ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካ መንግስት በኢራን ላይ የጣለውን ማዕቀብ እና በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት እየተባባሰ ቢመጣም ኢራናውያን ‹‹የአረንጓዴ እንቅስቃሴን›› አስረኛ ዓመት ለማክበር ተዘጋጅተዋል። ከአስር ዓመት በፊት በነበረው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ፕሬዚዳንት መሀመድ አህመዲን ነጃድ አሸንፍያለው በማለታቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። የፕሬዚዳንቱ ተፎካካሪ የነበሩት ሆሲን ሞአሲቭ እና መሀዲ ካሮቢ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም በማለታቸው ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።
አሁን ከአስር ዓመት በኋላ አብዛኛው ሰው እንደ ቀድሞው ‹‹አረንጓዴ እንቅስቃሴ›› በኢራን ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ናቸው። የአገሪቱ ምሁራን በኢራን በአሁን ወቅት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የተዳከሙ በመሆናቸው ምክንያት ህዝባዊ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል የሚል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ሌሎች ደግሞ ኢራን በአሁን ወቅት ያን ያክል ተቃውሞ የሚያሰጋት አይደለችም ብለው ይከራከራሉ። የትኛው እውነት እንደሆነ አይታወቅም። በቀጣይ ኢራን ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ታስተናግዳለች ወይንም የኢስላሚክ ሪፐብሊክ አስተዳደር የውጭ ግፊቶችን ተቋቁሞ ይቀጥላል የሚሉት የሚታዩ ይሆናል።
በረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥ ኢራን ከመካከለኛው ምስራቅ የበለጠ የተለያዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን አስተናግዳለች። እአአ 1979 ከኢራናውያን የለውጥ እንቅስቃሴ በኋላ የኢራን ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት መንፈስ ውስጥ ይገኛሉ። ይህም እንቅስቃሴ ከአስር ዓመት በፊት ተፈጥሮ ከነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በኢራን የሚገኙ ወጣቶች አብዛኛዎቹ የተማሩ ናቸው ከ81 ሚሊዮን ውስጥ 10 ሚሊዮኑ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን አራት ሚሊዮን ወጣቶች ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተማሩ ይገኛሉ። በኢራን ቀደም ብሎም ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ ሀሳብ የሚንሸራሸርበት ቦታ ነው። በዚህም ተማሪዎች በተቃውሞዎች ላይ ከሰራተኛውና ከነጋዴው ጎን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ናቸው።
የኢራን ህዝቦች ከሌሎች አለም አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸው። 64 በመቶ የኢራን ህዝቦች ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። በአገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥር 110 በመቶ ደርሷል። ይህም የሆነው አንዳንድ ኢራናዊ ዜጋ ከአንድ በላይ ስልክ ስላለው ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ሁሉም የኢራን ዜጎች አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ባለው ኢስላሚክ ሪፐብሊክ እምነት እያጡ ነው። በተለይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በአግባቡ እየመራ ባለመሆኑ ነው። አብዛኛው ህዝብ ከነጭራሹ በአስተዳደሩ ላይ ምንም አይነት ተስፋ የለውም በዚህም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው። አሁን አገሪቱን እየመሩ የሚገኙት ሀሰን ሮሀኒ ዘመናዊ መሪ ቢመስሉም በምርጫ ወቅት ቃል የገቡትን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ነፃነትን እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጡ አልቻሉም።
የአገሪቱ አስተዳደር ኢኮኖሚውን በአግባቡ መምራት ያቃተው ሲሆን ባለስልጣናቱ በሙስና የተዘፈቁ ናቸው። በተጨማሪም ፖለቲካውና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖዎች በመኖራቸው ኢራናውያን ከዚህ በኋላ አስተዳደሩ ካልተለወጠ መሰረታዊ የሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚል እምነት አሳድረዋል። በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እየተባባሱ መምጣት የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ስልጣኑን ለማቆየት ከፍተኛ ትግል ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
በዚህ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ኢራን ሌላ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደምታስተናግድ ነው። ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ላይ በአገሪቱ ተቃውሞ ተከስቶ የነበረ ሲሆን በሁሉም ቦታዎች ላይ ተዳርሶ እንዲቆም ተደርጓል። አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ በማስተናገዷ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መነጣጠሎችን ፈጥሮ ነበር። በተለይ ደግሞ በከተማውና በገጠሩ ማህበረሰብ ውስጥ መለያየቶች ተከስተዋል። ነገር ግን እንደ አየር ትንበያና መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህዝባዊ ተቃውሞ መቼ እንደሚከሰትና ምን ያክል ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል መገመት አይቻልም። ነገር ግን የሚፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በአሁኑ አስተዳደር ላይ የሚፈጥር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
አሜሪካዊው ሶሲዮሎጂስት ጀምስ ዲፍሮንዞ ፅንሰ ሃሳብ ላይ ተመርኩዞ እንዳለው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ለውጥ አምጪ የሚሆኑበት አምስት አይነት መንገዶች ሲከተሉ። እነሱም የህዝብ ብስጭት፣ ተቃዋሚ ምሁራን፣ አንድነት ያለው ተነሳሽነት፣ ፖለቲካዊ ቀውስ እና አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ናቸው። የተወሰኑት በአሁኑ ወቅት በኢራን ውስጥ የተከሰቱ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ገና አልተፈጠሩም።
ምንም እንኳን በቴክኒካዊ ደረጃው ላይ ብዙ ሕዝባዊ አለመረጋጋት ቢታይም ይህ ስሜት “አንድነት” ማለት አይደለም። የኢስላሚክ ሪፐብሊክ የኢራን ህብረተሰብን በተሳካ ሁኔታ እየተከተለ የሚገኝ እና በማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። በአብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች በሀሳብ የተከፋፈሉ በመሆኑ በሀገሪቱ ውስጥ ማህበራዊ መሠረት የላቸውም። የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን መንግስት የሚሰጠውን መረጃን የማፈን ሁኔታ በመስበር የተዛባ መረጃን በማሰራጨት እና የመንግስት ተፅዕኖ የሚያሳዩ መረጃዎች እያወጡ ይገኛሉ።
በተመሳሳይም በአስተዳደሩ አካል ውስጥ አንዳንድ አለመግባባቶች ቢኖሩም ሁሉም ለእስላማዊ ሪፑብሊክ ደህንነት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። እንደዚሁም የአገዛዙን ስርዓት ለመጠገን አፋጣኝ እርምጃ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይስማማሉ። ኢስላሚክ ሪፐብሊክ በመሳሪያና በሰው ሀይል የተደራጀ እንዲሁም ለሪፐብሊኩ ታማኝ የሆነ ወታደራዊ ሀይል ማቋቋም ይፈልጋሉ። እነዚህ ወታሮች በአግባቡ የሰለጠኑ በማድረግ ማንኛውንም ህዝባዊ ተቃውሞ የመቀልበስ ግዳጅ ይሰጣቸዋል።
በተመሳሳይም የአሜሪካ፣ ሳዑዲና እስራኤል ግፊት እየጨመረ ቢሆንም አለም አቀፋዊው ግፊት በኢራን ውስጥ ለሚፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ አስፈላጊ አይደለም። ሩስያና ቻይና ኢስላሚክ ሪፐብሊክ ከሚመጣበት ተቃውሞ እንዲተርፍ ለማድረግ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። በተመሳሳይ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሄዝቦላና በመካለኛው ምስራቅ የሚገኘው የሺሀ ወታደራዊ ቡድን ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አላቸው።
አብዛኛዎቹ ኢራናውያን የሚፈጠረው ሁኔታ ከወዲሁ በመገንዘብ ወደ ጎረቤት አገራት ለመሰደድ እየተዘጋጁ ናቸው። በህጋዊ መንገድ ከአገሪቱ ለመውጣት የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ይህ ቁጥር ባለስልጣናቱ ካወጡት መረጃ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በቅርብ በተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 30 በመቶ የኢራን ዜጎች በአገራቸው ከመኖር ይልቅ ሌሎች አገራት መኖርን ይመርጣሉ። ሌሎቹ የኢራን ዜጎች የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ በማድረግ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። አብዛኛዎቹ የኢራን ዜጎች በዚህ ጉዳይ ላይ ያወራሉ። ይህ እንቅስቃሴ እአአ 2003 ኢራቅ የአሜሪካን ወታደር ‹‹የነፃነት አጋዥ ሀይል›› ብለው ተቀብለው የተፈጠረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
ጦርነት ማካሄድ ተወደደም ተጠላም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት አለው። የኢራን ገጣሚ የሆነው መሀዲ አክሀቫን እአአ 1953 በብሀቪ አስተዳደር ወቅት ሲ አይ ኤ ድጋፍ ያደረገበት መፈንቅለ መንግስት በተካሄደበት ጊዜ ‹‹ካቪህ በቦታው መገኘት ነበረበት። አሌክሳንደር መኖር ነበረበት›› የሚል አንድምታ ያለው ግጥም ፅፎ ነበር። ካቪህ የኢራናውያን ጀግና ሲሆን አገሪቱን ከውጭ ወራሪዎች ነፃ ያደረገ ሰው ነው። አሌክሳንደር ደግሞ የሜሴዶን መሪ የነበረ ሲሆን ከሁለት ሺ 300 ዓመት በፊት የፕርሻን አቻሚንድ ስርወ መንግስትን ያስወገደ መሪ ነበር።
ልክ እንደ ፀሃፊው ነጥቡን ያነበበ ሰው ኬቭህ ተመልሶ እንደማይመጣ ያውቃል። ነገር ግን የኢራን ህዝብ እራሱን ነፃ ለማድረግ ሲሞክሩ የውጭ ወራሪ ቢመጣ እንደ አሌክሳንደር ኢስላሚክ ሪፑብሊክን የሚያድን ሰው መምጣት አለበት የሚል እምነት እንዲያድርበት ነው። ይህ ተስፋ መቼም የሚፈጠር ነገር አደለም። የአሜሪካ ጦር ሀይልም ኢራንን የመውረር ፍላጎት ያለው አይመስልም። በቀጣይ ግን አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ፍንጮች እየታዩ ነው። በዚህም የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ስልጣኑን ሊያጣ ይችላል። በአሁኑ ወቅት ኢራን በፖለቲካና በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ እየማቀቀች ትገኛለች። የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ወታደሮች ስልጣኑን ለማቆየት ትግል ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
መርድ ክፍሉ