ምርታማነትን ማሳደግ ከኑሮ ውድነት ለዘለቄታው መውጫ መንገዳችን ነው

የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት አሊያም የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበራት በየጊዜው የየሀገራትን የገንዘብ የመግዛት አቅምን፣ የኑሮ ውድነትን ወይም ግሽበትን በተመለከተ መረጃዎችን ያወጣሉ።

በሚወጡት መረጃዎች በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የምጣኔ ሀብቱ የደረሰበት ደረጃ ከዜጎች የገቢ ብሎም ኑሮ መመጣጠን አንፃር የልኬቱ አንዱ መስፈርት ሆኖ ይቀርባል። በተለይ ደግሞ ምጣኔ ሀብቱን ስናነሳ ዜጎች በሂደቱ ውስጥ ያላቸው ተጠቃሚነት ከገቢና ኑሮ ተመጣጣኝነት በኩል መመልከታችን የሚጠበቅ ነው።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ተመጣጣኝ የዋጋ ንረት አስፈላጊ ነው። ምን ያክል ነው የሚለው በጥናት የሚመለስ ቢሆንም ከተወሰነ በላይ ሲሆን ማህበረሰብን ይጎዳል። ሁሉ ነገር በሚወደድበት ጊዜ ኑሮ ይከብዳል። በውድነቱ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት ለኑሮ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ተለይተው ነው።

ከእነዚህ ውስጥ ምግብ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። የምግብ ሸቀጦች በሚወደዱበት ጊዜ ኑሮ በአጠቃላይ እንደተወደደ ተደርጎም ይወሰዳል። እውነታውም ይኸው ነው። ርግጥ ነው የኑሮ መወደድ የዓለም ሀገራት ችግር ከሆነ ሰነባብቷል። በመላው ዓለም ላይ የተከሰተ ጉዳይ መሆኑን የዓለም ባንክም ሆነ የዓለም ገንዘብ ድርጅት በየጊዜው የሚያወጧቸው ሪፖርቶች እያመላከቱ ነው።

ነገር ግን በአደጉት ሀገራት የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚያስችል የዳበረ አቅም አላቸው። የፈለገ ነገር ኑሮ እየጨመረ ቢውል ኑሯቸው ላይ የሚያስከትለው ነገር የለም። የኑሮ ውድነት አቅመ ደካሞች በሆነው ወይም ባላደግነው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ግን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል።

ለምሳሌ ሰሞኑን ሲኤንኤን ባቀረበው የውይይት መድረክ በአሜሪካ ኑሮ እጅግ እንደተወደደ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየተወያዩበት ነበር። አምና ይገዟቸው የነበሩ አንዳንድ እቃዎች፣ ምግቦችና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ እያንዳንዱ አሜሪካዊ የ925 ዶላር ጭማሪ ወይም ግሽበት /ኢንፍሌሽን እንደተጨመረባቸው በውይይታቸው ተጠቅሷል።

ለመጨመሩ ኮቪድ19፣ የዩክሬን ጦርነት፣ የጋዛን ጦርነትና ሌሎች ጉዳዮችን እንደ ምክንያት አቅርበዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ የጠቀሷቸው ምክንያቶች እኛም ሀገር ላይ ችግር ፈጥረዋል። ነገር ግን ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑ ነጋዴዎች የሚጨምሩት ሰው ሠራሽ /አርቴፊሻል ጭማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል።

በኢትዮጵያ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መባባስ መንስኤ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት በተደጋጋሚ ተነግሯል። ቅጥ ያጣው የግብይት ሥርዓት፣ ፈርጣማው የደላሎች እጅ ገበያን ለማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት በሚገባቸው ልክ የቁጥጥር ሥርዓት አለመዘርጋት፣ የማይገባ ትርፍን የሚፈልጉ ነጋዴዎች መበራከት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።

እነዚህን ምክንያቶች መነሻ በማድረግ በዋጋ ንረቱ ዙሪያ እየተወሰዱ ያሉ ማስተካከያ ርምጃዎች በሀገሪቱ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ወይም ጤናማ ያልሆነውን ንረት ማስተካከል እንደሚያስችሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በተለይ የህብረተሰቡ መሠረታዊ የሆኑ የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት በተለያዩ አማራጮችና ምርታማነትን በማሳደግ ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እንደ ቀጠለ ቢሆንም አሁንም ግን የኑሮ ውድነቱ ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየፈተነ ይገኛል።

ይህን የተረዳው መንግሥት ሀገራዊ የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር እና በምግብ ሰብሎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመከላከል በርካታ የመፍትሔ አማራጮችን ተግብሯል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ጤፍን ጨምሮ በሌሎችም የግብርና ምርቶች ላይ ከዚህ ቀደም የነበረን እሴት ታክስ ማንሳት ሲሆን ውሳኔው ገበያው ላይ መረጋጋትን በማምጣት ምርቶች በብዛት የሚገኙበትን አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።

ታዲያ ትግበራው መሬት ወርዶ ሥራው መሰራት ከተጀመረ ከአንድ ወር በላይ አልፎታል። በሂደቱ ግን እስካሁን ገበያው ላይ መረጋጋት አልተመለከትንም። ምግብ ነክ የሆኑ ግብዓቶች አሁንም ዋጋቸው እላይ እንደተሰቀለ ነው። እንዳውም አንዳንዶች የምግብ እህሎች ዋጋ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል።

የዚህ ምክንያት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እለት ከእለት ከሚጠቀማቸው የምግብ አቅርቦቶች ውስጥ የሚጠቀሱት ጤፍ፣ ስንዴ፣በቆሎ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች በሚፈለገው መጠን ገበያ ላይ አለመገኘታቸው ነው። የምርት አቅርቦታችን ያለበት ደረጃ ከፍላጎት ጋር ያለመመጣጠን የዋጋ ንረቱን አምጥቶታል።

የተሻለ ብር ያለው ብቻ ከፍሎ እንዲጠቀማቸው አድርጓል። በገበያው ውስጥ የሚፈለጉ ምርቶች በሚፈለገው መጠን ካልተመረተ አሊያም ገበያ ላይ ካልቀረበ የዋጋ ጭማሪን ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ሁኔታዎች ባልተመቻቹበት ሁኔታ የዋጋ ቅናሽን ማሰብ አይታሰብም። ታክሱ ሲነሳ ዋጋቸው ይቀንሳል ቢባልም የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ግን እሱን እያሳየ አይደለም።

ለምን አልሆነም ካልን ደግሞ የተመረቱት ምርቶች ያለ ተጨማሪ ወጪ፣ ያለ መጉላላት ወደ ገበያ የሚደርሱበት ሁኔታ በየጊዜው ከበድ እያለ መምጣቱ ነው። በተጨማሪም ተጨማሪ እሴት ታክሱ እንደተነሳ ዋጋቸው በአጭር ጊዜ ይቀንሳል ተብሎ አይታሰብም። በርግጥ የእህልና ጥራጥሬ የግብርና ምርቶችና የበሰሉ ወይም የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች በአዲሱ መወሰኛ መሠረት ነፃ መደረጋቸው በመሠረታዊነት ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል።

ሆኖም ግን የታሰበው ሳይሆን ነገሮች ባሉበት መቀጠላቸው የተወሰዱት ማሻሻያዎች ተፈፃሚነት ላይ ዜጎች ጥያቄ ማንሳታቸው የሚጠበቅ ነው። ማሻሻያዎቹ የታለመላቸውን ግብ አለመምታታቸው ከአቅራቢው እስከ ተቆጣጣሪዎቹ ያለውን አሰራር መፈተሽ እንደሚገባ የሚያመላክት ጉዳይ ነው። የሕግ የበላይነት በማስከበርና ተጠያቂነት በማስፈን ረገድ የተሰሩ ሥራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ እንዳልሆኑ የሚጠቁም ነው።

የቁጥጥር ሥራ የሚሰራው አካል የማስፈፀም አቅሙ ደካማ መሆኑንም ያሳያል። ማስፈፀም የሚችል ተቋም በደከመ መጠን የሚወጡ የመንግስሥ ስትራቴጂዎች ለማህበረሰቡ እንደማይጠቅሙም ማሳያ ይሆናል። ይህም በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱ ማህበረሰቡ ላይ ጫናው እንደበረታ ቀጥሏል። ዜጎች መግዛት እየፈለጉ እንዳይገዙ ገበያው ጫና ፈጥሮባቸዋል።

ብዙሃኑ የመግዛት አቅሙ እየተዳከመ ስለሄደ የሚጠቀማቸውንና የሚገዛቸውን መጠን በመቀነስ እየተጠቀም ይገኛል። ይህ ማለት ታክሱ ቢነሳም አቅርቦት አብሮት በመቀነሱ የኑሮ ጫናውን ሊያግዝ አልቻለም። አሁንም ዜጎች በዋጋ ግሽበቱ የተነሳ ኑሯቸው ላይ ጫና መፈጠሩ በግልፅ እየታየ ነው።

ችግሩን ለመፍታት መንግሥት አቅርቦት ላይ የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል። ቁጥጥሩንም ከቀደመው በተሻለ መሥራት የቤት ሥራው ሊያደርግ ይገባል። የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት ከተቻለ ከቀረጥ ነፃ አካሄድ በአግባቡ ተተግብሮ ዜጎች ከኑሮ ጫናው ይላቀቃሉ።

ግብይቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሳለጥ ማድረግም ያስፈልጋል። ቅጥ ያጣውንና እየተባባሰ የመጣውን የግብይት ሥርዓት በሕጋዊና በአስተዳደራዊ መንገዶች ማስተካከል ይገባል። በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከግማሽ በላይ ያለው የዋጋ ግሽበት ሰው ሠራሽ አሊያም ሴራን መሠረት ያደረገ ነው። ጎረቤታችን ኬንያ ወይም ሱዳን አሊያም ጅቡቲ የሚገዛ አንድ ልብስ ኢትዮጵያ ሲመጣ ሶስትና አራት እጥፍ የሚጨምርበት ምንም ምክንያት ሊኖረው አይችልም።

ለዋጋ ንረቱ አሁንም ሰው ሠራሽ ምክንያት የሚታከልበት ከሆነ የገበያ ሰንሰለቱ በዜጎች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ የገዘፈ ይሆናል። ስለዚህ መንግሥት የራሱን ሥርዓት/ሲስተም ከባለሀብቱ ሥርዓት ነጥሎ ማየት አለበት። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ርምጃ መውሰድ ይገባዋል። ገበያው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ የሚስችል አሠራርን መዘርጋትና ገበያውን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውንም ክስተቶች መቆጣጠር ያስፈልጋል።

በርግጥ ይህ ችግር በአደጉ ሀገራት ላይ ሙያዊ በሆነ መንገድ የሚወዳደሩ ቢዝነሶች/ድርጅቶች ወደ ሀገር ሲገቡ የሚፈታ ቢሆንም ዓለም አቀፍ አሠራር በመዘርጋት ዘልማዳዊ መንገድን መተው ግድ ይላል። ሙያዊ በሆነ መንገድ የማይሰራ ቢዝነስ /ግብይት ባለበት ሀገር ውስጥ ዜጎችን የሚጎዳ ሰው ሠራሽ ግሽበት መከሰቱ የማይቀር ነውና።

በአምራችና ሸማች መካከል ያለውን የፍላጎት እርቀት ማጥበብ አስፈላጊ ነው። በብዛት ከማምረት ይልቅ የምትሸምት ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በዜጎቿ ላይ የተፈጠረውን የኑሮ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ አሁንም መፍትሔ ያሸዋል። አንዱ መፍትሔ ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ ምርት እንዲኖር ማድረግ ነው።

ይህን ማድረግ ከተቻለ የዜጎችን የቀን ገቢንም ማሳደግ ይቻላል። ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ሲያተኩሩ፣ የማምረት አቅማቸውን በእጅጉ ሲያስተካክሉ፣ የማምረት ተነሳሽነታቸው ብቻም ሳይሆን አምርተው ለራሳቸውም ለሌሎችም መትረፍ የሚችሉበት መንገድና ሁኔታ ይመቻቻል።

ሌላኛው መፍትሔ የማክሮ ኢኮኖሚን አሠራር በአግባቡ በመዘርጋትና በማስፈፀም እንዲሁም ሥራን በክህሎት መሥራት ከተቻለ ምርትን አሳድጎ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። የብዙ ሀገራትን እጣ ፈንታ የቀየረው ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከቀደመው በበለጠ መሥራት ሲቻል ነው።

አንድ ዜጋ ሥራ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በልምዱ፣ በእውቀቱ፣ በክህሎቱ ውጤት ማምጣት የሚችልበት ዘርፍ ላይ ሥራ ሲያገኝና ሲሰራ ውጤታማ ሆኖ የተሻለ ምርት ማምረት ይችላል። የተሻለ ምርት ሲገኝ በሀገሪቱ ያለውን ፍላጎት ማርካት የሚችል ምርት ሀገሪቱ እያቀረበች ነው ማለት ነው።

የተሻለ ምርት አምራች የሆነ ዜጋ የተሻለ ገቢ ያገኛል። የተሻለ ገቢ አለው ማለት ደግሞ ምርትን መጠቀም የሚችል ዜጋ አለ ማለት ነው። በዚህም አቅርቦትና ፍላጎት ይጣጣማል፤ ምርት እንዲትረፈረፍ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በመሆኑም በምርታማነት ላይ በተለይም በስንዴ እርሻ ላይ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች የምግብ ምርቶች ማስፋትና የገበያውን ሥርዓት ማስተካከል ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም።

ባለፈው ወር ተስፋ የታየበትን የዋጋ ግሽበት ላይ የታየውን መሻሻል የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጠንካራ ምርታማነትን በሥርዓት ማስኬድ ያስፈልጋል። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያ ላይ የሚቀርብበትን መንገዶች ምቹ ማድረግ ደግሞ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You