
ስፖርት ለጉዳት መንስኤ ነው ባይባልም፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ግን ለጉዳት አጋላጭ መሆናቸው ይታወቃል። በዓለም ላይ ከሚዘወተሩ በርካታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካከልም እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ እና ቤዝቦል በጉዳት አጋላጭነታቸው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ኢትዮጵያ ስሟን ያስጠራችበትና ከቀዳሚዎቹ ተወዳጅ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው አትሌቲክስ ከጉዳት ጋር ያለው ቁርኝት ምን ይመስላል?
በዛሬው ዕትምም በአትሌቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ምክንያት፣ ህክምናው እንዲሁም በዚህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ያለው ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለውን ይዳስሳል። በዚህ አርዕስት ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡንም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትሌቲክስ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ እንዲሁም በጸረ- አበረታች ቅመሞች ጉዳይ ተጠሪዋ ቅድስት ታደሰ ናቸው።
ጉዳት በአትሌቲክስ ስፖርት
አትሌቲክስ ሰፊና በውስጡም በርካታ የውድድር ዓይነቶችን ያቀፈ ስፖርት እንደመሆኑ፤ የተለያዩ ጉዳቶች ይስተናገዳሉ። ከአጭር ርቀት ሩጫ እስከ ሜዳ ተግባራት ባሉት ስፖርቶች አትሌቶች በብዛት ከጡንቻ፣ ከህብለ ሰረሰር፣ ከጅማት፣ ከደም ቧንቧ፣ ከአጥንት … ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን ያስተናግዳሉ። ኢትዮጵያ በተለይ የምትታወቀው በሩጫ ስፖርቶች እንደመሆኑ በእግር ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች የሚያመዝኑ ሲሆን፤ ዓይነቱም ከቀላልና መካከለኛ ከፍተኛ ህክምና እስከሚያ ስፈልጋቸው ጉዳቶች ይዘልቃሉ። አንዳንድ የጉዳት ዓይነቶች እረፍት በማድረግና በቀላል ህክምና ሲድኑ፤ ስር የሰደደ ጉዳት ደግሞ ረጅም ጊዜ ሊወስድና እስከ ቀዶ ጥገና ሊደርስም ይችላል።
የጉዳት መንስኤዎች
የጉዳት መንስኤዎች እንደ ጉዳት ዓይነቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም፤ ከልምምድ ጋር በተያያዘ በደንብ ባለማሳሰብ፣ በቂ ውሃ ባለመውሰድ፣ በውድድር ላይ፣ በቂ እረፍት ባለማድረግ፣ እንደ ስፖርት ዓይነቱ ከሚጠቀሟቸው ቁሳቁሶች ጋር በተገናኘ፣ ከስነ-ምግብ አለመመጣጠን አሊያም አትሌቶቹ በዓመቱ መጀመሪያ ቅድመ ጤና ምርመራ ካለማድረግ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነችበት የረጅም ርቀት ሩጫ እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚታየው ጉዳት ከጫና ጋር በተያያዘ የሚደርስ ነው። በልምምድና ውድድር ጫና ምክንያትም አትሌቶች በተለይ ስብራትን ለመሰለ ጉዳት ተጋላጭ ይሆናሉ። በመካከለኛ እና አጭር ርቀት ሩጫዎች በአመዛኙ የሚስተዋለው ደግሞ ጡንቻ ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ነው።
ከጉዳት ለማገገም
በእርግጥ ከጉዳት በኃላ የሚኖረው የማገገሚያ ጊዜ እንደ አትሌቱ ጉዳት የሚወሰን እንደሚሆን ባለሙያዋ ያስረዳሉ። አትሌቱ የደረሰበት ጉዳት በህክምና ባለሙያዎች ከታየ በኃላ ከመንስኤው በመነሳት የማገገሚያ ጊዜው እንዲሁም የማገገሚያ ዓይነቱ ሊለያይ ይችላል። ከጉዳቱ ክብደት ባለፈም በሴት እና በወንድ አትሌቶች ላይ የሚደርሰው የጉዳት ዓይነት ልዩነት ሊኖረው ስለሚችልም ህክምናውም ሆነ የማገገሚያ ጊዜው ላይ ልዩነት ይኖራል።
ህክምናው በኢትዮጵያ
እንደሚታወቀው ስፖርት በኢትዮጵያ ከሳይንሳዊው መንገድ ይልቅ ወደ ተለምዶአዊ አሰለጣጠን ያደላል። አትሌቲክስ በዚህ ቅድሚያ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ባህላዊ ሊባል በሚችል መልኩ አትሌቶች አሰልጥነው እስከ ብሔራዊ ቡድን መድረሳቸውም እሙን ነው። በዚህ መልክ መሰልጠናቸው ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው ሊባል ባይችልም ግን በሳይንሳዊ መንገድ ማሰልጠን ቢቻል የውጤታማነት መንገዱ ሊቀል እንዲሁም ሊደርሱ ከሚችሉ ጉዳቶችና ያለ ዕድሜ ከስፖርቱ የመራቅ ችግር ሊቀረፍ ይችላል።
ጉዳትም በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ በተለይ በዚህ ወቅት ማሳጅ ቤቶችና ወጌሻዎች በየአካባቢው ተበራክተዋል። በብዛት እንደሚታየው ከሆነም አትሌቶች ጉዳት ሲያስተናግዱ ወደዚሁ መሄድን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነም፤ አትሌቱ በልምምድ ወቅት ከሚሰራቸው እንቅስቃሴዎች በተጓዳኝ ፊዚዮቴራፒ እና ማሳጅቴራፒ በጉዳት ላይ የራሱ ድርሻ አለው። ከዚህም ባሻገር የስፖርት ህክምና ከስነ-ምግብ እና ስነ-ልቦና ጋርም ተመጋጋቢ ነው።
አንዱን ከአንዱ መነጠል ከባድ ቢሆንም፤ አሁን ባለው አሰራር ግን እንደ ሃገር በርካታ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ። ከማሳጅና ወጌሻ ጋር በተያያዘ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካቶና የህክምና ባለሙያዎች ገብተውበት ከመስራት አኳያ በርካታ ክፍተቶች አሉ። ችግሩ በተለይ የሚስተዋለው ደግሞ በክለቦች እና በስልጠኛ ማዕከላት ላይ ነው። ለዚህ ምክንያት የሆነው የግንዛቤ ችግር፤ በስፖርቱ ባለድርሻ አካላትም ትኩረት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዋ ያመለክታሉ።
ቴራፒ ራሱን የቻለ ትልቅ ሙያ ሲሆን፤ በሌላው ዓለም ትምህርቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እሰከ ሶስተኛ ዲግሪ የሚሰጥ ነው። እዚህ የሚስተዋለው ባህላዊውን የህክምና ዘዴ በአንዴ ማውጣት ባይቻልም፤ በምን መልኩ መስተካከል ይገባዋል የሚለውም ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዋ ያስረዳሉ። ግንዛቤውም ለአትሌቶችና ከአትሌቶች ጋር አብረው ለሚሰሩ አካላት መስጠት አስፈላጊ ይሆናል።
የሙያ ማሻሻያ
ፌዴሬሽኑ ከኃላፊነቶቹ መካከል ለባለ ሙያዎች ስልጠና እና ድጋፍ መስጠት አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። በስፖርት ህክምና ላይ እንደ ሃገር ያለው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ ባይባልም፤ የሙያ ማሻሻያ ከሚሰጥባቸው ዘርፎች መካከልም አንዱ የስፖርት ህክምና ነው። ከሳምንታት በፊትም በስፖርት ፊዚዮቴራፒና ተጓዳኝ ርዕሶች ላይ ለሶስት ቀናት በባህር ዳር ከተማ ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
ስልጠናው 69 ባለሙያዎችን በመያዝ በሁለት ተከፍሎ የተሰጠ ሲሆን፤ የአትሌቲክስ አሰልጣኞች እንዲሁም በክለቦችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚገኙ የማሳጅና ፊዚዮ ቴራፒ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ ለጡንቻ እና በነርቭ ጉዳት ተጋላጭ የሆኑ አትሌቶችና ሰልጣኞች በባለሙያዎቹ ህክምና አግኝተዋል።
ስልጠናውን የሰጠው በስፔን የሚገኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለሙያዎች ቡድን በዓመታዊው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር ላይ የመገኘት ልምድ እንዳለው ባለሙያዋ ይጠቁማሉ። ስልጠናውን የሰጡት 33 ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ 27 የሚሆኑ በተለያዩ ክሊኒኮች የሚሰሩ ፊዚዮ ቴራፒስቶች እንዲሁም ስድስት የዘርፉ መምህራን ናቸው። የዚህን ዓመት ልዩ የሚያደርገውም ከስልጠናው ባሻገር ከፌዴሬሽኑ እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በአጭር እና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎች ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች
በሃገሪቷ ዘርፉ ያለው እንቅስቃሴ የጎላ አለመሆኑ ዋናው ክፍተት ሲሆን፤ ትምህርቱንም በተሻለ መልኩ በውጪ ሃገራት ነው ማግኘት የሚቻለው። በመሆኑም ልምድ ካላቸው የታወቁ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ትምህርቱ (ስልጠናው) ላይ መስራትና ራሱን የቻለ መስመር ቢዘረጋለት መልካም እንደሚሆን ባለሙያዋ ያመላክታሉ። ያሉትን ጅምሮችም አጠናክሮ በመቀጠል ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንዲቻል ባለድርሻ አካላት አጽንኦት መስጠት ተገቢ ነው።
ለቀጣይ
እንደሚታወቀው አትሌቲክስ ኢትዮጵያ የምትጠራበት ትልቁ ስፖርት ነው። በመሆኑም ሁሉም አካል ለስፖርት ህክምና አትኩሮት ኖሯቸው፤ ክለቦችና የማሰልጠኛ ማዕከላት በቂና በስርዓት የሰለጠኑ የስፖርት ህክምና ባለሙያዎች ቢኖሯቸው አትሌቶችን ከጉዳት ለመታደግ እንዲሁም የተሻለ ህክምና ለማግኘት ይቻላል። ይህንንም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ብርሃን ፈይሳ