ስግብግብ ነጋዴዎቻችን ልብ የሚገዙት መቼ ይ ሆን ?

የኑሮ ወድነቱ አንዱ የታዳጊ ሀገራት ፈተና ነው። ኢትዮጵያም የዚሁ ችግር ሰለባ ነች። ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም ሲዳከም ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የዘርፉ ባለሙያዎቸ ይገልጻሉ።

ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያቶች ከሚባሉት መካከል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የገበያ ምኅዳር ብልሽት ወይም ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት መብዛት በቀዳሚነት የሚነሱ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የምግብ ነክ ሸቀጦች፣ በተለይ የእህል ዋጋ መናር ነው።

ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንደ ሀገር ፈተና እየሆኑ ካሉ ችግሮች አንዱ ስግብግብ ነጋዴዎች በአቋራጭ ለማትረፍ የሚያደርጉት ሩጫ ነው። ሰሞኑን መንግሥት ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ከዶላር መጨመር ጋር ተያይዞ በመርካቶና በሌሎች ዋና ዋና የገበያ ስፍራዎች የሸቀጦችን ዋጋ ለማናርና በአቋራጭ ለመበልጸግ እየተደረጉ ያሉ ሩጫዎች ማሳያዎች ናቸው።

ይህንኑ ተከትሎ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፤ ምርትን በደበቁና ባከማቹ በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓቱን ተከትሎ የተደረገውን የዶላር ዋጋ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር ጥረት ባደረጉ 9 ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መውሰዱን አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።

የንግድ ቢሮው እየወሰደ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ቢሆንም ድርጊቱ ግን አስተዛዛቢ ነው። መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ማድረጉን ባስታወቀበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሸቀጦችን በመደበቅ፤ በማከማቸትና ከልካቸው በላይ ዋጋ በመቆለል የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር እና ኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ለማድረግ ሲሞክሩ ታይተዋል። እነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ምንም ሰብዓዊ ርህራሄ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ ከራሳቸው ሆድና የንዋይ ጥማት ውጭ ለሀገርም ሆነ ለወገን የሚጨነቅ ህሊና እንደሌላቸው በገሃድ ታይቷል።

ሀገር የሚጸናው በዜጎች ባለቤትነትና ተሳትፎ ነው። ስለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች ባሉበትና በማንኛውም ጉዳይ ላይ በባለቤትነት የሚሳተፉ ዜጎች በበዙበት ሀገር ላይ ልማት ይስፋፋል፤ ሰላም ይሰፍናል፤ ብልጽግና ያብባል። በተቃራኒው ስግብግቦች በበዙ ቁጥር ሀገር ሕገ ወጥነት ይስፋፋል፤ ወንጀል ይበራከታል። ማህበራዊ ቀውስ ይሰፍናል። ስለዚህም ስግብግቦችን ማጋለጥና ማውገዝ እንዲሁም ለሕግ አሳልፎ መስጠት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት።

ማንኛውም ወንጀልና ሕገ ወጥ ድርጊት ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም። ሕዝብ የማይሰማው፤ ሕዝብ የማያየው ሁኔታና ድርጊት የለም። ለዚህም ነው ሕዝብ ያመነበትና የተሳተፈበት ነገር ሁሉ ውጤት የሚያመጣው። በተለይም ሕዝብና መንግሥት እጅና ጓንት ሆነው የተሳተፉባቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ውጤት ማምጣታቸው፤ ፍሬ ማፍራታቸው አይቀርም።

በተለይም በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ከተገቢው በላይ የሚያጦዙና ከህብረተሰቡ ችግር ማትረፍ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥና ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ የሚቻለው ሕዝብ ሲተባበር ብቻ ነው። በህብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሰዓታት ልዩነት የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ህብረተሰቡን ለምሬት መዳረጋቸው የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ቢሆንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከሕዝብ ዓይን ሊያመልጡ አይችሉም። ስለሆነም ለእነዚህ ስግብግቦች ጊዜ መስጠት የበለጠ ዋጋ ያስከፍላልና ሕዝቡ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል።

ሕገወጦች ነፍስ የሚዘሩት ምንቸገረኝነት ሲሰፍን ነው። ሀገር የዜጎች ናትና ሕገወጥነትን አይቶ እንዳለየ ማለፍ ዜግነትን አሳልፎ መስጠትና ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ማድረግ መፍቀድ መሆኑም መረዳት ይገባል። በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎችም ቢሆኑ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚመጡ ጥቆማዎችን ዋጋ በመስጠት አጥፊዎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

በአጠቃላይ በምንቸገረኝነት የሚታለፉና የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ተደርገው የሚወሰዱ ውሳኔዎች በመጨረሻ የሚጎዱት ሕዝብ ነው። ስለዚህም ሕዝቡ በይገባኛል ስሜት በመንቀሳቀሰ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን ሊታገልና መስመር ሊያሲዛቸው ይገባል።

መንግሥት ይፋ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት ሀገሪቱ ለገባችበት የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ሁነኛ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ እሙን ቢሆንም ከወዲሁ ማሻሻያውን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚሯሯጡ ስግብግብ ነጋዴዎችን አደብ ማሳያዝ ግን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በእነዚህ ነጋዴዎች የተነሳ ህብረተሰቡ የበለጠ በኑሮ ውድነቱ ወገቡ መጉበጥ የለበትም።

የእነዚህ ነጋዴዎች ስግብግብነት ታክሎበት የዋጋ ግሽበት አሁንም ትልቁ የሀገሪቱ ፈተና ነው። አሁን ያለው የዋጋ ንረት አምናና ካቻምና ከነበረበት የ33 በመቶ ደረጃ ወደ 23ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ቢልም አሁንም የኑሮ ውድነቱን በማባባስ ረገድ ፈተና ሆኖ ዘልቋል። በተለይም የምግብ ዋጋ ንረት 27 በመቶ መሆኑ ችግሩ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ ነው።

ይህንን ችግር ለመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ጥረት መደረጉ፤ የገንዘብ ዝውውሩን ለመቀነስ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲ በጥብቅ መተግበሩና ነዳጅን በመሳሰሉ ቀጥተኛ የኑሮ ውድነትን በሚያስከትሉ ሸቀጦች ላይ ድጎማ መደረጉ የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለበት እንዳይጨምር አስተዋጽኦ ያደረጉ ቢሆንም ካለው የህብረተሰባችን የመግዛት አቅም አንጻር በቀጣይ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ የዋጋ ግሽበቱ ከተቻለ እንዲቀንስ ካልሆነ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም በንግድ ሥርዓቱ ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም የሚተዳደረው በግብርና ነው። ኢትዮጵያም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሚታረስ የእርሻ መሬትና በግብርና ምርት ቀዳሚ ሀገር ናት። ሆኖም በተቃራኒው የግብርና ምርቶችና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ካለባቸውና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው ሀገራትም አንዷ ናት። በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በተለያዩ ብልሹ አሰራሮች ምክንያት በየቀኑ እየጨመረ የሚሄደውም የሸቀጦች ዋጋ መናር በዜጋው ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመፍጠር ሕዝቡን ለምሬት እየዳረገው ነው።

በተለይም ህብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች እና በቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪው አሳሳቢ ሆኗል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው። ትራንስፖርት፣ የትምህር ቤት ክፍያና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት የሕዝቡን ኑሮ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው ነው።

በየቀኑና በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ በተለይም ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ኑሮ እንደምርጊት እንዲከብደው ምክንያት ሆኗል። መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ከገበያ ጠፍተዋል›› ፤ ‹‹ዋጋ ጨምሯል›› የሚሉት አገላለጾች ህብረተሰቡን በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር እያደረጉት ነው። ለዚህ ደግሞ የስግብግብ ነጋዴዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበቱ 23 በመቶ አካባቢ ነው። በአሃዝ የተቀመጠው የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ምንድነው ብሎ በደንብ አይቶ መፍትሔ መስጠቱ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ነው። የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አሃዝ ነው። በሠለጠነው ዓለም የዋጋ ግሽበት ከሁለት በመቶ ብዙም የዘለለ አይደለም። በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ደግሞ ከአራት እስከ ስድስት በመቶ እንዳይበልጥ ጥረት ይደረጋል። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያም በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ አመላካች ነው።

ለሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት የምርት እጥረት ብቻ የሚፈጥረው አይደለም። የዘመናዊ ግብይት ዕጦት እና የደላሎችና ሕገወጥ ነጋዴዎች መበራከት ለችግሩ መባባስ መንስዔ ናቸው። የኢትዮጵያ ገበያ 200 እና 300 በመቶ ትርፍ የሚያዝበት ነው። ይህ በዓለም ላይ የለም። ይኼ አካሄድም በፖሊሲ ጭምር ታግዞ ሊስተካከል ይገባል።

የሀገሪቷ ገበያ ሥርዓት ዘመናዊ ባለመሆኑ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል። ሰሞኑን መንግሥት ወደ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓትም ለዚህ ሁነኛ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በሀገራችን ውስብስብና ኋላ ቀር የሆነ፣ የገበያ ሥርጭት ነው ያለው። አንዳንድ ቦታ እንዲያውም በሞኖፖል የተያዘ ይመስላል። በተለይ ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ገበያው በሞኖፖል ተይዟል። ስለዚህ ይህንን በመፍታት አዳዲስ ኩባንያዎችን በማስገባት የውድድር ሜዳውን በማስፋት ረገድ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል። ዘርፉን ለሚቀላቀሉ የሀገር ውስጥና የውጭ አዳዲስ ኩባንያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ከተደረገ በአንድ ቀን አዳር ዋጋ የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ራሳቸውን ሚሊየነር ለማድረግ የሚጥሩት ስግብግብ ነጋዴዎች ከእንግዲህ ወዲያ ቦታ አይኖራቸውም።

ይህ አካሄድም በውድድር ዋጋ የሚቀንስበትን መንገድ በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ያደርጋል። ቀልጣፋ የሆነ አቅርቦትና ውድድር ከተፈጠረ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ይቻላል። አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ሁሉም ነገር በገበያ እንዲወሰን በር ስለከፈተ በጥቂት ነጋዴዎች ተይዘው የቆዩ ዘርፎችም በርካታ ተዋናዮች እንዲኖሩ በማድረግ ሸማቹ በርካታ አማራጮች እንዲኖሩት ያስችላል።

ግሽበቱን ለመቀነስ በቂ ምርት ሊኖር ይገባል ከተባለ ደግሞ ሸማቾች የሚጠቀሙባቸው ከሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኝ ምርት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ከፍ ማድረግ። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ግሽበቱ የሚታይ ከሆነ በቂ ምርት እንዳይኖር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላልና በቂ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ እያስተካከሉ መሄድ። አሁን ያለው አሠራር እየፈጠረ ያለው የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚቀረፀው ፖሊሲ የውጭ ኩባንያዎችንም በማስገባት እንዲረጋጋ ማድረግንም ይጠይቃል። የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ሥርዓቱም ለዚህ ምቹ ምህዳር ይፈጥራል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You