ተቋማዊ የጤና እንክብካቤ በ‹‹ተማሪ ኬር››

በኢትዮጵያ የሕክምና ተቋማት ቁጥር አሁን ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀሩ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም:: የሕክምና ባለሙያዎችም አሃዝ ቢሆን ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ፈፅሞ የሚጣጣም አይደለም:: ምንም እንኳን በአንድ የጤና ሥርዓት ውስጥ በሽታን መከላከል፣ ጤናን ማስተዋወቅ፣ ሕክምና፣ ሪሃቢሊቴሽንና ፓሊዬቲቭ ኬር /የሥነ ልቦና ሕክምና/ ወሳኝ መሆናቸው ቢነገርም በኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱ በአብዛኛው የሚያተኩረው ምርመራና ሕክምና ላይ ብቻ ነው:: ይህም ሕክምናው የተሟላ እንዳይሆን ያደርገዋል::

በዚህ ረገድ ክፍተት በመኖሩ ነው በሽታ መከላከል፣ ግንዛቤ ማስጨበጥና የጤና ትውውቅ ሥራዎች ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ መሥራት ወሳኝ መሆኑ በበርካታ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች የሚነገረው:: በተለይም የቅድመ ጤና ምርመራ በማድረግ ከከፋ የጤና ጉዳትና የሕክምና ወጪ መዳን እንደሚቻል ነው ብዙ ጊዜ በጤና ባለሙያዎች የሚመከረው::

በዚህ መነሻነትም ነው ባሳለፍነው ሳምንት የ2016 ዓ.ም የጤናው ዘርፍ የክረምት በጎ አድራጎት ትግበራ ”በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል ከፍለው መታከም ለማይችሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና አገልግሎት የተጀመረው:: በቅድመ ጤና ምርመራ ላይ በመሥራትና በተለይ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ወደተቋም እንዲወርድ በማድረግ በአይ ጤና ሄልዝ ኬር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ስር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ‹‹ተማሪ ኬር›› ፕሮጀክት ደግሞ የዚሁ ተግባር አንዱ ማሳያ ነው::

የተማሪ ኬር ፕሮጀክት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኪሩቤል ጫንያለው እንደሚናገሩት፣ እ.ኤ.አ በ2020 በዋናው እህት ኩባንያ አይ ጤና ሄልዝ ኬር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አማካኝነት ፕሮጀክቱ በሥራ ፈጠራ ውድድር ቀርቦ በጤና ተቋማት ላይ የሚሰጥ የጤና አሠራር ወይም ተቋማትን መሠረት ያደረገ የጤና እንክብካቤ በሚል አሸናፊ ሆኖ ነበር:: የሥራ ፈጠራ ውድድሩ ጭብጥ ሰው ወደ ሆስፒታል ከሚሄድ ሆስፒታል ለምን ወደ ህብረተሰቡ አይሄድም የሚል ነበር:: የፈጠራ ሃሳቡ አመንጪዎችን ጨምሮ በሕክምናው ዘርፍ የተመረቁ ባለሞያዎች ሥራ አጥነት መጨመር ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን መፍትሔ ለማምጣት በእጅጉ ገፋፍቷል::

ዩኒሴፍ ባወጣው መረጃ መሠረት የአሁኑ የኢትዮጵያ አማካይ እድሜ 18 ነጥብ 8 እንደሆነ ያሳያል:: ይህም ወጣት ትውልድ በብዛት ያለባት ሀገር መሆኗን ይጠቁማል:: ከ15 ዓመት እድሜ በታች ያሉት ደግሞ 48 ከመቶ ያህሉን የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሚይዙ ይኸው መረጃ ይጠቁማል:: 30 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝብ ደግሞ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይገመታል:: ይህም በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል:: በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሰው ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባትም ነው የተቋማዊ የጤና እንክብካቤ ለማድረግ ተማሪ ኬር ተብሎ ሃሳቡ ሊፈጠር የቻለው::

በኢትዮጵያ በጤና ሥርዓት ውስጥ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉት አምስት ምሰሶዎች ማለትም በሽታን መከላከል፣ ጤናን ማስተዋወቅ፣ ሕክምና፣ ሪሃቢሊቴሽንና ፓሊዬቲቭ ኬር በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እየተደረጉ አይደሉም:: በብዛት ተግባራዊ ሲደረግ የሚታይው ምርመራውና ሕክምናው ብቻ ነው:: ነገር ግን የፈጠራ ሃሳቡ አመንጪዎች በተቀሩት ምሶሶዎች ላይ ኢላማ አድርገው የመሥራት ሃሳብ ነው ያመጡት:: ከዚህ በመነሳት ፕሮጀክቱ በተማሪዎች ላይ መከላከልን፣ የጤና ትውውቅን የያዘ ስልጠና ከሕክምናውና ሪፈር ሥርዓቱ ጋር አጣምሮ አገልግሎት ይሰጥበታል:: የተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ማለትም ከ18 እስከ 60 የእድሜ ክልል ውስጥ ላለው ደግሞ ሌላ ፕሮጀክት እየተዘጋጀ ነው::

ሥራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት፣ ፕሮጀክቱን ለመጀመር በዋናነት ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት ቁጥር ተመጣጣኝ አለመሆንና ፈላጊው ታካሚና ተፈላጊው የሕክምና ባለሙያ አለመገናኘት ነው:: ታካሚውንና የሕክምና ባለሙያውን የሚያገናኝ ሁኔታ ባለመኖሩ ከዚህ ክፍተት በመነሳት ተማሪ ኬር የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ የሆነው:: የተለመደው አሠራር ሆስፒታል ገንብቶ ህብረተሰቡን ማከም ነው::

ነገር ግን መንግሥት ሁልጊዜ ሆስፒታል እየገነባ ህብረተሰቡን ያክም ቢባል ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው:: ለሆስፒታሎች ግንባታም የሚወስደው ጊዜ ቀላል የሚባል አይደለም:: ስለዚህ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ መፍትሔ ያስፈልጋል ማለት ነው:: በዚህ ፕሮጀክትም በጤናው ሥርዓት ክፍተቱን በማየት ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት ነው እየተሰራ ያለው::

ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የተማሪው ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብና ተማሪው ላይ በማተኮር ፕሮጀክቱ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል:: የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማም በቀጣዩ ትውልድ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ፣ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠርና የጤናውን ሥርዓት ለማዘመን ነው:: በጤናው ዘርፍ ሕክምና መስጠት አንዱ ሥራ ሆኖ ሳለ መከላከል፣ የጤና ትውውቅ፣ ግንዛቤ ደግሞ ሌላኛው አስፈላጊ ሥራ ነው:: ይህ ነው በተማሪ ኬር ፕሮጀክት አማካኝነት እየተከናወነ ያለው ሥራ::

ለምሳሌ በጊዜው በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ ከፍ ብሎ ነበር:: ነገር ግን በመከላከል ዙሪያ ግንዛቤ እየተሰጠ በመምጣቱና የጤና ማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ ወረርሽኙ ቀንሶ ታይቷል:: በተመሳሳይ ግንዛቤውና የጤና ማስተዋወቅ ሥራው ሲቀንስ ወረርሽኙ ዳግም አንሰራርቷል:: ይህም መከላከልና ጤና ማስተዋወቅ ትልቅ ቦታ እንዳለው ያሳያል::

ከዚህ በመነሳት የጤና ፌስቲቫሎችን በትምህርት ቤቶች በማዘጋጀት ከተማሪዎች ጀምሮ መላው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ እንዲገኙ ተደርጎ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ይቀርባሉ:: በመከላከል ሥራው ሁሉም ወላጅ ቤተሰቡን፣ ልጆቹን፣ ዘመዶቹን ይዞ መጥቶ የአንድ ወይም የሁለት ሰው ካርድ በሚከፈልበት ዋጋ ከዓይን፣ ጥርስ፣ ሥነ ልቦና፣ ሥነ ምግብ፣ ቆዳ፣ ሕፃናት፣ የውስጥ ደዌ ሐኪሞች ጋር ተገናኝተው ምርመራ፣ ምክርና ሕክምና አገልግሎት አግኝተው ይሄዳሉ:: ይህም የቅድመ ምርመራ ባሕልን ከማሳደግ አኳያ በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል::

በጤና ማስተዋወቅ ሥራ በፌስቲቫሉ ቀን ወላጆች የሚመርጧቸውና አስፈላጊ ናቸው ብለው ያመኑባቸውን የጤና ጉዳቶችን ያነሳሉ:: የፓናል ውይይቶች ተዘጋጅተው ወላጆች ከአመጋገብ ጋር፣ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋርና ከሌሎች የጤና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አንስተው ወይይት ተደርጎ ለጥያቄያዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል:: በባለሙያዎች ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታም ይመቻቻል::

ሌላው በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሰራው ሥራ ሲሆን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ረጅም ሰዓት ስለሚያሳልፉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴያቸው እየቀነሰ በመምጣቱ በተማሪ ኬር ፕሮጀክት ልጆች የሚሳተፉበት የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ ውድድሮች ይደረጋሉ:: በጤና ስፖርትና ዌልነስ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ከትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤቶች ማህበረሰብ ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲፈጠሩ በማድረግ ጤናን የመጠበቅ ሥራዎች ይሰራሉ::

ዋናው ጉዳይ ግንዛቤ መፍጠር በመሆኑ ተማሪዎች ከአመጋገብና ከሌላም የጤና ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ለወላጆቻቸው የጤና ኤግዚቢሽን እንዲያዘጋጁ ይደረጋል:: እድሜያቸው ከፍ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ የልብ፣ የሳምባ ሞዴሎችን ሰርተው በማቅረብ በነዚህ በሽታዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሰራሉ::

ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፣ በዚህ ፕሮጀክት ከነርስ ጀምሮ እስከ ስፔሽሊስት ሐኪሞች ድረስ ሙሉ የሕክምና ቡድን በመያዝና አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና መሳሪያዎችን በማሟላት በየትምህርት ቤቶች በመሄድ የምርመራ ብቻ ሳይሆን የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል:: በትምህርት ቤቶቹ ክሊኒክ ተከፍቶም ነው ምርመራና ሕክምናው የሚደረገው:: ሕክምናው ላብራቶሪ የሚፈልግ ከሆነ እዛው በትምህርት ቤቱ ውስጥ ይዘጋጃል:: ይህም በወላጅና በተማሪዎች በኩል ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል::

በዚሁ የፕሮጀክት እንቅስቃሴ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 8 ሺ የሚጠጉ ወላጆችና ተማሪዎችን በምርመራ መለየት ተችሏል:: ከነዚህ ውስጥ የዓይን ችግር የነበረባቸው ልጆች 10 ከመቶ ነበሩ:: ይህም ልጆቹ አስቀድመው ባይታዩና ባይመረመሩ ኖሮ ችግሩ የከፋ ሊሆንባቸው ይችል ነበር:: ወደ 83 ከመቶ ያህሉ ተማሪዎች ደግሞ የጥርስ ችግር ነበረባቸው:: 10 ከመቶ ያህሉ ከክብደታቸው በታች፣ 17 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ከክብደታቸው በላይ ሆነው የአመጋገብ ችግር ነበረባቸው:: በልየታው ወቅት ስኳርና የደም ግፊት የተገኘባቸው ወላጆችም ነበሩ:: ቀዶ ሕክምና የሚጠይቅ የዓይን ችግር የተገኘባቸውም አሉ::

ስለዚህ በዚህ የተማሪ ኬር ፕሮጀክት አማካኝነት 800 ብር ባለሞላ ዋጋ ተማሪ፣ የተማሪው ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ሙሉ ምርመራና ሕክምና ማግኘት ይችላል:: ስለጤናቸው መጠየቅ ያለባቸውን ጠይቀውና አውቀው ብሎም ተመካክረው የሚወጡበት ቤተሰባዊ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት ነው:: ይህ ደግሞ የቅድመ ጤና ምርመራ ባሕልን ያዳብራል:: የጤና አገልግሎት ተደራሽን ሁሉም እንደአቅሙ የሚያገኘው ማድረግ ይቻላል::

ፕሮጀክቱ በአብዛኛው ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው በአብዛኛው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ቢሆንም በግል ትምህርት ቤቶች ላይም እየተሰራበት ሲሆን ሥራውም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እውቅና አግኝቷል:: የአገልግሎት ክፍያ ዋጋውን ዝቅ በማድረግ የጤና አገልግሎት ተደራሽነቱ ላይ እየተሰራ የሚገኘው:: በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በምግባ ሥርዓት ውስጥ ላሉ ተማሪዎች ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው::

ለግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን የሚያገኙ ስለሆነ ፌስቲቫል በማዘጋጀት ነው እንዲከፍሉ የሚደረገው:: ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚመጡ ተማሪዎች ከ700 እስከ 800 ባለው መካከል እንዲከፍሉ ይደረጋል:: በዚህ የገንዘብ መጠን ወላጆችም ሆነ ተማሪዎች የጤና ምርመራና ሕክምና አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ አብዛኛዎቹ ደስተኛ ናቸው:: ይህንኑ አገልግሎት የሚሰጡ በፕሮጀክቱ ያሉ አጠቃላይ ሐኪሞች ቁጥር ደግሞ አስራ ሰባት ደርሷል::

እንዲህ ዓይነቱ የጤና አገልግሎት ተማሪዎች ህመም ሲሰማቸው ብቻ ሳይሆን ሳይታመሙም ጤናቸውን መንከባከብ የሚችሉበትን ባሕል እንዲያዳብሩ የሚያስችል ነው:: በየዓመቱ ጤናቸውን እንዲከታተሉ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የደምና የኩላሊት ምርመራ እንዲያደርጉ ትምህርት የሚሰጥ ነው:: የቅድመ ጤና ምርመራ ባሕልን ማሳደግ የሚቻል ከሆነ በተለይ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በየዓመቱ የሚወጣውን ሀገራዊ ወጪ መቀነስ ይቻላል:: በዛ ልክ ግንዛቤውን ማስፋት የሚቻል ከሆነ ደግሞ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል የሚሄደውን የህብረተሰብ ቁጥር መቀነስ ይቻላል:: ይህም በመንግሥት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ያግዛል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You