
ተማሪዎች ፈተና ጨርሰው ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ክረምት ልጆች የእረፍት ጊዜያቸውን በቤታቸው አለያም ወደሌላ አካባቢዎች በመሄድ ከዘመድ አዝማድ ጋር፣ ከሚወዷቸው ጓደኞቻቸው እና የዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር የሚያሳልፉበት ወቅት ነው።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሄዱ ወጣቶችም የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ጊዜ ነው።
በእውቀት የዳበረና በሥነልቦናው የጠነከረ ትውልድ መፍጠር ለነገ የማይባል ነው። ለዚህም ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው ሚና አላቸው። በተለይም በክረምት ወቅት ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህር ገበታ ስለሚርቁ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው እደሚገባ የልጆች ሥነልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ለመሆኑ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ፍሬያማ በሆነ መንገድ እንዲያሳልፉ ወላጆችና አሳዳጊዎች እንዴት ሊደግፏቸው ይገባል?
በአዲስ አበባ ከተማ የፊት አውራሪ አባይነህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ደረጀ ቶላ እንደሚናገሩት፤ ተማሪዎች በክረምቱ የሚኖራቸውን የእረፍት ጊዜ የፈጠራ ክህሎቶቻቸውን ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያሳልፉ ወላጆች ድጋፍ ማድረግ አለባቸው።
ተማሪዎች ክረምቱን በቴክኖሎጂ፣ በኪነጥበብ፣ በስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች እንደየ እድሜያቸውና ፍላጎቶቻቸው እንዲሳተፉ በማድረግ ችሎታቸውን እዲያዳብሩ መርዳት ጠቃሚ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደሥራው ዓለም በሚገቡበት ወቅት የራሳቸውን ውስጣዊ ክህሎት በመጠቀም ሥራ በመፍጠር ሀገራቸውን ማገልገል የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲፈጠር እንደሚያግዛቸው ይገልጻሉ።
እንደ መምህር ደረጀ ገለጻ፤ ከሁለንተናዊ እድገት ጋር ተያይዞ ተማሪዎች እንዴት በራሳቸው መተማመንና ራሳቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው፤ ክህሎቶቻቸውን አውጥጠው መጠቀም ስለሚችሉበት ሁኔታ እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ተግባቦት ምን መምሰል እንዳለበት ሥልጠናዎችን ቢወስዱ በብዙ ያተርፋሉ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚዘዋወሩ ይዘቶች ታዳጊዎች ለአቻ ግፊት እንዲዳረጉ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውን አንስተው፤ ይዘቶቹ ተማሪዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር እንዲያወዳድሩና ያዩትን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ እንዲነሳሱ ያደርጋሉ ይላሉ።
ስለዚህ ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ላይ ክፍተት እየታየ በመሆኑ ወላጆች በአግባቡ እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ማሳየት መቻል አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ።
ተማሪ ሳሮን ቸርነት በደጃዝማች ባልቻ አባነብሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናት።
የክረምት ወቅት ተማሪዎች በቤታቸው የሚያሳልፉበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት፣ ስለሀገራቸው ታሪክ በማንበብና የክረምት ትምህርት በመማር ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ትናገራለች።
እንደ ተማሪ ሳሮን ገለጻ፤ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ ማሳለፋቸው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ያላቸው ዝግጁነት የተሻለ እንዲሆን ያግዛቸዋል። እንዲሁም በየትኛው ሰዓታቸው ማንበብ፣ መጫወትና ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚችሉ ለይቶ በማወቅ ጊዜያቸውን በእቅድ መጠቀምን እንዲለምዱም ያደርጋቸዋል።
ታዳጊዎች የቤተሰብ፣ የመምህራን አለፍ ሲልም የሀገር ኃላፊነት እንዳለባቸው የምትገልጸው ተማሪ ሳሮን፤ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሰፊውን የእረፍት ጊዜያቸውን ቤት በሚያሳልፉበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወላጆቻቸውን በማክበርና ምክራቸውን በመቀበል ራሳቸውን ለማሳደግ ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸው ትገልጻለች።
አቶ መንግሥቴ አራጋው የተማሪ ልዑል መንግሥቴ ወላጅ አባት ናቸው። ልጃቸው ልዑል የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከመኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት ባለ ሜዳ ላይ እግር ኳስ መጫወትን ያዘወትራል። አሁን ላይም በታዳጊ ፕሮጀክት ታቅፎ እዚሁ ሜዳ ላይ ልምምድ እያደረገ እንደሚገኝ ወላጅ አባቱ ይገልጻሉ።
የክረምት ጊዜውን አልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ በማንበብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመሥራት በአካሉና በሥነ ልቦናው መጠንከሩ ለነገ ሕይወቱ እጅጉን ጠቃሚ መሆኑን የሚያነሱት አቶ መንግሥቴ፤ ልጃቸው ያለውን ክህሎት እንዲያዳብር የሚፈልገውን ማንኛውንም አይነት ነገር በማሟላት ድጋፍ እያደረጉለት እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ልጆች የኪነጥበብ፣ የስፖርት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሌሎችም የተለያዩ ክህሎቶች ያሏቸው በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ቀርበው በማነጋገርና ፍላጎታቸውን በመረዳት በጎ ክህሎቶቻቸውን እንዲያዳብሩ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ሲሉ መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ነፃነት አለሙ እና ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም