
ጋምቤላ፦ በጋምቤላ ክልል በተከሰተ የዓይን በሽታ ወረርሽኝ በአራት ሳምታት ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮት ጋትዌች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የዓይን ወረርሽኙ ከሐምሌ መጀመሪያ ጀምሮ በክልሉ ናሬ ወረዳ የተከሰተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሽታው ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ተከስቷል።
እስካሁንም ከአንድ ሺህ 300 በላይ ሰዎች በበሽታው የተያዙ መሆኑን አስታውቀው፤ ይህ መረጃም በመንግሥት ሆስፒታሎች የተገኘ ሪፖርት እንጂ በግል ህክምና ጣቢያ ወይም በቤት ውስጥ ህክምና የተሰጡትን የማያካትት መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ወረርሽኝ መሰል በሽታ በዓይን በማይታዩ ቫይረስ ወይም ባክቴሪያ በሚባሉ ተዋሕሲያን የሚከሰት በሽታ ሊሆን የሚችል መሆኑን ገምተው፤ የበሽታውን ምንነት ለማጣራትም ናሙና በመሰብሰብ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዓይን መቅላት፣ የሚቆጠቁጥ የዓይን ሕመም፣ የዕይታ መቀነስ፣ የዓይን እብጠት፣ የማያቋርጥ ፈሳሽ ወይም ዕንባ እንዲሁም የዓይን አር መኖር የበሽታው ዋና ምልክቶች ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።
በበሽታው የቀጥታ እጅ ንክኪ፣ ከተያዘ ሰው በሚወጡ የዓይን ፈሳሾች የተነካኩ ጨርቃ ጨርቅና መነፀር እንዲሁም የጋራ የውሃ ባኞ ቤቶች መጠቀም ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶቹ መሆኑም አስረድተዋል።
በመሆኑም እጅን ከዓይንም ሆነ ከቀጥታ ንክኪ መታቀብ፣ በበሽታው የተያዘ ሰው ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን አለመጠቀምም በወረርሽኙ ላለመያዝ መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪ በየጊዜው የእጅ ንጽህናን በውሃና ሳሙና፣ በአልኮል ወይም ሳኒታይዘር በተገቢው በመጠበቅ በሽታውን አስቀድሞ መከላከል የሚቻል መሆኑን ገልፀዋል።
እንዲሁም በበሽታው የተያዘ ሰው በአቅራቢያ ወደ ጤና ተቋም በመገኘት ሕክምና ማግኘት ጀምሮ በተቻለ መጠን የዓይንና እጅ ንክክኪ አለማድረግ፣ የግል እቃዎች ለይቶ መጠቀም እንዲሁም የዓይን መነጽር መጠቀም እንዳለባቸው ኃላፊው ተናግረዋል።
በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የአካባቢ ንጽህና በተጓደለባቸው እና በርካታ ቁጥር ነዋሪዎች ያሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ስለበሽታው ግንዛቤ የመስጠት ብሎም የቅኝትና ምላሽ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አቶ ሮት ገልፀዋል።
ይህ በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው የዓይን በሽታ ከፍተኛ የመተላለፍ ዕድል ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም