ከሥጦታዎች ሁሉ የከበረ የበጎ ፈቃድ ሥጦታ

በሀገራችን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከልጅ ልጅ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነባር ባህል ነው። የታመመን ማስታመም፣ የታረዘን ማልበስ፣ የተጠማና የተራበን ማብላት ማጠጣት፣ አደጋ የደረሰበትን ማሳከም፣ ሀዘኑንም ደስታውንም መካፈል፣ አብሮ መብላት መጠጣት፣ እንግዳ መቀበል እንዲሁም ከቤተሰብ አቅም በላይ በሆኑ (በእርሻ፣ በጎጆ ማዋቀር …) ሥራዎች መደጋገፍና መተጋገዝ… ወዘተ በርካታ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው በጎ ሥራዎች ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው የሚያከናውኗቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ በጎ ሥራዎችም ኢትዮጵያዊያን በዓለም መድረክ ይታወቃሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን በአካባቢ፣ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደራጀ ሁኔታ ለሀገርና ለሕዝብ ሁለንተናዊ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ በሚያበረክቱበት አግባብ ሳይከናወኑና ሳይመሩ እልፍ ዘመናት ነጉደዋል። ሥራውንም የሚያስተባብርና የሚያቀናጅ ዘመናዊ አደረጃጀቶች አልነበሩም።

በሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥምሪት፤ በ2003 ዓ.ም በተደራጀ መልኩ እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ። አገልግሎቱም የክረምትና የበጋ በሚሉ ክፍሎች በተለያዩ መስኮች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በተለይ በሀገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ከ2010 ዓ.ም የክረምት ወራት ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻዎች ይበልጥ ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በየዓመቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ክረምትን መሠረት አድርገው ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች የቤት ዕድሳት፣ የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡ አበይት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወጣቶችም አገልግሎቱን ከአካባቢ አልፈው ወሰንና ድንበር ተሻግረው ጭምር እየሰጡ ይገኛል።

በተያዘው የክረምት ወራትም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ14 የተለያዩ አንኳር ዘርፎች አገልግሎቱ እየተሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ደም ልገሳ ነው። ደም መለገስ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልስ ከበጎ አድራጎቶች ሁሉ የላቀ ውድ አገልግሎት ወይም ስጦታ ነው። ምክንያቱም የደም ህክምና የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን፤ በሌላ የህክምና ዘዴ ሕይወታቸውን ማትረፍ አይቻልም። ስለዚህ የደም ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች ሁሌም የደጋግ ወገኖቻቸውን ክንድ ይሻሉ።

ከዚህ አንጻር ከዓመት ወደ ዓመት በጎ ፈቃደኞች የሚለግሱት ደም እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን የደም ሕክምና ከሚፈልጉ ሕመምተኞች አንጻር ፍላጎቱን ለማሟላት ገና ብዙ የቤት ሥራ ይቀራል። በተለይ ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት መመዘኛ መስፈርት መሠረት ከአንድ ሀገር ሕዝብ ቁጥር ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ወይም ሰው ደም ለጋሽ መሆን አለበት። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር ብዛት አንጻር ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ቋሚ ደም ለጋሽ ሊሆኑ ይገባል። በድርጅቱ መስፈርት መሰረት ደግሞ ሀገሪቱ ሶስት ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ሰዎች ቋሚ ደም ለጋሽ ሊኖራት ይገባል።

ነገር ግን ህብረተሰቡ ደም መለገስ ልትቋረጥ የነበረችን ሕይወት እንደገና ተስፋዋን የማለምለም ሰብአዊ አገልግሎት መሆኑን ተረድቶ ደም ከመለገስ አኳያ ግንዛቤው አናሳ ነው። በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፈቃደኝነት ደም መለገስ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ የሚለግሱት 0 ነጥብ 4 በመቶዎቹ ብቻ ወይም ከ400 ሺህ የማይበልጡ ሰዎች እንደሆኑ ከየኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ልብ በሉ 120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላትና ፍላጎቱ ከፍተኛ በሆነበት ሀገር፤ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት አንጻር ሲታይም የለጋሾች ቁጥር ከግማሽ በታች ነው።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለይ በክረምት ወራት ከአየሩ ጸባይ ጋር ተያይዞ እንዲሁም ደግሞ ደም ልገሳ በስፋት የሚከናወንባቸው ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው የሚሰበሰበው ደም ዝቅተኛ እንደሆነ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህም ደምና የደም ተዋፅኦ በማጣት በርካታ የደም ህክምና የሚሹ ወገኖች ሕይወታቸው ያልፋል። በደም እጦት እናት ሕይወት ለመስጠት ሕይወቷን ታጣለች። በየሆስፒታሉ የደም ካንሰር ህክምና የሚያደርጉ ዘለው ያልጠገቡ እምቦቃቅላ ሕፃናት በደም ተዋፅዖ እጦት ይሰቃያሉ።

ስለዚህ ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት እድሜው ከ18 ዓመት እና ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሆነ ደም የመለገስ ቁመና ላይ ያለ ዜጋ ሁሉ ደም በመለገስ ልትቋረጥ ያለች ሕይወትን ለማስቀጠልና የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በክረምቱ የደም ልገሳ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ በስፋት መረባረብ ይገባል። አንድ እናት ሕይወት ለመስጠት ሕይወቷን እንዳታጣ ሁሉም ለእናቱ ክንዱን ሊዘረጋ ይገባል።

ሌላው አንድ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ በአንዴ ከሚለግሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም ሦስት የደም ተዋጽኦዎች (ፕላትሌት፣ ፕላዝማ፣ ቀይ የደም ሴል…) እንደሚመረቱ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። ስለዚህ አንድ ሰው አንዴ በሚለግሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም የሦስት ሰዎችን ሕይወት መታደግ ይችላል። በመሆኑም አንዴ በምንለግሰው ደም የሦስት ወገኖቻችንን ሕይወት ከመታደግ በላይ ምን የሚያስደስት፣ የሚያረካ ነገር ምድር ላይ አለ? ደም መለገስ ከበጎ አድራጎቶች ሁሉ የላቀ፣ ከስጦታዎች ሁሉ የከበረ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚታደግ ሰናይ ተግባር ነው። ከዛም ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን ከመፍጠር አኳያም ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ደም በመለገስ ልትቋረጥ ያለችን ሕይወት በማስቀጠል ከሚገኘው መንፈሳዊ እርካታ ባሻገር ዘርፈ ብዙ የጤና እንዲሁም ሌሎች ገጸ በረከቶች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ስለዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለይ ደግሞ ደም ልገሳን ሁሉም ማህበረሰብ ባህል ማድረግ አለበት። ለበጎ ሥራ እረፍዶ አያውቅምና ዛሬም፣ ነገም በቋሚነት ደም እንለግስ።

በጥቅሉ የበጎ ፈቃድ ሥራ በገንዘብ የማይገመት፣ የህሊና እርካታ የሚያስገኝና ሰዎች ለሰዎች ራሳቸውን የሚሰጡበት በጎ ተግባር ነው። ስለዚህ በተያዘው የክረምት ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በተለይ ወጣቱ በደም ልገሳ በጎ አድራጎት ሥራ ላይ በነቂስ ሊሳተፍ ይገባል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You