አዲስ አበባ፡- በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አጋማሽ አጠቃላይ ከ አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት(GDP) የኢንዱስትሪው ሴክተር ድርሻ ከ15 በመቶ ወደ 26 በመቶ ከፍ ሊል መቻሉ ተገለጸ፡፡ የግብርና እና አገልግሎት ዘርፎች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አመልክቷል፡፡
ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ የአፈጻጸም ሪፖርት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትናንት በሂልተን ሆቴል ለውይይት ሲቀርብ ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ እንደገለጹት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አጋማሽ ላይ አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት (GDP) ውስጥ የኢንዱስትሪው ሴክተር ድርሻ ከ15 በመቶ ወደ 26 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ይህ አበረታች ለውጥ የተስተዋለው በኮንስትራክሽንና መሰል ንኡስ ዘርፎች ነው፡፡ በአንጻሩ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች አፈጻጸም ዝቅተኛ ታይቷል፡፡
ለኢንዱስትሪው ዕድገትም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕድገትና መስፋፋት፣ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተስፋፉና እየዘመኑ መምጣታቸው አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የግብርናው እና የአገልግሎት ሴክተሩ አስተዋጽኦ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ በዚህ ምክንያት በሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ የሚፈለገውን የመዋቅራዊ ሽግግር ሊያዘገየው ይችላል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጻ፤ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የተመዘገበው የግሽበት መጠን በነጠላ አኃዝ እንዲወሰን ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም የበጀት ዓመቱ የምርት መጠንና የገንዘብ ፖሊሲው ትስስር አወንታዊ ውጤት ነው፡፡
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እኩሌታ አፈጻጸም በተለይም አማካይ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን እድገት (GDP) በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸው የአገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የዓለም የኢኮኖሚእድገት መቀዛቀዝ እና ድርቅ ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፤ የአገሪቱ ዋና ዋና ሴክተሮች የአፈጻጸም ሪፖርት መገምገሙ በቀጣይ ለመሻሻል መልካም እድሎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ውይይቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጡ መደረጉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ስኬት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በአንዳንድ የልማት መስኮች አበረታች ለውጦች መመዝገብ ቢችሉም የሚጠበቀውን ያህል መፈጸም አልተቻለም፡፡ በውይይቱ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መተግበር ከጀመረች ሦስት ዓመታት ያህል ተቆጥረዋል፡፡
‹‹እንደ ልማት አጋርነታችን ከኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ጎን ነን ያሉት ኮ ቼር ኦፍ ዘ ዴቭሎፕመንት አሲስታንስ ግሩፕ (DAG) ኤንድ ሄድ ኦፍ ዘ ሚሽን (UK DFID) ዶክተር ክርስቲያን ሮግ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሰፊና ከዓለም የዘላቂ እድገት ግቦች ጋር ትይዩ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ክርስቲያን ሮግ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ የቀጠለች ቢሆንም በ2016/2017 ያስመዘገበችው 10 ነጥብ ዘጠኝ የአጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት መጠን (GDP) ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ የአፈጻጸም ሪፖርት የተስተዋሉ ውስንነቶች ተቀርፈው በእቅድ ዘመኑ መጠናቀቂያ መሻሻሎች መታየት ይኖርባቸዋል ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
መሐመድ ሁሴን