ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው የሚተዳደረው በግብርናው ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል:: ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥም ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው:: ለጠቅላላ ዓመታዊ ምርት፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለምግብ ዋስትናና ምግብ ሥርዓት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበርከታል:: ለብዙ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ አድል በመፍጠርም ይጠቀሳል::
ዘርፉ ለሀገር ካለው ፋይዳ በመነጨም መንግሥት ለእዚህ ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ በትኩረት ይሠራል፤ በዘርፉ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን፣ የዘርፉን ፀጋዎች በማልማት በተከናወኑ ተግባሮችም ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ::
በግብርናው ዘርፍ ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከል ለረጅም ዓመታት አብሮን የኖረውን የተረጂነት አመለካከት ለመቀየር እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት በተከናወነው ተግባር በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የተመዘገበው ስኬት ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የደን ሽፋናችንን ለማሳደግ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የተከናወነው ተግባር በአብነት ይጠቀሳሉ:: በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል ላይ እየተሠራ ያለው እንደ ሌማት ቱሩፋት አይነቱ ሥራ፣ ግብርናን ለማዘመን በሜናካናይዜሽን መሣሪያዎችና በተለያዩ የግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና አጠቃቀም ላይ ያሉ ሪፎርሞችም ሌሎች በዘርፉ እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች መካከል በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው::
እንደ ሀገር ለሀገር የተከናወኑ ተግባሮች ከሀገርም አልፈው ሀገሪቱን ገጽታ መገንባት ችለዋል:: በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ የተመዘጉ ስኬቶች ሀገሪቱ ዓለምአቀፍ እውቅና ያተረፈችባቸው ናቸው:: በሌማት ትሩፋት የተገኙ ስኬቶችም የእንስሳት ተዋፅኦዎች ገበያን ከማረጋጋትና የሥራ እድልን ከማስፋት አኳያ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል::
በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል፣ የምግብ ዋስትናንና የምግብ ሥርዓትን ለማረጋገጥ፣ በቂ ምርት ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ፣ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ለመተካት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የዘርፉን የመልማት አቅም በመለየትና በቂ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ከእስከ አሁኑም በላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራትን ይጠይቃል::
ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያሳደገች ብትመጣም ያላት የመልማት አቅምና ከልማቱ ከሚፈለገው ምርት አኳያ ሲታይ ገና ብዙ መሥራት ያስፈልጋል:: እስከ አሁንም ይህን ታሳቢ በማድረግ ጭምር በተከናወነ ተግባር ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ መምጣት ተችሏል:: በቀጣይም ይሄው ነው መሆን ያለበት::
የግብርናው ዘርፍ ሥራ በተለያዩ ንኡስ ዘርፎች ተከፋፍሎ እንደሚካሄድ ይታወቃል:: ከእነዚህ ንኡስ ዘርፎች መካከልም ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለው የሆርቲካልቸር ልማት ይጠቀሳል:: ይህ ንኡስ ዘርፍ ለሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የሥራ እድል በመፍጠር ይታወቃል::
ይሁንና ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አኳያ ጥቅም ላይ የዋለው የተወሰነው መሆኑ ይታመናል:: ይህ ንኡስ ዘርፍ በተለይም ካለፉት ሁለት አስር ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ይታወቃል፤ በዘርፉ የግሉ ዘርፍ የሚያደርገው ተሳትፎ በፍጥነት እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የእድገት ፍጥነቱን ማስቀጠል ላይ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት መረጃዎች ይጠቁማሉ::
ከግብርና ሚኒስቴር መረጃ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው:: ሀገሪቱ በ2015 ዓ.ም ከሆርቲካልቸር ያገኘችው 658 ሚሊዮን ዶላር ዘንድሮ ወደ 525 ዶላር ዝቅ ብሏል:: ይህ ቀላል ማሽቆልቆል ተደርጎ የሚታይ አይደለም::
ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት መቀነስም ሆነ በውጭ ምንዛሬ ግኝት መንሸራተት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል:: ከእነዚህም መካከል የሰላም እጦት፣ የመልካም አስተዳደርና የመሠረተ ልማት ችግሮች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ::
ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ምርቶች የአንበሳ ድርሻውን የሚይዘው የአበባ ምርት ነው፤ ከአትክልትና ፍራፍሬው ዘርፍ ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታገኘው ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል:: ኢትዮጵያ እንደሀገር በጣም ትልቅ አቅም ያላት ለአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ሆኖ እያለ ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ግን ዝቅተኛ መሆን በእጅጉ ሊያስቆጭ ይገባል::
በአበባ ልማቱም ቢሆን ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም መጠቀም እየተቻለ አይደለም:: በአበባ ምርት የተያዘው መሬት ከአንድ ሺ 750 ሄክታር ያነሰ ነው፤ እንዲያም ሆኖ ኢንዱስትሪው በየአመቱ ከ500 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ገቢ ያመጣል:: የዘርፉ ችግሮች አለመፈታት ልማቱ እንዳይስፋፋ እያደረገ መሆኑ የማያሳስበው ሊኖር አይገባም::
እርግጥ ነው የዘርፉን ችግሮች ለመፍታትና ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም ዘርፉ ለኢኮኖሚው ሁነኛ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ በመንግሥት በኩል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል:: ከእነዚህ ጥረቶች መካከል በ2010 ዓ.ም በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ እስከ አሁን ጸድቆ ወደ ሥራ ያልገባው ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ አንዱ ነው::
ስትራቴጂው ዘርፉ በሥርዓት እንዲመራና በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት እንዲራመድ ያደርገዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ:: እንደታሰበው ግን አልሆነም፤ ሰነዱ ፀድቆ ተግባራዊ ባለመሆኑ የሆርቲካልቸር ልማቱ ከእነችግሩ እንዲቀጥል ሆኗል::
ይህ ሰነድ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንዲቃኝ እየተደረገ ነው:: ግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ የሆርቲካልቸር ንኡስ ዘርፍ ማነቆዎችና ተግዳሮቶች ለመፍታትና የምርምርና ኤክስቴንሽን ሥራን በማጠናከር ብሎም የድህረ ምርት አያያዝና መሠረታዊ መሠረተ ልማቶችን ለማሻሻል ያስችለው ዘንድ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በረቂቅ ሰነዱ ላይ የክለሳ ሥራ አከናውኗል::
የስትራቴጂው ዝግጅት በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ከመፍታት ባለፈ ፋይዳ እንዳለውም ታምኖበታል፤ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ እንድትሆን እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ እድሎችን ከመፍጠር፤ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚኖረውን አስተዋፅኦ ከማጎልበት አንፃር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ግንዛቤ ተይዞበታል::
ከምሁራንና ከዘርፉ ተዋናዮች እንዲሁም ከመንግሥት አካላት ጋር በተከታታይ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶችም ይህን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው:: ስትራቴጂው የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ትርጉም ወዳለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያደርሳል ተብሎ ታምኖበታል::
ስትራቴጂው በተለይም የአግሮሎጂስቲክ ችግሮችን ከመፍታት፣ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ከመፍጠር ፤ መልካም የግብርና ተሞክሮችን ከማጎልበት፣ የግብዓት አቅርቦቱን ከማሻሻል፣ የፋይናንስ አቅርቦቱንም ከማሳደግ አኳያ ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ ነው:: ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ዘርፉን ይበልጥ ተፎካካሪ ከማድረግ አኳያም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል:: በዓለም ገበያ ላይ በሆርቲካልቸር ምርት የኢትዮጵያን ተፎካካሪነት ከማሳደግ አንፃርም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል::
ዓለምአቀፍ የጥራት መስፈርትን የሚያሟሉና እውቅና ያላቸው እርሻዎች እምብዛም እንደመሆናቸው መጠን እርሻዎቹ እነዚህን መስፈርቶች እንዲያሟሉ ከማድረግ አንጻርም አስተዋፅኦ ይኖረዋል:: የዚህ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል እንደመሆኑም በተለይም በዘርፉ ተዋናዮች በተደጋጋሚ የሚነሱትን የግብዓት፣ የግብይትና የፋይናንስ ሥርዓቱን የማሻሻል ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችላል፤ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶአደሮች ከኮሜርሻል እርሻዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማጠናከርም ይጠቅማል ተብሏል::
ይሁንና አስቀድሜ ካነሳኋቸው የዘርፉ ተግዳሮቶች በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሀገሪቱ እየተከሰተ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተወሰኑ ዘርፉ ኢንቨስትመንቶች ከስራ ውጪ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ:: መንግሥት ለእነዚህ ባለሀብቶች ድጋፎችን በማድረግ ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረቶች ሲደረግ ቆይቷል::
ይሁንና ባለፉት ዓመታት ወደ አስር የሚሆኑ ኩባንያዎች ሙሉ ለሙሉ ማምረት ያቆሙበት ሁኔታ አለ:: ለአብነትም በእዚህ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ በአማራ ክልል በዘርፉ የተሠማሩ ወደ ስድስት የሆኑ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፤ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት ወደ ሥራ የተመለሱ ቢሆንም፤ ሁሉንም ወደ ሥራ ለመመለስ የተሻለ ድጋፍ መስጠት አለበት የሚል እምነት አለኝ:: የእነዚህ ባለሀብቶች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያን የሚሻም ይመስለኛል::
ለዘርፉ የሚደረገው የፋይንነስ አቅርቦት ይሻሻላል ተብሎ ይታመናል፤ የግብዓት አቅርቦትና የመሬት ሥርዓቱም አሁን ካለበት ይሻሻል ተብሎ ይታሰባል:: በእነዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ቀጣዩ ሥራ መሆን ይኖርበታል::
እንደ አጠቃላይ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች መፍታት ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት ለማሳካት ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ መሆኑ ታምኖበት ሊሠራበትም ይገባል:: እንደእኔ እምነትም የስትራቴጂውም ዓላማ የዘርፉን ውጤታማነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ ያሉትን ችግሮች በተደራጀ መልኩ ለመፍታት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል:: የዘርፉን ችግሮች ለመፍታትና ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማደረግ ስትራቴጂው በፍጥነት ዳብሮና ጽድቆ ወደ መሬት መውረድ ይኖርበታል፡ በስትራቴጂው የተቀመጡ አሠራሮችም ያለምንም መሸራረፍ መሬት ላይ ወርደው ሊሠራባቸው ይገባል:: በትግበራውም ሁሉም ተዋናዮች ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል::
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም