ሰላምና ኢኮኖሚ ለስኬታማ ዲፕሎማሲ

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ በክረምት ወቅት ደግሞ ከ86 በመቶ በላይ ለዓባይ ውሃ አስተዋፅኦ ታበረክታለች። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ በዓባይ ውሃ አንዳችም ጥቅም አልተጠቀመችም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የህዳሴ ግድብን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ስትነሳ ጫጫታው በርክቶ ነበር። አሁንም ድረስ በዚች ሀገር ላይ በእጅ አዙር ጭምር ጦርነቶች፣ግጭቶች፣አለመረጋጋቶች እንዲሰፍኑ ማድረግና ግድቡ እንዳይሞላ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ደባና ተንኮል ሲያሴሩ እንደነበር ይታወቃል።

92 ከመቶ የውሃ ሀብቷ ወሰን እየተሻገረ እንጥፍጣፊዋን ከጎረቤቶቿ የማታገኘው ኢትዮጵያ ስለጋራ ተጠቃሚነት ከማንም ቀድማ ወትዋች ናት። የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉባ ላይ መገንባት ስትጀምርም ይህን የዘመናት የትብብር ቀናይነቷን አሳይታለች። በወንዞቿ ለመጠቀምና ድህነትን ለማስወገድ በምታደርገው ጥረት ሁሉ ራሷን ብሎም ጎረቤቶቿን ጭምር ለመጥቀም እንጂ ማንንም ለመጉዳት አለመሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቃለች።

ኢትዮጵያ ህዳሴዋን እውን ለማድረግ ግድብ ለመገንባት ስትጀምር ለጋራ ተጠቃሚነት ጆሮዳባ ልበስ ብላ የቆየችው ግብፅ አራስ ነብር ሆና ብቅ አለች። መጀመሪያ መረጃ ስጡኝ በኋላ በገለልተኛ ቡድን ካልተጠና ከዚያም በሶስተኛ ወገን እንደራደር እያለች ካንጋሮአዊ አቋሟን ተያያዘችው። ኢትዮጵያ ግን የማይናወጥ አቋሟን በመሀላ ጭምር ገልፃ ግንባታዋን ቀጠለች እንጂ ለእንካሰላንቲያው ቦታ አልሰጠችም።

የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድንም ሆነ የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ቡድን ያቀረቡት ሪፖርት ለካይሮ ሹማምንት የሚዋጡ አልነበሩም። በመሪዎች ደረጃ የተደረጉ ውይይቶችም አጥጋቢ አልሆነላቸውም። እናም በገለልተኛ ሽፋን ሸሪኮቿን እንዲያደራድሯት አደራጀች፤ አሜሪካንና የዓለም ባንክን።

ኢትዮጵያ ግን ዋሽንግተንም ሆነች የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ያለፈ ሚና አይኖራቸውም በሚል ለፊርማ ያቀረቡትን ሰነድ አልፈርምም ብላ ውድቅ አደረገችው። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ግብፅ ግድቡን ታጋየዋለች እስከማለት ደረሱ። ትራምፕ ባዶ ፉከራ የትም እንደማያደርስ ቢረዱም የተለመደ የአዞ ለቅሷቸውን ቀጠሉ።

የህዳሴው ግድብ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ አድርጎ ሊይዘው ይገባል የሚል የውሃ ጉዳይን ተመልክቶ የማያውቀው የፀጥታው ምክር ቤት ይገላግለን ጥያቄአቸው ግን እንዳሻቸው አልሆነላቸውም። የኢትዮጵያ ልጆች እውነትን ይዘው አሸናፊ ሆኑ። ድል ጨብጠውም ስለትብብር እንጂ ሌላውን ስለመጉዳት አይናገሩም።

ኢትዮጵያ ስለጋራ እድገት ስትሰራ ግብፅ ግን ዜጎቿን በስጋት መወጠር ላይ ተጠምዳለች። መሪዎቿም ማስፈራሪያና እያንዳንዱን ነገር ከግድቡ ጋር የማገናኘት አባዜአቸው ለዘመናት ቅብብሎሽ የሚለወጥ አይመስልም።

ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ወትሮውንም የተፈጥሮ ሀብቷ ብዙ ጠላት ያፈራላት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ምክንያት በከባድ የዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ ከርማለች። በፈተናም ውስጥ ሆና ትብብር ላይ ያተኮረችው ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ እንደተጀመረ ሱዳንን ሁነኛ አጋር ለማድረግ ያደረገችው የዲፕሎማሲ ጥረት በፍሬአማነቱ ይነሳል። ሱዳን ይሁንታ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አልበሽር ለኢትዮጵያ የ10 ሚሊዮን ዶላር የግንባታ ማሽነሪ በእርዳታ ሰጥተዋል። እርዳታውንም ሲያስረክቡ ከፈለጋችሁ ለህዳሴ ግድብም ተጠቀሙበት ብለው ነበር።

ግብፅ ከአረብ ሊግ እስከ አውሮፓ ህብረት፣ከአሜሪካ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሀሰት መረጃ አጋር ፍለጋ ስታማትር ኢትዮጵያ በአንፃሩ የግድቡ ግንባታ ማፋጠንን፣የውሀ ሙሌቱን ማስጀመርን መርጣለች። ሀቁ በሂደት ይገለጣል በሚልም ስራ ይቅደም ብላለች። ይሁን እንጂ ጫናውን የሚያቃልሉ እውነታን ለዓለም የሚነግሩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን መስራት ቀጥላበታለች።

እንደዚህ ያሉ ጫናዎችን ኢትዮጵያ የምትቋቋመው ብቻዋን ሆና አይደለም። ከሌሎች ሀገራት ጋር አብራ መስራት ስትችል መሆኑን ቀድማ የተደራችው ኢትዮጵያ ትብብርንና የጋራ ተጠቃሚነትን አስቀድማለች። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። በዓለም ላይ ተሸጋሪ ወንዞችን የሚጠቀሙ ሀገራት በስምምነት በጋራና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እየተጠቀሙ ቢሆንም የናይል ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን በፍትሀዊነት እየተጠቀሙ አይደለም።

ይህ ኢፍትሀዊ አካሄድ ማብቃት አለበት በሚል የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እኤአ በ2006 የተዘጋጀ ሲሆን፤ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሀብቶችን በትብብር ማልማትና ማስተዳደር የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ነው። የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ /ኤን ቢ አይ የሽግግር ማዕቀፍ ሆኖ በዘጠኝ መስራች አባል ሀገራት የጋራ ራዕይ የተመሰረተና ቋሚ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እስከሚመሰረት የሽግግር ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ መቋቋሙ ይታወቃል።

ኢትዮጵያም የህዳሴ ግድብን በጀመረችበት ጊዜ የስምምነቱን ፊርማ አፅድቃለች። ሀገራት ስምምነቱን እንዳይፈርሙ ትልቅ ተፅዕኖ እንደነበረባቸው ይታወቃል። በገንዘብ ማባበያ፣ በማስፈራሪያ ምክንያት ጥቂት ሀገራት ብቻ ነበሩ ስምምነቱን የፈረሙት። በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ፈርማለች። እንዲህ መሆኑ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

በተለይ ደግሞ በውሃ አጠቃቀም ላይ ፍትሀዊነትን ለማስፈን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን እሳቤን በመያዝ በተለይ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን ለመፈረም አሻፈረኝ ብለው ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ከተፋሰሱ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ 50 በመቶ ያህሉ መፈረማቸው ለተሰራው ስራ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ በደቡብ ሱዳን መፅደቁ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን በቂ ድጋፍ አስገኝቷል። ረጅሙ የዓለማች ወንዝ የዓባይ ወንዝ አስራ አንድ የተፋሰስ ሀገራት ይጋሩታል። ሆኖም እስካሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በቀደመው ስምምነት ውሃውን ግብፅና ሱዳን ብቻ እንዲከፋፈሉት የሚል ነበር።

ታዲያ አዲሷ የተፋሰሱ ሀገር ደቡብ ሱዳን የወሰደችው እርምጃ ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው ተብሎለታል። ውሳኔው የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ለመሻርና በአዲስ ለመተካት የሚያስችለው የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ያደርጋል። አዲሱ ስምምነት ከአስራ አንዱ ናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ስድስት ሀገራት በፓርላማቸው ካፀደቁት ቋሚ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባት ይችላል።

በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለው ማዕቀፍ ምክንያታዊ፣ፍትሃዊ ሆኖ የናይልን ውሀ ለመጠቀም የሚረዳ ነው። ሀገራቱ ይህንን ተጠቅመው ማህበረሰባቸውን ለመጥቀም የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል። ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን መፈረሟ ሀገራቱ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን አቋቁመው በጋራ ሆነው ለማስተዳደርና ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናል። በሀገራቱ የሚኖረውን ጥምረት ያጠናክረዋል፤በተጨማሪም የናይል ተፋሰስ ማህበረሰብ የሚለውን ማንነት በቀጣናው ትስስር በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

የናይል ተፋሰስ የውሀ ምንጭ የሆኑት የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ፍትሀዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም የሚለውን መርህ የሚያሟላ መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። ስምምነቱ የውሀ ደህንነታችን እና ታሪካዊ ድርሻችንን ማረጋገጥ አለበት የሚል አቋም ያላቸው ግብፅና ሱዳን ደግሞ እስካሁን ስምምነቱን አልፈረሙም።

የደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር በመሆን ስምምነቱን ማፅደቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ይዞት የሚመጣው እድል ከፍ ያለ ነው። ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት ብቻ ነበሩ የፈረሙትና ያፀደቁት። ትጠበቅ የበረችው ስድስትኛዋ ሀገር ደቡብ ሱዳን አሁን አፅድቃለች። ይህ መሆኑ በተለይ ያልፈረሙ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት ስምምነቱን ተቀብለው እንዲያፀድቁ የሚያበረታታ ነው። ፍትሀዊና እኩል ተጠቃሚነት የሚለው ሀሳብ ውሀውን በብቸኝነት የመጠቀም ዝንባሌ የነበረውን የቅኝ ግዛት ውል ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርጋል።

ደቡብ ሱዳን ለቀጣናው ጠቃሚ የሚባል ውሳኔ ከመወሰኗ በላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጨምር እድል ይፈጥራል። የተፋሰሱ ሀገራት ወደ ስምምነት ሲደርሱ በጋራ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ውሃውን መጠቀምና ማስተዳደር እንችላለን የሚል እምነት ይዳብራል። በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን የናይል ስምምነት ማዕቀፍን መፈረሟ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነትም ያሳያል። ይህም ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ዙሪያ ያሉትን ሀገራት ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ የነበረና ይህም ሃሳቧ ተቀባይነትና ድጋፍ እያገኘ ስለመምጣቱ አንዱ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ይህ እውን እንዲሆን ያደረገችው ጥረት አወንታዊ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑ በውጤት የሚያሳይ ነው። ባለፉት ረጅም ዓመታት በዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ዙሪያ ፍትሀዊነት እንዲመጣ ሚናዋ ላቅ ያለ ነበር። የናይል ስምምነትን ለማፅደቅ ሂደቱ ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ኢትዮጵያ በኤምባሲዋ በኩል በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት ብዙ ትግል አድርጋለች። በሰራችው ስራም ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እየተቀናጀች ነው።

የዲፕሎማሲ ዋንኛ ዘዋሪው ግን ኢኮኖሚው ነውና ኢኮኖሚው መነቃቃት ሲጀምር በንቀትም ይሁን በርቀት ሲገፉን የነበሩ ሲመጡ እያየናቸው ነው። ያነሳነው ፍትሀዊ የወደብም ሆነ የውሀ ልማት ጥያቄ ቢያንስ ውሀውን በማንኪያ እንኳ መንካት አትችሉም ከሚል ድንፋታ ቀይ ባህር ላይ እድል፣ ፈንታ፣ ፅዋ፣ተርታ የላችሁም ከሚል ጫጫታም ተላቋል። የመልማት መብታችን ቢያንስ በመርህ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ከዚህ የበለጠ አድገን ከእህል ልመና ብንላቀቅና ራሳችንን ብንችል ከዚህም ከፍ ብለን ለሌሎች ብንተርፍ ደግሞ የት እንደሚደርስ መጠበቅ ነው። ኢኮኖሚያችን እነዚህን እድሎች ካመጣልን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ እገታዎችና የፀጥታ መደፍረሶች በሰላም ቢፈቱ፣መፈናቀሎች ቆመው ሁሉም ወደቀየው ቢመለስ ደግሞ ኢኮኖሚያችንም ዲፕሎማሲያችንም ጫፍ ላይ ወጥተው የመቀመጥ እድል አላቸው። እንደሕዝብ ከዚህ ዋነኛ ተጠቃሚዎቹ እኛው እስከሆንን ድረስ ሰላም እንዲሰፍን ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ልንሰራ ይገባል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You