በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በ1950ዎቹ በጋዜጣው የወጡት የተለያዩ ዘገባዎችን አቅርበናል። ከተመለከትናቸው ዘገባዎች መካከል የዓባይ ወንዝን ለማልማት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በትብብር የተካሄደ ጥናትን የተመለከተ ዘገባ ይገኝበታል። ዛሬ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ ጫፍ በደረሰበት ወቅት ላይ ሆነን ከ60 ዓመት በፊት ዓባይን በተመለከተ የነበረውን ሁኔታ ዘገባው ያስታውሰናል። በወቅቱ በቆቃ ግድብ ዙሪያ በክረምቱ እየተካሔደ ስለነበረ የደን ተከላ፤ የትራፊክ አደጋና የመሳሰሉ ዘገባዎችን አካተንም እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
የዓባይ ሸለቆ ጥናት
የዓባይ ሸለቆ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከፍ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሀብት ምንጭ ነው። የዚህ ሸለቆ ጥናት (ሰርቬይ) እ.ኤ.አ. በ1956 ዓ.ም. ተጀመረ፤ የዓባይ ሸለቆ ጥናት በሚገባ ያከናወኑት የአሜሪካ መንግሥት ቴክኒሺያኖች ናቸው። ከቴክኒሺያኖቹም ጋር ቁጥራቸው በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የጥናቱ ተካፋይ ሆነዋል። የዓባይ ሸለቆ ጥናት ሥራ ከብዙ ድካምና ችግር በኋላ በአራት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ተፈጽሟል።
በተደረገው ሰርቬይ መሠረት የዓባይ ሸለቆ ርዝመት አንድ መቶ ሃያ ሺህ እስኩዬር ማይልስ መሆኑ ታውቋል። ጥናቱ በተደረገበት ወቅት የሥራው ሁኔታና አቀማመጥ ፤ካርታና ፎቶግራፍ ለማንሳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የአሜሪካ መንግሥት ባደረጉት ስምምነት መሠረት፤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማዳበሪያ የአሜሪካ መንግሥት አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ሲያወጣ ፤ኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር ማውጣቷ ተገልጿል። የዓባይ ሸለቆ ጥናት የተሠራውም ከዚሁ ገንዘብ ነው።
የዓባይ ሸለቆ ጥናት በቀደምትነት እንዲሠራ መደረጉ ለልዩ ልዩ ኢንዱስትሪና የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ጣቢያ መቆሚያዎች የሆኑትን ሥፍራዎች ለማወቅ እንዲመች ተብሎ ነው። ከዚህም በቀር በዓባይ ሸለቆ ግራና ቀኝ የሚገኙት ሥፍራዎች ካርታ በማንሳት በጥቅም ላይ ለማዋል እንዲችሉ ታስቦ የተደረገ ነው። በእውነትም ለዓባይ ሸለቆ የሚጠብቀው ዕድል ከመጠን በላይ ነው። ለዚህም በጢስ ዓባይ ላይ የሚሠራው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ጣቢያ የመጀመሪያው ምስክር ሊሆን ይችላል።
(ሐምሌ 25 ቀን 1953 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
የልዩ ልዩ የደን ዛፎች ችግኝ ልማት
ከእርሻ ሚኒስቴር ከደን ክፍል የተገኘ
በአሁኑ ክረምት ወራት ከውጭ ሀገር የመጡና ከሀገር ውስጥም የሆኑ 4 ሚሊዮን ችግኞች በቆቃ ግድብ ፈሰስ አካባቢ የሚተከሉ መሆናቸውን ከእርሻ ሚኒስቴር የደን ክፍል የተገኘ ወሬ ገልጿል። ከእርሻ ሚኒስቴር ብሔራዊ የደን ልማት ፕሮግራም የዚህ ዓመት የማልማት ተግባር ዓላማ ፤የገነትን ፤የጉደርን ፤የቆቃንና የመናገሻ ሱባን ሥፍራዎች ይሸፍናል።
‹‹ቀደም ብሎ የዘነበው የክረምቱ ዝናም እንዳያመልጠን በመናገሻ ብሔራዊ ፓርክ ፤በቆቃና በዋታ ደለቻ ፤ከሚገኙ ችግኝ ማፊያዎች ፭፻ ሺህ ልዩ ልዩ ዓይነት ችግኞች ወስደን በመትከል ላይ እንገኛለን ›› በማለት የደን ክፍል መሥሪያ ቤት የቴክኒክ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወልደሚካኤል ከለቻ አስረድተዋል።
ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞች በመጥፎ አኳኋን የአፈር መበላት ጉዳት በደረሰባቸው በየረር ፤በዝቋላና በመናገሻ ማርያም ተራራዎች ላይ ፣በጐ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ረዳትነት እንተክላለን ፤የቀረው ሦስት ሚሊዮን የሚሆነው ችግኝ በየቦታው ላይ ተክል ለመትከል ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ በነፃ ይታደላል፤ይህም ሁኔታ በገጠር የሚኖሩት ሕዝቦች በየግል ቦታቸው ላይ ደን ያለሙ ዘንድ የሚያበረታታ ይሆናል በማለት አስታውቀዋል። ቀጥለውም የደን ክፍል መሥሪያ ቤት በሚያከናውነው የደን ልማት ተግባር ላይ ተቀዳሚነት የሚሰጠው በዝናም የመምዘቅ አደጋ ለደረሰባቸው ተራራዎችና የአፈር መሰነጣጠቅና መበላሸት አደጋ በቅርቡ እንደሚደርስባቸው ለሚያሰጉን ተረተሮች መሆኑን ከገለጹ በኋላ ፤ የሀገሪቱ የእርሻ ወራት ችሎታ ሊደገፍ የሚችለው ደንን በማልማትና መሬትን ከጎርፍ አደጋ በመጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚህም አያይዘው የደን ክፍል መሥሪያ ቤት በየጠቅላይ ግዛቱ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ለማቋቋም የሚጥር መሆኑን ሲያስረዱ ፤በጐጃም ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ‹‹ግልግል ዓባይ አንድ የችግኝ ማልሚያ ጣቢያ ተደራጅቶ ሥራውን የጀመረ ››መሆኑን አመልክተዋል።
ወደ ቆቃ ግድብ የሚገቡት ውሃዎች የሚጠናከሩበት አካባቢ በአፈር፤በውሃ መበላሸትና መሰርሰር ግድቡን በቶሎ በደለል የሚሞላ እንዳይሆንና ተግባሩንም እንዳሰናከለው በቅርቡ በዚህ ሥፍራ አካባቢዎች ከሀገር ውጭና ሀገር ውስጥ የዕጣን ችግኞች በመትከል የደኑ ልማት እንዲስፋፋ ይደረጋል በማለት አስታውቀዋል።
(ሐምሌ 22 ቀን 1953 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ወንዝ ውስጥ ገቡ
የመቶ አለቃ ታደሰ ዱባለ የተባሉ የክቡር ዘበኛ ባልደረባ ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ከምሽቱ ፫ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ሲሆን ፤የሰሌዳው ቁጥር ፮ሺህ ፰፻፹ የሆነ ሠራዊት ጂፕ መኪና ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኮከብ ወደ ሚያዝያ ፳፯ አደባባይ እየነዱ ሲሔዱ ራስ መኮንን ድልድይ ሲደርሱ ወደ ግራቸው ተጠምዝዘው የድልድዩን ድጋፍ ከሰበሩ በኋላ ፤ወንዝ ውስጥ ገብተው አደጋ ደርሶባቸዋል።
አደጋ መሆኑ እንደተሰማ፤የትራፊክ ፖሊሶች ከሥፍራው ደርሰው በእሳት አደጋ ወታደሮች ዕርዳታ ቁስለኛውን ከድልድዩ ውስጥ ካወጡ በኋላ ፤ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ወስደዋቸው የመጀመሪያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ፤የደረሰባቸ ቁስል ከባድ በመሆኑ ወደ ክቡር ዘበኛ ሆስፒታል ተዛውረው በዚያ ተኝተዋል።
እድልድዩ የገባው ጂፕ ትናንት በክቡር ዘበኛ መኪና ተጐትቶ ከወንዙ ውስጥ ወጥቷል።
(ሐምሌ 7 ቀን 1953 ዓም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኢትዮጵያ በፀጥታ ምክር ቤት መቀመጫ እንዲሰጣት ጠየቀች
ከተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያና ሞሪታንያ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አሁን በተባበረው ዓረብ ሪፐብሊክ የተያዘ የመካከለኛው መሥራቅ (ሥፍራ መቀመጫ) ለእኛ ይገባል ሲሉ ውድድር አቅርበዋል በማለት ከኒውየርክ የተገኘ ወሬ አስታውቋል።
ለምዕራበውያኑ አውሮፓ ክፍልና ለመካከለኛው መሥራቅ እንዲሆኑ ጠቅላላ ስምምነት ተደርሶባቸው የነበረው መቀመጫዎች፤ሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ለማግኘት በመከራከር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ሌሎች መቀመጫውን ለመያዝ የሚወዳደሩ አገሮች ኢራን ሞሮኮና አፍጋኒስታን እንደሆኑ ታውቋል።
(ነሐሴ 24 ቀን 1954 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን )
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም