የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ከውዥንብር የጠራ እንዲሆን

ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ መንግሥት ትልልቅ ሀገራዊ ውሳኔዎችን ሲወስንና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት በማሻሻል ‹‹ዜጎችን ከድህነት ሀገርንም ከኋላቀርነት ይታደጋሉ›› ተብሎ የሚታመንባቸው የግብርና፣ የትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ ስር ነቀል ሊባል የሚችሉ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ተደርጓል።

እነዚህ ግዙፍ ውሳኔዎች ጨከን ያሉ የአመራር እርምጃዎችን የጠየቁ፣ ቆየት ያሉ አስተሳሰቦችና ልማዶችን ለመቀየር ትግል የገጠማቸው ይሁኑ እንጂ የረጅም ጊዜ ውጤታቸውና ፍሬያማነታቸው የዛሬ ውሳኔያችንን እንድናመሰግን የሚያደርጉ መሆናቸው አያጠራጥርም።

የኢትዮጵያን መፃኢ እድል የሚወስኑ፤ ድፍረት እና ሰከን ያለ የአመራር ውሳኔ የሚሹ ውሳኔዎች አሁንም ከፊታችን ተደቅነዋል። የሀገሪቱ መንግሥትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለእነዚህ መሰል እርምጃዎች ቁርጠኛ አመራር እየሰጠ መሆኑንም እየተመለከትን ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን የሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ የፖሊሲ ማሻሻያ ነው።

በመግቢያዬ ላይ ላነሳኋቸው የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ይህ የመንግሥት እርምጃ በርካታ እድሎችን ይዞ መምጣቱን የዘርፉ የኢኮኖሚ ምሁራን ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት ምክረ ሃሳቦች ላይ በስፋት ሲነሳ አድምጠናል። በዋናነት ግን መዋቅራዊ ለውጡን፣ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያ ውሳኔዎቹን ተከትሎ በማህበረሰቡ ዘንድ ብዥታ እንዳይፈጥር፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስ፣ ወደ አዲስ የንግድና ግብይት ሥርዓት ሲገባ በሚኖር አለመረጋጋት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ቀጥተኛ ተጎጂ እንዳይሆኑ ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ነው። ይህ ቁልፍ ጉዳይ የራሱ የፖሊሲ አውጪው አካል ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንም ውሳኔው ይፋ በተደረገበት ወቅት በተሰጠ ዝርዝር መግለጫ ላይ በግልፅ ተቀምጦ ተመልክቻለሁ።

ኢትዮጵያ ረዘም ላሉ ዓመታት ቅድመ ዝግጅት ስታደርግበት የቆየችውና ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ የፖሊሲ ማሻሻያ (በተለይ የወቅቱን ገበያ ባገናዘበ በውጭ ምንዛሬ ተመን floating exchange rate እንዲመራ መወሰኑ) የሀገሪቱንና የዜጎችን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ዘላቂና አዎነታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ ‹‹የደፈረሰው እስኪጠራ›› በፖሊሲው ላይ ሁለንተናዊ ግንዛቤ እስኪፈጠር ድረስ እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ መደናገሮች እንደሚያጋጥም የሚታመን ነው። በዛሬው ርእሰ ጉዳይ ላይ በስፋት ላነሳው የወደድኩት ይህንኑ ጉዳይ ሲሆን ከዚህ እንደሚከተለው ዝርዝር ጉዳዮችን እዳስሳለሁ።

መንግሥት ይንን ታሪካዊ ውሳኔ ሲያስተላልፍ እንደገለጸው የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያው ብሄራዊ ጥቅምን ያገናዘበና ቀጣይ የሀገሪቱን የእድገት አቅጣጫ የሚወስን ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም አይነት ፖሊሲም ይሁን ሕግ ሲደነገግ ቅድሚያ የሚሰጠው ብሄራዊ ጥቅም ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከዜጎች በተለይ ደግሞ የሀገር ባለቤት ከሆኑት ብዙኃን ጥቅም ጋር የተሳሰረ መሆኑ እሙን ነው።

የምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲወሰን ሲደነገግ የዋጋ ንረትን ለማስተካከል እና ጤናማ የግብይት ሥርዓትን ለማስፈን እንደሚያስችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሆኖም ግን የመጫወቻ ሜዳው ጤናማ እንዲሆን የተረጋጋና ህግን የተከተለ ውድድር እንዲሰፍን መንግሥት በተቋሞቹ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል።

የፖሊሲ ማሻሻያውን ይፋ ያደረገው መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ክትትል እንደሚያደርግ ነግሮናል። ይህ እቅድ ከወረቀት ላይ አልፎ ተግባራዊ እርምጃዎችን የሚጠይቅ ነው። ፖሊሲው ተግባራዊ ከተደረገበት እለት አንስቶም ተቋማቱ አፈፃፀሙንና ተግባራዊነቱን መከታተል መጀመር አለባቸው።

ብዙውን ጊዜ ፖሊሲዎች መሬት ላይ መውረድ የሚሳናቸውና ኅብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚፈጥሩት በክትትልና ቁጥጥር ማነስ እንደሆነ ይነገራል። ብልሹ አሰራርና ሙሰኝነት ሲታከልበት ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። በመሆኑም ሀገርን መፃኢ እድል የሚወስን እና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ይህን መሰል የፖሊሲ ትግበራ በተቀናጀ ተቋማዊ አሰራርና በጠንካራ አመራር ሰጪነት ሊደገፍ ይገባል።

መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ቀጥተኛ ሚና ይኖራቸዋል ያላቸውን ተቋማት ለይቶ ማስቀመጡን ውሳኔውን ባሳለፈ ማግስት ነግሮናል። ከተቋማቶቹ ውስጥ ብሄራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ናቸው። ፖሊሲውን በማውጣትና በማስተግበር ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎና ድርሻም መለየቱን ሰምተናል። ይሁን እንጂ ተቋማቱ ከመንግሥት ጋር ከሚኖራቸው ቀጥተኛ ግንኙነት ባሻገር የሕዝብ ግንኙነት መረባቸው የተሰናሰለና ውጤታማ መሆን አለበት።

ምክንያቱም አብዛኛው ማህበረሰብ ጓዳ ድረስ የሚገባ ይህ ውሳኔ ‹‹ምን በጎና አሉታዊ›› ተፅእኖ እንደሚኖረው በተከታታይ መረጃ በመስጠት ኅብረተሰቡን ማንቃትና ማስተማር ይኖርባቸዋል። የነፃ ገበያ ሥርዓቱ የሚመራበትን ሕግና ሥርዓት ሁሉም ዜጎች ጠንቅቀው እንዲረዱት ለማስቻል ተቋማቱ በተናጠልና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም ዜጎች በንግድ ሥርዓቱ እኩል ተጠቃሚና ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ሀብትና ንብረት የሚያፈሩበት መደላደል መዘርጋቱን በክትትልና ቁጥጥር የማረጋገጥ ኃላፊነትም አለባቸው።

አባቶቻችን ‹‹እንቅልፍ ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› የሚል ብሂል አላቸው። ተወደደም ተጠላም በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም። በዚህ ሉዓላዊ ዓለም ላይ ጠንካራ፣ ሉዓላዊና ያደገች ሀገር መገንባት ካሻን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችንን ማሻሻል የግድ ይለናል። አሁን ያለው መጫወቻ ካርድ ደግሞ የሚያመለክተን የነፃ ገበያ መርህን የሚከተል፣ በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ተመንን የወቅቱን ገበያ መሠረት ያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ወቅቱን አገናዝቦ ማሻሻያ እና ውሳኔ አሳልፏ። በመሆኑም ውሳኔውን በበጎና አዎንታዊ ልቦና ተቀብሎ ለአፈፃፀሙ ስኬታማነት መስራት የተሻለው አካሄድ ይሆናል።

በእርግጥ ከላይ በዝርዝር ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በውሳኔው እና በፖሊሲና ሕግ ማሻሻያው ተጋላጭ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸው የማይካድ ነው። ለእነዚህ ዜጎች ግን መንግሥት ከለላ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጉን ነግሮናል። ይህንን እንደ በጎ ጅምር መውሰድ ይኖርብናል። ካለፉት ጊዜያት ተሞክሮዎች ለመረዳት እንደምንችለው በተለያዩ ጊዜዎች የሚወጡ ሕጎችን ተከትለው የማህበረሰቡን ጥቅም የሚጎዱ እንዲሁም ብልሹ አሰራርን በመዘርጋት ሕግና ሥርዓትን ለመጠምዘዝ የሚጥሩ ሕገወጦች መኖራቸውን ነው። እነዚህን አካላት በየጊዜው ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ድርሻ ነው።

ከሕገ ወጦች ባሻገር በራሱ በፖሊሲው ለውጥ ምክንያት የሚፈጠርን ክፍተት ለማረቅና የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት መሬት እንዲነኩ ለማስቻል መንግሥት የወሰደው ቁርጠኝነት መልካም ነው። ይህ ውሳኔም ከወረቀትና እቅድ ባሻገር መሬት መንካት ይኖርበታል። በተለይ የማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ድጎማ የማድረግ ሃሳቡ ከወዲሁ በተቀናጀ መንገድ መሬት መንካት ይኖርበታል።

መንግሥት ‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ የፖሊሲ ማሻሻያውን ተከትሎ ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሰራተኞች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ሊያስከትሉ ከሚችሉት የአጭር ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ የደሞዝ ድጎማና ማሻሻያዎች ለተወሰኑ ጊዜያት ይደረጋሉ›› የሚል ቃል ውሳኔውን ባስተላለፈበት እለት አያይዞ ነግሮናል። ይህ ውሳኔ ለማህበረሰቡ እፎይታን የሚሰጥ ነው።

ብዥታውን አጥርቶ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግም እንደ አንድ መንደርደሪያም ይሆናል። በመሆኑም ከቃል ያለፈ ፈጣን ውሳኔ ማሳለፍ አስፈላጊ ነው። ይህ ወሳኔ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር ገበያው የተረጋጋ እንዲሆን መስራትም ተገቢ ይሆናል። በተለይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መንግሥት በከፊል የሚደጉም መሆኑን ማሳወቁ ገበያው ላይ በፍጥነት ያልተጠበቀ ማሻቀብ እንዳይኖርና የኢኮኖሚ ስብራት እንዳያጋጥም አጋዥ ይሆናል። ይህን መሰል የተመረጠ ስልታዊ እርምጃዎችን መውሰድ የታለመውን ግብ ለመምታት ያግዛል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሂደት ቀጣይነት ያለው ግምገማ እንደሚደረግበት መንግሥት አስታውቋል። ይህ ውሳኔም ያልተጠበቁ ክስተቶች በሚኖርበት አጋጣሚ ማስተካከያዎችን ለማድረግ የሚረዳ ነው። ይህም ማለት አንዴ የወጣ ሕግ አሊያም የፖሊሲ ማሻሻያ የማይቀየር አሊያም የማይሻሻል እንዳልሆነ ያስገነዝበናል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱ በበጎ መልኩ ልንወስደው ይገባል።

በመጨረሻ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ምቹ አጋጣሚን ተጠቅመው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈፀም ከላይ እታች የሚሯሯጡ ሕገወጦችን በተቋማዊ ቅንጅት መከላከል ነው። እነዚህ አካላት ማንኛውንም የመንግሥት ውሳኔ በሚተላለፍበት፣ ሕግና ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ሕገወጥ አካሄዶችን ለመከተል ማድባታቸው አይቀርም።

በእርግጥ በዚህም ረገድ መንግሥት የራሱን ዝግጅት ማድረጉንና ‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል የነቃ ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ ይወስዳል›› በማለት ለበሽታው ማርከሻ ማዘጋጀቱን ነግሮናል። ይህ የጥንቃቄ ዝግጅት ግን ከኅብረተሰቡ ሙሉ ለሙሉ ድጋፍን የሚሻ ነው።

እንደሚታወቀው ሕገ ወጥነትን በመንግሥት መዋቅር ብቻ መቆጣጠር አይቻልም። በዚህ ድርጊት ላይ የመንግሥትን ስልጣን አላግባብ የሚጠቀሙ ሙሰኞች ሲታከሉበት ደግሞ ውጤቱ የከፋ ይሆናል። በመሆኑም የመንግሥትና የኅብረተሰቡ ቅንጅት በእጅጉ አስፈላጊ ይሆናል። እያንዳንዱ ዜጋ የማክሮ ኢኮኖሚው ትግበራ ጓዳው ድረስ ተፅእኖ እንደሚኖረው አውቆ በሕገወጥ መልኩ ሂደቱ እንደይሳካ የሚያስተጓጉሉ ደላሎች፣ ነጋዴዎችና ሙሰኛ ባለስልጣናትን የማጋለጥ፤ ሕግና ሥርዓት እንዲሰፍን ተባባሪ መሆን ይጠበቅበታል። ከሁሉም በላይ ግን የፖሊሲ ትግበራው ውጤታማነት እያደር የሚታይና በአንድ አዳር በጎ ለውጥን እንደማያመጣ ተረድቶ በትእግስት መጠበቅ የዜጎች ኃላፊነት ይሆናል።

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You