የሻምፖና የኮንጂሽነር ማምረቻ ማሽን በሀገር ልጅ

አሁን ያለንበት ‹‹ዘመነ ቴክኖሎጂ›› ቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገ ወደፊት በመገስገስ የሚገኝበት ነው። እናም ወቅቱ ከዘመኑ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ጊዜ፣ ወጪና ጉልበት የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች በቅርበት አግኝቶ መጠቀምን ይጠይቃል። ለዚህም ቴክኖሎጂን መጠቀም አንድ ነገር ሆኖ፣ የህብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ማመንጨትና ማፍለቅ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን መሥራትንም የግድ ይላል።

የህብረተሰቡን ችግር መነሻ ያደረጉ ሥራዎች ከሚሠሩ ተቋማት መካከል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይጠቀሳሉ። ተቋማቱ እንደ ሀገር በዘርፉ የሠለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን በማውጣት የበኩላቸውን እያደረጉ ናቸው። የሚሰሯቸው ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች በህብረተሰቡ ችግር ላይ ትኩረት አድርገው መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሠሯቸውን ሥራዎች በዓመቱ መጨረሻ በሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ያቀርባሉ። ዘንድሮም በ14ኛውን ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሳምንት የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ እና ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ ማሽኖችንና የመሳሰሉትን አቅርበዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጁ ነው። ኮሌጁ ካቀረባቸው ሥራዎች መካከል የሻምፖና የኮንጂሽነር ማምረቻ ማሽን ይጠቀሳል።

አቶ ወርቅነው ሰማኝ የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጁ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የብረታ ብረት አሠልጣኝ ናቸው። የሻምፖና የኮንጂሽነር ማምረቻ ማሽኑ በኮሌጁ አሠልጣኞች መሠራቱን ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማሽኑ ለየት ያለና የጥራት ደረጃውን ጠብቆ የተሠራ ሲሆን፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ የንጽህና መጠበቂያ የሻምፖና የኮንዲሽነር ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል። ማሽኑን ለመግዛት ይወጣ የነበረውን ወጪ ያስቀራል። ማሽኑ በሀገር ውስጥ መሠራቱ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት ከማስቻሉ ባሻገር ማሽኑን ለመግዛት እና ምርቶቹን ከውጭ ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል።

ማሽኑ ሁለት ኮንቴነሮች አሉት። የመጀመሪያው ኮንቴነር ዘይቱ የሚፈላበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኬሚካሎችና ውሃው የሚፈሉበት ነው። ማሽኑ 800 ሊትር ይይዛል። ሰዓት ለመቆጣጠር የሚያስችል ታይመር ተገጥሞለታል። የሚሠራው በኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፣ ሁለት ሂተሮችም ተገጥመውለታል፡፡

ማሽኑ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች የሚያመርት እንደመሆኑ ምርቶቹን ለማምረት ሲፈለግ የምርቶቹን ግብዓቶች በቅድሚያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። እነዚህን ምርቶች ለማምረት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶቹ መካከል ዋንኞቹ ዘይት፣ ኬሚካሎችና ውሃ ናቸው፡፡

ሻምፖ ለመሥራት የሚያስፈልገው ዘይት መፍላት የሚፈለገው 300 ዲግሪ ሴንቲ ግሪድ ሙቀት ነው። ዘይቱ በዚህ ደረጃ ከፈላ በሁዋላ፣ ውስጡ ያሉት ኬሚካሎችና ውሃው ደግሞ በ80 ዲግሪ ሴንቲግሪድ እንዲፈሉ ተደርገው ወደ ሻምፖነት ይቀይራሉ። በመሆኑም ማሽኑ ሻምፖ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ለማፍላት ምን ያህል የሙቀት መጠን ያስፈልጋል የሚለውን ለመለካት የሚያስችለው የተቀመጠለት መስፈርት አለ።

ማሽኑ ግብዓቶቹን የመፍላት መጠን ለማወቅ የሚያስችል የሰአት መቆጣጠሪያ /ታይመር/ ተገጥሞለታል፤ ምርቱን ለማምረት ሲፈለግ አስፈላጊ ግብዓቶች ከገቡ በኋላ የምንጠቀመው ግብዓት በምን ያህል የሙቀት መጠን መፍላት እንዳለበት ታይመሩ ስለሚያውቅና ስለሚቆጣጠረው መፍላቱ እንደበቃ ማሽኑን ይቆማል። ለምሳሌ ዘይቱን ለማፍላት የሚያስፈልገው የመፍላት መጠን 300 ዲግሪ ሴንቲ ግሪድ ስለሆነ ማሽኑ ልክ 300 ዲግሪ ሴንቲ ግሪድ ሲደርስ ይቆማል ማለት ነው።

ማሽኑ አስፈላጊ ግብዓቶችን ከሠጠነው በኋላ ምንም ሳንነካው በራሱ የምንፈልገውን የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና (ሻምፖ) ይሰጣል። ይህ ሻምፖ ለመሥራት ሲፈለግ የምንጠቀመው ነው። ኮንዲሽነር ለመሥራት ከተፈለገ ደግሞ ማሽኑን በማጠብ አስፈላጊ ግብዓቶች በመጠቀም ማምረት ይቻላል።

‹‹ማሽኑ 800 ሊትር የሚይዝ እንደመሆኑ በአንድ ጊዜ 800 ሊትር ምርት የሚያመርት ቢሆንም፣ ከዚያ በታች የምንፈልገውን ያህል ሊትር ምርት ያመርታል›› የሚሉት አሠልጣኝ ወርቅነው፤ ለአብነት 40 ሊትር ሻምፖ ለማምረት ቢፈለግ ከምንጠቀማቸው ኬሚካሎች መካከል ፎርማሊን 400 ሚሊ ሊትር፣ ሲዲኢኤ 640 ሚሊ ሊትር፣ ጨው አንድ ነጥብ 5 ኪሎ ግራም፣ ሽቶ / ፐርፊውም/ 80 ሚሊ ሊትር እና የመሳሰሉት ያስፈልጋሉ። ሌሎች ግብዓቶች ውሃና ዘይት ናቸው። ዘይቱ ደግሞ ለማሽን ተብሎ የሚዘጋጀው ነው፤ ከ30 እስከ 40 ሚሊ ሊትር ያህል ዘይት ጥቅም ላይ ይውላል። ዘይቱ ለብቻው ይፈላል። ማሽኑ ሁለት ሂተሮች የተገጠሙለት በመሆኑ ዘይቱን ለብቻ አፍልቶ ፤ በውስጡ ያለውን ኬሚካልና ውሃ ከፈሉ በኋላ ነው የሚፈለገው ምርት የሚወጣው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ኮሌጁ ይህንን ማሽን ለመሥራት የቻለው አንድ ኢንተርፕራይዝ ባቀረበው ጥያቄ መነሻነት መሆኑን አሠልጣኙ ይገልጻሉ። ይህ ማሽን እንዲሠራለት ፍላጎቱን ያሳየውና ጥያቄውን ያቀረበው ዘነበወርቅ አካባቢ ብረታብረት ማምረት ላይ የተሠማራ ኢንተርፕራይዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ኢንተርፕራይዝ ማሽኑን በራሱ ለመሥራት ጥረት አድርጎ መጨረሻ ላይ ልክ ሊመጣለት ስላልቻለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኮሌጁ እንዲሠራው ‹‹ ይህንን ማሽን ለመሥራት በምችለው ሁሉ ሞክሬ ሊመጣልኝ አልቻለም። እናንተ ደግሞ የተሻለ እውቀቱና ልምዱ ስለሚኖራቸው ይህን ማሽን መሥራት ተችላላችሁ ፤ እኔ የምችለውን ያህል ላግዛችሁ እና ስሩ። አብረን ሠርተን ውጤቱን እንየው፤ ተግባር ላይ እናውለው›› ሲል ኢንተርፕርይዙ መጠየቁን አሠልጣኝ ወርቅነው አስታወሰው፣ ኮሌጁ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ አብሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የኢንተርፕራይዙን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ይህ ማሽን ለመሥራት መቻሉን አመልክተው፣ ሥራው በሚሠራበት ጊዜ ኢንተርፕራይዙ አብሮ እንዲሠራና እንዲያግዝ መደረጉን ገልጸዋል። ሃሳቡን ወደ ተግባር በመለወጥ ውጤታማ ሥራ ተሠርቶ ኢንተርፕራይዙ በጣም ተደስቶበት እንዲሸጋገር የተደረገ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ሃሳቡን ያቀረበውና በሙከራ ደረጃም የሻምፖና የኮንዲሸነር መሥሪያ ማሽን ለመሥራት ሞክሮ የነበረው ኢንተርፕራይዝ፣ ይህ ማሽን ሲሠራ ጀምሮ አብሮ ስለነበረ ቀደም ሲል የሠራው ማሽን የጎደለውን በመለየቱ ያንን አሟልቶ ተግባር ላይ እንዲውል ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህ ማሽን የምርቱን ግብዓት ለማፍላት 300 ዲግሪ ሲንቲ ግሪድ ለመድረስ 40 ደቂቃ ይፈጃል። ይህ ማለት ማሽኑን መሙላት እንደሚቻል የሚያሳይ ሲሆን፤ ማሽኑን 800 ሊትር ተሞልቶ፤ ማሞቂያው /ሂተሩ/ 300 ዲግሪ ሲንቲ ግሪድ ከደረሰ ሙሉ አካሉ ስለሚያፈላው በ 40 ደቂቃ 800 ሊትር የሻምፖና የኮንዲሸነር ምርቶች ማምረት ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የሚመረቱት የንጽህና መጠበቂያ የሻምፖና የኮንዲሸነር ምርቶች ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላሉ። ሻምፖው ለእጅ፣ ለጸጉር ንጽህና መጠበቂያ የሚውል ሲሆን፤ ኮንዲሽነሩ ደግሞ ለጸጉር ንጽህና መጠበቂያ ይውላል።

ማሽኑን ለመሽራት ሂተር፣ እስቴንለስ እስቲል ሽት ሜታል፣ የእስቴለስእስቲል ራውንድ ፓይፕ፣ የእስቴለስ እስቲል ፍላት አይርን፣ እና ከውጫዊው ክፍል በኩል ጋልባናይዝድ ሸት፣ ኖርማል ማይልድ እስቲል ላሜራ፣ ማይልድ ስቲል እስኩየርፓይፕ የመሳሸሉ ቁሳቁስ ጥቅም ላይ ይውላሉ። እነዚህ ቁሶቁስ በአብዛኛው በኮሌጁ ከሚገኙ ቁሳቀስ በቀላሉ ማግኘት መቻሉንም ይገልጻሉ።

አሰልጣኝ ወርቅነው እንዳሉት፤ ማሽኑ ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጻር በዋጋም ቢሆን ተመጣጣኝ ነው። በኢንተርፕራይዙና መርካቶ ዶት ኮም ላይ ከተገኘው መረጃ መረዳት እንደተቻለውም፤ ከዚህ ማሽን ያነሳው ከውጭ የሚገባው ማሽን 650 ሺህ ብር ይሸጣል። ይህ በሀገር ውስጥ የተሠራው ማሽን ከውጭው ጋር ሲነጻጻር ግን፤ በመጠንም ቢሆን በጣም ከፍ ያለ ሆኖ የተሠራበት አጠቃላይ ውጭ ታስቦ 285 ሺህ564 ብር ዋጋ ተተምኖለታል ።

የማሽኑ የዋጋ ልዩነት ብቻ ያለው ሳይሆን መጠኑም ቢሆን ለንጽጽር እንኳን የማይቀርብና በጣም የተሻለ ምርት መሆኑ በሀገር ውስጥ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ገልጸው፤ ሀገር ውስጥ ያለን ውስጣዊ አቅም መጠቀም ከተቻለ ከዚህ በላይ የሆኑ የተሻሉ ሥራዎች መሥራት የሚያስችል አቅም እንዳለ ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ይህ ማሽን በጥራትም ቢሆን የተሻለ ጥራት እንዳለው ተረጋግጧል›› የሚሉት አሠልጣኙ፤ ማሽኑ ጥራቱን የጠበቀ ሲሆን የሚያመርታቸው ምርቶችም የተቀመጠላቸውን መስፈርት የሚያሟሉና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያስችላል።

ይህ ማሽን ሀገር ውስጥ መሠራቱ ተመራጭ ከሚያደርገው ዋንኛ ነገር ማሻሻል በተፈለገ ጊዜ በሚፈለገው መጠንና ልክ መሥራት የሚቻል መሆኑ ላይ ነው ያለት አሠልጣኙ፣ ጥገናም ሲያስፈልገው በቀላሉ ሊደረግለት እንደሚችል አስታውቀዋል። ማሽኑን ከመነሻው ጀምሮ እስከመጨረሻው ድረስ የሠሩት ባለሙያዎች በኮሌጁ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ማሽኑን ፈታትው መልሰው መግጠም እንደሚችሉና ጥገናም በሚፈልግ ጊዜ በፍጥነት አስፈላጊውን ጥገና ያደርጋሉ ሲሉ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከውጭ የሚገቡትን ማሽኖች ለመጠገን የማይቻልባቸው አጋጣሚዎች ይከሰታሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከውጭ የሚመጡ ማሽኖች የተደበቀ ነገር ስላላቸው አንዱን ነገር መጠገን ቢቻል ሌላ መጠገን የማይቻል ሊገጥም ይችላል። ከውጪ የሚመጡ ማሽኖች ሲጠገኑ ብዙ ነገሮች ሊባለሹ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

በኮሌጁ የተሠራው ይህ ማሽን ግን አብዛኛው ነገሩ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባብዛኛው በሀገር ውስጥ ባሉ መካኒኮች ሊጠገን የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። ካልሆነም ማሽኑን የሠራው አካል ጥገና እንዲያደርግለት መጠየቅ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ቴክኖሎጂዎች እንደየአ ሠራራቸው ለረጅም ጊዜያትና አጭር ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው ይሠራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከውጭ የሚመጡ ማሽኖችን ሲታዩ ውጫዊ ገጽታቸው ያመራል፤ ጥራታቸው በዚያኑ ልክ የሆነ ይመስለናል፤ ነገር ግን ውበታቸው ስለሚሰብ ብቻ ጥራትም ሆነ ጥንካሬ ላይኖራቸው ይቻላል። እርግጥ ነው አንድ ቴክኖሎጂ ጥራትን ከጥንካሬና ውበት ጋር አዋህዶ ቢይዝ ይመረጣል። አዲሱ ማሽን ጥራት ፣ ጥንካሬና ውበት እንዲኖረው ታስቦበት የተሠራ ነው።

እንደ አሠልጣኙ ማብራሪያ፤ ማሽኑን ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋሉት ቁሳቁስ መጠን ጥንካሬ ያላቸው በመሆኑ ማሽኑ ለረጅም ጊዜያት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። በውስጣዊ የማሽኑ ክፍሎች የተገጠሙት የፕሌትና ራውንድ ፓይፕ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው። ውጫዊው የማሸኑ ክፍሎችም በሚፈለገው ልክ ደረጃቸውን የጠበቁ ቁሳቁስ የተገጠመለት ነው።

ማሽኑ እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ጊዜ ከበራ በኋላ ምንም መንካት ሳያስፈልገው በራሱ ይጠፋል። የሰአት መቆጣጣሪያ /ታይመር/ ስላለው ታይመሩ የተሞላው ደቂቃ ሲደርስ ማሽኑ እንዲቆም ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት ማሽኑ በአውደርዕይ ቀርቦ ህብረተሰቡ አውቆት እንዲጠቀምበት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ማሽኑ ተመርቶ ለተጠቃሚ እንዲያቀርብ ለኢንተርፕራይዙ መሸጋገሩን አመልክተ ዋል። ኢንተርፕራይዙ አምርቶ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ራሱም ተጠቅሞ ሀገርም ለመጥቀም እንደሚችል አስታውቀዋል።

ኢንተርፕራይዙ ማሽኑን ከዚህ ባነሰም ሆነ በበዛ መጠን በሚፈለገው ልክ ማምረት እንደሚችል ጠቅሰው፤ የሃሳቡ አመንጪ ኢንተርፕራይዝ መጀመሪያ ላይ የጀመረው ማሽን ከአዲሱ ማሽን በመጠን ያነሰ እንደነበርም አስታውሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኮሌጁ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ሥራ ሊውሉ የሚችሉ ማሽኖችም አሉት። በተለይም ለዚህ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ወርክሾፖች አሉት። ከውጭ የሚመጡ ሁሉም ማሽኖች በሚባል ደረጃ ያሉት ሲሆን፣ በቂ አሠልጣኞችም አሉት። ይህ ሁሉ ብዙ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳለው ያመለክታል። በኮሌጁ የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ጊዜ ከኢንተርፕራይዙ ፍላጎት የመነጩ ናቸው። ‹‹እኛ ሠርተነው ኢንተርፕራይዙ ካላመረተው አንሥራም። ስለዚህ ኢንተርፕራይዞች አምርተው ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ተቋሙ በቀጣይም የኢንተርፕራይዞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂን እንደሚሠራ ገልጸው፣ በኮሌጁ የተሠሩት ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢንተርፕራይዞች ተሸጋግረው ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሆነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You