በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ከተመለከተቻቸውና የኢኮኖሚክስን መልክና ቁመት እንዲሁም አቅጣጫ ካስተካከሉ ስመጥር ምሁራን አንዱ ስለመሆናቸው በርካቶች በአንድ ድምፅ ይስማማሉ። አሜሪካዊ ናቸው። ውልደታቸው እኤአ በ1912 ነው። በገቢ እና በፍጆታ ላይ ባደረገው ጥናት እኤአ በ1976 በኢኮኖሚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ተቀብለዋል። እኚህ ታዋቂ ኢኮኖሚስትና የስታትስቲክ ምሁር ሚልተን ፍሬድማን ይባላሉ፡፡
ሰውየውን ምንጊዜም አይረሴ ከሚያደርጋቸው ጥናትና ምርምሮች ባሻገር በተለየ እይታና አስተያየታቸውም ይታወቃሉ። ከአስተያየቶቻቸው መካከልም ‹‹ማናቸውም የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች መተቸት ያለባቸው በውጤታቸው እንጂ በሃሳባቸው መሆን የለበትም ‹‹One of the great mistakes is to judge policies and programs by their intentions rather than their results.›› የሚለውን አንደኛው ነው። ይህ አስተያየት በአግባቡ የተረዱም ከወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር አይከብዳቸውም፡፡
እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ገብታለች። መንግሥት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫም፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች መካከል የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከልና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት አንዱ ነው። የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስና የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግና ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር ሌሎቹ ግቦች ናቸው።
በተጨማሪ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፤ ጠንካራ፣ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ግቦቹ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
የፖሊሲ ርምጃዎቹ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶቻችን ጋር ተጣጥመው ይከናወናሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበሩ መንግሥት ከፍተኛ የክትትልና የድጋፍ ማዕቀፎችን እንደሚዘረጉ ተጠቁሟል።
ለዚህም በሁሉም በሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥታዊ ተቋማት በኩል አስፈላጊ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል። በሁሉም በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል የፖሊሲ ትግበራ አፈጻጸም ወጥነት እንዲኖር መንግሥት ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያ አመራር መኖሩን ያረጋግጣል ብሏል፡፡
መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን አስታውቋል። አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና ኢ-መደበኛ አሠራር በማስቀረት ተወዳዳሪ፣ ግልጽና አመቺ ወደሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መግባትን የሚያበረታታ እንደሆነ ነው የገለጸው።
ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳም አመላክቷል።
ለፖሊሲው ስኬታማነት የሚወሰዱ ርምጃዎች ሰፊና በቂ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገም በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎምና እንዲሁም የገንዘብ ድጎማ ለመስጠትም መወሰኑን ገልጿል፡፡
ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉም ተከትሎም ከአቅጣጫው የተለያዩ አስተያየቶች በመዥጎድጎድ ላይ ናቸው። ከላይ በመግቢያችን እንደጠቀስነው ‹‹ማናቸውም የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች መተቸት ያለባቸው በውጤታቸው እንጂ በሃሳባቸው መሆን የለበትም። የአንድን ፖሊሲ ውጤት ለመረዳት ደግሞ ጊዜ መስጠት የግድ ነው። አንድ መድኃኒት ሊያሽርም ሆነ ላያሽር የሚችለው አስቀድሞ ሲወሰድ ነው። ከተወሰደ በኋላ ውጤቱን ለመገምገም የተወሰነ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አያከራክርም።
አንድን ሃሳብ፣ ውሳኔ ብሎም ፖሊሲ ማድነቅም መተቸትም ተገቢ ነው። የልክነት ትርጉሙና ፍቺው በአንድም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲታሰብ ደግሞ ማሰብ ብቻም ሳይሆን በምክንያት መሳብ ጋር ተያይዞ ይመጣል። ምክንያታዊነት ደግሞ በተንኮል ያልታጠፈ፣ በምቀኝነት ያልተቆለመመ፣ በራስ ወዳድነት ያልተንጋደደ ሃሳብና ምግባር ነው። ምክንያታዊነት፣ አመዛዛኝነት፣ አስተዋይነት ነገሮችን አንድ በአንድ በጥልቀት በማየትና በመመርመር እውን የሚሆን ነው። እንደ ሃሳብ ሁሉ የማንኛውም ፖሊሲ ትክክለኛ ምስል ለማግኘት ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆን፣ ከሁሉ በላይ ከጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ መራቅ የግድ ይላል፡፡
ከሰሞኑ ውሳኔ ጀርባ የሚሰሙ ጩኸቶች ግን ከዚህ እሳቤ በእጅጉ የተራራቁ ሆነው በመደመጥ ላይ ናቸው። በርካቶች ውሳኔውን የደረጃው ከመረዳትና ከመገምገም እንዲሁም ትችትም አስተያየትም ከመስጠት ይልቅ ከጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡
ስለ ውሳኔው አዎንታዊ ጎኑ የሚመሰክሩትን ይህል አሉታዊ መልኩ የሚታያቸውም በርካቶች ናቸው። በተለይ «እኛ ከሌለንበት» የሚሉ፤ ከመተቸት ቅርብ የሆኑ ግላዊ የልዩ ፍጡርነት ስሜት false or wrong self-perception ሰለባዎች እዚህም እዚያም እየጮሁ ናቸው፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ እድገት የሚከስሩ፣ በውድቀቷ የሚያተርፉ የዘመናት የሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት የሆነውን ሁለንተናዊ እድገት የመትከልና የማጽናት ትግልን ለመቀልበስ የሚጥሩ ከተደበቁበት ብቅ ብቅ ብለዋል። ለውሳኔው ሁለንተናዊ ውጤታማነት እገዛ ከማድረግ ይልቅ ከውስጥም ከውጭም በባዕዳን ነዋይ ተደልለው በገዛ ሀገራቸው ላይ የጸረ አንድነት መፈክር የሚያሰሙ አልሞት ባይ ተጋዳዮችም ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡
የሰሞኑን የፖሊሲ ውሳኔ ሁለንተናዊ ፋይዳ በቅጡ ከመረዳት ይልቅ በጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ የተጠመዱና ስለፖሊሲው ጠንቅቆ ለመረዳት የተዘጉና የተገዘቱትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ቀድመው የሰሙትን አምነው የተቀበሉና በተቃውሞ ሃሳባቸው ዋሻ መሽገውና የሚዛን በራቸውን ዘግተው የተቀመጡ በርካቶች ናቸው፡፡
በትንሹ ተረድተው በትልቁ የሚፈርዱ መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱና ካልተናገሩ የሌሉ የሚመስላቸው፣ ስለተመለከቱትም ሆነ ስላደመጡት እንዲሁም ስላነበቡት ምንነቱን በቅጡ ያልተረዱ፣ ብቻ በሩቁና በጭፍን የሚደመድሙና በአቃቂር ጫፍ የደረሰም አሉ፡፡
የፖሊሲው ሁለንተናዊ ፋይዳ መረዳት ፈልገው በአግባቡ የሚያስረዳቸው ያላገኙም በርካቶች ናቸው። ይሁንን ከዚህ በአንፃር ሆን ብለው ፖሊሲው ተግባራዊ ቢሆን ሊያጡት የሚችሉትን ሂሳብ በመሥራት «ለምን እየሰረቅን እየዘረፍን አንኖርም?» የሚል ትልቅ ሀፍረትና ህሊና ቢስ ጥያቄና ሙግት የሚገጥሙ፣ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ፣ ለማስለቀስ፣ ድህነት መስቀል ላይ ቸንክረው ለማሳቃየት የሚተጉም እዚህም እዛም አሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች እንዴት እንዲህ ይሆናል ሲሉ እንዴት እንዲህ አይሆንም ለሚለው ቦታ የላቸውም። ሃሳብ፣ ተግባርን ህልማቸው ቡድናዊ፣ በደንብ ሲጠና ደግሞ ግላዊ ነው። በቀላሉ መታዘብ እንደሚቻለው ከሆነ ምክንያት አልባዎች የአንድን ውሳኔ ጥቅምና ጉዳቱን ፈልቅቆ ለማግኘት አቅምም፣ ዝንባሌም ሆነ ፍላጎቱ ሲያጥራቸው መታዘብ ቀላል ነው፡፡
አለን የሚሉት የእሳቤ ማስረጃም በአብዛኛው ከዕውቀት ጋር ያልተዋሀደ ነው። ስለሚያወግዙት ግማሽ መንገድ ተራምደው አይጠይቁም። ማጣጣል እንጂ ማድነቅ ምርጫቸው አይደለም። የምክንያት አልባነት ሰለባ ተጠቂዎች እንዲህ ብናደርግ ሲባሉ ቢያንስ ሞክረው ውጤቱን ለመመልከት አዋጭ ከሆነ መቀጠል ካልሆነም ለማቋረጥ ዝግጁና ተባባሪነት አይታይባቸውም። ይልቁንም ሳይጀምሩ ይጨርሳሉ፡፡
ይህን ጫና ከፍ ሲልም ፕሮፖጋንዳ ተከትሎም በውሳኔው የተናጡና የሚደናገጡም እዚህም እዛም ይታያሉ። ይሁንና የመንግሥት ውሳኔ ያማረ ነው ወይስ የመረረ ለማለት አስቀድሞና ጊዜ ሰጥቶ መቅመስ ከፍ ሲልም ማጣጣም ግድ ይላል። ይህ ደግሞ መረጋጋትን ይጠይቃል። ጊዜም ይፈልጋል፡፡
ይሁንና አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ሃቅ ቢኖር እኛ ያልነው ብቻ ልክ ነው ሌሎችን አትስሙ በሚል ትችት ብቻ ማዝነብ፣ ከግዙፉ ነጭ ይልቅ ነጥቧን ጥቁር በማጉላት የሀገርን የብልፅግና ጉዞ ለማድነቅ የድንጋይን ሚና መያዝ ተገቢ አይደለም። እንዲህ ብንደርግስ፣ እንዲህ ሊደረግ ታስቧል እንዲህ ተደረገ በተባሉ ቁጥር ለጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ መቸኩር ጤነኝነት አይደለም። መሰል ምክንያት አልባነትና ጭፍን ድምዳሜ ምንም አይለውጥም። አይቀይርም። አያዘምንም። አያሰለጥንም። ለማወቅ ለመመርመር፣ ለመሰልጠን አዳዲስ መንገዶችን ለመፈተሽ ዕድል አይሰጥም። ማንንም አያስተምርም።
ሕዝብም ቢሆን መሰል ውሳኔዎች በተላለፉ ቁጥር ቶሎ ብሎ ወደ መራድ የሚሄድ ከሆነ በመሠረቱ ትክክል አይደለም። በጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ ከመዋጥና ከመደናገጥ ይልቅ የፖሊሲው አሉታዊና አዎንታዊ ጎን ምንድነው፣ ከመልካሙ ለመጠቀም ከመጥፎው ለመሸሽ ምን ማድረግ ይገባል የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ ለመልሱም በአግባቡ ስለ መዘጋጀት መጨነቅ አዋጭ ነው።
ከዚህ ባለፈ ገና በጠዋቱ ሃሳቡ ተግባራዊ በሆነበትና ውጤቱ ባልታየበት ሁኔታ መሸበር እንድንወድቅ ለሚፈልጉ መመቸት መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ነው። ይህ ማለት ግን ፖሊሲው ጫና የለውም ከፍ ሲልም መንገጫገጮችን አያስከትልም ማለት አይደለም። ይሁንና አስቀድሞ የተሸነፈ እንደሚባለው ከወዲሁ በፕሮፖጋንዳው ሰለባ መሆን ያልተፈለገ ዋጋን እንድንከፍል ሊያደርገን እንደሚችል ጠንቅቆ ሊገባን ይገባል፡፡
እዚህ ጋር ስለፖሊሲው እንቅልፍ አጥተን የጥፋት አቅሙን ብቻ ለማሳየት የሚታትሩት እነማን እንደሆኑ መገንዘብም ተገቢ ነው። የእነዚህ ግለሰቦች ፍላጎት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለያይቶ እንዲያስብና ተግባብቶ እንዳይኖር መሆኑን፣ ፍላጎታቸውም የሚመኙትን ስልጣን ለመቆናጠጥ የሕዝብ ማሰቢያ ላይ የበላይነትና የበታችነት ወላፈን በመዝራት ስሜት በማነሳሳት ንዴት ማስታጠቅና እንዳሻቸው ሕዝቡን እየዘረፉ ሀብት ማከማቸት መሆኑን ጠንቅቆ ሊረዳ ይገባል።
ከሁሉም ቀድሞ ውሳኔው ይዞት የተነሳው ትልቅ ራዕይና አላማ በቅጡ መረዳት ይኖርብናል። ችኮላ አደገኛ መሆኑን መገንዘብና የምንፈልገው ነገር ዛሬውኑ ካልተደረገልን ሙግት ማስወገድ የግድ ይለናል። መልካም ውጤቱን «ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ» ከሚል ልጓም አልባ ስሜታዊነት ወጥተን፣ ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አመለካከት ‹‹critical and constructive way of thinking››ን በማስቀደም የመነሻችን፣ የሂደታችንና የመዳረሻችን ምንነትና እንዴትነት በአግባቡ መረዳት ግድ ይላል።
ማንኛውም ትልም በተንጥል ጉዞ አይሳካም። የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚረጋገጠውም እንደ አንድ ነጋችን ታሳቢ በማድረግ በምንጽፈው ታሪክ፤ በምንወረውራት እያንዳንዷ ጠጠር ነው። እርስ በእርስ ትስስር፣ መተማመን፣ መግባባት ወንድማማችነት ከሁሉም በላይ የሀገር ባለቤትነት ስሜት ነው፡፡
ከተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ ሰዓት ሳንቆጥር፣ ድካማችንን ሳናስተዋል፣ ልዩነቶቻችን ለሀገር ልማት እንቅፋት ሳይሆን ካለፈው ታሪካችን ተምረን ለትውልድ የምወርሰው ስራ ለመሥራትና ለዚሁ የሚሆን መሠረት ለማስቀመጥ እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርብናል። ተመካክረንና ተደማምጠን ከሠራን፣ ተወያይተንና ተከራክረን ከተጓዝን፣ ተባብረንና ተጋግዘን፣ ተቻችለንና ተፈቃቅረን ወደፊት ከገሰገስን ኢትዮጵያን ከፈተና ወደ ልዕልና ከፍ ማድረግ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ይሆናል።
እስከዛሬ በመጣንበት መንገድ እየተባላን እየተናከስን በጎሳ እየተቧድንን ከተጓዝን ያው ጨለማ ውስጥ እንዳክራለን። ይህ እንዳይሆን ዙፋናዊ ጥማታቸውን ለማርካት ፀብን እየዘሩ ጥላቻን እያጎረሱ የሚኖሩ መንደርተኞች ልንታገላቸው ይገባል። ጨለማው እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው በመረዳት የእኩይ ተልዕኮአቸው ማስፈፀሚያ እንዳንሆን ማስተዋልና ጥንቃቄን መታጠቅም ይኖርብናል፡፡
መንግሥትም መሰል የፖሊሲ ለውጦችን ሲያደርግ አስቀድሞም ሆነ በተግበራ ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ በተለይም የሕዝብን ሥነ ልቦና የሚሰልቡ ፕሮፖጋንዳዎችን መከላከልና ፈጣንና በቂ መረጃን ተደራሽ ስለማድረግ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። ውሳኔን ተከትሎም ኢንቨስተሮች በስፋት እንዲገቡ ሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ለነገ መባል የለበትም፡፡
በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከሕዝብ ደኅንነትና ከሀገር ህልውና የሚቀድም የለም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ትልልቅ ትልም ማለምም ማቀድ ፈታኝ ነው። ይህ እንደመሆኑም መንግሥት የዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በሰላም የመኖር፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት በተጨባጭ ማረጋገጥ ግድ ይለዋል፡፡
ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ስለተፈለገ የሚመጣ አይደለም። ሰላምን በሰለጠነ መንገድ ወንበር ስቦ በሃሳብ የበላይነት የሚገኝ ነው። የጠመንጃ ቃታ በመሳብ የሚገኝ ሰላም የለም፤ ኖሮም አያውቅ። በዚህ መንገድ ሰላምን ለማምጣት የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጥረት ትርፉ ኪሳራ ነው። የኪሳራው ዓይነት ደግሞ በማይተካ የሰው ሕይወትን ላይ የቆመ ነው፡፡
ሰላም በመፈለግ ብቻ አትመጣም፤ በተግባር መተርጎምና ቁርጠኛ መሆን ትፈልጋለች። ይህ እንደመሆኑም እንደ ሕዝቡም በዚህ ወቅት ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ አቅም በሚሆን ሁናቴ ልዩነቶችን በመግራትና በማስተናገድ በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል፡፡
መንግሥትም ሰላምን ከማረጋገጥ ባሻገር ፖሊሲው ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እየተራመደ ስለመሆኑ በቅርብ ርቀት መከታተልና ለዚህም የሚሆን የማስፈጸም አቅም መገንባት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነም በውሳኔው ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚዘውሩት አደገኛ መሣሪያ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት የፖሊሲውን የትግበራ ሂደት አፈፃፀም በየጊዜው በመከታተል የተፈለገውን ውጤት አምጥቷል፣ አላመጣም፣ የሚለውን መገምገም ይኖርበታል። ከዚህም ከፍ ሲል ውጤቱ እየታየ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡
በተለይም ከሰላም እና ጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች ፈጣን እልባት መስጠት፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ በቋሚነት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግና ከውስጥ ፍላጎት አልፎም የውጭ ምንዛሬ ማስገባት የሚያስችሉ ዋና ዋና ምርቶችን በስፋት በሀገር ውስጥ ማምረት ብሎም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ታሳቢ ማድረግ ይገባል። በኢኮኖሚ የላቁ ሀገራት የከፍታቸው አብይ ምክንያት ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም መገንባታቸው ነው። ይህ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ለተቋማት ፈጠራና ሁለንተናዊ አቅም መጎልበት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ ይላል፡፡
መገናኛ ብዙሃንም ውሳኔውን ሁለንተናዊ ፋይዳ አብዛኛው ማህበረሰብ በቀላሉ ሊረዳው በሚችል መልኩ ማስረዳትና ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከፋይዳው ባሻገር በትግበራ ሂደት ሊያጋጥሙ በሚችሉ መንገጫገጮችና ከፍ ሲልም አደጋዎች ማስገንዘብ አለባቸው። በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ሕገወጦችን እንዲፋለም ማንቃትም እጅጉን ወሳኝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ሕዝብም በአሁን ወቅትም በተለይም ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች ምርት ያለ አግባብ በማከማቸትና እጥረት ያለ በማስመሰል የሚፈጥሩትን ኢኮኖሚያዊ አሻጥርና ምክንያት አልባ የዋጋ ንረት በማርገብ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል። ‹‹መንስኤ ሳይሆን መፍትሔ›› መሆን አለብን በሚል የፀና አቋም ተጠቃሚው ላልተፈለገ የዋጋ ንረት እንዳይጋለጥ ትልቅ አቅም መሆን አለበት፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም