡበት ብልሹው የግብይት ሥርዓት፣ በዘፈቀደ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሳይሆን በተጠና መንገድ መስመር እንዲይዝ ማድረግ ይገባል፡፡
በዚህም አለአግባብ በምርቶች ላይ ዋጋ የሚጨምሩና ምርት የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል። በተጨማሪም መንግሥት ከነጋዴው ጋር ተቀራርቦና ተመካክሮ መስራት ይኖርበታል። ህብረተሰቡ አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግና ምርት የሚያከማች ነጋዴን በመጠቆምና በማጋለጥ ተባባሪ መሆን ይኖርበታል።
በጥቅሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስተዋወቀው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው የውጭ ምንዛሬ የገበያ ሥርዓት ትግበራ ጥንቃቄን ይፈልጋል። የፖሊሲውን ተግባራዊነት በጩሉሌዎች ተጠልፎ መንገዱን ከሳተ ከባድ ሀገራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል እሙን ነው ። የፖሊሲውን ተግባራዊነት በብልሃት እንዲጓዝ በማድረግ መንገዱን እንዳይስት መንግሥት ፈጣን መፍትሔ በመስጠት ረገድ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት። በተለይም ፖሊሲውን በህግ በመደገፍ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ አለበት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ላይ ለባለድርሻ አካላት በተሰጠ ማብራሪያ ላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሕግ አስፈጻሚ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ማንሳታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በእርግጥም በነጻ ገበያ ስም ሕዝብ መዘረፍ የለበትም፡፡ይህ እንደመሆኑም አስፈጻሚ አካላት የፖሊሲ ለውጡን ተከትሎ በህብረተሰቡ ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ከሚያደርጉ ነጋዴዎች ሕዝቡን በመታደግ ኃላፊነቱን ከወትሮ በተለየ መልኩ በትኩረትና በቅንጅት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም