አዲስ አበባ፡- ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር በብድር የተገኘው 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሪፎርም ሥራዎችን ለመደገፍ እንደሚውል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 3ኛ አመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ አጽድቋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር በብድር የተገኘው 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለመደገፍ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥትን የ2017 በጀት በቀጥታ ለመደገፍ እንደሚውል ገልጸዋል።
ተጠሪ ሚኒስትሩ የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከለውጡ በኋላ ገቢራዊ የሆነው የመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መልካም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም በአማካይ 6 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑንም ጠቁመው፣ በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንቅስቃሴ የማክሮ ስብራቶችን ለመጠገን እንዲሁም በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በተለይም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና የመዋቅር ማስተካከያ ለማምጣት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል።
ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር መልካም ውጤት ያስመዘገበውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለመደገፍ፣ ለመጀመሪያው ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚውል አንድ ቢሊዮን ዶላር ርዳታና 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመስጠት በመስማማቱ ከማኅበሩ ጋር የገንዘብ ድጋፍና የብድር ሥምምነት መፈረሙን የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
500 ሚሊዮን ዶላር ብድሩ ከወለድ ነፃ፤ ባንኩ በሚወስነው መሠረት ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድር ገንዘብ ላይ በዓመት እስከ 0 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት የሚችል፤ ባንኩ የብድሩን ገንዘብ በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0 ነጥብ 75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት እንዲሁም የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን አስረድተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የብድር ስምምነቱን አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ያገኘውን ድጋፍና ብድር የያዘ ተጨማሪ በጀት በቅርቡ ለምክር ቤቱ አቅርቦ እንደሚያስጸድቅ ጠቁመዋል።
ተጨማሪ በጀቱ ለዝቅተኛ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች ለሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም ለነዳጅ፣ ለዘይት፣ ለማዳበሪያ እና መድኃኒት ድጎማ የሚውል መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱም በብድር ስምምነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ የቀረበው አዋጅ 1345/2016 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 /2016 ዓ.ም