ለአዲስ አበባ ሞገስና ውበት ተጨማሪ አቅም የሆኑ የልማት ሥራዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ:: በእኚህ ስድስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ከኢኮኖሚውና ከሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር በከተማ ማስዋብ ሥራ ላይ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል… እየተሠሩም ይገኛሉ::

እንደሚታወቀው አብዛኛው የሀገራችን ከተሞች የከተማነትን መስፈርት ያሟሉ ናቸው ብሎ መናገር ይከብዳል:: ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተሠራው የግንዛቤ ለውጥ ግን በብዙ ከተሞች ላይ ከፍተኛ መሻሻልን እያየን የመጣንበት ሁኔታ አለ:: ሁሉንም እንቃኝ ብንል ጊዜ ስለማይበቃን ለዛሬ የመዲናችንን የአዲስ አበባን የበጎ ዐሻራ የከተማ ውበት ላስቃኛችሁ::

መዲናችን አዲስ አበባ ከዋና ከተማነት ባለፈ የአፍሪካ መዲናም ጭምር ናት:: በዚያም ሳያበቃ የዓለም የዲፕሎማሲ መቀመጫ፣ የአፍሪካ ህብረት ቢሮ መገኛ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት ትልቅ ከተማ ናት:: እንደ መዲናችን የአገልግሎት ስፋትና ዓይነት ግን ዜጎችን የሚመጥን በቂና አስተማማኝ የመዝናኛም ሆነ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች በጥራትና በዓይነት የላትም::

ይህንን የከተማዋን ችግር ለመፍታት ተአምር በሚመስል ሁኔታ ለዛውም በጥቂት ጊዜ ውስጥ እየተሠራ ያለው ሥራ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መደነቂያ እየሆነ ነው፤ ለዚህ ደግሞ በከተማዋ የተገነቡ ለከተማዋ ሞገስ እና ውበት ምንጭ የሆኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል:: በኮሪደር ልማት ረገድም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገራሚና ለከተማችን የሚመጥኑ መንገዶችንና ተያያዥ ሥራዎች ተከናውነዋል::

በትላንትና በዛሬ ውህድ ቀለም እየነከርን የጻፍናቸው የአብሮነት ገጾች በውብ ከተማችን ላይ ተገልጠው ውበትን ከዘመናዊነትና ከጤና ጋር አቆራኝተው ለከተማችን ውበትን ለሕዝቡ ደግሞ ጤናንና ዘመናዊነትን ጀባ ብለዋል:: እኚህ ውብ ገጾች ስለ ኢትዮጵያ የሚዘምሩ፣ ስለ ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ የሚናገሩ የአብሮነት ዐሻራዎች ናቸው:: እኚህ ውብ ገጽታዎች ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ያቆሙ፣ ዘመኑን የዋጁ የተስፋ ምልክቶች ናቸው::

በከተማ ውበትና በኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆንንና በቀጣይም በላቀና በበረታ መልኩ ከተማችንን ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የማድረግ ተልዕኮ እንዳለ ብዙ ማሳያዎች አሉ:: የማይቻሉ የሚመስሉ የተለያዩ ሥራዎችን በጋራ ሰርተን የላቀ ውጤት አምጥተናል::

በመጥፎ ጠረንና እዛም እዚም በሚጣሉ ቆሻሻዋ የምትታወቀው መዲናችን አምራና ተውባ እንደ ሙሽራ የታየችበት አሁናዊ ገጽታዋ ‹ጽዱ ከተማን ከማህበረሰብ ጤና ጋር አስተሳስረን የተነሳንበትን አላማ በጉልህ የሚያሳይ ነው:: እያወራን ያለነው በአዲስ አበባ እየተሠሩ ካሉ የልማት እቅዶች አንዱን መዘን ነው:: የተጀመሩትንና ሊጀመሩ የታሰቡትን እንዘርዝር ካልን ጊዜ ላይበቃን ይችላል::

በሸገር ገበታ የተጀመረው የልማት መነቃቃት ወደ ኮሪደር ልማት አድጎ አዲስ አበባን ተሻግሮ በክልልና በወረዳ ድረስ ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው:: እንደ አብነት ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ በኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ከተሞች ናቸው:: በቅርቡ በርካታ ከተሞች የዚህ ንቅናቄ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል::

አዲስ አበባችን የመጀመሪያ ፓርኳን /አንድነት ፓርክን ያየችው በጠቅላይ ሚንስትራችን የላቀ መነሳሳት ነው:: አንድነት ፓርክ ከፓርክነቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ድሮአዊና አሁናዊ ታሪኮችን የያዘ ራሱን የቻለ ሙዚየም ነው:: እኔና እናንተ ከነውበታችን፣ ከነቀለማችን፣ ከባህልና ሥርዓታችን ጋር በአንድ ስፍራ በአንድነት ፓርክ ውስጥ ታሪክ እያወራን አለን::

ታሪክና ትውፊትን በእንደዚህ ዓይነት ዘመን ተሻጋሪ በጎ ሥራ በኩል ለትውልድ ማስቀመጥ እጅግ ብልህነት ነው:: ሕብረ ብሔራዊነትን በአንድ ቦታ ለዛውም በሚስብና ለእይታ ምቹ በሆነ ስፍራ ማግኘት ይበል የሚያሰኝ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ አንድነት ፓርክ ቤተመንግሥት ጊቢ ውስጥ መሠራቱ ልዩ ያደርገዋል:: ከልዩነቱ አንዱ ቤተመንግሥትን ለሕዝብ ክፍት ከማድረግ ጋር የሚመሳሰል ትርጉም ያለው ነው::

ስለ አንድነት ፓርክ አውርተን ሳንጨርስ፣ ተገርመንና ተደንቀን ሳናበቃ ሁላችንንም በአንድ ያስገረመ እንጦጦ ፓርክ ተመረቀ:: እንጦጦ ፓርክ ፓርክ ብቻ አይደለም ለዚህ ደግሞ ፓርኩን ሄዳችሁ ያያችሁ ምስክሮች ናችሁ:: እንጦጦ ፓርክ የኢትዮጵያዊነት አለላ መልኮች የተጣመሩበት ከመዝናኛ ባለፈ ብዙ ትርጉም ያለው መናፈሻ ነው::

ፓሪስና ዱባይን፣ አውሮፓንና ኢሲያን የሚስተካከል አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ የሚያስንቅ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው:: ይህ ውብ መልክ ደግሞ ዝም ብሎ አልመጣም ለውበትና ለጤና ከሰጠነው የገዘፈ ቦታ የፈለቀ ነው:: አሁን ላይ እንጦጦ ፓርክን ለብዙ ነገር እየተጠየቀምነው እንገኛለን:: የከተማችን ቁጥር አንድ መዝናኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሠርግና መሰል የደስታ በዓላትን እናሳልፍበታለን::

ለፊልምና ለተለያዩ ቀረጻዎች እየተጠቀምንበት እንገኛለን:: ለተለያዩ ስብሰባዎች እያገለገለን ያለ ዘመናዊና ታሪካዊ፣ የብዙ ሃሳቦች፣ የብዙ ህልሞች ውብ ስፍራ ነው ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አድርጋለሁ:: የከተማ ውበት ግስጋሴያችን ወደ ሌላም ይወስደናል… በአንድነት ፓርክ ጀምረን በእንጦጦ ቀጥለን በወዳጅነት ፓርክ አሰልሰናል::

የወዳጅነት ፓርክ እንደስሙ አንድነትንና አብሮነትን የሚገልጥ፣ የውህደትና የትስስር ምልክት ነው:: ኢትዮጵያዊነት ከመልክና ከወዙ ጋር የሚታይበት የፍቅርና የመቻቻል ፓርክ ነው:: ከስሙ ጀምሮ እስከ ግብሩ ድረስ አያይዞና አሰባስቦ በጋራ የሚያማክር ቦታ ነው:: በርካታ ብሔር ብሔረሰብ በአንድነትና በወዳጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድ ሃሳብ የሚያስቡበት፣ አንድ ህልም የሚያልሙበት የጥቁርነት ቀለም ነው:: እኚህ ፓርኮች ከመዝናኛነት ባለፈ አብሮነትን ከማስቀጠል ረገድ ሚናቸው የላቀ ነው:: ውበትን ከምቾትና ከከተማ ገጽታ ጋር አስተሳስረው ያሉ የትጋት ውጤቶች ናቸው::

በነዚህ ፓርኮች አማካኝነት ለብዙዎች የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል:: በእነዚህ ፓርኮች አማካኝነት የይቻላል በጎ መንፈስን በውስጣችን አስርጸናል:: እኚህ ፓርኮች እንደብሔራዊ ድል አንድነታችን የታየባቸው ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ አንድምታን የሚያንጸባርቁ ናቸው:: ሌላው ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳውና የአዲስ አበባን ገጽታ በትልቁ ከቀየሩ አጋጣሚዎች አንዱ መስቀል አደባባይ ነው::

ሀገር ትላንትናም ዛሬ ነገም የራሷ የሆነ መልክና ደም ግባት አላት:: የዛሬ የከተማ ልማቶች ለነገው ትውልድ ምቾትና የጤና መድህን ሆነው መቀመጣቸው እሙን ቢሆንም እንደ ሀገር ትርፋቸውም የት የሌለ ነው:: መስቀል አደባባይ የከተማዋ ትልቁ አደባባይ ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ መንፈሳዊና ዓለማዊ በዓላት ሲካሄዱበት ቆይቷል::

የመስቀል በዓልን ጨምሮ፣ የተለያዩ የሕዝብ በዓላት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ መንግሥታዊ ዝግጅቶች ከተስተናገዱበት ዝግጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው:: ይሄን በዓይነቱ ትልቅ የሆነ አደባባይ መንግሥት ከዘጠኝ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ 2.6 ቢሊዮን በሆነ የገንዘብ ወጪ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ አሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት ካደረገው ዓመታት ተቆጥረዋል:: እስከ ማዘጋጃ ቤት ድረስ የሚዘልቀው ይሄው የመስቀል አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መንግሥት ለከተማ ውበት የሰጠውን ዋጋ በግዝፈት የሚያሳይ ነው::

አዲስ አበባ ከተማ እንደ ሀገሪቱ ዋና ከተማነት፣ እንደ አፍሪካ መዲናነቱ፣ እንደ ዓለም አቀፍ እውቅናው ከዚህም በላይ ማማርና መበልጸግ የሚገባው እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ ግዙፍ የዋና ከተማ አደባባይ ላይ የከተማውን ገጽታ የሚጨምሩ እጅግ ሰፊና ማራኪ የሆኑ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ሀምሳ (1450) የሚደርሱ መኪናዎችን መያዝ የሚችል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፓርክ ያካተተ ነው::

የተለያዩ ሱቆች፣ መጸዳጃ ቤቶች የተካተተበት፤ የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ የተለየዩ ስክሪኖችም የተገጠሙለት አውሮፓ ስታንዳርድ አደባባይ ነው:: ይህ እንግዲህ ለከተማ ውበትና ለማህበረሰብ ጤና ቅድሚያ ተሰጥቶ የተሠራ የባለፈው ዓመታት የታሪክ ሰነድ ነው::

ከላይ እንዳየነው ያለፉት ዓመታት በከተማ ገጽታ እና ውበት በኩል ብዙ ሥራዎችን የሰራንባቸውና እንደ ስኬት የምናወሳቸው ዓመታት እንደነበሩ በድፍረት መናገር ይቻላል:: ለዚህ ነፃ ሃሳብ እንደ ማሰሪያና እንደ ዋና ማጠንጠኛ የሚሆነው አሁናዊው የኮሪደር ልማት አፈጻጸም ነው::

ስድስትና ሰባት ወራት የተያዘለት በአምስት የኮሪደር ልማት የተጀመረው አዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ከተማችንን ልዩ ድባብ ሰጥቷታል:: ይሄ መንፈስ ወደ መላው ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ከተሞች በኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ:: የኮሪደር ልማትም ሆነ የከተማን ውበት የሚመለከቱ ሌሎች ሥራዎች ዘመናዊነትን ከስልጣኔና ከኑሮ ምቹነት ጋር የሚገልጡ ናቸው::

ሀገር ለማህበረሰብ ምቹ ከባቢ ሳይኖራት በዋና ከተማ መጠራቷና የዓለም የዲፕሎማት መቀመጫ መሆኗ ብቻውን ትርጉም የለውም:: በነገራችን እኛ ብቻ አይደለንም ለተለያየ ጉዳይ ከውጭ ወደሀገራችን የሚመጡ ነጮች ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ባለመኖሩ፣ አረንጓዴ የለበሰ መዝናኛ ስፍራ ባለመኖሩ ቅሬታ የሚያነሱ ናቸው::

እሱ ብቻ አይደለም ከአፍሪካ ምርጡን አየር መንገድ ይዘን ምርጥ እና ለኑሮ እንዲሁም ለጎብኚዎች ተስማሚ አዲስ አበባን ካልፈጠርን ምቹ አየር መንገድ ብቻውን ገጽታችንን አይገነባም:: አንድ ቱሪስት የውጭ ዜጋ ምቹ ሆቴል፣ የሚዝናናበት ምቹ መዝናኛ ስፍራ፣ ወጣ ብሎ የሚያየው አረንጓዴ ከባቢ ያስፈልገዋል::

በውጪው ዓለም የዘመናዊነት ልኬት ከሆኑት ውስጥ እንደ ፎቅ ሁሉ አረንጓዴ ከባቢዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው:: ስለሆነም የኮሪደር ልማቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅም አላቸው እንደ ሀገር ከውበትና ከጤና ጋር የተሳሰሩ ሲሆኑ በተጨማሪም የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ፣ የሥራ እድሎችን በመፍጠር በጎ ዐሻራ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው::

ልቀንና በርትተን በቀጣይም የተሻሉና የበለጡ ኢትዮጵያዊነትን በላቀ መልኩ የሚያጎሉ ሥራዎች እንደምንሰራ ተስፋ አለኝ:: ሁልጊዜም ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ይበልጣል:: ያሉትን እንደ መንደርደሪያ በመውሰድ ለላቀ ክዋኔ የምንበረታባቸው እንደሚሆኑ አምናለሁ::

በብዙሃን ተሳትፎ፣ በቀን ሃያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን በሚሰሩ ትጉ እጆች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባንና አካባቢዋን በዚህ ልክ ማሳመር ከተቻለ ቀጣዩ ጊዜ ምን እንደሚመስል መገመት አይከብድም:: በከተማ ማስዋብ ሥራ ያለፉት ጥቂት ወራት የአምስትና አስር ዓመታትን ያክል ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ ውጤታቸው ይመሰክራል::

ከምንም በላይ ቃል በተግባር የታየበት፣ የእውነት፣ የጽናትና የይቻላል መንፈስ ተንጸባርቆ ያለፈበት ጊዜ ነበር:: በዲዛይንና በፈጠራ፣ በአብሮነትና በቅንጅት አክሱምንና ላሊበላን ያነጹ እጆቻችን ዛሬም ተዐምር መሥራት እንደሚችሉ በተግባር አይተናል:: ‹ጽዱ ከተማ ኑሮ በጤና› ዘመናዊነትና የኑሮ ዋስትና የሚረጋገጥባቸው የተሃድሶ መሪ ሃሳቦች ናቸው:: ሰላም ለእናንተ ይሁን::

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You