ሴቶች እንደ አልማዝ እንዲያበሩ

እየሩሳሌም ሙሉዘውድ የአስራ ሰባት ዓመት ታዳጊ ናት። በዘንድሮው ዓመት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስዳለች። እናቷ ናቸው ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ወደተሰኘው ወላጅ አልባ ህፃናትና መበለቶች መርጃ ድርጅት ያመጧት። እናቷ ወደዚህ ድርጅት ያመጧት ከባለቤታቸው ጋር በመለያየታቸው ብቻቸውን ማሳደግ ስላልቻሉ ነበር።

እየሩሳሌም ወደ ላይፍ ሴንተር ከመጣች ወዲህ በርካታ አገልግሎቶችን በነፃ ማግኘት ችላለች። ትምህርቷን በሚገባ እየተከታተለችም ነው። ለትምህርቷ አጋዥ የሆኑ መፅሃፍቶችን ከድርጅቱ ታገኛለች። ቤተ መፃህፍት እንደልቧ ትጠቀማለች። በየዓመቱ የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ ይደረግላታል። በመምህራን የጥናት አገልግሎት ታገኛለች። ዓመታዊ የተማሪዎች የመዝናኛና የጉዞ ፕሮግራሞች ላይም ትገኛለች።

ከዚህ ባለፈ እየሩሳሌም ድርጅቱ በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው የልጃገረዶች የሕይወት ልምድና ማይንድ ሴት ሥልጠናዎች ላይ ትሳተፋለች። በተለይ በአፍላ የእድሜ ክልል ውስጥ እንዴት አመዛዝኖ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንደሚቻል በቅርቡ ከወሰደችው ሥልጠና መገንዘብ ችላለች። በሕይወት ውስጥ ፈተናዎችን እንዴት ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚቻልም ነው ከዚህ ሥልጠና የተረዳችው። በቀጣይም ጥሩ ውጤት አምጥታ ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባም ተስፋ ሰንቃለች።

ወይዘሮ ሙሉ ግርማይ የላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ያዘጋጀው ሥልጠና እድሜያቸው ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ለሆኑ ልጃገረዶች ነው። ሥልጠናውን ለማዘጋጀት የተፈለገውም በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በርካታ ውጣውረዶችን ስለሚያልፉና በሴትነታቸው የሚገጥሟቸውን ልዩ ልዩ ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ለዚያም ነው ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኘው። ሴቶች በየእድሜ ደረጃቸው ማወቅ የሚገባቸውን ነገር እያወቁ እንዲሄዱ፣ በሳልና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲወስኑ ለማድረግም ነው ሥልጠናዎችን በየጊዜው የሚያመቻቸው።

እስካሁን በተሰጠው ሥልጠና ሴቶቹ በብዙ መልኩ ተቀይረዋል። ነገር ግን ሥልጠና ብቻውን በቂ አይደለም። ሥልጠናው ተከታታይና ወቅታዊ መሆን ይጠበቅበታል። የአሁኑ ሥልጠና መሪ ቃልም ‹‹shine out›› የሚል ነው። ይህ መሪ ቃል የተመረጠበት ምክንያት ሴቶች እንደሴቶች የሚያልፉባቸው በርካታ ችግሮች ስላለ ነው። ነገር ግን ሴቶች ችግር እንደ አልማዝ እንዲያጠነክራቸው፣ ተደብቀው እንዳይቀሩ፣ እንዳይጎዱ፣ ህብረተሰቡ እንዳይደብቃቸው፣ አጉል ባህል ወደኋላ እንዳያስቀራቸውና ተሸንፈው እንዳይቀሩ ነው የሚፈለገው።

ከአፈር ወጥተው መሰናክሎች ሳያቆሟቸው እንደ አልማዝ እንዲያበሩ፣ ህብረተሰቡን እንዲጠቅሙ፣ ለራሳቸው እንዲቆሙ፣ ጠንካራ ሴቶች እንዲሆኑ አሁን የተዘጋጀው ሥልጠና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች ቢዳረስ መልካም ነው። ለጊዜው ግን ላይፍ ሴንተር የሚረዳቸው ሴቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል።

ወይዘሮ ሙሉ እንደሚናገሩት፣ ሥልጠናው ዋናው ዓላማ ልጃገረዶች በአእምሮና በአስተሳሰብ እንዲያድጉ ለማስቻል ነው። ሴቶች በሕይወት የሚያልፉባቸው መሰናክሎች እንደመኖራቸው፣ በእኩል የማይታዩ እንደመሆናቸውና ካሉባቸው በርካታ ተፅእኖዎች አንፃር ጠቃሚ ዜጋዎች እንዲሆኑና ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ ማስቻል የሥልጠናው ዓላማ ነው። አዕምሯቸውን የማሳደግ፣ ውሳኔያቸውን እንዲያስተካክሉ ለማድረግም ነው ሥልጠናው የተዘጋጀው።

ልጃገረዶች በዚህ እድሜያቸው መሰናክሎች ሳያስቀሯቸው ለራሳቸው እንደ አልማዝ በርተው ሌሎች አቻዎቻቸውም ምሳሌ እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው። ሴቶቹ ወድቀው እንዲቀሩና ከትምህርት ቤት እንዲያቋርጡ አይፈለግም። የማያስፈልግ ግንኙነት ውስጥ ገብተው ከሕይወታቸው ወደ ኋላ እንዲቀሩ አያስፈልግም። ስለዚህ መጠንከር አለባቸው። ይህ ደግሞ የሚመጣው በሥልጠና ነው።

በዚህ ሥልጠና 50 ልጃገረዶች ተሳትፈዋል። ልጃገረዶቹ በሕይወታቸው እንዲያውቁ፣ እንዲማሩና እንዲበስሉ ስለሚፈለግ ከዚህ ሥልጠና በኋላ ውሳኔያቸው ጤናማ እንዲሆን ነው የሚጠበቀው። አልባሌ ቦታ ላይና ጥፋት ላይ እንዳይገኙ፣ ለሀገር ሸክም እንዳይሆኑ፣ ተምረው ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ጀግናና መሪ ሴቶች እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው። ይህ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ባይሆንም ቀስ በቀስ ግን ይህንን እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው።

ፓስተር ጆይ ሜጋኒዝ ደግሞ ተቀማጭነቱን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የሆራይዘን ኢንተርናሽናል በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። ድርጅታቸው ወላጅ አልባ ህፃናት ላይ የሚሠራ ሲሆን ከላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ይሠራል። ላለፉት አስር ዓመታትም ከላይፍ ሴንተር ጋር ሲሠራ ቆይቷል። በዚሁ ትብብር መሠረትም ነው ለልጃገረዶች ሥልጠና ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው።

ልጃገረዶች በየቀኑ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው በጨለማ ውስጥ እንዲያንፀባርቁ ነው የሕይወት ልምድ ሥልጠና የተሰጣቸው። ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ሥልጠናዎች ሰጥቷል። የሥልጠናው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሴቶች ችግሮችን ተቋቁመው እንዴት ወደ ስኬት መውጣት እንደሚችሉ ነው። በአካል፣ በአዕምሮና በመንፈስ የጠንራና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችል ነው። በሥልጠናውም ሴቶች የተለያዩ የሕይወት ልምዶችንና የበሰሉ ውሳኔ ሰጪነትን ተምረዋል። ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ድርጅቱ ከላይፍ ሴንተር ጋር ሆኖ እገዛ እያደረገ ይገኛል። ወደፊትም ይህን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You