የቴፒዋ እናት

በሆቴሉ በረንዳ ላይ ተቀምጬ ቡና እየጠጣሁ ነው። አካባቢውን እየቃኘሁና በተፈጥሮ ፀጋ እየተደመምኩ፤ ዓይኔ ድንገት ፀጉራቸውን ባጭሩ የተቆረጡ፣ ረዘም ያሉና እርጋታ የሚታይባቸው እንደነገሩ ለብሰው ነጠላ ጣል ያደረጉ ሴት ላይ አረፈ። ገጽታቸው ልብ ያስደነግጣል። መካከለኛ እድሜ ላይ ቢሆኑም ውበታቸው አልደበዘዘም። በወጣትነታቸው ሽክ ባለ አለባበስ በዓይነ ህሊናዬ ሳልኳቸው፤ ይጠብቋቸው ወደነበሩ እንግዶች ሲያመሩ ዓይኔ እየተከተላቸው ነበር።

እንግዶቹ ሰፋ ያለ ጽሑፍ የያዘ ወረቀት እያሳዩዋቸው ወደእርሳቸው ያመጣቸውን ጉዳይ ያስረዷቸዋል። እንግዶቹ ሲያቀርቡላቸው የነበረው የትብብር ድጋፍ ጥያቄ ነበር። ‹‹የአቅሜን አግዛለሁ›› ብለው እንግዶቹን ሲሸኗቸው ሰማኋቸው። ፍቃደኝነታቸውን ገልጸው ወደጉዳያቸው ለመሄድ ሲዘጋጁ እኔም ላልፋቸው አልፈለኩም ሰላምታ ሰጠኋቸው።

እርሳቸውም በአክብሮት ምላሽ ሰጡኝ። የጎረቤት ልጅ ታማ እርስዋን ወደ ሕክምና ለመውሰድ መቸኮላቸውን ነገሩኝ። ለጎረቤት ልጅ መጣደፋቸው ቅርበታቸው ምን ያህል ቢሆን ነው? ወይንስ መልካምነታቸው? የሚለው ሃሳብ ፈጥኖ ወደ አእምሮዬ መጣ። ይሄን ማሰቤ፤ ጎረቤት ለጎረቤት ደንግጦ መድረስ፣ የችግሩ ተካፋይ መሆን የቆየ የኢትዮጵያውያን ባሕል መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም። ነገር ግን ሁኔታዎች እንደድሮ አይደሉም። የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴቱ ሳስቷል፣ ተብሎ አብዝቶ በሚነገርበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለውን ነገር በመስማቴ አዲስ ግኝት አደረኩት። የቆየው መተሳሰባችንን በእኚህ ሴት በማየቴ ደስም ብሎኛል።

እኚህ ሴት የጎረቤታቸው ልጅ ምኗን አመማት? ሐኪም ቤት ሄደች? አላሉም። እንደሰሙ ሐኪም ቤት ሊወስዷት ተዘጋጅተው ከቤታቸው ወጡ። እንዲህ ያለው መልካምነት ተፈጥሯዊም ጭምር ነው። መታደልም ነው። ሰብዓዊነት ያላቸው ሴት እንደሆኑ በአጭር ጊዜ ቆይታችን ተረድቻለሁ።

ማህበራዊ ኑሯቸው

ወይዘሮ ትጓደድ ባንተይርጋ ይባላሉ። ሲተዋወቁኝ ስማቸው የተለመደ ባለመሆኑ ግር ሲለኝ አይተው ትኩራ፣ ትዝናና፣ ትለመን እንደማለት ነው ብለው አስረዱኝ። ከወይዘሮ ትጓደድ ጋር የተዋወቅነው ተወልደው ባደጉበት ቴፒ ከተማ ነው። ቴፒ ከተማ ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል በፊት በአዲስ መልክ በተዋቀረው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ውስጥ ትገኛለች።

ወይዘሮ ትጓደድ ጨዋታቸውን የጀመሩት በአካባቢያቸው ስላለው መተሳሰብ፣ መልካም የሆነውን እሴት እንዲሁም ቴፒንም ጭምር በማስተዋወቅ ነበር። ‹‹ቴፒ ለእኔ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ናት። አንተ ከየትነህ የማይባልባት፣ ሁሉ ሰው ተስማምቶና ተከባብሮ የሚኖርባት ምርጥ አካባቢ ናት። በእንግድነት ወደተለያዩ አካባቢዎች ስሄድ የታዘብኩት፤ ጉርብትናም ሆነ መቀራረብ ምን አለው? ምን አላት? በሚል ዓይነት ስሜት ውስጥ የተመሠረተ ነው።

እኔ ባለሁበት ቴፒ ውስጥ ግን የጎረቤት ልጅ የራስ ልጅ ነው። ችግር ሲደርስ ኃላፊነቱ ችግሩ የደረሰበት ቤተሰብ ብቻ አይደለም። የጎረቤቱም ጭምር ነው። በገንዘብም፣ በሃሳብም፣ በጉልበትም ባለው አቅም ሁሉም ይተባበራል። ልጅ ወስዶ ማሳደግ ካለበትም ጎረቤት ያሳድጋል። ተወልጄ ያደኩት እንዲህ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ ነው ። እኔም የታመመችውን የጎረቤቴን ልጅ ለመርዳት የተነሳሁት ለዚህ ነው። መረዳዳት፣ መተጋገዝ ያደኩበትና የኖርኩበት ነው›› ሲሉ መልካም የሆነውን የአካባቢያቸውን እሴት አጫወቱኝ።

የቴፒን የእድገት ሁኔታም በቁጭት አንስተውልኛል። እርሳቸው እንዳሉት የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የማምረት አቅም ያላት ሊያውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ቡና በስፋት የሚለማባት ሆና በውስጧ እንደያዘቸው ሀብቷ ያደገች አለመሆኗ ያስቆጫቸዋል። ለዚህም ትልቅ ማነቆ የሆነው በአካባቢው ላይ የተመረተውን ምርት ወደ ማዕከል እና ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ለገበያ ለማውጣት መንገድ አለመኖር ነው። የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ዘመናትን ያስቆጠረና አሁንም ያልተሻገሩት ከባድ ፈተና እንደሆነባቸውም አጫወቱን።

ልጅነት ትዳር እና ሥራ

ወይዘሮ ትጓደድ ልጅነታቸውን መለስ ብለው እንዲህ አጫወቱን። አባታቸው ጎበዝ ከሚባሉ ገበሬዎች አንዱ ናቸው። አባታቸው ጎበዝ ገበሬ መሆናቸው የግብርናውን ሥራ ለማወቅ እድል ሰጥቷቸዋል። ያላቸውን የግብርና እውቀት ስለነገሩን፣ የጎበዝ ገበሬ ልጅም በመሆናቸው የተወለዱትም ቡና አብቃይ በሆነ አካባቢ በመሆኑ በቡና ልማቱ ውስጥ የሚገኙ የቡና ነጋዴ ይሆናሉ የሚል ግምት ነበረን። ግምታችን ግን ትክክል አልነበረም። በመንግሥት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል።

እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል። እዚህ ደረጃ የደረሱት ግን በአንድ ጊዜ አይደለም። በመካከል ላይ ለማቋረጥ ተገደዋል። የአካባቢው ባሕል በሚያዘውና በቤተሰብም ፍላጎት በልጅነት መዳር ግድ ነው። ወይዘሮ ትጓደድ ከባሕሉ መውጣት አይችሉም። ግን ደግሞ አንድ ነገር ማድረግ ነበረባቸው፤ የማይቀረውን ትዳር ግን በራሳቸው መንገድ መረጡ። ከአንድ ወጣት ጋር ቀድመው ፍቅር ጀምረው ስለነበር ፍቅረኛቸውን እንዳያጡት ከቤተሰብ ትእዛዝ ውጭ መሆን ነበረባቸው። የፈለጉትንም አደረጉ። ውሳኔያቸው ግን በቤተሰብ በኩል ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

ከቤተሰብ ውጭ የሆነ ትእዛዝ መፈጸም አይደገፍም። ግን ደግሞ የሚፈልጉትን ለማሳካት ወጣ ያለ ባህሪ ማሳየት ነበረባቸው። ሶስት ጉልቻ ሲመሰርቱ ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ። ትዳር ሲመሠርቱ ትምህርታቸው ተቋረጠ። ‹‹ልጅ በልጅነት›› በሚለው የኢትዮጵያ ብሂል የ30 ዓመት ልጅ አድርሰዋል። የሶስት ልጆች አያትም ሆነዋል።

ሥራ የተቀጠሩት በትምህርታቸው ሳይዘልቁ ገና የ17 ዓመት ታዳጊ ሆነው ነበር ። ጎደሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተቋቋመው በቀድሞ የመንግሥት ቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት ውስጥ የመልእክት ሠራተኛ ሆነው ሥራ ጀመሩ። ከትዳር አጋራቸው ጋርም የተገናኙት በዚሁ በሚሰሩበት ድርጅት ውስጥ ነው። እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩት በትዳር ውስጥ እያሉና ሥራም እየሰሩ ነበር። የትምህርት ደረጃቸውን እያሻሻሉ፣ የሥራ ልምድም እያዳበሩ ሲመጡ የሥራ ዘርፋቸውን ቀየሩ። በመልእክት ሠራተኛነት ለሶስት ወራት ካገለገሉ በኋላ የመረጃ ክፍል ሠራተኛ ሆኑ፤ በመቀጠልም ሬዲዮ ኦፕሬተር፣ ሂሣብ ሠራተኛ ሽያጭ ሰብሳቢ፣ አስተዳደርና ፋይናንስ፣ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ተዘዋውረው ለ16 ዓመታት አገልግለዋል።

ወይዘሮ ትጓደድ ተቀጥሮ ለመሥራት ሌላኛው ምክንያታቸው በወቅቱ የግብርናው ሥራ የሚያበረታታ ሆኖ ስላላገኙት ነበር። አሁን ላይ ደግሞ የግብርናው ሥራ እንደሚሻል ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝበዋል። በመንግሥትም የተሰጠው ትኩረትና ግብርናው ላይ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተገንዝበዋል። በእርሳቸው የወጣትነት ዘመን የነበረው እሳቤም ተምሮ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ መሥራት የሚለው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። ወይዘሮ ትጓደድ ሥራ መቀጠራቸውም ሆነ እስከ 12ኛ ክፍል መማራቸው እራሳቸውን እንደ እድለኛ እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል። በትምህርታቸውም ለመግፋት ፍላጎቱ ነበራቸው፤ ነገር ግን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ላይ ያመጡት ውጤት ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃቸው ባለመሆኑ በዛው የትምህርት ደረጃ ለመገደብ ተገደዱ።

በእድሜ እየበሰሉ፤ በሥራም ያገኙት ልምድ፣ ነገሮችንም የማገናዘብ አቅማቸው የበለጠ ሲያድግ የሃሳብ ለውጡም አብሮ መጣ። አሁን ላይ በኑሯቸውም የተለያየ ነገር በመፈጠሩ ነገሮች ተቀይረዋል። ወይዘሮ ትጓደድ አሁን ላይ ተቀጣሪ ሠራተኛ አይደሉም። የግል ሥራቸውን ጀምረዋል። የተሰማሩት በምግብ ሥራ ላይ ነው ። ለተወሰነ ጊዜ የሰሩት በኪራይ ቤት ውስጥ ነው። በአካባቢው ላይ ሆቴል ያላቸው አንድ የሆቴል ባለቤት ሊያበረታቷቸው ስለፈለጉ ሬስቶራታቸውን በነፃ እንዲሰሩበት ፈቅደውላቸው አሁን ከኪራይ ነፃ ሆነው እየሰሩ ናቸው።

ግለሰቡ ያደረጉላቸው ማበረታቻ መልካም ነታቸውን እንደሚያሳይ የሚገልጹት ወይዘሮ ትጓደድ፣ እርሳቸውም ዕድሉን ተጥቅመው ውጤታማ ለመሆን እየተጉ እንደሆነ ነው የነገሩን። ቴፒን የሚመጥን የሆቴል አገልግሎት ሊኖር ይገባል ይላሉ። ቴፒ የመልማት አቅም እያላት ግን በሆቴል ኢንዱስትሪው እንዳላደገች ያነሳሉ። ፍላጎታቸው ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች በቂ ማረፊያ እንዲያገኙና በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ በተሻለ በመንቀሳቀስ አካባቢው ላይ ምቹ ነገር በመፍጠር ዐሻራቸውን ለማሳረፍ ነው። በ2000 ካሬ መሬት ላይ የሚገነባ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ለመሥራት አቅደዋል። እቅዳቸውንም ለከተማ አስተዳደሩ አቅርበው መልስ እየጠበቁ ነው። መሬቱ እንደተፈቀደላቸው ግንባታውን ለመጀመር ተዘጋጅተዋል።

ከወይዘሮ ትጓደድ ጋር በነበረን ቆይታ ስለ ግል ሕይወታቸውና ኑሯቸው አንስተን ስንጨዋወት፤ በሀዘን እንደተጎዱ ነገሩኝ። ባለቤታቸውንና አንድ ልጃቸውን በሞት አጥተዋል። በሥጋ አንድ ልጅ አላቸው። በሥጋ የማይገናኙ ግን የሚያሳድጓቸው ብዙ ልጆች አሏቸው። ወይዘሮ ትጓደድ ሰብዓዊነታቸውን ጎልቶ የሚታይበት ሥራቸው፤ በቤታቸው ውስጥም ከቤታቸው ውጭም አይዞአችሁ አለሁላችሁ የሚሏቸው ሰዎች መኖራቸው ነው። በእኔ ጉትጎታ እንጂ ይህን ሃሳብም ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም። እንዲህ አድርጌያለሁ ብሎ መናገር ጥቅም የለውም ከሚል እሳቤ ነው።

ወይዘሮ ትጓደድ እንዳጫወቱን የሚያግዟቸው ሰዎች በተለያየ እድሜና በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እናት እና አባት፣ ወይም አንደኛው ወላጅ የሌላቸው፣ ረዳት ያጡ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነው ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ያልቻሉ ይገኙበታል። ከሚያግዟቸው መካከል አንዳንዶቹ በሥራቸው ቦታ በመኖሪያቸው ውስጥ የሚገኙ አሉ። አካባቢያቸው ላይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ሚዛን ቴፒ በመሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲው በጣም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያመነባቸውን እንዲሰጣቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ቀድመው ተነጋግረዋል።

የሚይዟቸው ተማሪዎች በቁጥር አምስት ይሆናሉ። ይሄ በየዓመቱ ሲሰላ የተማሪዎቹ ቁጥር ከፍተኛ ነው። ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ የሚያሟሉላቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ነው። እርሳቸው አግዟቸው የተመረቁ፤ በጥሩ ሥራ ውስጥ የሚገኙ መኖራቸውንና ውጤታማ መሆናቸውም እንደሚያስደስታቸው ይገልጻሉ።

ወይዘሮ ትጓደድን ለእዚህ በጎ የሆነ ተግባር ያነሳሳቸው በጎ የመሆን የልጅነት እርሾ አለ። ወላጅ እናታቸው ወይዘሮ ላኩብሽ እንየው ተማሪዎችን ሲረዱ፣ ከተቸገሩት ጎን ሲሆኑ፣ በቤታቸው ውስጥም ዘመድ የሆነም ሆነ ዘመድ ያልሆነውንም ሰብስበው ከልጆቻቸው ጋር ሲያሳድጉ እያዩ ስላደጉ የእርሳቸውን በጎ ሥራ ወርስዋል።

ልጅን ማጣት

ጎበዝ፣ መንፈሳዊ፣ ፈርሀ እግዚአብሔር ያለው ጥሩ ልጄ ነው የሚሉት ሁለተኛ ልጃቸው ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ትምህርት በመከታተል ላይ እያለ በብዙ ችግር እና ፈተና ውስጥ ያልፋል። ስለታሪኩም እንዳጫወቱን ችግር ውስጥ እንዳይገባ ብለው በዛ ያለ ገንዘብ ይልኩለት ነበር። ብዙ ጓዶኞችም ነበሩት። ከጓደኞቹ ጋር የሚላክለት ገንዘብ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ አደረገው።

ብዙ ጓደኛ በማፍራቱ ከሥነ ምግባር ውጭ ያልተገቡ ነገሮችን እንዲያደርግ ምክንያት ሆነው እንጂ፤ ወይዘሮ ትጓደድ በልጃቸው መልካም የሆነ ሥነ ምግባር ጥርጣሬ አልነበራቸውም። ልጃቸው ችግር ውስጥ የገባው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙም ሳይቆይ ነበር። የገባበት ችግርም አስጨንቆታል። የሆነውን ሁሉ ቤተሰብ ቢያውቅበት ምን ሊፈጠር እንደሚችል እያሰበና ቤተሰብ በእርሱ ላይ ያለውን ተስፋ የሚያሳጣ መሆኑ ሲሰማው የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ይሄ ነገር ተባብሶ አክሱም ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረው የ23 ዓመት ልጃቸውን በሞት አጥተውታል።

‹‹ልጄን ሳላውቅለት ብቻውን በጭንቀት በራሱ ላይ ወስኖ ተጎዳብኝ። እኔም በሀዘን አለሁ›› ይላሉ። ከዓመታት በፊት ተከስቶ በነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በኋላም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ምክንያት ዩኒቨርሲቲው በመዘጋቱ እርሳቸው ጋር ሆኖ በሥራ እያገዛቸውና በግል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየተማረ ለአራት ወራት ያህል አብሯቸው አሳልፏል። የጀመሩትን የሆቴል ሥራም ጥሩ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ያደረገው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነበር። እንዲህ ተጋግዘው እየሰሩ በአንዱ ቀን መጥፎ አጋጣሚ ልጃቸው በሞት ተለያቸው።

ወይዘሮ ትጓደድ የልጃቸው ጭንቀትና ስቃይ ያወቁት ከተለያቸው በኋላ ነው። ልጃቸው በሕይወት እያለ የየእለት ውሎውን የሚያሰፍርበትን የግል ማስታወሻ (ዲያሪ) አግኝተው ልጃቸው ከፃፈው ማስታወሻ ላይ አግኝተው በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ለማወቅ ቻሉ። በማስታወሻው ላይ ያነበቧቸው ሁሉ ልብ የሚሰብር ሆኖ አገኙት። ቀድመው አውቀው ቢሆን ልጃቸውን ያተርፉ እንደነበር በማስብ አብዝተው ይቆጫሉ።

ሌሎችን ለማትረፍ

እርሳቸው ልጃቸውን ቢያጡም ሌሎች ይትረፉ ብለው ከልጃቸው ማስታወሻ ላይ ያነበቡትን መሠረት አድርገው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማገዝ ተነሳሱ። እርሳቸው እንደሚሉት ልጃቸው የቤተሰብ ድጋፍ እያለው ችግር ውስጥ ከወደቀ ምንም ዓይነት የቤተሰብ ድጋፍ የሌላቸው፤ ምን ዓይነት ነገር እንደሚገጥማቸው ቀድመው ግንዛቤ ሳይኖራቸው ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ልጆች ችግር ውስጥ እንዳይገቡ እንደ እናት በመቅረብ ማገዝን ዋና ተግባራቸው አድርገው ተያይዘውታል።

በዚህ ተግባር ውስጥ ከገቡ በኋላ ያስተዋሉትን እንዳጫወቱን፤ አንዳንድ ተማሪዎች በሚኖራቸው ትርፍ ሰዓት ሥራ ለመሥራት በተለያዩ የሆቴል ቤቶችና ሥራ ይገኝበታል ብለው በሚያስቧቸው ቦታዎች ሁሉ እንዲያሰሯቸው ይጠይቃሉ። ተማሪዎቹ ይሄን የሚያደርጉት ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው ሰው ስለሌላቸው ነው። ወይዘሮ ትጓደድ እንዲህ ዓይነት ልጆች ወደ እርሳቸው ሲመጡ ግን ሥራ ሳይሆን የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል። በትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው ጠንክረው እንዲማሩ ያበረታቷቸዋል።

በዚህ መልኩ አግዘዋቸው አራት ተማሪዎች ተመርቀው ሥራ ይዘዋል። አሁን ላይ ደግሞ የሚያግዟቸው ተማሪዎች አምስት ናቸው። ቤተሰብ እየከፈለለት በግል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማር አንድ ተማሪም እንዲሁ እያገዙት ነው። ቤተሰቡ በቂ ገንዘብ የሚልክለት ባለመሆኑ ተማሪውን እርሳቸውም ያግዙታል። ተመርቀው ሥራ እየፈለጉ ያሉ ማረፊያ የሌላቸውንም ቢሆን በቤታቸው ውስጥ ያቆዩዋቸዋል። ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ከእርሳቸው ጋር ቤተሰብ ሆነው ይኖራሉ። በተለያየ መንገድ የሚረዷቸውን ጨምሮ በሆቴል ቤታቸው ተቀጥረው ከሚሰሩት ጋር 33 ሰዎችን ያስተዳድራሉ።

ወይዘሮ ትጓደድ ይሄን በጎ ተግባር የሚያደርጉት የተለየ ወይም ከፍተኛ የሆነ የገቢ ምንጭ ኖራቸው አይደለም። ከሆቴል ንግዱ ከሚያገኙት ገቢ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ወጪያቸው ብዙ ነው። ለሠራተኞች ደሞዝ ይከፍላሉ። የተለያዩ ወጪዎችም አሉባቸው። ገቢና ወጪ አይመጣጠንም። ግን ያለውን ለወገን ማካፈል ወገናዊነት ነው ብለው ያምናሉ። ሰው መሆን ለእርሳቸው ትልቅ ትርጉም አለው። ሰው መሆን ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም መኖር ነው ብለው ያምናሉ። ‹‹እኔ እየበላሁ ሌላው ሳይበላ ማደር የለበትም። በምችለው ልክ ሰው ሆኖ መገኘትን እፈልጋለሁ›› ሲሉም ይገልጻሉ። በሚሰሩት በጎ ሥራም ሰዎች እንዲረዷቸውና እንዲያግዟቸው ብለው እንዳልሆነ፣ ከሰውም ብዙ እንደማይጠብቁና ህሊናቸው በሚያዛቸው እንደሚመሩ አጫወቱን።

በወይዘሮ ትጓደድ እምነት ወጣቶች ላይ ብዙ መሠራት አለበት። ሰዎች እያተኮሩ ያሉት አረጋውያንና ሕፃናት ላይ ብቻ ነው። ሀገር ይረከባል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ወጣት፣ በሚሰራበት እድሜ ላይ ሆኖ በሱስና በተለያየ አልባሌ ነገር ውስጥ ሆኖ በዝምታ ማለፉ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም። ወላጆችም ልጆቻቸው ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱላቸው እንደ ትልቅ ስኬት አይተው ልጆቻቸውን ከመከታተል መቆጠብ የለባቸውም። ወላጆች ዩኒቨርሲቲ የገቡ ልጆቻቸውን እንደ ጓደኛ ቀርበው ሥነ ልቦናቸውን፣ ችግሮቻቸውንና ሌሎችንም ነገር መረዳት አለባቸው ይላሉ።

ልጆቹ ያልተፈለገ ነገር ውስጥ ገብተው የሚገኙት ድንገት ነው የሚሉት ወይዘሮ ትጓደድ፤ ሳያመልጡ መቅደም ከወላጆች፣ ከአሳዳጊዎች የሚጠበቅ ቢሆንም ደጋፊና የሚከታተላቸው የሌላቸውን መርዳት የሌሎቻችን ኃላፊነት ነው ይላሉ። ልጆቹ በትምህርታቸውና በሥራቸው ውጤታማ ሲሆኑ ቤተሰባቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ማህበረሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚያገለግሉ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ይላሉ።

የልጃቸው የግል ማስታወሻ

ከልጃቸው ዕለታዊ የግል ማስታወሻ ላይ አግኝተው ያነበቡትንም እንዲህ አስታውሰዋል፤ ‹‹ከቤተሰቤ የሚላክልኝ ብዙ ገንዘብ ብዙ ጓደኛ እንዳፈራ አደረገኝ። በመጀመሪያ ላይ ስፈጽም የነበረው ከእናቴ የተማርኩትን ደግነት ነበር። ለኮፒና ለተለያየ ነገር ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ለሴት ተማሪዎች ከገንዘቤ ላይ እሰጣቸው ነበር። በኋላ ግን ያገኘኋቸው ብዙ ጓደኞቼ የሚያጨሱ፣ የሚቅሙና የተለያየ ነገር የሚያደርጉ ነበሩ። ወደ እነርሱ እንድቀላቀል ብዙ ተጽእኖ ያሳድሩብኝ ነበር። ሞክረው፤ አንተ የባላገር ልጅ ነህ የሚሉ ቃላቶችንም ይሰነዝሩብኝ ነበሩ። ጫናውን ለመቋቋምና እራሴን ለመግዛት ከስድስት ወር በላይ አልቆየሁም።

ትምህርት በጀመርኩ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የአጫሾች፣ የጠጪዎችና ደባል ሱስ ያለባቸው ተማሪዎች አባል ሆንኩ። እኔም እንደነርሱ ሱሰኛ ሆንኩ። ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቼ የሰጡኝን አደራም ሆነ የእኔን መስመር ሳትኩ። እነርሱ በሱስ ውስጥ ሆነው መማር ይችላሉ። እኔ ግን ትምህርቴን ለመከታተል ተቸገርኩ። ክፍል ከምገባበት የማልገባበት ጊዜም እየበዛ መጣ። ሁሉም ነገር አቃተኝ። በመጀመሪያው መንፈቅ ባመጣሁት ውጤት በትምህርት ላይ ለመቆየት አልቻልኩም።

ከሱስ ለመውጣት ብዙ ትግል አድርጊያለሁ። ግን በጣም ያሳሰበኝ እናቴ ብትሰማ ትሞታለች የሚለው ነበር። ያደረኩት ነገር ይጸጽተኝም ነበር። እንቅልፍም ነሳኝ። ›› ብሎ በማስታወሻው አስፍሮ ነበር። ሰው ሳይፈልግ የማይፈልግበት ቦታ ውሎ እንዴት ለችግር እንደሚጋለጥ ከልጃቸው የግል ማስታወሻ ላይ ያገኙት ትልቅ ትምህርት ሰጪ እንደሆነም አንስተዋል።

ልጃቸው ስህተት ውስጥ ይገባል ብለው አስበው ባያውቁም ሰው እንደሚሸነፍ በጠንካራው ልጃቸው መገንዘባቸውንም ነው ወይዘሮ ትጓደድ የሚናገሩት። በልጃቸው በመተማመናቸው እንዳይቸግረው ብለው ይልኩለት የነበረው ገንዘብ ወዳልተገባ ነገር እንዲገባ ምክንያት ይሆናል የሚል ግምት ቢኖራቸውም ለምን ያውለዋል፣ እንዴት ይጠቀምበታል የሚለው ክትትል አስፈላጊ እንደነበር የገባቸው አሁን ነው።

ወይዘሮ ትጓደድ በልጃቸው ምክንያት ለዩኒቨርሲቲ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። እርሳቸው ልጃቸውን በቅርበት ለመከታተል ልጃቸው የሚማርበትና የእርሳቸው መኖሪያ መራራቅ ገድቧቸዋል። ዩኒቨርሲቲው ግን ከመማር ማስተማር ባሻገር በተማሪዎች ሥነ ምግባር ላይም ክትትል ቢያደርግ ብዙዎችን መታደግ ይቻል ነበር ይላሉ።

የሕይወት ውጣ ውረድ

የሕይወት ውጣ ውረድ ለወይዘሮ ትጓደድ ‹‹የምወደውን ለብዙ ነገር የጠበኩትን ልጄን የትዳር አጋሬን የልጆቼን አባት በሞት ካጣሁ በኋላ ሀዘኔ ከባድ ነው። ግን ደግሞ ሁሉም ከእኔ አቅም በላይ ነው። የምኖረው እግዚአብሔር ያለልኝ፣ የፈቀደለኝን ነው። ሕይወትም መቀጠል ስላለበት ተስፋ ሳልቆርጥ ለመኖር እየታገልኩ ነው። አሁንም ቀድሞ እንደነበር ዓይነት ኑሮም ሆነ ደስታ የለኝም። ፍላጎቴ ቀሪውን የእድሜ ዘመኔን በበጎ ነገሮች ማሳለፍ ነው። ይሄን ለማሳካት ደግሞ መሥራት አለብኝ። በሆቴል ኢንዱስትሪው ውስጥ ለመግባት ያለኝን ፍላጎት ለማሳካት በምችለው ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ›› የሚለው ከብዙ በጥቂቱ ያካፈሉን ሃሳብ ነው።

ወይዘሮ ትጓደድ መልእክትም አስተላልፈዋል። ‹‹ሁሉም ሰው በየእምነቱ መልካም ነገርን ለመሥራት ቢተጋ፣ ጥሩ ቢሆን ደግ ቢሆን፣ በፍቅር በሰላም አብሮነትን ቢያጠናክር መልካም ነው›› ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። ተወልደው ያደጉባት ቴፒ ከተማም ትላልቅ ተብለው ከሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ ሆና ማየትንም ይመኛሉ። እየኖሩባትም የሚናፍቋት ከተማ እንደሆነችም ይገልጻሉ። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ሆነ ከሀገር ውጭ የመኖር ዕድሉ ኖሯቸው ቴፒ ከተማን ለቆ መሄድ እንዳልሆነላቸውም አጫውተውናል። እኔም ምኞታቸውና ፍላጎታቸው ሁሉ ተሳክቶላቸው በአጋጣሚ በድጋሚ ለመገናኘት እንድንችል አመስግነን ተሰነባበትን።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You