ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚሻው የሆርቲካልቸር ዘርፍ

በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላቸው የልማት ዘርፎች መካከል የሆርቲካልቸር ልማት ይጠቀሳል:: ይህ ንኡስ ዘርፍ በተለይም ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር፣ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደግ አኳያ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል::

የግሉ ዘርፍ የግብርናው ዘርፍ ተሳትፎ በፍጥነት እያደገ እንዲመጣም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው፤ የእድገት ፍጥነቱን ከማስቀጠል አኳያ ግን ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እየቀነሰ ለመምጣቱ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የነበረው ድርሻ እየተንሸራተተ ስላለበት ሁኔታ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች እንዳሉ እየተጠቆመ ነው:: ከተግዳሮቶቹም መካከል እንደ ሀገር የሰላም እጦትና የተረጋጋ ሁኔታ አለመኖር፣ የመልካም አስተዳደርና የመሠረተ ልማት ችግሮች በዋናነት ይጠቀሳሉ::

መንግሥት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ሲያከናውናቸው ከቆዩ ተግባሮች መካከል በ2010 ዓ.ም በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ አንዱ ነው:: ይህ ረቂቅ ሰነድ ግን እስከ አሁንም ሳይጸድቅ ቆይቷል:: በአሁኑ ወቅት ሰነዱን የመከለስ ሥራ እየተካሄደም ይገኛል::

በዚህ ሰነድ ላይ የሚነጋገር መድረክ በቅርቡ በተካሄደበት ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ረቂቅ ሰነዱን መከለስ ያስፈለገው ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በማለም ነው:: ሚኒስቴሩ ስትራቴጂውን በማዘጋጀትና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ በማዳበር መተግበር አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ የውይይት መድረኮችን ሲያካሂድ ቆይቷል::

ስትራቴጂውን አሁናዊ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ባገናዘበ መልኩ በመከለስ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ የንኡስ ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሀገሪቱ ያላትን አቅም በመለየትና በአርሶ አደሮችና በግል ባለሀብቶች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለመደገፍ እንደሚያስችል አመልክተዋል:: የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስና ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንዲያስችል ተደርጎ መዘጋጀቱንም ይጠቅሳሉ::

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በሆርቲካልቸር ንኡስ ዘርፍ የአበባ፣ አትክልትና እፀ ጣዕም፣ ፍራፍሬ እና ስራስር ልማትን ለማስፋፋት አርሶ አደሮችና በግል ባለሀብቶች የሚሰሩ ሥራዎችን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ የንኡስ ዘርፉን ፀጋዎች በሚፈለገው ደረጃ ለመጠቀም በማምረትና በግብይት ሥርዓት ሂደት ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ላይ ውስንነቶች ይታያሉ::

ይህም በመሆኑ እንደ ሀገር ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተው፣ ለእዚህም ‹‹ ዘርፉ ካለፈው በጀት ዓመት መጠነኛ ቅናሽ ያለው ገቢ በ2016 በጀት ዓመት /535 ሚሊዮን ዶላር ብቻ/ ያስገኘበትን ሁኔታ በአብነት ጠቅሰዋል::

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ እንደቀድሞውም ባይሆንም ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም ሲሉ ጠቅሰው፣ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ከተቻለ በተሻለ መጠን የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከምርት አንፃር ትልቁን ሽፋን የያዘው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ነው፤ የአበባ ምርት ግን በበጀት ዓመቱ አነስተኛ የሚባል ነው:: በሌላ በኩል አነስተኛ ይዞታ ያለው አርሶ አደር አበባ ልማት ላይ አይሳተፍም፤ የፍራፍሬ ልማቱም ሰፊ የሚባል አይደለም፤ አሁን ላይ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩና እንዲሁም አርሶ አደሩና ክልሎችም ባላቸው ኢኒሼቲቭ የፍራፍሬ ልማት እድገቱ ከፍ እያለ ቢሆንም ገና ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቃል:: በእሱ ልክ ግን የገበያ ተደራሽነት ላይ እየተሠራ ባለመሆኑ ዘርፉ ለሀገር እድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዳይወጣ ሆኗል::

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሆርቲካልቸር ዘርፉ በወጪ ንግድ ሰፊ ድርሻ እንደነበረው ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ የሚላከው አበባ መጠን ቀንሷል ብለዋል:: እንደ አቦካዶ ያሉ ፍራፍሬዎችና ማዕዛማ ሰብሎች በተወሰነ ደረጃ ወደ ሶማሊያና ጅቡቲ እንዲሁም በጣም ጥቂት ደግሞ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይላካሉ ያሉት ዶክተር ሶፊያ፣ ይህም ቢሆን ካለው ትልቅ አቅም አኳያ የሚላከው ምርት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉትም፤ ለሆርቲካልቸር ዘርፉ አፈፃፀም ደካማ መሆን በርካታ ችግሮች በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ:: የመሬት አቅርቦት፣ የመሠረተ ልማት በተለይም የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት ችግሮች ይስተዋላሉ:: አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጎርፍ በስፋት ስለሚከሰት አምራቾችን ከሥራ ውጭ የሚያደርግበት ሁኔታ ይታያል::

የፋይናንስ እጥረት ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑንም ጠቁመው፣ የግብዓትና አቅርቦት ለማሟላት ፋይናንስ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፤ ከዚህም አንጻር ውስንነት እንዳለ ጠቅሰዋል:: ‹‹በተለይ አዳዲስ ዘርፉን ለሚቀላቀሉ አካላት በቂ የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር፣ የገበያና የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ውስንነት፤ የማበረታቻ ሥርዓት አለመዘርጋቱና የመልካም እርሻ አስተዳደር አለመኖር አልሚዎች በስፋት እንዳያመርቱ ማነቆ መሆናቸውን አመልክተዋል::

ሚኒስትር ዴኤታዋ በመሬት አቅርቦት ላይ የሚታየው ችግርም ዋነኛው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረው፣ በተለይ አማራ ክልል ላይ ለሆርቲካልቸር ልማት የታሰበ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የተደረገበት ሁኔታ አለ›› እንዳለ ጠቅሰዋል:: ይህ መሬት ለአልሚዎች በጊዜው እንዲተላለፍ ባለመደረጉ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ያስረዳሉ:: መሬቱ የሆርቲካልቸር ልማት በክላስተር ለመሥራት በአማራ ክልል ታስቦ የተዘጋጀ እንደነበር ያመለክታሉ::

ይህን አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም የአማራ ክልሉን የቆንዝላ ሆርቲ ፓርክ ጠቅሰዋል:: በአካባቢው ወደ 155 ሄክታር መሬት ለአልሚዎች መተላለፍ ሲገባው አለመተላለፉ እንደ ሀገር ለታየው ደካማ አፈፃፀም አብይ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል:: ችግሩ ከስድስት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የዘለቀ መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹ከዚህ ቀደም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን ግን መፍትሔ አላገኘም›› ሲሉ ያነሳሉ::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ መሬቱ ለአልሚዎች ላለመተላለፉ በርካታ ችግሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ:: የኃይል አቅርቦት፣ የ21 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ አለመጠናቀቅ፣ የፀጥታ ችግር መሬት ለአልሚዎች እንዳይተላለፍ ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ:: በእነዚህ ችግሮች ምክንያት 32 ሺ ቶን ምርት ሳይገኝ ቀርቷል፤ ከዚህ ይገኝ የነበረ 140 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት አልተቻለም:: ከ4ሺ 80 በላይ የሥራ እድል መፍጠር አልተቻለም::

ዶክተር ሶፊያ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በማጠናቀቅ ፣ የኃይል አቅርቦቱንም በማስፋፋትና መስኖውን በማገናኘት፣ የተጀመረውን የ21 ኪሎ ሜትር መንገድ ዝርጋታ በመጠናቀቅ መሬቱን በአፋጣኝ ወደ ልማት ማስገባት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ:: ወደ መሬት ባንክ የተመለሰውን መሬትም ለባለሀብቶች በአግባቡ ማስተላለፍ ይገባል ይላሉ:: ለእዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለስልጣን እና የአማራ ክልል የሚመለከተው አካል በቀጣይ በጀት ዓመት ኃላፊነታቸውን ወስደው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል:: በማምረት ሂደት ላይ ያሉ ኩባንያዎችም የመሬታቸውን አቅም አሟጠው ያለመጠቀም ችግር እንደታየባቸውም ተጠቁሟል::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ እንደ ሀገር በሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ 138 ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ 27 ሺ 629 ሄክታር የሚለማ መሬት አለ:: ከዚህ ውስጥ 21ሺ 718 ሄክታር ነው የለማው፤ 5ሺ 911 ሄክታሩ አለማም:: ከዚህ ውስጥ አንድ ሺ 300 ሄክታሩ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ነው:: ይህንን መሬት ወደ ልማት ለማስገባት ከአልሚዎችና ከክልሎች ጋር መግባባት ተፈጥሮ እየተሠራ ነው::

መሬቱ ያለማበት ምክንያትም ተለይቷል፤ አንዳንዱ አልሚ መሬቱን ከያዘ በኋላ ሌላ ፍላጎት የሚያማትርበት ሁኔታ እንዳለ ታውቋል:: የአበባ ገበያ መቀዛቀዙን ተከትሎ ወደ እንጆሪ ልማት የዞሩ አልሚዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ‹‹በተለይም የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ፍቃድ ሰጥቷቸው ወደ እንጆሪ ልማት የገቡ ኩባንያዎች አሉ›› ይላሉ::

በአቅም ውስንነት፣ በሎጅስቲክ እጥረትና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት አልሚዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዳያለሙ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል:: ‹‹በእነዚህ ምክንያቶች በአበባ ብቻ ቢያንስ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጥተናል፤ ይህ እጅግ ያስቆጫል፤ አቅሙም ሀብቱም እያለ ያለመሥራታችን ውጤት ነው›› ሲሉም ይናገራሉ:: ሆኖም ከ2017 ጀምሮ ለልማት ያልዋለውን መሬት ወደ ልማት ማስገባት ከተቻለ ከእቅዱም በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት የሚቻልበት እድል እንዳለ ጠቁመዋል::

በመድረኩ ለዚህ የመፍትሔ ሃሳብ ተብሎ የተቀመጠው የኩባንያዎችን የመሬት አጠቃቀም ወቅታዊ በማድረግና የቀረቡ ጥናቶችን በማደራጀት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ነው:: አሁን ከእያንዳንዱ ኩባንያ ጋር የማነበብ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ የቀረውን መሬት ወደ ልማት መግባት ይገባዋል የሚል አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል::

ዶክተር ሶፊያ ‹‹በቀረበው የዳሰሳ ጥናት መሠረት ውሳኔው ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ግን መሬቱ ለሌላ አላማ ይዋል ሳይሆን አምራቾቹን በመደገፍ በትክክል ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረጉ ነው ተመራጭ የሚሆነው›› ሲሉም ያስገነዝባሉ:: ይህንንም ግብርና ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋራ ሆነው ድጋፍና ክትትል በማድረግ ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ባይ ናቸው::

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ፤ ለኢንቨስትመንት ቦታ የተሰጣቸውና በአበባ ልማት ላይ ተሰማርተው በኤክስፖርት ምርት ሙከራ ላይ የነበሩ ኩባንያዎች ሥራ ያቆሙ አሉ፤ ከእነዚህም መካከል በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሥራ ያቆመው አቢሲኒያ የተባለ ኩባንያ ይጠቀሳል:: በዚሁ ክልል ቆቦ አካባቢም ሰባት አትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች ሥራ ያቆሙበት ሁኔታ እንዳለ ተጠቁሟል::

‹‹በእነዚህ ምክንያቶች ብቻ 17 ሺ 920 ቶን አትክልትና ፍራፍሬ ሳይለማ ቀርቷል ፤ በዚህም ወደ 14 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ገቢ ማጣት ውስጥ ተገብቷል›› የሚሉት ዶክተር ሶፊያ፤ ያለማውን መሬት ወደ ሥራ ለማስገባት መሬቱ ያለበትን አካባቢና የአልሚውን ሁኔታ በማጥናትና በድጋሚ በማደራጀት የውሳኔ ሃሳብ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: እነዚህ ኩባንያዎች ማልማት የማይችሉ ከሆነ ከክልሎች ጋር በመነጋገር መሬቱ ወደ ሌሎች አልሚዎች እንዲተላለፍ ማድረግ ይጠበቃል ሲሉም ጠቁመዋል:: በተቻለ መጠን እስከ አራተኛው ሩብ ዓመት ድረስ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል አቅጣጫ መያዙንም ነው ያመለከቱት::

በሌላ በኩል ባለሀብቶችን በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ የከፈሉበትን መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ያለመስጠት ሁኔታ በዘርፉ ተዋናዮች እንደ ትልቅ ተግዳሮት ይነሳ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ረገድ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ይነሳ የነበረው ቅሬታ በአሁኑ ወቅት ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል:: ከመሠረተ ልማት አኳ,ያ የሚነሱ ቅሬታዎችንም በተለይ የኃይልና የቴሌኮም አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም የበርካታ ኩባንያዎች ቅሬታ በተናጠል የተፈተላቸው መሆኑን ተናግረዋል::

ጎርፍ በቢሾፍቱ፣ ሰበታና ወልቂጤ አካባቢ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተው፤ ‹‹ቢሾፍቱ ከባቡር መንገድ ግንባታው ጋር ተያይዞ የጎርፍ ችግር አለ:: ለዚህ ችግር ባለቤቱ ማነው የሚለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ አንስተናል፤ ባለሀብቶቹም ችግሩን ለመፍታት ለመተባበር ፈቃደኛ ናቸው፤ በቀጣይ ዓመት የሚፈቱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት›› በማለት ተናግረዋል::

‹‹ግን ቋሚ መፍትሔ የሚፈልግ በመሆኑ በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነቱ አለ፤ እየተሠራም ነው::›› ሲሉም አስታውቀዋል:: ሁሉም ችግር በመንግሥት እንደማይፈታ ጠቁመው፣ የግል ባለሀብቱ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻል እንዳለበትም አስገንዘበዋል::

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን የሆርቲካልቸር ዘርፉን ችግር ለመፍታትም የዘርፉ አንኳር ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦችን ያጠቃለለ ብሔራዊ የአስር ዓመት ረቂቅ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል:: ዘርፉ አሁን ለ200 ሺ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸው፣ የስትራቴጂው ትግበራ በሚጠናቀቅበት 2026 ላይ ቁጥሩን ወደ ሁለት ሚሊዮን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል::

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የዘርፉ ተዋናዮች በበኩላቸው ሀገሪቱ በሆርቲካልቸር ዘርፍ የሚገባትን ያህል ገቢ እንድታገኝ ከተፈለገ ከመሠረተ ልማት፣ ከፀጥታና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: በተለይ ችግሩን ተቋቁመው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶችን በመደገፍ ምርታማነታቸው እንዲጎለብትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት አሁን ከሚገኘው በላይ በላቀ ሁኔታ እንዲጨምር መሥራት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል::

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You