አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞችን መመገብ የሚችል ሮቦት

ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት ቀላል ያደርጋል፤ ይህን በመጠቀም ሰዎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ መቆጠብ ችለዋል፤ ከእንግልት ድነዋል፤ ምርታማ ሆነዋል፤ ወዘተ.።

ቴክኖሎጂን ብዙኃኑን የማከለና አካታች እንዲሆን በማድረግም የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። በተለይ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። በዘርፉ የፈጠራ ሃሳብ መማነጨት የሚችሉና ፍላጎቱ ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ላይ መሥራትም ይጠበቅባቸዋል።

የፈጠራ ሃሳብ ለችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ በሚሰሩ ሰዎች የሚመነጭ እንደመሆኑ በቅርበት የሚታየውን የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው፣ ጥናት ላይ የተመረኮዙ ችግሮችን ሊፍቱ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎች እንደሚሰሩም ይታወቃል። በጥናት ላይ የተደገፉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት ከሚታወቁት መካከል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይጠቀሳሉ።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ጉልህ ድርሻ አላቸው። ዘንድሮም በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በርካታ ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ተሰርተው በ14ተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ ርዕይ ላይ ቀርበዋል። ከእነዚህ መካከል የጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰልጣኙ ወጣት ዳግም ጋርጠው የሰራት አካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካሞችንና ሕፃናትን መመገብ የምትችል ሮቦት ትጠቀሳለች።

ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ትልቁ ችግር የሆነ ራስን ችሎ ከቦታ ወደ መንቀሳቀስ አለመቻል ብቻ አይደለም፤ ምግብ በራሳቸው መመገብ አለመቻላቸውም ይነሳል። ይህ ችግር የሚመግባቸው ሌላ ሰው እንዲኖር የግድ ሲልም ይስተዋላል። ራሳቸውን ችለው እንዲመገቡ የሚያስችላቸው ሁኔታ ቢኖር ግን ሰው ላያስፈልግ ይችላል። ወጣት ዳግም አካል ጉዳተኞችን በመመገብ ይህን ችግር መፍታት የምትችል ሮቦት ነው የሰራው።

ከአንገት በታች ያለው የሰውነት ክፍላቸው የማይሰራ ወይም ፓራላይዝድ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ፤ የነርቭ ችግር ያለባቸው፣ እጃቸው የሚንቀጠቀጥባቸው አካል ጉዳተኞችም አሉ። በተፈጥሮ ከአካል ጉዳት ጋር የሚወለዱ ሕፃናትም የችግሩ ሰለባ ናቸው። በተለይ ሕፃናቱ የሰውን ርዳታ በእጅጉ የሚፈልጉ ከመሆናቸውም በላይ ያለ ሰው ድጋፍ ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ወላጆቻቸው በተለይም እናቶቻቸው ሌላ ሥራ መሥራት ትተው እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ እነሱን ሲንከባከቡ ለማሳለፍ ሲገደዱ ይታያሉ።

በተቋማት ደረጃም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ሰብሰበው የሚንከባከቡና የሚረዱ እንደ መቄዶንያ ዓይነት አረጋዊያን መንከባከቢያ ማዕከላት አሉ። እነዚህን ሁሉ የተመለከተው ወጣት ዳግም የእነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ምን ባደርግ የተሻለ ነገር መሥራት እችል ይሆን? ብሎ በጥልቀት በማሰብ ጥናት አድርጎበት ሁሉንም አካታች የሆነ የፈጠራ ሥራ መሥራቱን ይናገራል።

ወጣት ዳግም እንደሚለው፤ ሮቦቷ ፕሮግራም ተደርጋ በቻርጀር ብቻ መንቀሳቀስ የምትችል ተደርጋ ነው የተሰራችው። የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ለማገልገል ታስባ የተሰራች በመሆኗም ጉልበት፣ ጊዜና ወጪን ትቆጥባለች። በቀላሉ በአነስተኛ ዋጋ እንድትገኝ ተደርጋ የተሰራች ከመሆኗ በተጨማሪ ብዙ ሰው ሊጠቀምባት እንድትችል ተደርጋ ተሰርታለች። ‹‹ሮቦቷን ለመሥራት ትምህርት ቤት የሚማርባቸውን ቁሳቁስ ተጠቅሜለሁ። መቆጣጠሪያ፣ ሞተርና በዋጋቸው ቀላል የሆነ ቁሳቁስ ሥራ ላይ አውያለሁ›› ይላል።

ዳግም አካል ጉዳተኞችን መመገብ የምትችል ሮቦት ለመሥራት ሃሳቡን አመንጭቶ ከጠነሰሰ በኋላ በችግሩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችንም ተመልክቷል። ጥናቶቹ ችግሩ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ጠቁመውታል። ጊዜ ሳያጠፋ በፍጥነት ወደ መፍትሔ ፍለጋ መግባት እንዳለበትም አስገንዝበውታል።

በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ሲያብራራ እንደገለጸውም፤ በዓለም ላይ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ አካል ጉዳተኞች አሉ። በኢትዮጵያ ደግሞ 19 ሚሊዮን የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ።

እነዚህን አካል ጉዳተኞች የማገዙ ሥራ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በሚፈቅድው ልክ መሥራትን ይጠይቃል። በተለይ በዚህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በተራቀቀበት ዘመን እነሱን ለማገዝ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መሥራት ይገባል። ወጣት ዳግምም በዚህ ሃሳብ መነሻነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታገዝ ሮቦት ሰርቷል።

ወጣት ዳግም እንደሚለው፤ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በራሳቸው መመገብ ቢችሉም እንኳን በመሀል እየተመገቡ መሆናቸውን ረስተው ጀምረው የሚተውባቸው አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ምግቡን የጎረሱ እየመሰላቸው የሚደፉበት ሁኔታም ይኖራል። በዚህ ጊዜ ምግብ የበሉ ይመስላቸውና ተደፍቶ ሲያልቅ ተበሳጭተው እስከነአካቴው የምግብ ፍላጎታቸው እንዲጠፋ ይሆናል። ይቺ ሮቦት ግን እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ትችላለች።

ሮቦቷ ለተጠቃሚዎች የምትሰጠው አገልግሎት ምግብ መመገብ ብቻ ሳይሆን መጠጥ የማጠጣት አገልግሎትም ትሰጣለች። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ሁሉም የምግብ ዓይነቶች ለመመገብ አትችልም። ቀለል ያሉ ምግቦችን ነው መመገብ የምትችለው።

ለምሳሌ እንደ መኮሮኒ፣ ሩዝ እና ፍርፍር እና ሾርባዎች ያሉ በተለይ በማንኪያ መበላት የሚችሉ የምግብ ዓይነቶችን መመገብ ትችላለች። በአንድ ጊዜ ሁለት ዓይነት ምግቦችንም ትመግባለች። በመጠጥም በኩል ውሃ፣ ጁስ፣ ወተትና መሰል ሌሎች የመጠጥ ዓይነቶች በመቀያየር ታጠጣለች።

ሮቦቷ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ፕሮግራም የተደረገች ሲሆን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ማይክሮ ኮንትሮለርና እንቅስቃሴ የምታደርግባቸው ሞተሮች የተገጠሙላትም ናት፤ ፕሮግራሙ አንድ ጊዜ የተጫነ በመሆኑ በቀላሉ ለማዘዝም ሆነ ለመቆጣጣር ይቻላል።

ፕሮግራምም ሲጫን አንድ ሰው በአንድ ጊዜ መመገብ የሚችለው የማንኪያ መጠንና በምን ያህል ፍጥነት መመገብ ይችላል? የሚሉት ይቆጠሩለታል። ይህ ከተቆጠረ በኋላ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ መመገብ የሚችለው መጠን በአማካይ ይቀመጣል። ለአንድ ሰው የሚመጠነው የአንድ ጊዜ ምግብም በፓኬጅ መልኩ ለሮቦቷ ይሞላል። አገልግሎቱን ለመስጠት ሲፈለግ ሮቦቷ አገልግሎቱን እንድትጀምር የሚያደርግ አንድ ሰው ያስፈልጋል። ሰውዬው አገልግሎቱን ካስጀመረለት በኋላ ሮቦቷ ራሷን ችላ ምግቡን መግባ መቆም ባለበት ሰዓት ስለምታቆም በዚያው የምገባ አገልግሎቱ ይጠናቀቃል።

ሮቦቷ አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን ለመመገብ የተዘጋጀች እንደመሆኑ እነሱ የሚመገቡበትን የጊዜ ልዩነት በደንብ ከግንዛቤ በማስገባት ጥናት ተደርጎ ያንን የጊዜ ገደብ እንዲጠብቅ ተደርጎ ፕሮግራም የተደረገ መሆኑን የሚገልጸው ወጣት ዳግም፤ ይሁንና ፍጥነቱን መጨመርና መቀነስ ከተፈለገ በተጠቃሚ ፍላጎት እንዲሆን ይደረጋል።

‹‹ፍጥነት ለመቀነስ የተቀመጠውን የጊዜ ልዩነት ስንቀንስ ሮቦቷም በዚያም ልክ የፍጥነት መጠኗን ትቀንሳለች ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ፍጥነት በመጨመር ቶሎ ቶሎ መመገብ የሚፈልግ ተጠቃሚ ቢያጋጥምም እንደዚሁ የተቀመጠውን የሰዓት ልዩነት በመጨመር ፍጥነት እንድትጨምር ማድረግ እንችላለን›› ይላል።

እንደ እሱ ማብራሪያ፤ ሮቦቷ በዚህ መልኩ ተሰርታ ተግባር ላይ ትዋል እንጂ ያልተሟሉ ጥቃቅን ነገሮች አሏት። ለምሳሌ ውጫዊ ክፍሏ ቢቀየርና ሴንሰሮች ቢጨመሩላት የተሻለ አገልግሎት መስጠት ትችላለች። ምክንያቱም ሁሉም አካል ጉዳተኛም ሆነ አቅመ ደካማ ያለበት ችግር አንድ ዓይነት ስላልሆነ ይህን በማድረግ ሁሉንም እንደየሁኔታቸው ለማስተናገድ ይቻላል። ለአብነት ዓይነስውራን ሆነው መመገብ የማይችሉን ብንወስድ በሮቦቷ አማካኝነት እንዲመገቡ ሲደረግ ተመጋቢዎቹ በሴንሰሮች አማካኝነት መመገብ እንዲችሉ ብዙ ሴንሰሮች ስለሚያስፈልግ ይህን በማካተት መሻሻል ይቻላል።

እነዚህን ሥራዎች መሥራት ቀላል ቢሆንም የፋይናንስ አቅም እንደሚጠይቁ ጠቅሶ፤ በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን በማሻሻል የተሻለ ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርግ ይገልጻል። ‹‹ሮቦት ለመሥሪያ የሚያገለግሉ ሮቦቲክስ ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነው›› የሚለው ወጣት ዳግም፤ ሮቦቷን ለመሥራት ያጋጠሙት ተግዳሮቶች እንደ ሀገር ያሉና የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ያነሳል። ለሮቦቱ መሥሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ የሚገኙባቸው ቦታዎች ውስን ከመሆናቸውም በላይ የፋይናንስ አቅምን የሚጠይቁ መሆናቸውም ይገልጻል።

‹‹እኔ ይቺን ሮቦት ስሰራ ለሮቦቱ መሥሪያ የሚውሉ ቁሳቁስን ድጋፍ ያደረገልኝ ኮሌጁ ነው። የቁሳቁሱ አለመሟላት ለሥራዬ እንቅፋት ሆኖብኛል፤ ሥራው እንዲዘገይ ምክንያትም ሆኗል። ኮሌጁ ድጋፍ ባይደርግልኝ ኖሮ በራሴ ለመሥራት በፋይናንስ አቅም ሳቢያ እቸገር ነበር›› ይላል።

በዚህም የተነሳ የሮቦቷ ሃሳብ እንደመነጨለት በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሰራች መሆኗን ጠቅሶ፣ መጠነኛ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል። አሁን ላይ ያለው የሮቦቷ ሥራ ሙሉ ባይሆንም ከፕሮቶፓይፕ ደረጃ ከፍ ያለና ባለበት ሁኔታም አገልግሎት መስጠት የምትችል ናት። ሮቦቷ አገልግሎቱን መስጠት እንደምትችል ለማረጋገጥ በተደረገላት ፈተሻ አገልግሎት ላይ መዋል እንደምትችል ማረጋገጥ ተችሏል ሲል ያስረዳል።

ሮቦቷን በማሻሻል ከዚህ በበለጠ መልኩ ለመሥራት የተለያዩ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሶ፤ ለአብነትም የሮቦቷ ውጫዊ አካል ጥንካሬ እንዲኖረው ማሻሻያ ተደርጎ አሁን ከተሰራበት ውጭ በሆነ በሌላ ቁሳቁስ እንድትስራ ቢደረግ ጥንካሬ ያለው ሮቦት መሥራት እንደሚቻል ነው ያስገነዘበው።

አሁንም ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፣ በቀጣይም እነዚህን ሥራዎች በማጠናቀቅ ጥቅም ላይ በማዋል ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት እንደሚያደርግ ይገልጻል። ኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪካል ኮንትሮለር ቴክኖሎጂ የተሰኘ ትምህርት እየተማረ መሆኑን ጠቅሶ፤ ትምህርቱም በአብዛኛው በኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ትኩረት እንደሚያደርግ ያስረዳል። በዚህ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ለማበርከት የበኩሉን እንደሚሰራ ያመለክታል።

አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በሰው ኃይል እንደሚሰሩ ጠቅሶ፣ ብዙ የሰው ኃይል የሚጠቀሙና ጊዜን የሚወሰዱ እንዲሁም አደጋም ሊያስከትሉ የሚችሉ ሥራዎች የሚሰሩባቸው እንደሆኑ ይጠቁማል። ይህም በቴክኖሎጂ ቢቀየር ጉልበት፣ ጊዜን፣ ወጪንና ብዙ ነገሮች ሊቆጥብ እንደሚችል ይናገራል። እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች እንዲሻሻሉ ለማድረግ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

እንደ ወጣት ዳግም ገለፃ፤ እሱ ወደ ፈጠራ ሥራዎች የገባው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እየተማረ ባለበት ወቅት ነበር፤ በትምህርት ቤት ቆይታውም የፈጠራ ሥራዎችን ሰርቶ ለውድድር በማብቃት አሸናፊ ሆኖም ያውቃል። በዚህም የምስክር ወረቀት፣ የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማቶች አግኝቷል። ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል የከተማ ማጽጃ፣ አውቶማቲክ ቡና ማፊያ ማሽንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

ወጣት ዳግም የግሉ የፈጠራ ሥራ የሆነችው ይቺ ሮቦት በዘንድሮው 14ተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይ አንደኛ መውጣቷንም ጠቅሶ፣ በዚህም የሰርተፌኬትና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል። ይህም ለቀጣይ ሥራ ሞራልና ማበረታታ እንደፈጠረለት ይናገራል።

በተለይ በፈጠራ ሥራዎች የሚሰሩ ወጣቶች ማወቅና መገንዘብ ያለባቸው የፈጠራ ሥራ ብዙ ተግዳሮት እንዳለበት ወጣት ዳግም አመልክቷል። የፈጠራ ክህሎቱ፣ እውቀቱና የመሥራት አቅሙ ያለው ሰው፣ በፋይናንስ እጦት የሚከሰቱ ተግዳሮቶችንም በአሸናፊነት ለማለፍ ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝቧል። የፈጠራ ሥራዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ዝቅተኛ ነው ሲል ጠቅሶ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ በመሥራት የፈለጉትን አላማ ማሳካት እንደሚቻል በማመን ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘበው።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You