ማንኛችንም የማንክደው ዓለም ሁሉ የሚመሰክረው አንድ እውነታ አለ። ኢትዮጵያ ሀገራችን ከማንም በላይ የአንጡራ ሀብት ባለቤት ናት። ከኛ ልጆቿ በስተቀር ክብሯን ማንም ያልነካው ባለግርማ እመቤት ናት። የ3 ሺህ ዘመናት ታሪክ ያላት ወርቃማ ባለታሪክ ናት።
ከምንም በላይ ደግሞ ሁሉም የሚመኟትና የሚጎመዧት ድንግል ንግሥት ናት። ገና ምኑም ያልተነካ አንጡራ ሀብት፣ እግዜር እንደፈጠረው ቁጭ ያለ ድንግልና፣ የሚመለከቷት እንጂ የማይገቡባት ገነት፣ የሚመጻደቁባት እንጂ የማይጸድቁባት መቅደስ፣ የሚኖሩባት እንጂ የማያኖሯት እርስት ላይ ነን።
የወደቁት ተነስተው በእግራቸው ቆሙ። ኋለኞችም ተስፈንጥረው ፊተኞች ሆኑ። የሞቱት መቃብር እንኳን ሳር አብቅሎ ለመለመ። ተርበው የጫማ መርገጫ የበሉም ዳቦ ማደል ጀመሩ። እኛ ግን የተፈጥሮ ድንግልናን ታቅፈን ህልም ስናይ 3 ሺህ ዘመን ባተ። ከሰው ዘር መጀመሪያ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ድንግልና ለምን? ፈጣሪ በምድር ባርኮ የሰጠንን፣ ብሉ ደግሞም አብሏት ያለንን በረከት ይዘን ስንዘምርለት ብቻ የምንኖረው ለሰማይ ቤት ወይንስ ከሩቅ ለሚመጣው ትውልድ አስበን?
ያለን የተሰጠን ኩራት ነበር። አላወቅንም፤ አልገባንም እንጂ አሁን ሀፍረት ነው የሆነብን። ዓለም ሁሉ የሚፈልጋትና የሚያውቅላትን ሀገር አሁን ግን ዓለም ሁሉ ቁልቁል የሚያያት ምስኪን ምንዱባን አድርገናታል። ማን? እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ ሁላችንም። ሁሌም ግን የምንለው “እነርሱ!…እሷና እሱ” ነው። “እነርሱ” የምንለው ማንን ነው? እነርሱስ እነማን ናቸው? “እነ እገሌ እኮ ጥሩ ሠርተው ነበር፤ እነ እንቶኔ ግን ይህችን ሀገር ቀበሯት” የምንለው የለንም።
የምናወራው ስለ 3ሺህ ዘመን ድንግልና ነውና ሁላችንም ባለዕዳዎች ነን። “ኢትዮጵያ ማለት እኮ አፈሯ ገራገር፣ ምድሯም ለምለም ነው” እንላለን። ግን አፈራቸው ደረቅ፣ በድንጋይ ላይ የሚኖሩት እነዚያ የምናውቃቸው ሀገራት ዛሬ የት ደርሰዋል? “ሀገራችን በጠላት ያልተወረረች፣ ዓለምን ሁሉ ያንቀጠቀጠች እኮ ናት” እንላለን እንሸልላለን።
ግን በጠላቶቻቸው እግር ስር ወድቀው የተንቀጠቀጡ ዛሬ ያሉበትን ስንመለከት ከቶ አናፍርም ይሆን? በቀዝቃዛ የድንጋይ ዋሻ ውስጥ ተቀምጠን የድሮ አያቶቻችንን ጀብዱና ለተራበው እንጀራና ዳቦ የለገስንበትን ዘመን ስናወሳ ሰውነታችን ከቶ ስለምንስ አይሳቀቅም?
ታሪክ አናውራ፣ በነበረንም አንኩራ አይደለም። ካላከልንበት እነርሱንም እጀ ሰባራ አመድ አፋሽ እናደርጋለን። ቀጣይ ለኛም የሚወራልንን የራሳችንን ታሪክ መሥራት አለብን። ስንሠራ ስለአሁንም ሆነ ስለድሮው የሚያወራልን ብዙ ነው። ሁላችንም በአፈ ታሪክም ሆነ ከብራናና ከመሰል መዛግብቶች ላይ ስንሰማው የኖርነው ነገር አለ።
“ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ማዕድናት የተከበበችና የበለጸገች ናት። የእኚህንም መገኛ የሚያውቁና በአደራ ተቀብለው በምስጢራዊ መንገድ ከትውልድ ትውልድ የሚያቀባብሉ የተመረጡ ሰዎችም አሉ” ለሚለው ማናችንም እንግዳ አይደለንም። ታዲያ እኛ እየተራብንና በችጋር እየተጠበስን ይህንን እውነት፣ ይህንን ድንግልና ደርሶ የሚበላው ትውልድ የትኛው ትውልድ ነው? ወይንስ እንደ ታቦት ጽላት በክብር ይዘን እስከ ምጽአት ቀን ልንጠብቅ ነው? ያልገባን፣ ያልተረዳነው አንድ ነገር ሳይኖር አይቀርም።
አለኝ አለኝ ማለት ብቻ ዋጋ ቢስ ነው። “ኩራት እራት አይሆንም” እንደምንለው ሁሉ ጽድቅ የሌለበት የድንግልና ዝማሬ ኩነኔ ነው። ስብከት አይሁንና በቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ የሚገኝን አንድ ታሪክ ያስታውሰናል። አንድ ጠቢብ ለገበሬዎቹ ለእያንዳንዳቸው እንቁ ፍሬ ሰጣቸው። በለምለም መሬት ላይ የዘራውም ፍሬው መቶና ሃምሳ ብዙ እጥፍ አፈራለት። ጠቢቡ መጥቶ በተመለከተ ጊዜም እጅግ አመሰገነው።
ቀሪዎቹን እንዝላልና ወደ መጨረሻው ሰው መጣና ፍሬውን ከወዴት አኖርከው? ባለው ጊዜም ቃል በቃል ባይሆንም እንዲህ ነበር የመለሰው “ጌታዬ! የሰጠኸኝን ሌባ እንዳይሰርቀኝና እንዳይበላሽ አድርጌ በታማኝነት አኑሬልሀለሁና እንካ” ሲል ያቺኑ አንድ ፍሬ መልሶ ሰጠው። የኛም ነገርና የሀገራችን ድንግልና ልክ እንደዚሁ ታሪክ ነው። የሰጠን እንድንሰራበት፣ ፍሬ አፍርቶ ብዙ እጥፍ እንዲሆን እንጂ በአደራ ይዘን እንደተሰጠን ሳንነካው ደብቀን እንድናኖረው አይደለም። ሀገራዊና ምስጢራዊ ሀብት ይዘን የምንቀባበልም ብንኖር በመጨረሻው ስንጠየቅበት እንዲሁ ነው።
ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊ ሌላ ማንም የላትም። ገራገሩን አፈሯን አርሰን ካልዘራን፣ አዝመራውን ካላጨድን፣ ወቅተን ጎተራውን ካልሞላን የልምላሜ መዝሙራችን ከንቱ ነው። ከገበሬ ገበሬ፣ ከጠቢብ ጠቢብ፣ ከምሁር ምሁር አለን። ሁሉንም የዚህችን ሀገር ጣጣ ገበሬው ላይ ጥለን ቀሪ አብዛኛዎቻችን ግን አውሮፓና አሜሪካ ነን። ዛሬ ላይ የት አለ ምሁሩ? የትነው ሳይንቲስቱ? ወዴት ነው ዶክተሩ? ብለን ብንፈልግ የአብዛኛዎቹ መገኛ ከዚያ ያላለፈ ነው። ዕውቀትና ጥበባችንን የምንጠቀምበት ሀገራችንን ለማበልጸግ ሳይሆን ከሀገራችን ሸሽተን ለማምለጥ ነው።
በስኮላር ሺፕ የበለጠ ዕውቀትና ክህሎት አዳብረን ለዚህች ሀገር ስንታሰብ አብዛኛዎቻችን ግን ቀልጠን እንቀራለን። ሀገር ወክለን ለስፖርት ሄደን እንኳን በዚያው እንጠፋለን። “ኑሮን ለማሸነፍ፣ ፖለቲካን በመጸየፍ…” እያልን ራሳችንና ሕዝባችንን እናሞኛለን። ናሳን ጨምሮ ዓለማችን ላይ አሉ በተባሉ ግዙፍ የምርምርና የቴክኖሎጂ ማዕከላትና በተለያዩ ትላልቅ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ማግኘት የሚያስገርም አይደለም።
ለየባዕድ ሀገሩ ተአምራትን እንሠራለን። ጠንቋይ ግን ለራሱ አያውቅም። ሀብታሙም ድሀውም፣ የተማረም ያልተማረም፣ ፕሮፌሰር ነጋዴውም ሁላችንም ኑሮ ከብዶን ከሀገር ከወጣን፣ ሁላችንም ፖለቲካን ፈርተን እግሬ አውጪኝ ካልን፣ ታዲያ ማነው ለዚህች ሀገር በመስዋዕትነት የተፈረደበት? ሁሉም ራሱን ከደሙ አንጽቶ ገለል ሲል ማንስ ለብቻው የበላው ዕዳ አለበትና እዚህ ቁጭ ብሎ ለሀገሩ ሻማ ይሆናል? በሀገርህ ስለሀገርህ ኑር ተብሎ የገዘቱትም ሆነ ያስማሉት ማንም የለም። እያንዳንዳችን፣ ሁላችንም ተጠያቂ ባለአደራዎች ነን።
ቢመቸውና ቢቀናው ሁሉም ሰው ከአውሮፓና አሜሪካ ደርሶ የሚያስገባው ስለት ካለበት የዚህችን ሀገር የድንግልና ዳቦ ቆርሶ የሚያበላት ማነው? እዚህ ሀገራችን ውስጥ የተቀመጥንስ ዕድሉን ባለማግኘታችን አማራጭ ስላጣን ነውን? ከሆነስ ብንኖርም የለንም። ሌላኛው ያልተገረሰሰ ድንግልናችንም ባዕድ ናፋቂነታችን ነው። አንውጣ አንሥራ አይደለም፤ የትም ዓለም ያለ ነውና። ነገር ግን ያለንን ይዘን እንደወጣን ቀርተን፣ እንደወጣን አንሙት።
ሀብታም ሀገር አለችን። ውብና ድንግል እናት አለችን። ግን አልሠራንባትም፤ አልሠራንላትም። አልበላንም፤ አላበላናትም። የምንኖረው የተሰጠንን ህይወት አይደለም። ማስተዋል ካቃተን ውቧን ድንግል ሀገር የኮሰሰች አሮጊት አድርገን፣ ወርቋን እንደ ድንጋይ ተንተርሰን እንኖራለን። የኛ ችግር ችግራችንን የምንመለከትበት መንጽርም ጭምር ነው። ተጠላልፈን ከወደቅንበት ተሠርተንና ሠርተን ለመነሳት ስንችል ስለወደቅንበትና ስለቆምንበት የኋላ ዘመን እያነሳን እንወድቃለን።
እኔ እንዲህ አደረኩና ለሀገሪቱ ምንስ ልፈጠር… አንበል። ምክንያቱም ሁሉም እንዲህ ነው የሚለው። እንዲህ እያለ ነው ከኃላፊነቱ የሚሸሸው። በሀገራችን ለሀገራችን ብቻ ሠርተን፣ አበልጽገን መበልጸግ ስንችል ቁራሽ እንጀራ ፍለጋ ባዕድ ለባዕድ፣ በረሀ ለበረሀ እንዋትታለን። እስከመቼ ማንን እንጠብቅ? ለምለም እንጀራ እንጂ ለምለም የድንግልና ተስፋ እየበላን ብቻ አንኑር!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም