ያልተፈታው የቢሮክራሲ ሸምቀቆ

በአመራር ጥበብና ብቃታቸው ‹‹ምርጥ›› ከሚባሉ እንዲሁም ስኬታማ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ ናቸው:: በርካቶችም ዓለማችን ከተመለከተቻቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች አንዱ ናቸው ‹‹greatest C.E.O. of the modern age›› ሲሉም ስለ ሥራና አመራር ብቃታቸው ይመሰክራሉ:: እኤአ በ1999ኝም ‹‹የክፍለ ዘመኑ ምርጥ የሥራ መሪ በሚል ተመርጠዋል:: እኚህ ሰው ጃክ ፍራንሲስ ዌልች ወይም በአጭሩ ጃክ ዌልች ይባላሉ::

እ.ኤ.አ በ1935 በአሜሪካ ማሳቹሴት የተወለዱት እኚህ ሰው፣ ከጀማሪ ባለሙያነት ተነስተው የአውሮፕላን/ የአቪየሽን/ የሕክምና እና የፋይናንስ ቁሳቁሶችን በማምረት የሚታወቀው የጀነራል ኤሌክትሪክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ሊቀመንበር ሆነው ሠርተዋል:: በዚህ ኩባንያ ውስጥ ለአራት አስርት ዓመታት ከጀማሪ ባለሙያነት ተነስተው የላይኛውን የአመራር እርካብ በመጨበጥ ስኬትን በስኬት ላይ ደራርበዋል።

የኩባንያው የገበያ ዋጋ እአአ በ1981 ከነበረበት 12 ቢሊዮን ዶላር በ2001 ወደ 410 ቢሊዮን ዶላር መወንጨፉም የሰውየውን የአመራር ጥበብ፣ ብቃትና ስኬታማነት ለመረዳት በቂ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ የሚችል ነው:: ሰውየው በአመራር ዘመናቸው የኩባንያው የገበያ ድርሻ እየሰፋ ትርፍን በትርፍ ላይ እየደረበ እንዲጓዝና ስምና ዝናው ከምርጦች ተርታ እንዲሰለፍ ለማድረጋቸው ታዲያ በተለይም የሚከተሉት ዋነኛ የሥራ አመራር ፍልስፍና ብሎም ማጠንጠኛ እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ ይታመናል:: ይህ ፍልስፍናም ‹‹ለሌሎች መማሪያ መሆን ይችላል›› በሚል በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ‹‹ዌልቺዝም›› ቲዮሪ በሚል ተቀምሮ በርካቶች ዘንድ ደርሷል።

በሰውየው የአመራር ጥበብና ስኬት ዙሪያ በተለይም ዌልቺዝም ፍልስፍናን በሚመለከት የተጻፉ ጽሑፎችም፣ ለዌልች የስኬት ምክንያት ከሁሉም በላይ ውጤት ላያ ማተኮር፣ የአስተዳደር እርከን ሠንሠለትን ማሳጠርና የተስተካከለ ቢሮክራሲን መተግበር የምርትና ምርታማነት ቁልፍ ነው የሚል አስተሳሰብና የፀና አቋማቸው ስለመሆኑ ያትታሉ::

‹‹የተስተካከለ ቢሮክራሲ የሁለንተናዊ እድገት ቁልፍ ነው›› የሚሉት እኒህ ሰው፣ እሳቤያቸውን በስኬት አስደግፈው በአደባባይ ማስመስከር የቻሉ እንደመሆኑ በአካል ባይኖሩም ዛሬም ድረስ የበርካቶች ድጋፍና አድናቆት አላቸው:: የአመራር ጥበብና ይህ እሳቤያቸውን የሚከተሉና ሥራ ላይ የሚተገብሩ ተቋማት፣ ሃገራትና አመራሮችም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም::

በእርግጥም ቢሮክራሲ በተቋማት ብቻ ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ አሉታዊ ወይንም አዎንታዊ ሊሆን ይችላል። ይህም ተፅዕኖ ሊወሰን የሚችለው በቢሮክራቲክ አሠራር መኖር አለመኖር ሳይሆን ቢሮክራሲው በተዋቀረበትና በሚተገበርበት ሂደት ላይ ነው። ይህም ማለት የቢሮክራሲ አሠራር በብቃት፣ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የቢሮክራሲው አወቃቀር ሥራዎችን ሊያቀሉ የሚችሉ ዘመናዊ ስልቶችንና ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም ከሆነ የሰው ኃይልንና የቁሳቁስ ብክነትን በመቀነስ በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያስመለክት ይችላል።

ቢሮክራሲ በጣም የተንዛዛና ኋላቀር ከሆነ የሀገርን ኢኮኖሚ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። በሌላ መልኩ ደግሞ የቢሮክራሲ አተገባበር ከአድልዎ፤ ከስርቆትና ከሙስና ፅዱ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ የሀገርን ሀብት በቢሮክራሲ ስም የመበዝበዝ ሁኔታ ስለሚፈጠር በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

በተስተካከለ ቢሮክራሲ እጦት፣ በሙስና፣ በጣም በተጓተተ የሥራ ሂደትና ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት ምክንያት የሃገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ይጎተታል:: በተቋማት ውስጥ ቢሮክራሲያዊ ብልሽቶች ሲፈጠሩ ሙስናን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች ይፈፀማሉ:: ሕዝብ በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ እንዲሸረሸር ከፍ ሲልም እንዲሟጠጥ ያደርጋል።

ዘርፉ ምሑራን እንደሚያስረዱን ከሆነም፣ የአንድ ሃገር የቢሮክራሲ አወቃቀር የሀገሪቱን ጥንካሬና ሁለንተናዊ እድገት ፍንትው አድርጎ ያሳያል:: ጠንካራ ሀገረ መንግሥታትም ምንጊዜም ቢሮክራሲያቸውን የሚያዋቅሩትና የሚገነቡት ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርገው ነው::

ለአብነትም የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ፈለግ አብነት ተደርጋ የምትጠቀሰው ጃፓን፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስመዝገብ የቻለችው ጠንካራ ቢሮክራሲ በመገንባቷ መሆኑ ይታመናል::

በኢትዮጵያ ቢሮክራሲው ብዙ ጊዜ በቀርፋፋነት ወይም ቀልጣፋ ባለመሆንና በውጤታማነት ማነስ ትችት የሚሰነዘርበት ነው:: በሀገሪቱ ቢሮክራሲ ያልተፈታ ሸምቀቆ ነው:: ቢሮክራሲው ያልተስተካከለና በተለይ ቀርፋፋ በመሆኑ ለፈጣንና ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ራሱን አላዘጋጀም:: የአቅምና የግንዛቤ ችግር ስላለበት ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት ያመነታል:: ‹‹እሺ›› ከማለት ይልቅ ‹‹እንቢ›› ማለት ይቀናዋል:: ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚራመዱ ብልህ ቢሮክራቶች ስለመኖራቸው ባይካድም አብዛኞቹ ግን የአቅም ግንባታ ከፍ ሲልም ተግሳፅና ማስጠንቀቂያ የሚያስፈልጋቸው ናቸው::

በእርግጥ የለውጡ መንግሥት ቢሮክራሲውን “ለማዘመን” ባደረገው ጥረት ብዙ ለውጦች ተደርገዋል:: ውጤት የታየባቸውም በርካቶች ናቸው:: ይሁንና ለውጡ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ የሚፈልገውን ቀልጣፋ፣ በባለሙያ የተሞላ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓትን በማስፈን ረገድ ብዙ እንደሚቀር ለክርክር የሚያስቀምጥ አጀንዳ አይደለም:: በሀገሪቱ ከውስን ተቋማት በስተቀር አብዛኞቹ አገልግሎት አሰጣጣቸው የተጓተተና የሚያማርር እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው::

በተለይ አንዳንድ አመራሮች ቢሮክራሲያዊ አሠራርን በማንሻፈፍ ዜጎችና ባለጉዳዮች እንዲማረሩ በማድረጉ በኩል የተካኑ ስለመሆናቸው ሲገለፅ መስማት የተለመደ ነው:: በአንዳንድ ቦታዎች በስንት ማግባባት የመጣን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር እንደማይፈለግ እንግዳ የማየት አሳዛኝ ድርጊት ይፈጸማል::

ማክስ ዌበርን ጨምሮ ሌሎችም ምሑራን፣ የቢሮክራሲ ፅንሰ-ሀሳብ ተዋረዳዊ መዋቅርን፣ በግልጽ የተለዩ ሚናዎችንና ኃላፊነቶችን፣ መደበኛ ሕጎችንና ሂደቶችን እንዲሁም ግላዊ ያልሆኑ ግንኙነቶችንና መስተጋብሮችን እንደሚያካትት በግልፅ አመላክተዋል:: ይሁንና በሀገራችን ይህን ፅንሰ ሃሳብ በተግባር መሬት ላይ የሚተገብሩ ተቋማት ቁጥር ‹‹ጥቂት›› በሚል ብቻ የሚገለፅ አይደለም::

በአንዳንድ ተቋማት የሚገኙ አመራሮች በተለይም በግልጽ የተለዩ ሚናና ኃላፊነቶቻቸውን እንዲሁም መደበኛ ሕጎችንና ሂደቶችን በአግባቡ መወጣት ሲሳናቸው እንዲሁም በሌሎች የሥራ ሂደቶች መከናወን ያለባቸውን ተግባራት ጭምር ‹‹ካልጠቀለልኩ ሞቼ እገኛለሁ›› በሚል እጃቸውን ሲያስገቡ ካልሆነም ለማስገባት ሲታትሩ እንደሚውሉ ይነገራል::

መሰል አመራሮች ሚናና ኃላፊነቶቻቸው በማይፈቅድላቸው ሁኔታ ውስጥ ታች ወርደው ሲደክሙ የሚውሉት በአብዛኛው ለተቀመጡበት ወንበር በሚመጥን መልኩ ሃገርና ተቋምን ለመቀየር ለሚያግዝ የለውጥ ሃሳብና ተግባር ማዋጣት ሲከብዳቸው ነው:: ይህ ካልሆነም የግል ፍላጎትን ታሳቢ አድርገው የሚወዱትን ለመጥቀም፣ የሚጠሉትን ለማጥቃት ነው:: መታወቅ ያለበት ሐቅ ግን መሰል የሙጥኞች፣ የቢሮክራሲን ሸምቀቆ በማጥበቅ ለሥራ ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ያላቸው ፋይዳ ከዜሮ ጋር የሚደመር መሆኑን ነው::

ቢሮክራሲ ለእድገትን ለውድቀትም እጅግ ወሳኝ ሚና ያለው እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ምድር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሲታሰብ መሰል ድክመቶችን ማረምና ቢሮክራሲውን በአግባቡ መምራት ማስኬድና መግዛት ትኩረት ከሚሠጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ማድረግ አማራጭ ሳይሆን የግድ ነው:: ያልተፈታው የቢሮክራሲ ሸምቀቆ መፍታት የሁሉም ቁልፍ መሆኑን ጠንቅቄ መረዳትና ለመፍትሔው መሥራትም የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባር ሊሆን ይገባል::

Bureaucratic red tape ተብሎ የሚወገዘው ቅጥ ያጣ መጓተት የሚወገደው በጥሩ አመራር ነው:: ለዚህ ደግሞ ብቃቱ ያላቸው አመራሮችን ማፍራት የግድ ነው:: ይህን በማድረግም ሥራን ማፋጠን እንዲሁም የባለጉዳዮችን የጊዜ ብክነትን መቀነስም ይኖርብናል::

የቢሮክራሲን ሸምቀቆ ለማላላት ከተቻለም ለመፍታት መንግሥትም ሆነ ፖሊሲዎችን ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ውስጣዊ አሠራራቸውን በመፈተሽ ዘመናዊና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተወዳዳሪነት ለመራመድ የሚችል የቢሮክራሲ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርባቸዋል።

የሃገር ገጽታን ከሚያጨለሙ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ጉዳይ ካልታሰበበት አሳሳቢ ነው:: ልፋቶችን በሙሉ በዜሮ ያባዛል:: ይህን ችግር ለስር መሠረቱ ለማስተካከል መንግሥት ቢሮክራሲውን ትራንስፎርም ማድረግ ይኖርበታል:: በተለይ ሕዝብን የሚያስለቅሱ፣ የሚበድሉ፣ የሚመዘብሩ፣ ፍትሕን የሚረግጡ፣ ሲያሻቸውም በመንግሥት መመሪያ ስም እያጭበረበሩ ሲላቸውም የጠሉትን ለመበቀል የወደዱትን ለመጥቀም የሚራወጡ ቢሮክራቶችን አድኖ ከወንበራቸው ማስነሳት አለበት::

አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የአሠራር ሥርዓታቸውን ቀልጣፋ፣ ግልጸኝነት የተሞላበት ማድረግ እንዲሁም ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር በፀዳ መልኩ መተግበር ይኖርባቸዋል። ዘመናዊ ቢሮክራሲ ባሕልና ባለሙያዊነትን ማዳበርም አስፈላጊ ነው:: በሀገሪቱ ከሚገኙ ቢሮክራሲን በአግባቡ ማስኬድ ከቻሉ ተቋማት ልምድ መቀመርም ለውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው:: ከሁሉ በላይ ያልተፈታው የቢሮክራሲ ሸምቀቆ መፍታት የሁለንተናዊ የብልፅግና ቁልፍ መሆኑን ጠንቅቄ መረዳትና ለመትፍሔው መሥራት የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባር መሆን አለበት::

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You