
በጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሰሞኑን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የሟቾች ቁጥር 226 ደርሷል፡፡ አሰቃቂውን አደጋ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የቆየ ብሔራዊ ኀዘን ማወጁም ይታወሳል፡፡
ከሰኔ እስከ መስከረም ወራት ድረስ እጅግ በጣም የከፋ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የውሃ ሙላትን ሊያስከትል የሚችል ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ትንበያ እንደነበር የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን መረጃ ያሳያል::
የዘርፉ ባለሙያዎች ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች በጥናት መለየትና ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ይላሉ:: ለረጅም ዓመታት እንዲህ አይነት አደጋ ተሰምቶ ባይታወቅም የሁኔታዎች መለዋወጥ ክስተቱን ተደጋጋሚ እንዳያደርገው ቅድመ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ያሳስባሉ::
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በየአካባቢው ከፍተኛ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ የወንዝ ሙላትና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የተተነበየው ነገር እየተከሰተ ነው::
በተዳፋት አካባቢዎችና በወንዞች ዳርቻ የሚገኝ ማህበረሰብ ትልቅ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ በየደረጃው የሚገኙ በአስተባባሪ ኮሚቴዎች ተጋላጭ አካባቢዎችን ለይተው እንዲሠሩ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተከናወነ እንደሚገኝም ይጠቁማሉ::
ከሠብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን በዘላቂነት የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በተደራጀና በባለሙያ ጥናት በሚለይ ቦታ ለማከናወን ጥናቶች እየተሠሩ ናቸው፣ እንዲህ አይነት ክስተት ሲያጋጥሙ ለነፍስ አድን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሌላ የከፋ ጉዳት የማያስከትሉ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ጎፋ ላይ የተመለከትነው ይህንን ነው ይላሉ::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ጌትነት መዋ (ዶ/ር)፤ ሰሞኑን አደጋ ያስተናገደው አካባቢ ለም፣ ከዓመት ዓመት ዝናብ የማያጣው መሆኑን ይገልጻሉ::
49 በመቶ የኢትዮጵያ መሬት ለዚህ አይነት ችግር ተጋላጭ በመሆኑ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ ለውሳኔ ሰጪ አካላት በሚጠቅም መልኩ አካባቢዎችን በደንብ ማወቅ፣ መለየትና ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችሉ ዝርዝር ጥናቶች ሊደረጉ እንደሚገባም ያሳስባሉ::
ህብረተሰቡ ለመደጋገፍና ለመተጋገዝ የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳይና የሚደገፍ ቢሆንም ትብብር ሲደረግ ተጨማሪ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ::
እንዲህ አይነት ችግር ባለባቸውና ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ተዳፋት በሆኑ፣ በወንዝ ዳርቻዎች ጉድጓዶች፣ ወንዞች፣ ረግረጎች አካባቢ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል:: የነፍስ ማዳን ተግባሩም ቢሆን ከየአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመመካከር የሚሠራ መሆን እንዳለበትም ነው አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) የሚያሳስቡት::
ጌትነት (ዶ/ር) የመሬት መንሸራተት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ሁኔታ ለመሸርሸር አመቺ የሆነ አፈር ወይም የበሰበሰ ድንጋይ ከጠንካራው አለት በላይ በዛ ብሎ መቀመጥ አንዱ ምክንያት መሆኑንም ይጠቁማሉ::
የመሬት ተዳፋት መሆን ከፍተኛ የዝናብ መጠን መዝነብን ተከትሎ ለመሬት መሸርሸር ዝግጁ የሆነ አፈር ውሃውን ይጠጣውና በግፊት ቁልቁል የመንሸራተት ክስተት እንደሚፈጥርም ያመለክታሉ::
የሰዎች ተጽእኖም ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉት ተመራማሪው፤ ለመኖሪያና ለእርሻ ሥራ እጽዋትን መመንጠር መሬቱን በቀላሉ ለመሸርሸር ዝግጁ ያደርገዋል ነው የሚሉት:: ላለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ሀብትን ለማግኘት ሁሉም በየአካባቢው ሽሚያ ስለሚያደርግ መሬት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩንም ይጠቁማሉ::
በሙስና፣ በግዴለሽነት፣ በእውቀት ማነስም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች በመሬት አጠቃቀም ላይ የወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች አለመፈጸማቸው መሬቱ ባለቤት አልባና ለዚህ አይነት ችግር ተጋላጭ እንዲሆን እንዳደረገው ተመራማሪው ይጠቁማሉ::
በሀገር ደረጃ በመሰል የተፈጥሮ አደጋ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው በተከለሰው ደግሞ እስከ 800 ሺህ ማህበረሰብ ሊያፈናቅል እንደሚችል መተንበዩን የሚያመለክቱት ሽፈራው (ዶ/ር) ፤ በየክልሉ ግምት የተወሰደባቸው አካባቢዎች ላይ ኮሚቴ ተቋቁሟል ታክስ ፎርሶችም እየሠሩ ይገኛሉ ይላሉ::
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ገዛ ጎፋ ላይ ካሉት 29 ቀበሌዎች 15 ቀበሌዎች የተጋላጭነት ደረጃቸው በድሮን፣ በሜትሮሎጂ ባለሙያዎችና በጂዮሎጂስቶችና በጂዮስፓሻል ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ዳሰሳ እየተሠራ ነው:: በዳሰሳው የሚገኙ መረጃዎች ላይ በመመሥረት በተጨማሪነት የመልሶ ማስፈርና ሌሎች ሥራዎች ይሠራሉ::
ጌትነት (ዶ/ር) የአደጋ አካባቢውን በትክክል ለይቶ ህብረተሰቡ የት ቦታ መስፈር እንዳለበት መወሰን፤ አካባቢውን ከእዚህ ችግር መቅረፍ የሚቻለው ምን አይነት ተግባር በማከናወን እንደሆነ ማሰብ እና በሳይንሳዊ መንገድ ብዙ ውሃ ሊመጡ የሚችሉ የዛፍ አይነቶችን ለይቶ በአካባቢው መትከል ይገባል ነው የሚሉት::
የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በአግባቡ በመሥራት የችግሩን ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል የሚሉት ጌትነት ዶ/ር፤ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አማራጭ ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር በመሬት ላይ ጥገኛ የሚሆኑበትንና መሬት የሚጎዳበትን ሁኔታ መቀነስ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ::
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) የፌዴራል መንግሥት ሁሉም ዘርፎች ከክልሎች ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ጊዜ ስጋት ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሟል:: ከተጋላጭ አካባቢዎች ማህበረሰቦችን ለማውጣት እየተሠራ ነው፤ እስካሁን ስድስት ሺህ 600 ሰዎች ተለይተዋል:: የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የጋራ ትብብር እንዲኖር የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ይጠቁማሉ::
አያይዘውም፤ ተፈጥሯዊም ሰው ሠራሽም አደጋዎች የመከሰታቸው ሁኔታ ዓለም አቀፍ ባህሪ ነው:: አቅም ባላቸው ሀገሮች ጭምር ይህ ሁኔታ ፈተና ነው:: የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም የእሳት አደጋ ባልታሰበ ሰዓት ሊከሰት ይችላል:: እነዚህን አደጋዎች ቀድሞ ለይቶ መዘጋጀትን የሚጠይቅ አቅም እየገነቡ መሄድ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ይጠቀልላሉ::
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 /2016 ዓ.ም