‹‹ትውልዱን ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ ጊዜ የማይሰጥ ሥራ ነው››

ታላቁ ሊቅ ዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በሚል ርእስ በ1956 ዓ.ም ካሳተሙትና አሁን ላይ እንደ ክላሲክ ድርሳን በሚታየው መጽሐፋቸው ‹‹ትምህርት ከሰው ሥራ ወይም ከሰው ሕይወት ከዋነኞቹ ክፍሎች አንዱ ነው። ስለዚህ በተለይ ሊጠና ሊመረመር ይገባዋል›› ሲሉ ይገልጹታል። ትምህርት የሰው ልጅ በዘመናት መካከል በብዙ ጥረትና ድካም ያገኛቸው ያከማቻቸው የዕውቀት ዘርፎች ተቀምረው፤ ተተንትነውና ተደራጅተው የሚገኙበት መስክ፣ ይህም የተገኘና የተደራጀ ዕውቀት በተሟላ መልኩ ለትውልድ ማስተላለፊያ ነው።

ታላቁ አሪስቶትል “ሜታፊዚክስ” በተባለው ድርሳኑ መግቢያ ላይ፣ “የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለማወቅ በብርቱ የሚሻ ፍጥረት ነው” ይላል። ትምህርት ደግሞ የሰው ልጅ የማወቅ ፍላጎት ሕሊናውን እና ልቦናውን ከነካው ጊዜ ጀምሮ ዘወትር በንቃት እና ያለ ዕረፍት ባለመታከት ያስገኘው እንዲሁም ያደራጀው ዋናው የሕሊናው ፍሬው ነው።

በመሠረቱ፣ ስለ ትምህርት ትክክለኛ አስተያየት ከተያዘ እና በቂ ትኩረት ከተቸረው ደግሞ ማንኛውንም የሕይወት ችግር ሊፈታ መቻሉን ለአቅመ ማሰብ የደረሰ ሁሉ የሚጠፋው ሃቅ አይሆንም። ትምህርትም ከሰው ልጅ የሕይወት ጥረቶች ውስጥ እንደ አንዱ እንደመሆኑ ከዘመንና ከቦታ ጋር የተቆራኘ ነው።

ትምህርት ምንጊዜም ቢሆን ከዘመንና ከቦታ ጋር የተያያዘ ነውና እንደቦታውና እንደዘመኑ የሚገጥሙትም ችግሮች የተለያዩ ይሆናሉ። በዚህ ሂደት አዳዲስ ችግሮች በየጊዜው እንደማጋጠማቸው ጊዜያቸውን የዋጁ አዳዲስ መፍትሄዎች ማስፈለጋቸው ከጊዜ ወደጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

በዚህ ረገድ የጊዜያችን እና የወደፊቱ ጊዜ የትምህርቱ ዘርፍ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ የሚዘልቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚያስከትለው ተጽእኖ መሆኑ በገሀድ እየታየ ነው። ሰው ሰራሽ አስተውሎት ደግሞ የቴክኖሎጂውን ተፅእኖ በግልፅ በማስመልከት ላይ ከሚገኙት ፈጠራዎች ዋነኛው ነው።

ለመሆኑ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ ሌሎች ሁሉ ለትምህርት ዘርፉ የሰጠው ፈተናና እድል ምን ይሆን? ሀገር በተለይም ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ ለማዋልና መልካም በረከቱን እንድትቋደስ ምን ማድረግ ይገባል? ከሰሞኑ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ይፋ የሆነው “ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ” ቴክኖሎጂው ለትምህርት ዘርፉ ምን ይዞ መጥቷል የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ከዩኒቨርሲቲው መምህርና ከቴክኖሎጂው ፈጣሪ ሕዝቅያስ ታደሰ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎና ትምህርት

ባለንበት ፈጣንና ተለዋዋጭ የዲጂታል ዘመን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ከጤናው መስከ እስከ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ ከንግድ እስከ የመጓጓዣ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪው መላውን የዓለም ሕብረተሰብ ገጽታ በመቀየር ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ ወደ አዕምራችን ቀድመው ከሚታወሱ ጥያቄዎች ውስጥ የትምህርቱ ነገርስ? የሚል ነው።

ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የሕይወት ዘርፍ መልሶ በማበጀትና በመበየኑ ረገድ ወሳኝ በሆነበት በዚህ ዘመን የትምህርትም እጣ ፈንታ ከዚ የራቀ ሆኖ አይገኝም። ዘርፉን እንዴት ነው የሚነካው የሚለውን ጉዳይ አሁን ላይ በቅጡ ለመበየን ቢከብድም፣ የትምህርቱን ሥርዓት በበጎም ይሁን በመጥፎ የመለወጥ አቅሙን መካድ ግን አይቻልም።

በትምህርቱ ዘርፍ ያለው ተፅእኖ ለመረዳት በተለይም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት መመልከት በቂ ነው። ተማሪዎች ላይ በተካሄደው በዚህ ጥናት ከ 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ አጋዥ የማስተማሪያ ቁስ መካተቱ ለመማርና ለማወቅ ባላቸው ተነሳሽነትና የትምህርት ተሳትፏቸው ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅእኖ እንደፈጠረላቸው መናገራቸውን አመላክቷል።

ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ማህበር (ISTE) የተገኘ ሌላ ጥናት ደግሞ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በትምህርት ውስጥ መገልገል የተማሪዎችን አፈጻጸም/performance እስከ 30 በመቶ እንደሚያሻሽለው ይፋ አድርጓል። ከተማሪዎች ባሻገር መምህሩ ላይ ያለውን ተፅእኖ በሚመለከት ሚኬንዚ/McK­insey ባካሄደው ጥናት ደግሞ፣ የተወሰኑ ስራዎችን ብቻ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አውቶሜት/automate በማድረግ ብቻ በሳምንት እስከ 13 ሰዓት የሚደርስ የመምህራንን የስራ ጫና መቀነስ እንደሚቻል ተጠቁማል። ይሄም የመምህራንን የሥራ ጫና በመቀነስ መምህራኑ ይበልጥ ወሳኝ በሆኑ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ያስችላል ይላል ።

በተመሳሳይ በኢስኩል ኒውስ/eSchool News የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነም፣ 47 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት ተቋማት መማር ማስተማሩን ለማጎልበት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንደመፍትሔ መጠቀማቸውን ይገልፅልናል።

የቴክኖሎጂው የገንዘብ አቅም

በዘርፉ የሚንቀሳቀሰውም ገንዘብ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት እየተሰጠ ያለውን ልዩ ትኩረት በይበልጥ የሚያሳይ ነው። ለዚህም ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ለአብነትም ሆለንአይኪው/HolonIQ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በ2025 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ በትምህርቱ መስክ ብቻ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንቨስት የተደረገው አጠቃላይ ወጪ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ያስቀምጣል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስጋት ወይስ በረከት

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሁለት የአመለካከት አዝማሚያዎች መካከል ተወጥሮ ይገኛል። ማለትም ለትምህርት ዘርፉ ስጋት ወይስ በረከት? የሚለውን በመበየኑ ረገድ በዋናነት ሁለት ተፎካካሪ ሙግቶች ይቀርባሉ።

በአንድ ወገን ቁሱን በዓለም ዙሪያ ላሉ በርካታ የትምህርቱ ዘርፍ ማነቆዎች እና ፈተናዎች ሁሉ መፍትሄ ይሆናል ብለው የሚያምኑና የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው። በአንጻሩ ይህን እሳቤ የሚቃረኑ ሌላ ጽንፎችና በተለይም በትምህርት ቤቶች Chat GPT (በህዳር ወር 2022 እ.ኤ.አ. ኦፕንኤአይ በተሰኘ ድርጅት የተለቀቀ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መጠሪያ ስያሜ ነው) እንዲታገድ ጥረት ያደረጉ ተጠራጣሪዎችም ይስተዋላሉ።

እዚህ ጋር በተለይም ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ “አንድ ሰው ለራሱ የማይመስለውን ነገር ለማፍረስ ብቻ ይሰለፋል። ሌላው ደግሞ ማፍረስን ለሌላው ትቶ በገዛ ሃሳቡ መሠረት አዲስ ለመገንባት ብቻ ያስባል። የተሻለው ዘዴ ሁለተኛው ይመስለናል።” ያሉትን ተከትሎ እያሰላሰሉ መራመድ አግባብ ሆኖ ይገኛል።

ይህ ማለት የኛም ጥረት በገዛ ሃሳባችን መሠረት አዲስ ቤት ለመሥራት እንጂ በአሮጌ ቤት የሚኖረውን ሰው ተጠግተን ‘ቤትህ የማይረባ ነው’ ለማለት አይደለም። ከዛ ይልቅ ሊቁ እንዳሉት “ከበረቱት አጠገብ አዲስ ቤት መሥራት ነው። ይህ አዲሱ ቤት ስለራሱም አዲስነት ስለሌላውም አሮጌነት ብቻውን ይናገራል።” ብለን በክርክሩ በቀጥታ ከመሳተፍ ይልቅ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዴት ለዘርፉ በረከት እንደሚሆን ወይም መሆን እንደሚችል ለማመላከት በመስክ የተፈተነውን የጥረታችንን የመጀመሪያ ሙከራ መመልከት እንችላለን።

የዲጂታል አጋዥ ወይንም አስጠኚ ውልደት

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ይፋ የሆነው “ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ” የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች ጥረት መነሻ በፈተና ዝግጅት ወቅት ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዴት መሻገር ይችላሉ ማለትን ታሳቢ ያደረገ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን ያነበቡትን በቅጡ መረዳት ብሎም በማስታወስና ጊዜን በአግባቡ ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት የመመደብ ድክመት እንዲሁም የሚነበቡ መጻሕፍት መብዛት ወደ አካዳሚክ ስኬት የሚደረገውን ጉዞ ፈታኝ እንደሚያደርጉት ይታወቃል። ተማሪዎች ለከፍተኛ ተቋም መውጫ ፈተና የሚዘጋጁ ከሆኑ ደግሞ የሚያጋጥሟቸው ችግሮችና ፈተናዎች ይበልጡኑ ያይላሉ።

በዚህ ረገድ ያነበቡትን በቅጡ ለመረዳት መቸገርን ጨምሮ ያነበቡትን ለማስታወስ መቸገር፣ ጊዜን በአግባቡ ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት መመደብ አለመቻል፣ የበዙ የሚነበቡ መጻሕፍትን፣ ሞጁሎችን፣ ሃንድ አውቶችንና የማጣቀሻ መጻሕፍትን አንብቦ ለመሸፈን መቸገር ድረስ ለከፍተኛ ተቋም መውጫ ፈተና የሚሰናዱ ተማሪዎችን ሲገጥም የሚስተዋል ስር የሰደደ አይነተኛ ችግር ነው።

እነዚህንና መሰል የተማሪዎችን ችግሮች ለማቅለል በፈተናዎቻቸውም የላቀ ውጤት እንዲያመጡ ለማገዝና ለማስቻል አዲስ ችግር ፈቺ መፍትሄ ማስፈለጉ የሚያከራክር አይደለም። በዚህ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥናትን ምርምር በማድረግ መፍትሄ ይሆን ዘንድ “ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ” ቴክኖሎጂውን ማበልፀግ አስፈላጊ ሆኗል። ይህ መፍትሄ ‹‹ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ/AI-powered chatbot/Personal Learning Companion Chatbot ይሠኛል።

ይህ ጅምር የቴክኖሎጂ ቁስ ለትምህርታዊ ዓላማ እንዲውል የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI)ን አቅም በመጠቀም ለመውጫ ፈተና ለሚዘጋጁ ተማሪዎች እንደ ረዳት መምህር ወይም አስጠኚ ሆኖ እንዲያገለግል የተዘጋጀ ነው። በአጭሩ የተማሪው ቨርቹዋል አጋዥ/ደጋፊ ወይንም አስጠኚ ልንለው እንችላለን። በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ለተማሪዎችም ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል።

በዚህም ከላይ ለተጠቀሱት መሰል ችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት ለመርዳት በቴክኖሎጂው አበልጻጊዎች ብዙ ጥረት ተደርጓል። ቴክኖሎጂው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሞከረ እንደመሆኑ ከስህተት ፈፅሞ የራቀ ነው ለማለት ግን አያስደፍርም። የቴክኖሎጂው አበልጻጊዎች ዶክተር እጓለ እንደሚሉት፣ ‹‹ምንም ባናስገኝም ጥረታችን ይበቃናል››። የሚል እምነት አላቸው።

ይሁንና የውጤታማነትና የተግባራዊነት ስኬታቸው በተማሪዎቻቸው ሚዛን የሚለካ ነው ባይ ናቸው። የቴክኖሊጂው የእገዛ አቅምም ከራሳቸው ተማሪዎች አንደበት ማረጋገጥ የሚቻል ነው ይላሉ። (ይህን ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ መመልከት አልያም መሞከር የሚፈልግም በዚ መስፈንጠሪያ link: https://www.temaribet.edu.et/) በመግባት መመልከትና መሞከር እንደሚችል ይጠቁማሉ።

በጥቅሉ የቴክኖሎጂው ዓላማ ለመውጫ ፈተና የሚዘጋጁ ተማሪዎችን ማገዝ እናም ለብሔራዊ የመውጫ የፈተና ሥርዓተ-ትምህርት የተዘጋጁ አጠቃላይ የጥናት መሣሪያዎችንና መርጃዎችን ማቅረብ ሲሆን የሚከተሉትንም ዝርዝር ፋይዳዎች ይሰጣል።

የቴክኖሎጂው ፋይዳዎች

በዋናነት ጥያቄዎችን ይመልሳል። ማብራሪያዎችን ይሰጣል። የመለማመጃ ጥያቄዎችን ያዘጋጃል። የተለያዩ የጥናት መረጃዎችን ጨምሮ ወርክሾፖችን፣ ግራፊክ ኦርጋናይዘሮችን፣ ፍላሽ ካርዶች፣ ኔሞኒክ ዲቫይሶችን ያዘጋጃል። ከዚህ ባሻገር የአጠናን ስልትን ይቀይሳል። የጊዜ አጠቃቀም መመሪያዎችንና የጥናት ልምድን ለማሻሻል የሚበጁ መመሪያዎችን ይነድፋል።

ይህ ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ ቴክኖሎጂ ከብሔራዊ ፈተና ሥርዓተ ትምህርት ጋር ተስምምቶ በመዘጋጀቱም ተማሪዎች ውስብስብ የሆኑ ጽንሰ-ሀሳቦችን በትክክልና በቀላሉ እንዲገነዘቡ የሚረዱ ዝርዝር ማብራሪያዎች፣ ምሳሌዎችና የማስታወሻ ዘዴዎችን በመስጠት ተማሪዎችን ለመውጫ ፈተና እንዲዘጋጁ ያደርጋል። በመሰል አበርክቶውም ተማሪዎች ለመውጫ ፈተና በሚገባ እንዲዘጋጁና በራስ የመተማመን መንፈሳቸውም ከፍ እንዲል እንዲሁም ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳል።

ይህ ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ በበይነ መረብ/ኢንተርኔት ግንኙነት ማንኛውንም ተማሪ ለመውጫ ፈተና እንዲዘጋጅ ያደርጋል። ከባህላዊ የጥናት ዘዴ በተለየ መልኩ ተማሪውን 24/7 እንዲያግዝ የተዘጋጀ ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ የእያንዳንዱን ተማሪ የተለያየ የመረዳት ዝንባሌ እና ስልት ብሎም የመማርና የመገንዘብ ፍጥነት ባገናዘበ መልኩ በልፅጎ መዘጋጀቱም ልዩ ያደርገዋል።

ቴክኖሎጂዎቹ ላይ የሚስተዋሉ ድክመቶች

የዚህ አይነት የሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታን የሚጠቀሙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ የሚቀርቡ ትችቶችንና ነቀፌታዎች አሉ። በአብዛኛው የሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታን የሚጠቀሙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያመነጩትን አልያም የሚሰጡትን ምላሽ (response) በተመለከተ በስፋት የሚነሳው ነቀፌታ የይዘቱን ጥራት የተመለከተ ነው። በዚህ ረገድ ተደጋግመው ከሚሰሙ የተቃውሞ ድምጾች ውስጥ ‘በኤ አይ የሚመነጭ ነገር ጥራት ይጎድለዋል፣ ውጤቶቹ ተዓማኒነት ይጎድላቸዋል’የሚሉት ጎልተው የሚሠሙ ናቸው።

ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት ችግር ይፋ በተደረገው ቴክኖሎጂ ላይ እንደማይስተዋል አበልፃጊዎቹ ሙሉ እምነት አላቸው። ምክንያታቸውም ይህንን አሳሳቢ ችግር አስመልክቶ ቀደም ብለው መፍትሔ ማበጀት መቻላቸው ነው። ይህ ቨርቹዋል አጋዥ ቴክኖሎጂ የሚያጣቅሰው እያንዳንዱ የዕውቀት ቋቱ (knowledge base) የተደራጀው በጥንቃቄ ለመውጫ ፈተና ዝግጅት ተብሎ በከፍተኛ ተቋም መምህራን በተዘጋጀ፣ ከእነሱም በተሰበሰበ፣ የእነሱንም ይሁንታ ባገኘ የሰነዶች ስብስብ ግብአትነት በመሆኑ ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋር እንዳይተዋወቅ ያደርገዋል። በዚህም ለተፈታኝ ተማሪዎች ለፈተናቸው በቀጥታ የሚጠቅሙ፣ ትክክለኛና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምላሾች ያቀርባል።

በመሠረቱ፣ በአሁኑ ወቅት የበዙ ተማሪዎች በልማዳዊው የአጠናንና የፈተና ዝግጅት ዘዴዎች በትምህርታቸው ስኬታማ ለመሆን ሲቸገሩ ይስተዋላል። ቨርቹዋል አጋዥ እውን መሆን ለዚህ ትልቅ መፍትሄ ነው። በተለይም የተማሪዎችን ተሳታፊነት በማሳደጉ፣ የመረዳት ደረጃቸው መለያየቱን አልያም በተለያየ የመረዳት ደረጃ ላይ መገኘታቸውን ታሳቢ በማድረጉ፣ የእያንዳንዱን ተማሪ የተለያየ የመረዳት ዝንባሌ እና ስልት በመለየቱ፣ ለሁሉም ተደራሽ በመሆኑም ተመራጭ እና ጊዜውን የዋጀ ያደርገዋል።

ቀጣይ እርምጃና ፍላጎት

ይህ ጥረት ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ አይደለም። በአሁኑ ወቅት የአንደኛ ደረጃ ማጠቃለያ ፈተና ለሚወስዱና ወደ ከፍተኛ ተቋም መግቢያ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ማለትም ለ8 ተኛ እና ለ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች አዲስ ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚ እያዘጋጁ ይገኛሉ። መሰል የቴክኖሎጂ በረከት ለሁሉም የሀገሪቱ ተማሪዎች ለማድረስ የሚደረግ ጥረት ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አይደለም። እዚህም እዚያም ማነቆዎች ያጋጥማሉ። የቴክኖሎጂው አበልጻጊዎችም የዚሁ ፈተና ተጋፋጮች ናቸው።

ትምህርቱን ብሎም ትውልዱን የማገዝና የመደገፍ መሰል ቅን ሃሳብ በተናጠል ጉዞና ከባለድርሻ አካላት ትኩረትና ድጋፍ ውጪ ብዙ ርቀት መራመድ አይቻለውም። ይህ እንደመሆኑም ከሁለንተናዊ ፋይዳው አንፃር ቨርቹዋል አጋዥ ወይንም አስጠኚም ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን የበርካቶች የሃሳብም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ይሻል።

ትምህርት እና መጪው ጊዜ

በመሠረቱ፣ ትምህርት ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ አሁን ላይ የደረሰውን ዕውቀት መጠበቂያና እና መንከባከቢያ እንዲሁም በተሟላ መልኩ ለትውልድ ማሳወቂያና ማስተላለፊያ እንደመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑ ማንም የሚያውቀው ሃቅ ነው።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት እውን ማድረግ የሚቻለውም ከሁሉ በላይ በትምህርት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። የትምህርት አንዱ ዓይነተኛ ዓላማ ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀውን እውቀትና ችሎታ በማስታጠቅ ትውልዱን ዘመን ይዞ ለሚመጣበት ፈተናዎች ማዘጋጀት፣ በጥቅሉ ለወደፊት ኑሮው ማሰልጠንና ብቁ ማድረግ ነው። ይህም የመጪውን ጊዜ ፈተና አሁን ላይ ሆኖ መተለምን፤ ይህንንም ትልም የትምህርቱ ስልቶች አድርጎ መንደፍን፤ ትውልዱንም ለዚህ ማዘጋጀትን ሁሉ የሚያካትት ተግባርን ይሻል።

መጪው ጊዜ ደግሞ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በብዙ የሕይወት ዘርፎች የሚነግስበት ዘመኑም ዘመነ ኤአይ እንደሚሆን ለመገመት ብዙ ፍንጮች ስላሉ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። ስለዚህ ትውልዱን ለእነዚህና መሰል ዘመኑ ይዞት ከሚመጣው የዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ማላመድ እጅግ አስፈላጊ እና ጊዜ የማይሰጥ ስራ ነው። ከሁሉ በላይ የቴክኖሎጂን መልካም ስጦታ ለመቀበል መዘጋጀት ያስፈልጋል።

ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ “አንድ ሰው ወይም ሕዝብ በመሻሻል ወደፊት ለመራመድ ያለውን ምኞትና ናፍቆት በሥራ ለማዋል መፈለጉ የሚታወቀው ለወጣቱ ትውልድ የትምህርት ዓላማ ይሆን ዘንድ በሚወስነው ነገር ነው”። ማለታቸውን ለትምህርት መድከም/መጣር ምንኛ የተገባ እንደሆነ ጠንቅቆ ይገባን ዘንድ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You