ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በሁለቱም ፆታ በ8 መቶ ሜትር ፍፃሜ ሜዳሊያ ውስጥ የገባችበት ታሪክ የላትም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ የኦሊምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ ቀርቶ በፍፃሜ ሲፋለሙ የሚታወስ አጋጣሚም እምብዛም ነው። ዘንድሮ ግን ወጣቷ አትሌት ፅጌ ዱጉማ ይህን ታሪክ ፓሪስ ላይ መቀየር ችላለች። ትናንት ምሽት 4:45 በተካሄደው የሴቶች 8 መቶ ሜትር ፍፃሜ ፅጌ ዱጉማ 1:57.15 በሆነ የግሏ ፈጣን ሰአት ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ በርቀቱ ታሪክ በሁለቱም ፆታ የመጀመሪያዋ ሜዳሊያ ያጠለቀች አትሌት ሆናለች። ወርቁ ያመለጣትም በሚያስቆጭ ሁኔታ በጥቂት የታክቲክ ስህተት ነበር። እንደመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ግን ውጤቷ ትልቅ አድናቆት አስገኝቶላታል።
የ23 ዓመቷ ወጣት አትሌት ጽጌ ድጉማ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ፍሬ እንዲሁም የንግድ ባንክ ክለብ አትሌት ናት። ሀገሯን እአአ በ2017 በአልጄሪያ አዘጋጅነት በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በመወከል በ200 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች።በ400 ሜትር ደግሞ ከ2019 እስከ 2022 በተከታታይ በኢትዮጵያ ቻምፒዮና የሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ቆይታለች። በ800 ሜትር ቀዳሚ
ውድድሯን በቤልጂየም አድርጋ በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ የቱር ውድድር 1:59:66 በሆነ ፈጣን ሰዓት ቀዳሚ ነበረች። ልቃ በታየችበት የግላስኮው የቤት ውስጥ ዓለም ቻምፒዮናም ውድድሩን ተቆጣጥራ በመሮጥና የመጨረሻውን ዙር በፈጣን
አሯሯጧ ልዩነት በመፍጠር 2:01.90 በመሆነ ሰዓት በመሸፈን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በርቀቱ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ጋና ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎችም የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ሎስአንጀለስ ላይ 2ኛ ሆና ስታጠናቅቅ 1:57.56 የሆነ የራሷን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። በኦሊምፒኩ ጠንካራ የሩብና ግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች ላይ ያሳየችው ድንቅ ብቃትም ለሜዳሊያ እንድትጠበቅ አድርጓታል።
ተጠባቂ በነበረው የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከስድስት ኦሊምፒኮች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሜዳሊያ ውጪ ሆናለች። ኬንያውያኑ ቢትሪስ ቺቤትና ፌይዝ ኪፕዬጎን ተከታትለው ቢገቡም ኪፕዬጎን በውድድሩ መሃል ላይ ከጉዳፍ ጋር በነበራት መገፋፋት ውጤቷ ተሰርዟል። በዚህም ሦስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ብሩን ወስዳለች። ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ እጅጋየሁ ታዬ 6ኛ፣ መዲና ኢሳ 7ኛ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ 9ኛ ሆነው አጠናቀዋል። ይህም ከ24 ዓመት በኋላ ለኢትዮጵያ በርቀቱ ዝቅተኛው ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተመዘገቡ ውጤቶች አጠቃላይ በ3 ወርቅ፣ 1 ብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያ ከዓለም ቀዳሚዋ ስኬታማ ሀገር ነች። ኬንያ በ2 ወርቅ፣ አንድ ብርና 5 ነሐስ ትከተላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም