የረሲብ ጠይብ ኤርዶጋን አፍቃሪ ደጋፊዎች፤ ትናንትን ዋቢ በማድረግ ፐሬዚዳንቱ «ቱርክን ከፖለቲካና ምጣኔ ሀብታዊ ውድቅት እንድታንሰራራና በአጭር ጊዜ ውስጥ በተዓምራዊ የዕድገት ጎዳና ላይ ሽምጥ እንድትጋልብ ያስቻሉ የዘመናችን ታላቅ መሪ ናቸው ሲሉ» ያሞካሹዋቸዋል። ባሳለፍነው ዓመት በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ለበርካታ ዓመታት የቱርክን ፖለቲካ ተቆጣጠረው ለቆዩት ኤርዶጋን ተጨማሪ አምስት ዓመታትን በሥልጣን እንዲቆዩ ድምፃቸውን ሰጥተዋቸዋል።
እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ ቱርክን ለአስራ አንድ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ኤርዶጋን እ.ኤ.አ ከ2014 አንስቶም እስካሁን አገራቸውን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ይህ የሥልጣን ቆይታቸውም በአመዛኙ አልጋ በአልጋ ሆኖ መቆየቱን ይነገራል።
ምንም እንኳን ከሦስት ዓመታት በፊት የመፈንቅለ መንገሥት ሙከራ ቢካሄድባቸውም፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ የህዝብ ድምፅ አግኘቶ እርሳቸውንም ሆነ ፓርቲያቸውን የሚገዳደር ተቀናቃኝ ግን አልገጠማቸውም።
ይሁንና ከቀናት በፊት በኢስታንቡል በተካሄደ ምርጫ ፓርቲያቸው ወግ አጥባቂው የፍትህና ልማት ፓርቲ /ኤ ኬ ፒ/ በተቃዋሚው ሪፐብሊክ ፓርቲ (CHP) አስድንጋጭ የተባለ ሽነፈት እንደደረሰበት ታውቋል።
ይህ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ባሳልፈነው መጋቢት ወር መጨረሻ በተካሄደው ምርጫ የተቃዋሚው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ኤክረም ኢማም ኦሎ ያሸነፉ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለቱ መደገሙ ይታወሳል።
በዳግም ምርጫው «ሁሉም ነገር መልካን ይሆናል» በሚል የምረጡኝ ቅስቀሳ መርህ የተወዳደሩት የተቃዋሚው ሪፐብሊክ ፓርቲ (CHP) እጩ ኤክረም ኢማም 54 ነጥብ 2 በመቶ የህዝብ ድምፅ ማግኘታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ የኤርዶጋን ፓርቲ ደግሞ 45 በመቶ የህዝብ ድምፅ ማግኘቱም ተመላክቷል።
የ 49 ዓመቱ ኤክረም ኢማም፤ በምርጫው ካሸነፉ በኋላ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ፊት ተገኝተው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በርካቶችም ሰውየው የከተማዋን ህዝብ ድምፅ ለማግኘት የህዝቡን ፍላጎት በመንተራስ የተሻለ አማራጭ በማቅረብ ብቃታቸውና የማሳመን አቅማቸው አድንቀውላቸዋል።
ከዚህ በአንፃሩ ውጤቱ ለኤርዶጋንና ለፓርቲያቸው ከባድ ኪሳራ ሰለመሆኑ በስፋት እየተዘገበ ሲሆን፤ ከ17 ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ በአሁኑ ወቅት የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ ተዳክሟል እንዲባልም ምክንያት ሆኗል።
ፕሬዚዳንቱና ፓርቲያቸው ከወራት በፊት በተካሄደ አካባቢያዊ ምርጫ በአገሪቱ ዋና መዲና አንካራም መሸነፋቸውን ያስታወሰው ኤፒ የዜና አውታር፤ አሁን ደግሞ ኢስታንፑል ላይ መሸነፋቸው ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆንባቸው አትቷል።
በዚህ እሳቤ የሚስማማውና ፓርቲውም ሆነ ፕሬዚዳንቱ አስደንጋጭ ሽንፈት የደረሰባቸው መሆኑ በሰፊው የተነተነው አልጀዚራም፤ ሽንፈቱ ከባድ መሆኑንና ገዥው ፓርቲ በኢስታንቡል ሲሸነፍ ከ 25 ዓመት በኋላ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን አመላክቷል።
የኤቢሲ ዜና እውታሩ የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሐፊ ኤሪን ሃንድሊ በበኩሉ፤ «ታሪካዊቷና ከአገሪቱ ሦስት ታላላቅ ከተሞች አንዷ የሆነቸው ኢስታንቡል ከ 25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃዋሚዎች እጅ ወደቀች » ሲል አስነብቧል።
በአንካራ ቢልኬንት ዩኒቨርሲቲ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዘርፎች የሚያስተምሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ብሬክ ኢሴን በበኩላቸው፤ ገዥው ፓርቲ በኢስታንቡል በመሸነፉ የሚያደርሰበትን ከባድ ቀውስ ለመሸሸግ በሚል ምንም ያልተፈጠረ የሚመስል ድራማ መሥራቱን ጠቅሰው፤ ፕሬዚዳንቱ በአገር ውስጥ ከባድ የቤት ሥራና የፖለቲካ ተፋላሚ እንደመጣባቸው አስረድተዋል።
ከሁሉም በላይ በኢስታንቡል የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ማሸነፉን ተከትሎ በቱርክ የሚኖሩ ስደተኞች ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውም እየተነገረ ነው። ሥጋቱ የተፈጠረው ተቃዋሚ ፓርቲው ስደተኞችን የማይፈልግ መሆኑና ምርጫውን ካሸነፈ በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን በተለይ ደግሞ የሶሪያ ስደተኞችን እንደሚያስወጣ መዛቱን ተከትሎ ነው።
በአሁኑ ወቅት በቱርክ ከሶሪያ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ከሦስት ሚሊየን በላይ ስደተኞች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።የዥው ፓርቲ በኢስታንቡል ከተማ የደረሰበት ሽንፈት በስደተኞች ላይ ያለው ለዘብተኛ አቋም የወለደው ስለመሆኑም የሚገልፁም አሉ።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በተለይ እ.ኤ.አ 2016 ከተሞከረውና ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ፕሬዚዳንቱ እጅጉን አፋኝ እየሆኑ መምጣታቸው፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተንገጫገጨ መሆኑና ይህን ተከትሎም ባለሀለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ፣ በተለይም ሥራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱ የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ ኢስታንቡልን ለማጣት ዋና ዋና ምክንያቶች ስለመሆናቸው የሚያትቱ ፀሐፍትና የፖለቲካ ምሁራን ተበራክተዋል።
የኢስታንቡሉ ሽንፈት ከሁሉም በላይ አገሪቱ ከአራት ዓመታት በኋላ በምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ሲሆን፣ ለገዥው ፓርቲም ቀይ መብራት ሰለመሆኑ የሚጠቁሙ መገናኛ ብዙሃንም በርክተዋል።
የዚህ እሳቤ ተቃራኒዎች በአንፃሩ፤ ኤርዶጋን ያጡትን የህዝብ ድምፅና አመኔታ ቀጣዩ ምርጫ እስከሚደርስ መልስ የሚያስገኙላቸውን ተግባራት ሊሠሩ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።ይህን ለማድረግም በቂ ጊዜ እንዳላቸውም አመላክተዋል። ሽንፈቱም ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ በፓርቲያቸው ውስጥ ሁነኛ የተባለ ለውጥ እንዲያካሂዱና በተለይ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር እንዲያድረጉ ሊገፋፋቸው እንደሚችልም ተገምቷል።
የኤርዶጋንና የኢስታንቡል ዝምድና እ.ኤ.አ ከ1994 ነው የተጀመረው።ለአራት ዓመታት በዘለቀው የከማዋ ከንቲባነት ሃላፊነታቸውም ፈርጀ ብዙ ችግሮች ውስጥ በነበረችው ከተማ ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣታቸው በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑ ይነገራል።
ፕሬዚዳንቱ ከንቲባ ሆነው የፖለቲካውን ህይወታቸውን ያጠናከሩባትን ኢስታንቡል ክምንም በላይ ልዩ ስፍራ እንደሚሰጧት ይገለፃል።የዚህችን ከተማ ህዝብ ድምፀ ማጣት ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በተደጋጋሚ ሲገልፁም ተደምጠዋል።
ይህን እሳቤያቸውን ዋቢ በማድረግ አልሞኒተር ላይ ሰፊ ትንታኔ ያስፈረው ካድሪ ጉርሴል ‹‹ፕሬዚዳንቱ በኢስታንቡል ተሸነፍን ማለት፤ በመላ ቱርክ ተሸነፍን ማለት ነው›› ሲሉ መደመጣቸውንም በዋቢነት አስታውሷል።
«ከ15 ሚሊየን ህዝብ በላይ በሚኖርባትና የአገሪቱ ፖለቲካ ምህዋር እንብርት ሰለመሆኗ በሚታመነው ኢስታንቡል መሸነፍ በመላ ቱርክ ከመሸነፍ አይተናንስም፤ይህ ውጤትም የኤርዶጋንን ከቱርክ የመፋታት ሥጋት እውን ያደርገዋል» ሲል አትቷል።
የኢስታንቡሉ ምርጫ ውጤት የቱርክን ፖለቲካ በተለየ አቅጣጫ መዘወሩ አይቀሬ ስለመሆኑም ተጠቁሟል። በዚህ ረገድም የቮክስ ኒውስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ፀሐፊዋ ጄን ኪርባጄን የተቃዋሚው ሪፐብሊክ ፓርቲ (CHP) እጩ ኤክረም ኢማም በመዲናዋ በሚከናወኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ በገዥው ፓርቲ አመራሮች ይፈፀማሉ የተባሉ የሙስና ወንጀሎችን ለማጋለጥና የኤርዶጋንን ሙሉ ሥልጣን ለመገዳደር ምቹ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው እንደሚችል አብራርታለች።
የኢስታንቡል ሽንፈት በገዥው ፓርቲ ላይ የሚያድርሰው ኪሳራ ቀላል ባይሆንም፣ አሁንም የፖለቲካ ሚዛኑ ለፕሬዚዳንቱ እንደሚያደላ የሚገልፁም አልጠፉም። በዚህ ረገድ ሰፊ ሃተታቸውን ዘ ኔሽን ላይ ያሰፈሩት ዶክተር ሲሞን ዋልድማን እ.ኤ.አ በ2017 በህዝበ ውሳኔ የቱርክ ሕገ መንግሥት መሻሻሉ ለኤርዶጋን ፖለቲካዊ የሥልጣን ኃይል ይበልጥ እንደቸራቸው ጠቅሰዋል።
የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የህዝብ እንደራሴዎችን፣ ሚኒስትሮችንና ምክትል ፕሬዚዳንቶችን በቀጥታ መሾም እንዲሁም ወታደራዊ ሃይሉን በበላይነት መቆጣጠርንና በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ላይ ጣልቃ የመግባት ፈቃድ ሰጥቷቸዋል» ያሉት ዶክተር ዋልድማን፤ ይህ ከፍተኛ ሥልጣንም መጪው ጊዜ ለኤርዶጋን ከባድ እንዳይሆን ከበቂ በላይ ዋስትና እንደሚሰጣቸው ያብራራሉ።
ይህንን ሃሳብ የተጋሩት በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ፀሐፍትም፤ ፕሬዚዳንቱ ሕገ መንግሠቱን በህዝበ ውሳኔ በማሻሻል ያገኙት ሁለንተናዊ ሥልጣንን እንዳሻቸው እየለዋወጡ በመፈፀም ከ25 ዓመታት በኋላ ኢስታንቡልን የነጠቋቸውን የተቃዋሚው ሪፐብሊክ ፓርቲ እጩ ኤክረም ኢማም ቀጣይ የሥራ ህይወት ከባድ እንደሚያደርጉባቸው አስምረውበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011