ለፖሊሲው ውጤታማነት በይቻላል መንፈስ የተቃኘ የተሻለ አስተሳሰብ ያስፈልጋል

የሀገራችን ኢኮኖሚ ስብራት ዓመታትን ያስቆጠረ፣ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል የቆየ ስለመሆኑ ብዙም ለሰሚ አዲስ አይደለም። ችግሩን ለመፍታት የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማዘጋጀትም ወደ ሥራ ገብቷል።

ፖሊሲው ላለፉት ስድስት ዓመታት ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻለ፣ ሀገር ገብታበት ከነበረው አጣብቂኝ እንድትወጣ ጥልቅ አቅም የፈጠረ ነው። የሀገሪቱ ኢኮኖሚም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖም በየዓመቱ እድገት እንዲያሳይ ረድቷል። ይህም ፖሊሲው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል ።

ሰሞኑን እንደ ሀገር ተግባራዊ እየሆነ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የዚሁ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ማሻሻያው አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ሊብራላይዝድ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት አንድ አካል ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ገበያ መር እንዲሆን ወሳኝ ድርሻ ያለው ነው። በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት ለማሻሻልም ይረዳል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ላይ የተመሠረተና በቀጣይ ሥራ ላይ ከሚውሉ ሰፊ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ ነው። ዋና ግቡ ቀጣይነት ያለው፣ መሠረተ ሰፊና ሁሉን አሳታፊ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን ማረጋገጥ ነው።

ሀገራት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሲገቡ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ የተለመደ ነው። በዚህ ውስጥም በርካታ ያለፉ ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል። ለአብነትም ሕንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል በተለያዩ ወቅቶች የሪፎርም እና በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ችግሮቻቸውን ለማለፍ ችለዋል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት በርካታ ሀገራት አያሌ ምክረ ሃሳቦችን ተግብረዋል። በዚያው ልክ ደግሞ የምዕራባውያን የምጣኔ ሀብት ፍልስፍና እንደ ወረደ ለመተግበር ሞክረው ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉ ሀገራትም አሉ።

በኢትዮጵያም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ እና ወቅቱ የሚጠይቀው ቢሆንም አተገባበሩ ግን እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ እውቀት እና ብስለትን የሚጠይቅ ነው። ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ያለፈችባቸውን ችግሮች በማቃለል አስተማማኝ ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚያስችል፤ የሁሉንም ዜጋ ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ ነው።

መንግሥት እንደገለፀው፤ የማሻሻያ እርምጃዎቹ በመደረጋቸው ምክንያት፤ ‹‹በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢከኖሚ በአማካይ ስምንት በመቶ ያህል ያድጋል፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ የተጠጋ ይሆናል። የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ ይደርሳል፣ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ይላል።

የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊዮን ዶላር (የ3.3 ወራት የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ለመሸፈን የሚበቃ) በላይ ይሆናል››። እነዚህ ትንበያዎች በቀጣይ ዓመታት ከላይ በተጠቀሱት ማሻሻያዎች ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ሽግግር ደረጃ የሚያመለክቱ ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ለውጦችን ማምጣት ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ከተለመደው አሠራርና አስተሳሰብ ወጥቶ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። በተለይም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና የተቋማቱ አመራሮች ጉዳዩ ሀገርን የማሻገር ጥልቅ ታሪካዊ ጉዳይ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝበው በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት የነበረው የንግድ ሚዛን መዛባት ለማስተካከል የሀገር ውስጥ ምርትን በብዙ እጥፍ ማሳደግ ፣ ዘመናዊ ቴክሎጂዎችን፣ ሳይንሳዊ አሠራሮችን፣ ምሑራዊ ምክሮችንና እይታዎችን በመተንተን ወደ ተግባር መቀየር ይኖርባቸዋል። ወጣቶችም ሥራ ጠባቂ ከመሆን ወደ ሥራ ፈጣሪ የሚሸጋገሩበት ዕድል ማመቻቸትም ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ጠንካራ አቋም መያዝና ማስተካከል እጅጉን ወሳኝ ነው። ከባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ ወደ መደበኛ ሥርዓት ማስገባት፤ ከሁሉም በላይ አስተማማኝ ሠላም ማስፈን ያስፈልጋል።

ከውጭ የሚገቡ በርካታ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ቦታ ሊለቁ ይገባል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ እያመጣ ያለውን ውጤት በየወቅቱ መገምገም፤ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ትርፋማ ወደሚሆኑበት ሁኔታ ማሸጋገር፣ የሀገሪቱን ትልቁን ሀብት የተሸከሙትን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የማምረትና አገልግሎት የመስጠት አቅማቸው አሁን ካሉበት ሁኔታ እጅግ የላቀ አፈፃፀም እንዲኖራቸው መትጋት መሥራት ይገባል።

በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከገጠማት የማክሮ ኢኮኖሚ ሕመም ሙሉ ለሙሉ ለማገገምና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማ ለማድረግ ከመጣንበት መንገድ ላቅ ባለ ሁኔታ በይቻላል መንፈስ የተቃኘ የተሻለ አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ምሑራን በእውቀታቸው፣ ባለሃብቶች በገንዘባቸው፣ ፖለቲከኞች በሐሳባቸው እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You