የትውልድ ስፍራቸው ደሴ ከተማ መሃል ፒያሳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ ገና ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ የተለያዩ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት በመውሰድ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮም ተሰሚነት ያላቸው በመሆናቸው በብዙ ቦታዎች ላይ ግንባር ቀደም ሆነው የሚገኙ ናቸው – የዛሬው እንግዳችን ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፡፡
እንግዳችን፣ ከወጣትነታቸውም ጀምሮ ችግር ባለበት ጊዜ ሁሉ በመገኘት ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል፡፡ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሚኖሩ የመብት ጥያቄዎች በመሳተፍ ረገድ ፊተኛው መስመር ላይ የሚገኙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለዓላማቸውና ለነጻነት እስከመታሰር ድረስ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
በተለያዩ ኢስላማዊ ድርጅቶች ውስጥ በመስራችነትና በቦርድ አባልነትም ይታወቃሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ መልካም እንቅስቃሴያቸውና በሕይወታቸው ሕልም እንዲኖራቸው ያደረጓቸው አባታቸው ሲሆኑ፤ በሚያከናውኑት የተለያዩ ተግባራት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የዛሬው እንግዳችን፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከእውነተኛነትና ከታማኝነት ፈቀቅ ብለው አያውቁም፡፡ በሀገራቸው ላይ ያላቸው አቋምም ቀጥተኛና ግልጽ በመሆኑ አዲስ ዘመን በኢትዮጵያ ጉዳይ የዛሬው እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው በርካታ ታሪኮች አሏት፤ ከዚህ ውስጥ ዓድዋ ተጠቃሽ ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ አንገቷን የሚያስደፏት እንደርዳታ መጠበቅና ልመና አይነት ታሪክ አላት::እነዚህን ሁለት ጉዳዮች እንዴት ያይዋቸዋል ?
ኡስታዝ አቡበከር፡- እንደ ሀገር በተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ አልፈናል:: ዓድዋ የአንድነት፣ የከፍታና የድል ታሪካችን ነው:: ታሪክ በራሱ የከፍታም የዝቅታም ሊሆን ይችላል:: እንዲያ ሲባል ታሪክ በዘመናት ውስጥ የሚያልፉ ትውልዶች መገለጫ ነው ማለት ይቻላል:: ትውልድ በሚሰራው ሥራ ልክ ከፍታን እንደሚያገኝ ሁሉ ከዚያ ተቃራኒ በሆነው ዝቅታ ውስጥም ይኖራሉ::
ዓድዋ የድል እና የከፍታ ታሪክ ነው:: እንደማኅበረሰብ ደግሞ የጥንካሬና ብዙ ነገር ያለን መሆኑ ማሳያ ታሪካችን ነው:: ትናንት ለነገአችን የተሻለ እንዲሆን ትልቅ ማሳያ እና መስታወትም ነው:: እኛ ደግሞ የበለጠ አሳምረነው ልናስቀጥልና እኛነታችንን ልንገልጽበት የምንችልበት ነው ብዬ አምናለሁ::
እኔ እንደ አንድ ሙስሊም መምህር የእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ኢትዮጵያ ትልቅ ድርሻ አላቸው ከሚባሉ ሀገራት ውስጥ ናት:: እስልምና በፈተናዎች ውስጥ በወደቀ ጊዜ ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ቅርብ የሚባሉ ቤተሰቦቻቸውንና ወሳኝ የሚባሉ ባልደረቦቻቸውን ወደኢትዮጵያ ምድር ልከዋል:: በዘመኑ ኃያል ከነበሩ ሀገራት መካከል መርጠው ኢትዮጵያ ላይ ባልደረቦቻቸውን ሲልኩ ኢትዮጵያን የመምረጣቸው ምክንያት አንዱ ጠንካራ የፋይናንስ ሥርዓትና ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም የነበራት ሀገር በመሆኗ ጭምር ነው::
ነብዩ መሐመድና ባልደረቦቻቸውን ከዚህ ሀገር ለመውሰድ እጅ መንሻ ይዘው የመጡት እስልምናን የሚቃወሙት የቁሬይሽ አባላት ነበሩ:: ለመጀመሪያ ጊዜ እጅ መንሻን ያልተቀበሉ፤ ጉቦን የተጠየፉ፤ ሰውን በእምነት ነጻነቱና በሃሳብ ነጻነቱ መከበር አለበት ብለው የሚያምኑ መሪ ያለበት ሀገር ነበረችና እንግዶችን ተቀብላ አስተናግዳለች::
ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋጋ ሀገር ናት:: በኢኮኖሚም ጠንካራ ናት:: ተመጽዋችም የሌላውን ፈላጊም አልነበረችም:: ይህ ደግሞ እንድትመረጥ ያደረጋት መገለጫዋ ነበር:: እሱ እንደ ታሪክና ማንነት ዛሬም ልንኖረውና ልንተገብረው የተገባው:: ይህ ታሪክ በዚህች ምድር ላይ የተተገበረው ከአንድ ሺ 400 ዓመት በፊት ነው:: ትናንት በዚህ መልኩ የከፍታ ታሪክ ያለን ሕዝቦች፤ ዛሬ በእኛ ዘመን፤ ምን ጉዳይ ላይ ነው ያለነው የሚለው ነገር የመጀመሪያው ሃሳቤ ነው::
ስለዚህ ይህ የትናንት የእኛነታችን መገለጫ ነው፡። ዛሬ ደግሞ የተሻለ ሆኖ መገኘት አሊያም ያንኑ መድገም አለብን:: መልካም ልጅ ማለት የአባቶቹን ስራ የሚደግም ከእነርሱ የተሻለ ሆኖ የሚገኝ ነው:: ከእዛ በታች ከሆነ ልጅነቱም አደጋ ላይ ነው ማለት ይቻላል:: በዚህ መልኩ ያንን ማምጣት የምንችለው በመሥራት እንጂ በማውራት እና በትናንት ታሪክ በመጣላት አይደለም:: እኛ ባልኖርንበትና የታሪክ አካል ባልሆንበት ጉዳይ ላይ እየተጨቃጨቅንና እየተገፋፋን መቀጠል አይኖርብንም:: እየሰራን፤ እየተለወጥን፤ ለሀገርና ለማኅበረሰብ ከፍታ መትጋት አለብን::
ኢትዮጵያን ስሟን ከፍ ማድረግ የሚቻለውና የሚመጥናት ቁመና ላይ እንድትሆን የሚያደርገው በተግባር መንቀሳቀስ ሲቻል ነው:: የሥራ ባህላችን ሊቃኝ የሚገባው ነው:: እንደ ሀገር ያለን እይታችንና ሀገርን ካለችበት ወደተሻለ ስፍራ ለማሸጋገር የምንሰራበት መስመር መስተካከል አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ከመናቅ የተነሳ ሥራ የለም የሚል አተያይ እንዳላቸው ይነገራል፤ እርስዎ ከዚህ አንጻር የትውልዱን የሥራ ባህል እንዴት ይገልጹታል? ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲኖረንስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ኡስታዝ አቡበከር፡- መጀመሪያ ከሥራ ባህላችንም በፊት እንደ አንድ ማኅበረሰብ መሥራት መቻል አለብን ብለን ማመን ይገባናል:: ምክንያቱም ለውጥ ማምጣት የምንችለው በጋራ መሥራት ስንችል ነው:: በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ በጣም ትኩረት አድርጎ ከሚጠቅሳቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ከተረጂነት አመለካከት የወጣና የሚሠራ ጠንካራ የሆነ ማንነት ያለውን ሲሆን፤ አስተምሮው፣ ሥራን ወዶ የሠራ ዋጋው ከፍተኛ እንደሆነና እንዲሁም ከፍታ እንደሚኖረው ይገልጸዋል:: ስለዚህም በዚህ መልክ ሥራን ያበረታታል:: ሰዎችን ለሥራ ይገፋል::
በየትኛውም የእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ማስተዋል ከተቻለ በምድር ላይ የተላኩ ነብያት ወደ ምድር የሚመጡት የፈጣሪን መመሪያና ኃላፊነት ይዘው ሕዝብን ከፈጣሪ ጋር ለማገናኘት ሲሆን፤ የሚመጡትም በአንድ የሙያ ዘርፍ ብቁ ሆነው ነው:: ለአብነት ያህል ነብያቱ፣ ወይ ነጋዴ ናቸው፤ አሊያም አናጺ፤ ወይም ደግሞ ብረት አቅላጭ ናቸው:: አንድ የሙያ አይነት ያልነበረው ነብይ ምድር ላይ አልተላከም ማለት ይቻላል:: በአንድ ነገር ላይ ስልጡን ያልሆነ ነብይ የለም ማለት ይቻላል:: አብዛኞቹ ነብያት እረኞች ነበሩ:: ሌሎች የሚታወቁበት ፕሮፌሽናል ሥራ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው:: እሱ ማለት የሚያሳየው ነገር በሕይወታቸው ውስጥ ውጣ ውረድን መልመድ፣ በተለያዩ ፈታኝ በሆኑ ነገሮች ውስጥ ማለፍ፣ በራስ መተማመን እንዲኖር ማድረግ፣ የሰውን እጅ ጠባቂ እንዳይኖር ማድረግና በራስ ሰርቶ የማደር ስሜት እንዲፈጠርባቸው ማድረግ ነው::
እንደ አማኝ ማኅበረሰብ የመጀመሪያው ነገር መሥራት አለብን የሚለውን ነገር ማመን ነው:: መሥራት አለብን ብለን ካመንን ብዙ ነገር መለወጥ ይቻላል:: ዛሬ ኢትዮጵያ ለማደግ እየተፍጨረጨረች ነው::ስለዚህም ዜጎቿ አብረው ለሥራ መፍጨርጨር አለባቸው::ምክንያቱም ተከፍሏቸው የሚኖሩ እንደስካንዲቪያ ሀገራት ያሉ ዜጎች እንኳ ቢሆን ሰው ሥራ ይሠራል:: ሥራ የሚሠራ ትውልድ ደግሞ የነቃ፣ ተጠያቂነት ያለው፣ ከራሱ አልፎ ለሌላው መኖር የሚችል መሆን ነው:: ሥራ ስንሠራ እኛነታችንን ብቻ አስበን መሥራት የለብንም:: ነገን፣ ትውልድን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን አስበን መሆን አለበት::
ሁሉም ሰው የተለየ የሙያ ዘርፍ ይኖረዋል::በመረጠው ሙያ እንዲሠራ ታዝዟል፤ መሥራትም አለበት:: ምክንያቱም ያለሥራ የሚመጣ ውጤት የለም:: መሥራት አለብን ብለን ካመንን ደግሞ ሥራ እኛ ዘንድ ይጠፋል ብለን አናስብም:: ምክንያቱም በሀገራችን የተጀመሩ እንጂ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ባለበት ሀገር ውስጥ ሥራ የለም ማለት አይቻልም፤ ዛሬ ዛሬ ከሀገር ተሰድደው ሔደው ሥራ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ወደ ውጭ ሀገር ሔደው የሚሰሩት ሥራ ኢትዮጵያ እያሉ የናቁት ሥራን ነው:: ለውጡ ምንድን ከተባለ ምናልባት እዛ ክፍያው ከፍ ሊል ይችላል:: ነገር ግን ከታች ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችላል:: ያውም ሰው ሀገር ላይ ሳይዋረዱ፣ በማንነታቸው ሳይሸማቀቁና ሳይገፉ በሀገር ላይ ክብርን አግኝተው መኖር ይቻላል:: የብዙ ሰዎች ሕይወት በዚህ መልኩ እንዳለፈ እናውቃለን፡። የሠሩ ሰዎች ውጤት ያገኛሉ::
በሀገራችን የሥራ እድሎች አሉ፤ እንዲያውም ያልተሰራ የሥራ እድል ያለው እኛ ሀገር ነው:: ሌላው ዓለም ላይ ሥራው እያለቀ ነው ማለት ይቻላል:: ታላላቅ ናቸው የተባሉ ሀገራት ላይ ብዙ ነገር ላይ የደረሱ ናቸው፡። እኛ ሀገር ላይ ሁሉ ነገር ገና ጅምር ላይ ነው:: ያልተነካ ነው::
እኔ፣ የሃይማኖት መምህር ብሆንም ነጋዴ ነኝ:: ንግዴን እንዴት አድርጌ ላሳድገው? ላስፋው እላለሁ:: ምክንያቱም ዘርፉ ገና ነው፤ ፍላጎቱ ብዙ ነው:: ሀገር ገና እየተገነባ ነው ያለው:: ማኅብረሰብም ገና እያደገ ነው:: ስለዚህ ሥራ የመሥራት ፍላጎት ያለው ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላል:: ከመቀጠር ተነስቶ ትልቅ ቦታ ላይ መድረስ ይችላል:: ነገር ግን ይህ የሚሆነው እኔ የሰው እጅ ማየት የለብኝም፤ መሥራት አለብኝ ብሎ ሲያምን ነው::
ሁልጊዜ ከላይ ያለች እጅ ከታች ካለችው እጅ በላይ በላጭ ናት፤ የሚሰጥ እጅ ከላይ ሲሆን፣ የሚቀበል እጅ ከታች ናት:: ተቀባይነትን የሚጸየፍና የሚጠላ፤ ነገር ግን መሥራት አለብኝ ብሎ ለሌላው የሚተርፍ ማንነት ያለው አስተሳሰብን ካዳበርን ሥራ አልጠፋም::
እንደ ሀገር የከሰርነውና ዛሬም ፈተና ውስጥ የወደቅነው ወጣቱ ለብዙ ችግር ተጋላጭ ሆኖ ነው:: አሁን አሁን የምናስተውለው ሽማግሌ የሆኑ ወጣቶችን ናቸው:: እድሜያቸው የገፉ አባቶች ሲታገሉ እናያቸዋለን:: በወጣትነቱ ደግሞ የሚተኛ፣ በሱስና በተለያየ ነገር ተጠምዶ ተረጂ የሆነ ወጣት ነው:: በዚህች ሀገር ላይ ያለው የሚጦር ወጣት ነው:: አካሉ የወጣት ነው፤ አቅሙ ግን የሽማግሌ ነው:: የተሰጠንን የወጣትነት አቅም በአግባቡ ለጠቀም ከወሰንን ሥራ አልጠፋም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ሥራ በጣም ሞልቷል:: እኛ ውስጥ የጠፋው የመሥራት አቅምና ሃሳቡ ነው:: ያንን ማድረግ ካልቻልን ደግሞ ራሳችንን፣ ማኅበረሰባችንንና ሀገራችንን አይለወጥም:: ስለዚህ ሁልጊዜ ተመጽዋች፣ ሁልጊዜ ተረጂ፣ ሁልጊዜ ጡረተኛ ሆኖ የሚኖር ሰው ወጣት የሆነ ሽማግሌ ነው፤ ከክብር ውርደትን መርጧል ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ሀብት ቢኖራትም ኢትዮጵያ ግን ርዳታ በጠበቅም በመለመንም ላይ ናት ፤ በዚህ የምትቀጥል ከሆነ የሚያጋጥመው ነገር ምንድን ነው? መፍትሔውስ?
ኡስታዝ አቡበከር፡– እንደ አንድ ሀገር ሀገራችን ያለችበትን ወቅት መረዳት ተገቢ ነው:: ታሪክ ያለን ሀገር ነን፤ በትናንት ታሪክ ግን አንቆምም:: ትናንት የነበሩ የእኛነታችን መገለጫና ማሳያ የነበሩ ዛሬ ካላደጉ የትንናት ታሪክ ለእኛ ለትውልዱ ዛሬ ላይ ታሪክ አይሆኑም:: ታሪክ የሚሆነው ተምረንበት የተሻለ ነገር ለመሥራት ስንዘጋጅ ነው:: ስለዚህ ከተረጂነት የወጣች ሀገር እንድትኖረን ካስፈለገ እንደ ሀገር ትልቅ ነገር ለመሥራት መዘጋጀት አለብን::
ሁልጊዜ መረዳት ካለ መረገጥ አለ:: ምክንያቱም ረጂ ሀገራት ሁሌም ቢሆን የየራሳቸው ፍላጎት አላቸው:: የሚረዱ ሀገራት የየራሳቸው ሃሳብ አላቸው:: የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ፣ ማውጣትና ማውረድ ይፈልጋሉ:: በዚህች ሀገር ላይ ጫና መፍጠር ይሻሉ:: እሱ ነገር እንዳይደርስብን ከፈለገን እኛ ማድረግ ያለብን መሥራት ነው:: ሀገር የምትገለጸው በልጆቿ ነው:: ሀገር የምትገለጸው በዜጎቿ ነው:: ያ ዜጋ በዚህ ስሜት መፈጠር አለበት ብዬ የማምነው የሀገር ፍቅር ሲኖር ነው:: ይህ የሀገር ፍቅር የሚባለው ስሜት ግን አሁን አሁን እየጠፋ የመጣ ይመስለኛል::
በመነሻችን ላይ ዓድዋን እንዳነሳነው በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የሀገራችን ክፍል ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጠራርተው ወደስፍራው አቆራርጠው የደረሱት በእግራቸው ነው:: ያንን ታሪካዊ የሆነ ድል መቀዳጀት የቻሉትም የሀገር ፍቅር ስሜት ስላላቸው ነው:: ዜጋው፣ ሀገር ስትነካ መተኛት ስላቃተውና ጥሪ አለብኝ ብሎ መንቀሳቀስ ስለቻለ ታሪክ መሥራት ቻለ::
የዛሬው ትውልድ ሀገራችን ሁልጊዜ በርዳታና በድጋፍ መኖር የለባትም ብሎ መወሰን አለበት:: ምክንያቱም ሁሌ በድጋፍና በርዳታ የምትኖር ሀገር ካለችን ውርደት እሱ ነው:: እንዲያ የምናደርግ ከሆንን ከከፍታ ውርደትን መርጠናል ማለት ነው።
ሀገር ስትራቴጂ የሚቀረጽለት፣ ሃሳብ የሚወጣለት፣ ወደፊት የሚቀጥልበት ብዙ ስራዎች ይፈልጋል:: ከላይ ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ እስከታች ያለው ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ትውልዱም ጭምር የሥራ ባህሉን ማሳደግና ሀገሩን መውደድ መቻል አለበት:: ዜጋው፣ ስለ ሀገሩ፣ ስለትውልዱ፣ ስለነገው እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ነው::
ሰው ዛሬን ብቻ ኖሮ የሚያልፍ ፍጥረት መሆን የለበትም፤ ሰው ማለት ለነገ የሚተርፍ እና ለሌሎች ተስፋ መሆን የሚችል ነው፡። ሀገሩንና ማኅበረሰቡን ከፍ ማድረግ የሚችልና ያንን ሥርዓት የመለወጥ ኃላፊነት ደግሞ የሁላችንም ነው:: ከዚህ አኳያ ቤተ እምነቶች ትውልዱን የማንቃት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ:: የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ትልቁን ሥራ የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው:: ሊሠሩ የማይወዱ እጆች መኖር እንደማይገባቸው ማስተማር አለባቸው:: ይህ ደግሞ የእምነቱም ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ::
ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የማይሰሩ እጆችን፣ የሚለምኑ እጆችን የሚያወግዟቸው በዚያ መልኩ ነበር:: እርሳቸው፤ “አላህ ዘንድ ተወዳጅ ባሪያ ማለት በሥራ የደከመ ባሪያ ነው” ይላሉ:: የደከመና የተሰነጣጠቀ እጅ ተመልክተው “የምወዳት እጅ፣ በሥራ የደከመች እጅ” እያሉ ነበር ሰዎችን ያበረታቱ የነበረው:: ሊለምን የመጣን ሰው “እዚህ ለልመና መስጂድ ላይ ከምትቆም በአጥንትህ ወይም በአጽምህ ሰው ፊት ብትቆም ይሻልህ ነበር::” ይላሉ:: ምክንያቱም ይህን የሚሉት ልመና ውርደት እንጂ ክብር እንዳልሆነ ለመግለጽ ነው::
እኛም መሥራት የማንፈልገው ሀገር በዚያ ልክ እንድትዋረድ እና በዚያ ልክ ዝቅ እንድትል ከፈለግን ነው:: ሥራ መሥራት የምንጠላ ከሆነ ደግሞ ውጭ ሀገር ብንሆንም ተከብረን መኖር አንችልም:: የትም ስፍራ ብንኖር ካልሰራን ክብር አይኖረንም:: ሀገራችን በእርዳታ እና በጥገኝነት እንድትኖር ከመረጥን ዜጋው የራሱ የሆነ ማንነት የሌለው፣ የሌሎችን የፖለቲካ ሐሳብና ፍላጎት የሚያስፈጽም አገር እንዲኖረን መርጠናልና አማራጭ የለንም:: መምረጥ ያለብን ከሁለት አንዱን ነው:: ከፍታን ከመረጥን ለዚያ ለከፍታ የሚሆን ሥራ እንደዜጋ፣ እንደ ማኅበረሰብ ኃላፊነታችንን መወጣት ነው:: ውርደቱን ከመረጥን ደግሞ ምርጫችንን የመረጥነው እኛው ራሳችን ስለሆንን ምንም የምንወቅሰውና የምንተቸው አካል መኖር የለበትም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከውርደትም ከዝቅተኝነትም ስፍራ መውጣት እንድትችል ዜጎቿ ምን ማድረግ አለባቸው? ትውልዱ ልመናን እንዲጸየፍስ ምን ይመክራሉ?
ኡስታዝ አቡበከር፡- እኔ በመጀመሪያ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን እላለሁ:: እኔ፣ ሀገሬ እንድትኖር የምፈልገው ትናንት በነበራት ቁመና ከዚያም አለፍ ሲል በተሻለ ማንነት ውስጥ ነው:: እንደእስልምና ታሪኬ ደግሞ የተመረጠች፣ ለሰው ዘር መጠጊያ የሆነች፣ ለእምነት ነጻነት ዋስትና የሰጠች ፣ብዙዎችን አክብራ መኖር የቻለች፣ በሰላምም በኢኮኖሚም የተሟላ ዋስትና ያላት ሀገር እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ:: ያ እንዲኖረኝ ግን የእኔ አበርክቶ ምንድን ነው? ብዬ ማሰብ ይጠበቅብኛል:: ወደ እንቅስቃሴ ውስጥም መግባት ይጠበቅብኛል::
የእኛ አስተምህሮ መለወጥ አለበት ባይ ነኝ:: ማኅበረሰቡን ከመቅረጻችን በፊት ጅማሬያችን ከቤት ውስጥ መሆን አለበት:: ልጆቻችን ጤነኛ ሆነው እንዲያድጉ ያለንን ቁርጠኝነት ማጤን ይጠበቅብናል እላለሁ:: ትምህርት ቤት ስናስተምራቸውስ በምን አይነት መልኩ እየተማሩ ነው? የሚለውን ማገናዘቡ መልካም ነው:: እየፈጠርን ያለነው ምን አይነት ትውልድ ነው? መለመንን፣ ውርደትን፣ የበታችነትን፣ መስረቅን ወይም ደግሞ ጉቦን የሚጠየፍ ትውልድ ካልፈጠርን ችግር ነው:: ይህ መሰራት ያለበት ከታች ከቤተሰብ እና ከትምህርት ቤት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት በኩል ነው:: ይህን የእምነቱ ኃላፊነት፣ የማኅበረሰቡ ኃላፊነት በጥቅሉ የሀገር ኃላፊነታችን ነው ብለን ማመን አለብን:: ስለዚህም የሁሉም ድርሻ መቀናጀት መቻል አለበት:: ማኅበረሰባችንን የምናገኘው መቼም በሰራነው ልክ ነው:: ያልሞላነውን ከየትም አናመጣውም:: ምክንያቱም የውሃው ማንቆርቆሪያ የተሞላው ውሃ እስከሆነ ድረስ የሚቀዳው ውሃ እንጂ ወተት አይደለም:: ወተት እንዲወጣልን ስንፈልግ ማንቆርቆሪያውን መሙላት የሚጠበቅብን ወተት ነው:: ሁሉም የሚያወጣው ውስጡ ያለውን ነው::
ልመናን፣ ራስን አለመቻልን፣ ተመጽዋችነትንና የበታችነትን የሚጠየፍ ትውልድ መፍጠር የጋራ ኃላፊነት ነው:: በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ የማኅበረሰብ መሪዎቻችን በዚያ ልክ ትውልዱን ማነጽና ማስተማር ይጠበቅባቸዋል:: ሰዎች አዕምሯቸው የሚያድገው በተሰጣቸው ልክ ነው:: ጥሩ ነገር ማግኘት የሚቻለው አዕምሮ በወጉ ሲገነባ ነው::
እኛ ዛሬ ትልቁ ጭንቀታችን ከአንገት በታች ላለው አካላችን ሆነ:: ትልቁን ሥራ ማድረግ እና መልፋት የነበረብን አዕምሮ ላይ ነው:: ወጪም መውጣት የነበረው ከአንገት በላይ ለሆነው የአካል ክፍል ነው:: ምክንያቱም እሱ ሲስተካከል ሁሉም መስተካከል ይችላል:: እኛ ግን በአብዛኛው ክብር የሰጠነው ከአንገት በታች ላለው የአካል ክፍላችን ነው:: ስለዚህ ሁሉም መስተካከል እንዲችል የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው:: ያንን መስራት ከቻልን የማይለወጥ ነገር አይኖርም:: ለዚህ ደግሞ ብዙ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል::
ለምሳሌ አዲስ አበባ ቀደም ሲል የነበራት ምስልና አሁን ያላት በጣም የተለያየ ነው:: አሁን የመጣውን ለውጥ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ማየት አንችልም ነበር:: የተለወጠው አስተሳሰብ ብቻ ነው:: ማድረግ እንችላለን የሚል አመለካከት ሲመጣ ማከናወን ይቻላል ማለት ነው፡። ከዚያ የተነሳ ዛሬ አዲስ አበባን በተለየ ቁመና ውስጥ እያየናት አንገኛለን:: ይህንን ትናንትናም ማድረግ ይቻል ነበር:: ነገር ግን አስተሳሰብ ይፈልጋል:: ይህን የሚያቀናጅ እና የሚመራ አካል ይፈልጋል:: ይህን አስተሳሰብም መቀበል የሚችል ትውልድም ይፈልጋል:: የማንችላቸው የሚመስሉን ነገሮች የምንችላቸው ሆነው አግኝተናቸዋል:: ቀደም ሲልም መሥራት ያልቻልነው አንችልም ብለን ስለመጣን ነው:: አዲስ አበባ ዛሬ ያለችበትን አይነት ቁመና ሌሎቹ ክልሎቻችንም መሆን ይችላሉ:: የሚፈልጉት የማኅበረሰቡን ጥረት ነው:: የሚፈልጉት የጋራ ጥረትን ነው:: ሁሉም የየድርሻውን ከተወጣ የማይቻል ምንም ነገር አይኖርም::
ወደቻይና እና ሌላው አካባቢ ሔደን ብናይ ልጆች በየትምህርት ቤታቸው የሚማሩት ለነገ ሕይወታቸው መሰረት የሚሆነውን ነገር ነው፤ ዛሬ ላይ የሚመገቡበትን ሳህን ራሳቸው እንዲያጥቡ ከማድረግ የሚጀምር ትምህርት ከተማሩ ነገ እንዴት መስራት እንዳለባቸው የሚጠፋቸው አይሆንም:: እናም ሀገራት ልጆች እንዲያድጉ የሚያደርጓቸው በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሥራ ባህል እንዲኖራቸው ነው:: መሆን ያለበትም ይህ ነው:: የእኛ አስተምህሮ እና ቤተ እምነቶቻችን ይህን ማድረግ ካልቻልን አሁንም ትውልድም ሀገርም እያጣን እንሄዳለንና የሁላችንን ጥረትና ርብርብ የሚፈልግ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በእስልምና አስተምህሮ ሥራ ከመሥራት ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ የሚገለጸው እንዴት ነው ?
ኡስታዝ አቡበከር፡– በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ ለሥራ የተለየ ቦታ ይሰጣል:: የሰው ልጅ ዝቅ ብሎ እንዲታይ የማይፈልግ ማኅብረሰብ የተሻለ ቁመና ላይ እንዲቆም የሚሻ ነው:: በመሰረቱ ይህች ምድር ስትፈጠር ለሰው ልጅ እንድትጠቅም ነው:: የምንጠቀምባት እኛ ሰዎች ደግሞ ሥራችን መሆን ያለበት ተጠቅመንባት አጥፍተን እንድትሔድ አይደለም:: የሚፈለገው አልምተናት፣ ለውጠናት እና ቀይረናት እንድንሔድ ነው::
ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) በተለዩ መልዕክቶቻቸው ላይ “በሥራ ደክሞ ያደረ እጅ በአላህ ዘንድ የተማረ ነው::” ይላሉ:: አስቀድሜ እንዳልኩት “አላህ የሚወዳት እጅ በሥራ የደከመች እጅ ናት” ይላሉ:: ከሰው ጠባቂ ያልሆነ ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን የሚደግፍ ነው:: በምንም አይነት መልኩ ለሰው ዝቅ እንዳንል ሥራ የእኛ ኃላፊነት ስለሆነ “ሥራችሁን ሥሩ፤ አላህ ሥራችሁን ይመለከታል::” ሲሉ ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ገልጸዋል:: ሥራ የአማኞች ባህል ነው:: ለዚህም ነው ነብያት ሳይቀሩ በሥራ ውስጥ እንዲያልፉ የመደረጉ ምስጢር:: አማኝ ሆኖ ይህን የሥራ መንፈስ ያላከበረ እምነቱን አላወቀም፤ አልተረዳምም:: ከእምነቱ ራሱን እንዳገለለና ከእምነቱ ውጪ እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ታላላቆችን የማክበር ባህላችንና ሽማግሌዎችን የመስማት ባህላችን በጣም ደብዝዟል:: እዚህ ላይ የሚሉን ነገር ይኖር ይሆን? የሚመክሩትም ነገር ካለ አይይዘው ቢገልጹልን::
ኡስታዝ አቡበከር፡– ይህ የሆነበት ምክንያቱ የሥራችን ውጤት ነው ማለት ይቻላል:: ምክንያቱም ያልዘራነውን አናጭድም:: አስተምህሮቱ መፈተሽና መታየት መቻል አለባቸው:: ብዙ ጊዜ የእምነት አባቶች ጋር ስንገናኝ ቤቶቻችንን ዘግተን ልንነጋገርባቸው የተገቡ ጉዳዮች አሉ ብዬ አምናለሁ:: ይህ ደግሞ የሁላችንም ችግር ስለሆነ ነው::
ወላጅን፣ ታላላቅን አለማክበርና የሚገባቸውን ቦታ አለመስጠት ላይ ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የተናገሩት ነገር አለ፤ ይኸውም “ታላቁን የማያከብር፣ ለታናሹ የማያዝን ከእኛ አይደለም፣ ከአማኞች ጎራ አይደለም::” የሚል ነው:: ይህ ማለት እንደ ማኅበረሰብ ዛሬ የሃይማኖት አባትን የሚሰድብ፣ መሪን የሚሰድብ፣ ታላቅን የሚሰድብ፣ መምህርን የሚሰድብ ትውልድ ፈጥረናል:: ይህ ትውልድ የወጣው ከማንም አይደለም፤ ከእኛው ከራሳችን የወጣ ትውልድ ነው:: ከእኛው ቤተ እምነት የወጣ ነው:: ማን ቀረጸው? ማንስ አነጸው? ለምን እዚህ ደረጃ ደረስን? ብለን ሌላውን ከመውቀሳችን በፊት መጠየቅ ያለብን እኛው ራሳችንን ነው::
ትውልዱ እኛ ያላስተማርነውን ከየትም ማምጣት አይችልም:: ለምሳሌ አባት ቤት ተቀምጦ እያለ “ቤት የለም በል” የሚል አባት ነገ ጠዋት ልጁ ቢዋሸው ለምን ይቀጣዋል? ልጁ የደገመው እሱ ያስተማረውን ውሸት ነው:: ምክንያቱም ያላደገበትን ነገር ከየት ያመጣዋል? ስለዚህም ነው መከባበሩ እንዲጠፋ እያደረግን ያለነው እኛው ራሳችን በእጃችን በሠራነው ሥራ ነው የምለው::
ለዚህ ደግሞ ቤተ እምነቶች ትልቅ ድርሻ አለባቸው:: ልጆቻችን ምን ላይ ነው ያሉት? ብሎ መፈተሽ፣ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ ማየት ያስፈልጋል:: የምናስተምረው ትምህርት ያረፈው ምን ላይ ነው? ያስተማርናቸው እንዴት አድርገን ነው? ከሙስሊሙ መስጂድ ተነስቶ ክርስቲያኑን የሚሰድብ፤ ከክርስቲያኑ ቤተ ክርስቲያን ተነስቶ ሙስሊሙን የሚሰድብ ነገ ጠዋት ቄሱን እና ሼኪውን ላለመስደቡ ምንም ዋስትና የለውም:: ደግሞም ይሳደባል፡። ምክንያቱም ያስተማርነው እኛው ነን:: ሲሳደብ መሳደብ ክልክል እንደሆነ ያልነገርነው እኛ ነን:: ለሌሎች ሲሆን እንደሚፈቀድ አሳይተነዋል::
እስልምናችን ግን የሚለው “የሌሎችን እምነት አትሳደብ፤ የሌሎችን ፈጣሪ አትሳደብ:: የእናንተን ፈጣሪ ይሰድቡባችኋልና ወንጀለኞቹ እናንተ ትሆናላችሁ፤ ምክንያቱም ፈጣሪያችሁ እንዲሰደብ ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁና:: ክብሩ እንዲጣስ ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ:: ምክንያቱም የእነርሱን ክብር ባትነኩ ኖሮ የእናንተን ክብር አይነኩም ነበር፡። ተጠያቂዎቹ እናንተ ናችሁ::” ይላል::
ስለዚህ በየቤተ እምነቶቻችን እንመለስና እንፈትሽ፤ ትውልዱ አማኙ የት ላይ ነው:: ኅብረተሰባችን የት ላይ ነው። ልጆቻችን ምን ላይ ናቸው ብለን እንመልከታቸው:: ይህን መሥራት ከቻልን የወደፊታችንን ማስተካከል እንችላለን፡። ካልሆነ ግን ከዚህ የከፋ ነገር ይመጣል:: ሰው ሲሰቀል ያየንበት ሀገር ነው:: ወገን ወገኑን ሲያሳድድ እያየነው ነው:: “እኔ ልሙት እንጂ ይህን መጥፎ ተግባር አትፈጽሙም” የሚል ሽማግሌ የጠፋበት፣ የሃይማኖት መሪ የሌለበት ሀገር ነው:: “እኔ ልሙት እንጂ ሀገር ሲጠፋ፤ ማኅበረሰብ ሲጎዳ አላይም፤ አቁሙ” ብሎ እዛ ክፉ ነገር ፊት የቆመ የሃይማኖት አባት ተመልክተናል? አላየንም፤ ከየት ይምጣ? ይህ ነው ችግሩ ብዬ አስባለሁ:: እኛ ነን የሃይማኖት ትምህርታችንን ልንፈትሽና ልናስተካክል ያለብን ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- እንግዳችን ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ::
ኡስታዝ አቡበከር፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም