ነገን ለመለወጥ የምንችለው ሁላችንም ነገን አስበን ሥንሠራ ነው። ነገን አስበን የምንሠራው ደግሞ ትናንት ላይ ከተቸከለ አስተሳሰብ ወጥተን ነገን ማየትና ማለም፤ የጋራ ራዕይ ኖሮን ለመሻገር በጋራ መስራትና መመካከር፤ ተመካክረንም መግባባት ስንችል ነው። ይሄ ደግሞ ሕዝብ ወክዬና በሕዝብ ተመርጬ ነገ ሀገር እመራለሁ ከሚል የፖለቲካ ፓርቲና ፖለቲከኛ ጋ ሲሆን ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡
ምክንያቱም ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ ፓርቲ ከግለሰባዊ እሳቤ ከፍ ያለ ነው፤ ሀገርን ማወቅ፣ ሕዝብን ማድመጥና መረዳትን፤ ሀገርና ሕዝብ የሚሹትንና ሊደርሱ የሚፈልጉትን ቀድሞ መተንበይን፤ ከትናንት ክስተትና ሁነት ላይ ዕይታን አንስቶ፣ የነገ መዳረሻን ማማተርና ለዛም ራስን ማስገዛትን፤… በብዙ መልኩ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእኔ እና ከፓርቲዬ ሀገሬ ትቀድማለች ብሎ መነሳት፤ ሀገር ከምንም በላይ ናት ብሎ ማሰብ ይገባል።
ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ንግግር፣ በአንድ ሀገር እድገትና ልዕልና፣ ለሕዝቦቿም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን መሆን ዜጎች፣ በተለይም የፖለቲካ ተዋናዮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው፤ ራሳቸውን በምን መልኩ መግለጥ እንደሚገባቸው፤ በምን አይነት እሳቤ ሀገርና ሕዝብን አስቀድመው መሄድና መሥራት እንዳለባቸው የሚያመላክትም፤ የሚያሳስብም በመሆኑ ነው ለሃሳቤ መንደርደሪያ የተጠቀምኩት፡፡
ወደራሴ ሃሳብ ስመለስ፣ መቼም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያገባው ሰው ወይም ፓርቲ ወይም ድርጅት… ማነው የሚል ጥያቄ አላነሳም። ምክንያቱም በሀገሩ ጉዳይ የማያገባው የለምና ፤ ይህን ስል በሀገሩ ጉዳይ ላይ ተመልካች ፤ ታዛቢ፣ ምን ቸገረኝ ባይ አላዋቂ ወይም ደግሞ ሀገር ስትበጠበጥ አተርፋለሁ ባይ፣ ሁከትና የሰላም መደፍረስን የሚሻ ግን አይኖርም ብሎ አለማሰብ አይቻልም። ይኖራል ፤ ደግሞም አለ።
ግን አርቀን ማሰብ፣ ቆም ብለን በበሰለ አእምሮ አውጥተንና አውርደን መድረስና መቀበል ያለብን ነገር ቢኖር፤ ሀገር ከምንም ከማንም በላይ መሆኗን ላይ ነው። ከማንም በላይ የሆነችው ሀገራችን ሀገር ሆና እንድትቀጥል ደግሞ የእያንዳንዳችን የፖለቲካ ፓርቲ፣ አባላቶችና ደጋፊዎች ትልቅ ሃላፊነት አለብን። ይሄንን ነው ጠንቅቀን ማወቅና መረዳት ያለብን።
አንዳንዱ ’ኮ ጭር ሲል አልወድም ጥግ ይዞ በወሬ ብቻ ሲፈትል የሚውል ነው። ሌላ ሁለተኛና ሶስተኛ ሀገር ያለው ይመስል፣ ለሀገሩ እድገት ሳይሆን ውድቀት፤ ሰላምን ሳይሆን ግጭትን ሲጠምቅና የጥላቻ መርዝ ሲግት የሚያድር አይጠፋም። ግን ለምን ኩርፊያ?! ልጅ እናቱን ያኮርፋል? አኩርፎስ የት ይደርሳል። እናት እኮ ሁልጊዜም እናት ናት። እንድትጠፋ፣ እንድትጎዳ፣ እንድትጎሳቆል የሚፈልግ ማንም ልጅ አይኖርም። የእናት ጉስቁልና የሁሉም ነውና ጉስቁልናዋን ማየት የሚመኝና የሚወድ የለም። ይልቁንም የቸገራትን ሞልቶ፣ የጎበጠውን አቅንቶ አለሁ አይዞሽ ነው የምትባለው።
ሀገርም እንደዚች እናት ናት። ብዙ ጉድለት ሊኖር ይችላል (ከገዢው ፓርቲ፣ ከአስፈጻሚዎች፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች…) ፤ ብዙ ጥፋቶች ተፈጽመው ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ የራስን ስህተት ካለማየት የሀገር መሪን ስህተት ብቻ የመቁጠር ነገር ሊኖር ይችላል። ወይም ደግሞ እኔ ያልገባሁበት፣ እኔ ይሁን ያላልኩት ልማት ልማት አይደለም ብሎ ከማሰብ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ምንም ይሁን ምን ግን ሁሉም ነገር ትክክል ሊሆን የሚችለው ቀና ማሰብ ስንችል፤ ቀና የሚያሰቡ ሰዎችን፣ አመራሮችንና ሌሎችንም በቀና መንፈስ መረዳትና መደገፍ ስንችል ነው።
አሁን ባለው አመራር ምንም ጥፋት ወይም ችግር የለም ብሎ ማሰብ አይቻልም። ብዙ ችግሮች አሉ። ሙስናው በየመስኩ አይን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጦ ከትንሽ እስከ ትልቁ ይታያል። ይህን እውነት እየመረረንም ቢሆን መቀበል ይገባል። ነገር ግን በድፍኑ እንቃወም ካልን ቀጥ ያለው ሁሉ ጠማማ ፤ ነጩ ጥቁር ይሆንብናል። ብርሃን ከማየት ይልቅ ጨለማውን ማማተር ያመዝንብናል።
እናም ማድረግ የምንችለው በመጀመሪያ የራስን ቀናነት ይዞ መገኘት ነው። ነገሮችን ሁሉ አጣምሞ ከመመልከት ቀና አድርጎ ማየት በእይታ ውስጥ የተጣመመ ነገር ቢኖር እንኳን እሱ የሚቃነበትን ነገር መሻት ነው። ደግሞም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሀገር ሀገር ናት። ለማንም የማንተዋት ምትክ የሌላት ናት። እኛም ከእሷ የማንወጣና የማንርቅ ዜጎች ስለሆንን ጉስቁልናዋን ሳይሆን እድገቷን መመኘት ለእድገቷ መሥራትና መልፋት ያስፈልጋል። የሆነ ፓርቲን፣ የሆነ መሪን ስለጠላን ብቻ ሀገራችንን የሀገራችንን ብራንድ የሆኑ ተቋማትን ስም ጥላሸት ስንቀባ መኖር አይገባም።
ምክንያቱም የትኛው ሀገር በየትኛውም መልኩ እድገታቸው አልጋ በአልጋ አልሆነም። ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ሁሌም የምናነሳቸው እነ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር ድህነት በዳዴ ያስኬዳቸው ሀገሮች ነበሩ። ቻይና ዛሬ የዓለም ተጠቃሽ ሀገር የሆነችው ከዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት ምን ያህል በድህነት ውስጥ እንደነበሩ ታሪካቸውን ደረታቸውን ነፍተው፣ አንገታቸውን ቀና አድርገው ይነግሩናል። ሌላው ቀርቶ የሚልሱት የሚቀሱት አጥተው ቆዳን ምግብ አድርገው ማሳለፋቸውን እንደ ጀብዱ ያነሱታል። ዛሬ እሱ ታሪክ የለምና። ታሪክ ሰርተው ታሪካቸውን ቀይረዋልና የበለጸጉ ሀገሮች እንድንላቸው ግድ ሆኗልና።
ኢትዮጵያውያንም የጀግንነት የድል ታሪኮቻችንን፣ ካለዘመናዊ መሣሪያ ሙሉ የሀገር ፍቅርና ክብርን አንግበን በአሸናፊነት ተወጥተናል ብለን አኩሪ ታሪካችንን እንደምናወሳው ሁሉ፤ እነሱም ከድህነት ወጥተው በከፍታ ማማ ላይ የተፈናጠጡበትን ታሪክ በኩራት ያወሱታል። እውነት ነው የአንድ ታሪክ ባለቤት እንደመሆን ለትውልድ የሚያኮራ እንደ ጀግንነት የሚወሳ ነገር የለም።
ዛሬም ለሀገራችን የምንመኘው የዚህ ትውልድ የልማት አርበኛ ፤ ሀገርን ከድህነት ያወጣ ትውልድ ተብለን በታሪክ መዝገብ መስፈርን ነው። ተረጂ ሳንሆን ረጂ ሆነን በዓለም ዙሪያ የምንታወስ ሀገር መሆንን ነው። ለዚህ ደግሞ የሃሳብ አንድነት ያስፈልጋል። እኩል ስለሀገር ማሰብ የታሰበውን መልካም ነገር ወደ ተግባር መለወጥና መሥራት፣ ለልማትና ዕድገት ቅድሚያ መስጠት ፣ ወዘተ ያስፈልጋል። ለዚህ መሻታችን እውን መሆን ደግሞ ተፎካካሪና ገዢ ፓርቲ ሳንል ለአንድ ሀገር እድገት እንደ አንድ ሆነን መቆምን ይጠይቃል ።
ሆኖም አሁን አሁን አንድ የምንታዘበው ጉዳይ አለ። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉዳይ። የተፎካካሪ ፓርቲዎች አለን የሚሉትና ድምጻቸውን የሚያሰሙት ምረጡን እያሉ የሚያደርቁን መቼ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። አምስት ዓመት ጠብቀው በምርጫ ወቅት ቲሸርቱ፣ በራሪ ወረቀቱ ፤ ወሬው ሁሉ ይደራል ። ሀገር በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ናት እስክንል ድረስ፤ የፓርቲዎች አይነትና ብዛት ሁሉ አስደማሚ ይሆናል። ይሄ ሁሉ ፖለቲካ ፓርቲ ከየት ተፈለፈለ እስክንል ።
ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ደግሞ እስካሁን እንዳየነው ሁሉ መኖራቸው እስኪጠፋን ስማቸው ከአእምሯችን እስኪፋቅ ድረስ ድምጻቸውም ስማቸውም ይጠፋል። “አሉ እንዴ?“ የሚለውን ሃሳብ እንኳን ለማንሳት የሚያስገድዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰበሰቧቸው ሲባሉ ብቻ ይሆናል። ካልሆነ ግን በየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ በየትኛውም የልማት አጀንዳ ላይ በየትኛውም መልኩ ሲሳተፉ አይታዩም።
ይሁን እንጂ በሀገራዊ የልማት ተግባር ላይ መሳተፍ (ለምሳሌ፣ በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ መሠማራት ማለት፣ ችግኝ ተከላ ላይ መገኘት ፤ የአረጋውያን ቤት እድሳት ላይ መሳተፍ በሌሎችም ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ አለን ብሎ መቆም) ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ቢሆንም፤ በእኛ ሀገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን ይሄ የተለመደ ተግባር አይደለም፡፡ ይሄን ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ለምን አይሳተፉም ? ለምን የሀገር ጉዳይ ጉዳያቸው መሆኑን ተገንዝበው ከፊት ቀድመው ስለ ሕዝብ ጥቅም አያቀነቅኑም? ለምን መንግሥት የሚሠራውን ልማት ማበረታታት ጉዳያቸው አይሆንም? የመንግሥትን ስህተቶች ለቅሞ ማውጣት ለምን አልቻሉም… እያልን መጠየቃችን አልቀረም።
ዛሬ ሀገር እየመራ ያለው ገዢው ፓርቲ ነገ ላይኖር ይችላል። ትናንት ሀገር ሲመሩ የነበሩ መሪዎችና ፓርቲዎችም ዛሬ የሉም። ከትናንት ወዲያ ከዛም በፊት የነበሩ የሀገር መሪዎች አሁን የታሪካችን አካል ነው የሆኑት ፤ ሀገር ግን አለች። ሕዝብ ግን አለ ። ሀገር ላይ ብንሠራ ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ ለሚመጣው ትውልድ የተመቸች ሀገር ማቆየት ይሆናል።
ዛሬ የምንጠቀመውኮ ከዚህ ቀደም የነበሩ መሪዎች የሠሩልን እና ያሠሩልን ነው፡፡ እኛም እየሠራን ያለነው የእነሱ ሥራ እርሾ ሆኖን ነው። አሁን ደግሞ ዘመኑን የዋጀ ልማት ፣ የቴክኖሎጂ እና የትምህርት እውቀት ልማት ያስፈልገናል። ለእዛ ደግሞ ተጠሪዎች እኛ ነን። ተቃዋሚና ተፎካካሪ፣ እንዲሁም ደጋፊ ሳንባባል ለሀገራችን መሥራት አለብን። ሀገራችን ላይ ሠርተን ታሪካችንን በደማቁ በማጻፍ ዐሻራችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል።
ይህ ሲሆን ስንኖር በስራችን ተደስተን በልማቱ ተጠቃሚ ሆነን እንቆያለን ፤ ስናልፍ ታሪክ አስቀምጠን ዐሻራችንን አኑረን ይሆናል፤ እናም የአሁን ዘመን ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን ሁሉንም ነገር እያዩት ያለው ከዚህ አንጻር ይሆን? ወይስ ሁሉንም ነገር በመቃወም? ሁሉንም ነገር በመቃወም ከሆነ ስህተቱ እዚህ ላይ ይሆናል። የአእምሮ ቅኝቱ መስተካከል የለበትም ?
እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። ለወቀሳና ለመቃወም ብቻ አዳራሽ ሞልቶ ትችት ማቅረብ ከጥቅሙ ይለቅ ትዝብቱ ይሰፋል። አዳራሽ ሙሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አሁንም ካሉን በምርጫ ወቅት ከ100 በላይ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ብቅ ካሉ ምነው ልማቱ ላይስ ብለን እንጠይቃለን። እንደ አንድ ዜጋ አሁን ከየት በቀሉ ማለታችን አይቀርም።
ይሄ እንዳይሆን ከፓርቲዎች ብዙ መሥራት በሀገር ጉዳይ መተባባር ይጠበቃል። ይሄ መንግሥትን መደገፍ፣ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲን ማገዝ አይደለም ። ለሀገር መሥራት ነው። ሕዝብን ማገዝ እና መደገፍ ነው። ምነው ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውን ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው በበጎ ፍቃድ ሥራ ላይ አይሰማሩም? ቤት ማደስ ለምን አይሳተፉም? ቤት የሚታደሰውና የሚኖርበት መቼም መንግሥት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን አይሆንም፤ ይልቁንም በችግር ውስጥ ያለው ምስኪን ዜጋ፣ የከተማው ነዋሪ ነው።
አርሶ አደሩን በእርሻ ሥራ፣ በእርሻ መሳሪያ ብናግዘው ያገዝነው ያንን አርሶ አደሩ የሚኖርበትን ክልል ሃላፊ ወይም የመንግሥትን አካል አይደለም፡፡ ነገ ምርቱን የሚያቀርብልንን አርሶ አደር ነው። በደም ልገሳ ብንሳተፍ የምንረዳው የመንግሥት ባለሥልጣንን አይደለም፡፡ ደም በማጣት በደም መፍሰስ ሕይወት ሰጥታ ሕይወቷን የምታጣውን እናት ነው። ሌላም ሌላም ማንሳት ይቻላል። ብዙ ብዙ መጻፍ ይቻላል።
ዋናው ነገር ግን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የት ናችሁ ለማለት ነው። በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል ለማለት ነው። አሁን የመንግሥትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የታየው የውይይት መድረክ በውይይት መድረኩ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተነሱ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦች ናቸው ፡፡ እየተነጋገሩ እየተራረሙ መሄድ የሚያስችሉ ናቸው።
ይሄ ሲባል ግን በመንግሥት በኩል የመንግሥት አስተዳደር ፍጹም ትክክል ነው ገፊ ምክንያቶች የሉም ለማለት አይቻልም። ይኖራሉ፤ መቼም ፉክክር ብሎ ሁሉንም ነገር አልጋ በአልጋ አድርጉ መጠበቅ አይቻልም። ችግሮች ያጋጥማሉ፣ ጎርባጭ መሰናክሎች ይኖራሉ፤ እነሱን በጥበብና በዘዴ እያለፉና እየተነጋገሩ ማስቀረት ባይቻል እንኳን መቀነስ ይቻላል። ምክንያቱም አርቀን የምናማትረው ሀገር አለችንና ነው።
በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊነት ቦታዎች የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች ተቀምጠዋል። መቀመጣቸው ጠቀመ እንጂ ሀገርን አልጎዳም። ይልቁንም የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋ ጅምር ጭላንጭል፤ የሠለጠነ የፖለቲካ ምህዳርና አሠራርን የሚፈጥር ነው። ይሄ እንዲሰፋ ለማድረግ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ያስፈልጋል። ጥሩ ተፎካካሪ መሆን መቃወም ብቻ አይደለም።
የሠለጠነ ፖለቲካ ማለትም ይሄው ነው፤ ምክንያቱም የሠለጠነ ፖለቲካን የሚያራምድ ግለሰብና ቡድን የተሻለ ሃሳቦችን የሚያመነጭ፣ ችግሮቹን ፈልፍሎ በማውጣት እንዲታረሙ የሚያደርግ፤ ጠንካራ የፖሊሲ ሃሳብ አመንጪ ነው። በመነጋገር እና በመወያየት ለውጥ ለማምጣት የሚሞክር ነው። በመሆኑም ይሄን እውን የሚያደርግ በሁሉም መልኩ የሠለጠነ ፖለቲካ ከሁሉም በፊት ሀገርን የሚያስቀድም መሆን አለበት። ሰላም!
አዶኒስ (ከሲ.ኤም.ሲ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 /2016 ዓ.ም