ለትምህርት ጥራት ተጨማሪ የማንቂያ ደወል!

የትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን አንድ አስደንጋጭ በሌላ በኩል ደግሞ የማንቂያ ደወል የሆነ ዜና አሰምቶናል። ዜናው ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ካስፈተናቸው መካከል ፈተናውን ያለፉት 13 በመቶ ብቻ ናቸው፤ 22 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ምንም ተማሪ አላሳለፉም የሚል ነው። ይሄ እንደ አንድ የሀገር ዜጋ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዜና ነው።

ተቋማቱ ምን ሲሠሩ ከረሙ፤ ተማሪውስ የሚል ከባድ ጥያቄን ያስነሳል። ፈተና መጀመሩና እያንዳንዱ ተቋምም ሆነ ተማሪ የት እንዳለ እንዲያውቅ የሚያደርግ አሠራር በትምህርት ሚኒስቴር በኩል መጀመሩ ደግሞ ነገ ሀገርን ከውድቀት ለማትረፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ትዝ ያለኝን ላጋራችሁ፤

አንድ ወዳጄ ሁለተኛ ዲግሪዋን የምትማረው በአንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ ነው። በተለይ የትምህርት ፕሮግራሟ ቅዳሜና እሁድ እንደሆነ አወቃለሁ። ብዙ ጊዜ ግን ወደ ትምህርት ተቋሙ ስታመራ አላያትም እንዳውም ቅዳሜ መደበኛ ሥራዋ ላይ ታሳልፋለች። እናም ሁልጊዜም ይደንቀኛል።

እሷም አንድም ቀን የትምህርት ጉዳይ አሳስቧት ስታነሳ አልሰማም። እየተማረች ይሆን አቋርጣው እያልኩ ማሰላሰሌን ግን አላቆምኩም። ሰሞኑን የተማሪዎች መመረቂያ ሰሞን ስለሆነ መሰለኝ አስታወስኳትና የአንቺ ምርቃት መቼ ነው ወይስ ተራዝሟል አልኳት።

ረጅም ሳቅ ሳቀች “ተራዝሟል? ምኑ በቀጠሮ አይደለም እኮ የምማረው!” አለችኝ፤ እኔም ደንገጥ ብዬ መጠየቅ የነበረብኝ ትምህርት እንዴት ነው በሚል እንደነበር ለራሴ ማረሚያ ሰጥቼ ጨዋታውን ቀየርኩ ማለቴ ምርቃቱ መቼ ነው ስል አከልኩ። “ተመረቅን እኮ! ግብዣው ይብራባችሁ” አለች። እኔ ድሮም ቢሆን ግብዣው አልነበረም ያሳሰበኝ በዚህ ሁኔታ የተማረችው ትምህርት የት ደርሶ ይሁን የሚለው ነው።

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ሲነሳ ሁሌም አሳሳቢው ሀገርና ትውልድ እየሞተ ነው የሚለው ነው። ኩረጃ፤ ለሌላ ሰው መፈተን፣ ማስፈተን፤ በግዢ የሚወጡ የትምህርት ማስረጃዎች፣ በገንዘብ የሚሠሩ የመመረቂያ ጽሑፎች፣ ለአስፈታኞች ተከፍሎ ተማሪዎች እንዲኮራረጁ የሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች ጉዳይ፣ መመረቅና ማስመረቅ የቀለለባቸው ተቋማት … ብቻ ብዙ ማለት ይቻላል።

ይሄ ሁሉ ተሰባስቦ ውጤቱ የሚታየው ያው በሀገር ላይ አይደል? ባይቆጭ ያንገበግባል። ራሳቸውን በትክክል መግለጽ የማይችሉ፣ ሙያና እውቀቱን ያልተካኑ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሰርተፍኬት ደርድረው እውቀት ብርቅ የሆነባቸው “ምሑራን” ተቋም ሲመሩ እንደማየት የሚከብድ ነገር ምንም የለም።

የትምህርት ጥራት ሁልጊዜም የሚነሳ ወሳኝ ጉዳያችን ነው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደግለሰብ አሳሳቢም ነው። አሁን አሁን ግን የምንሰማቸው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና፣ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የትምህርት ጥራት ምን ላይ እንዳለ እያሳዩን ነው። ከመተማማት አልፈን በተጨባጭ ማን ምን መሆናችንን እየነገሩን ነው። ኧረ አስረግጠው ተቋሞቻችንን ፣መምህራኖቻችንን፣ ተማሪዎቻችንን ሁሉ እንድንፈትሽ እያደረጉን ይገኛሉ ።

የትምህርት ጥራት ምን ያህል ወድቆ እንደቆየ ልክ ልካችንን እየነገረን ነወ። እናም ለዲግሪ ብቻ ሳይሆን ለማስተርስ ፕሮግራምም የመውጫ ፈተና በኖረው፤ ይሄ ከምንም አይደለም አብዛኛውን የትምህርት ጊዜ ከትምህርት ቤት ውጪ የሚያሳልፉ አንድም ቀን ተማሪ ሆነው እንደተማሪ ሲያጠኑ ቤተመጽሐፍትና ሲጎበኙ ተቸክለው የማይታዩ ሁሉ በትምህርት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ወራቶች ተመራቂ ነኝ ሲሉ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ በሚባል መልኩ አልነበረም። ከየገበያ በሚገዙ የትምህርት ማስረጃ ወረቀቶች ሀገርንና ሕዝብን ምን ያህል ጐድቶ እንደነበር የታየው በመንግሥት የሥራ ቦታዎች ላይ የሠራተኞችና የአመራሮች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት ይረጋገጥ በተባለበት ወቅት ነው። በዚህ የችግሩን ግዝፈት ማየት አስችሏል። እሱም ቢሆን ውጤቱ ዳር ሳይደርስ ተዳፍኖ ቀርቷል።

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ሲነሳ በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ የሚታይ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ አንደርስም ፤ ወረርሽኙ በመንግሥት ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎችም ተመሳሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ምስክር አያስፈልግም። በተከታታይ ከትምህርት ሚኒስቴር የወጡት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቶች፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናም ውጤት የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።

ዘንድሮ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ካስፈተኗቸው አጠቃላይ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ያለፉት 58 በመቶ ናቸው፡፡ ይሄም ቢሆን የሚያኮራ ሳይሆን የት ነው ያለነው ብለን ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርግ የማንቂያ ደወል ነው። የሁሉም ድምር ውጤት የሚያሳየው ግን ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በየደረጃው በቂ እውቀት አለመቅሰማቸውን ነው።

የዩኒቨርስቲ መግቢያውን ውጤት በየትኛውም በኩል ቢያገኙት ውጤታማ ሆነው መውጣት አልቻሉም። ይሄ እንደ ሀገር ውድቀት ነው። ለቀጣዩ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ለሚሠራው ሥራ ደግሞ የመሠረት ድንጋይ ነው ። ተማሪውም የት ላይ እንዳሉና ምን እንደሚጠበቅባቸው፤ ዩኒቨርሲዎችም ምንም እየሠሩ ዲግሪ በገንዘብ እየቸበቸቡ መክረማቸውን አሁን ግን በዚያ መንገድ መሄድ እንደማይችሉ የማስጠንቀቂያ ደውል መሆኑን የሚረዱበት ነው። ይሄ አንድ ሊበረታታ የሚገባው እርምጃ ነው። ከዚህም አለፍ ብሎ መሄድን ግን ይጠይቃል።

ለምሳሌ የትምህርት ጥራት መለካት ያለበት ተማሪዎች ትምህርት ሲያጠናቅቁ ብቻ መሆን የለበትም። ይሄንን ሁሉ ዓመት ተማሪም አስተማሪም ወላጅም ደክሞ ውጤት አልባ ተማሪ ተገኘ ከማለት ይልቅ ቀድሞ ብቁ የሆኑትን በመግቢያ ፈተና ለይቶ ማስገባት ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ ከገቡ በኋላ ቀደም ሲል እንደነበረው አጥጋቢ ውጤት የሌላቸው በ “ኪሪስመስ” መሸኘት ይገባል። ለዚህም ብቁ የሆነ መምህር በቂ የሆነ ትምህርትና ምዘና ከተሰጠ ማለቴ ነው።

መምህር እንዳሻው ማርክ የሚሰጥበት ተማሪም በቀላሉ የሚሸመትብት አይነት አካሄድ ቁጥጥር ያስፈልገዋል። መምህሩም ትልቅ ኃላፊነት አለበትና የእስከዛሬው አካሄድ ለታሪክ ትተነው የነገዋን ሀገር የሚተካ ትውልድ ለመፍጠር ይሄንን የማንቂያ ደወል ሁላችንም በተለይ የትምህርት ማኅበረሰቡ በአግባቡ ሊገነዘበው ይገባል።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You