ከአዲስ አበባ በ505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአርባ ምንጭ ከተማ በ1955 ዓ.ም እንደተቆረቆረች መረጃዎች ያመለክታሉ። በውብ ተፈጥሮ ሀብቶች የታደለችዋ ይህች ከተማ፣ ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶቿ መካከልም የአባያና ጫሞ ሀይቆች ፣ የአርባዎቹ ምንጮች፣ በአቅራቢያዋ የሚገኘው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ይጠቀሳሉ።
የአየር ንብረቷም ለነዋሪዎቿ፣ ለጎብኚዎቿ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማቷ ምቹ የሆነችው አርባ ምንጭ ከተማ በሙዝ ምርቷም በእጅጉ ትታወቃለች። የአሳ ሀብቷም በእጅጉ ታዋቂ አድርጓታል። በአባያ ሐይቅ ቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኙት ተዋቂ ሆቴሎች አረፍ ብሎ ወደ ሐይቁ ለተመለከተ ከተማዋ ከፍታ ስር እስከ አባያና ጫሞ ሐይቅ ድረስ የተዘረጋውና ልዩ ውበት እንድትጎናጸፍ ያደረጋት የደን ሀብት ባለቤትም ናት።
ይህች የበርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተቻችሎ መኖሪያ በመሆን የምትታወቀው ከተማ፣ በብሔሮቹና ብሔረሰቦቹ ውብ ባሕላዊ እስቶችም በእጅጉ ትታወቃለች። ከተማዋንና የመስህብ ስፍራዎቿን ብለው ቱሪስቶች የሚጎርፉባት አርባ ምንጭ፣ እሷን ብለው ከሚመጡት ቱሪስቶች በተጨማሪ ወደ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ጉዞ የሚያደርጉ ቱሪስቶች መተላለፊያም በመሆን ትታወቃለች።
ሌላው የከተማዋ ውበት የአዞ ራንች ነው። በእዚህም አዞን መጎብኘት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሯ በተጨማሪ፣ የአዞ ቆዳ ለውጭ ገበያ በማቅረብም ትታወቃለች።
ከተማዋ በመሠረተ ልማት በኩልም በብዙ መልኩ በአዎንታዊ የምትጠቀስ ናት፤ ከአዲስ አበባ ወደ ኮንሶ የሚዘልቀው የአስፋልት መንገድ ከተማዋን ሰንጥቆ ነው የሚያልፈው። የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም በአስፋልትና በኮብል ስቶን በሚገባ የተገነቡ ናቸው። የአውሮፕላን ማረፊያ፣ በርካታ ተዋቂ ሆቴሎችና ሪዞርቶች፣ ዩኒቨርሲቲ በውስጥ አቅፋ ይዛለች። የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ጨምሮ ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች መናኸሪያም ናት።
ከውጭና ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ዋና ምርጫ መካከል አንዷ የሆነችው ይህች ከተማ፣ እንደ ውሃ ኤሌክትሪክና ቴሌኮም ያሉ መሠረተ ልማቶቿም ከተማዋን ተመራጭ ካደረጓት መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህች ከተማ በቅርቡ ደግሞ ሌላ ውበት የሚያላብሳት ተመራጭ እንድትሆን የሚያደርጋትን፣ ለከተማዋ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብና በአቅራቢያዋ ለሚገኙ ክልሎች ሕዝቦች የሚሆን ግዙፍ ሆስፒታል ተገንብቶላታል። ወትሮም ባለሞገስ የሆነችው ይህች ከተማ ሆስፒታሉ ደግሞ በሞገስ ላይ ሞገስ አጎናጽፏታል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ኢንጂነር ቤዛ ተስፋዬ፤ የሆስፒታሉ ግንባታ የተካሄደው በይርጋለም ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ድርጅት መሆኑን አስታውቀዋል። ተቋራጩ ግንባታውን ያካሄደው ሆስፒታሉ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖም መሆኑን ጠቅሰው፣ በተሰጠው ዲዛይን መሠረት ግንባታውን ማካሄዱን አስታውቀዋል። ዲዛይኑም ጨምሮ በዘመናዊ ሁኔታ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ግንባታው መካሄዱንም አመልክተዋል። በተለይም የውጭ ሕክምና አገልግሎትን ማስቀረት በሚችል ደረጃ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ሲሉም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ የሆስፒታሉ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተጣለው በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም መሆኑን ጠቅሰው፣ ለግንባታውም አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ግንባታው 98 በመቶ መድረሱንና በከፊል ሥራ መጀመሩን አመልክተው፣ ቀሪ ውስን የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ እንደሚቀሩም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የሕክምና፣ የአስተዳደር እና 650 ተኝቶ መታከሚያ አልጋዎችም አሉት። ለአገልግሎትም 100 በመቶ ብቁ ነው። ከሐምሌ አራት ጀምሮ በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
አጠቃላይ የሆስፒታሉ ሕንፃ 21 ብሎኮች አሉት፤ እያንዳንዳቸውም ሶስት ፓርቲሽኖች አሏቸው። ፓርቲሸን ኤ፣ ፓርቲሸን፣ ቢ፣ ፓርቲሽን ሲ ተብሎ ተከፋፍሏል። ፓርቲሸን ኤ አገልግሎት የሚሰጠው ላውንደሪዎችን፣ ኪችኖችን እና ተኝቶ መታከሚያን ይይዛል።
ፓርቲሸን ቢ በተመሳሳይ ቢሮዎችንና፣ የኦፕሬሽን ክፍሎችን፣ የኤም አር አይ፣ የሲቲስካን እና ሌሎች ዘርፎችን እንዲሁም የአስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ይይዛል። ፓርቲሸን ሲ ላይ ደግሞ ዋናው በስተግራ በኩል የድንገተኛ ክፍሎች፣ በስተቀኝ በኩል የሕፃናት የድንገተኛ ክፍሎችን ይዟል። የሕፃናት ድንገተኛ እና ተኝቶ መታከሚያ የኦፕሬሽን እና አይሲ የመሳሰሉ የሕክምና አገልግሎቶችን መስጫ ክፍሎችም ይገኝበታል።
የሆስፒታሉ የተለያዩ ሕንፃዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። ሕንፃዎቹ የመብራት፣ የውሃ፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጨምሮ ዘመኑን ተከትሎ የተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ከሕንፃው ጋር የተያያዙ ቀሪ ሥራዎች አለመኖሩን ጠቅሰው በርክክብ ወቅት ያሉ የእርምት ሥራዎችን ጨምሮ የዋናው መግቢያ ሥራ ብቻ እንደሚቀሩ ኢንጂነር አቶ ቤዛ አስታውቀዋል።
ሌሎች መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ይህ በአጠቃላይና ስፔሻሊቲ ደረጃ የተገነባ ሆስፒታል፣ ለአካባቢው የመጀመሪያ የሚባል ተርሸሪ ሆስፒታል ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና በአጎራባች ክልሎችና ዞኖች የሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵውያንን ያገለግላል ተብሎም ይጠበቃል። የአካባቢው ማህበረሰብ በዚህ የሆስፒታል መሠረተ ልማት ግንባታ ትልቅ ተስፋ እንዳደረበትም እየገለጸ ነው።
ይህ በ25 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ እንደ ሀገር ሲታይም ከፍተኛ ደረጃ ያለው መሆኑ በምረቃው ወቅትም ተጠቁሟል። አሁን ባለበት ደረጃ በአጠቃላይና ስፔሻሊቲ ደረጃ ከ600 በላይ የታካሚ አልጋዎች አሉት።
የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ጥገና ፣ የአጥንት፣ የማህፀንና ፅንስ፣ የሕፃናት፣ የእናቶች፣ ከአንገት በላይ፣ የሥነ አእምሮና ሕክምናዎችን በተመላላሽ እንዲሁም በተኝቶ ሕክምና ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎም ነው የተገነባው። ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ ለምርመራ ይደረጉ የነበሩ ጉዞዎችን የሚያስቀሩና የተለያዩ ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች ያካተቱ የምርመራ ማሽኖች፣ ሲቲ.ስካን፣ ኤም.አር.አይ፣ ዲጂታል የኤክስሬይ ማሽኖች፣ ዘመናዊ የአልትራሳውንድ ማሽኖች፣ የተሻሻሉ የደም ምርመራ ማሽኖችና የተለያዩ የምርመራ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ላቦራቶሪዎችም ዝግጁ ተደርገውለታል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ አንዳርጌ ሆስፒታሉ ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል። አሁን ላይ በሕፃናት፣ በማህፀንና ፅንስ፣ በውስጥ ደዌና በቀዶ ጥገና ተመላላሽ ሕክምና እንዲሁም በተለያዩ የላቦራቶሪና የኤሜጂንግ ክፍሎች በተመላሽ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመላላሽ የሚመጡ የአጥንት ኬዞችን፣ የኦፕራሲዮን አገልግሎቶች እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ የሚያገለግል ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ክፍል መሳሪያ ለመግዛት የታሰበ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ቀደም ሲል አብዛኛው ሰው ሲቲ.ስካን፣ ኤም.አር.አይ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሀዋሳ፣ አዲስ አበባ፣ ሶዶ ከተሞች ለመሄድ ይገደድ የነበረበትን ሁኔታ ያስቀራል ይላሉ። አሁን በተመላላሽ አገልግሎት የጀመረው ሆስፒታሉ የድንገተኛ ሕክምና እና አስተኝቶ ሕክምና ቦታዎቹም ዝግጁ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የላቦራቶሪና የኢሜጂንግ አገልግሎቶች ሲቲ.ስካንን ጨምሮ አገልግሎት ይሰጣል። ሆስፒታሉ አዲስ እንደመሆኑም በሰው ሀብት ላይ ያለበትን የባለሙያ እጥረትም አለበት። ለዚህም በጊዜያዊ ድጋፍ ቅጥር እና ዝውውር የሰው ኃይል ለማሟላት ከትምህርት ሚኒስቴር እና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ ነው። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከአንገት በላይ፣ የቆዳ፣ ከፍተኛ የሥነ አዕምሮና የዓይን እንዲሁም የተኝቶ ሕክምና አገልግሎቶችንም ይጀምራል።
ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች አኳያ አብዛኛው ግንባታው የተጠናቀቀ መሆኑን እሳቸውም ገልጸዋል። የተወሰኑ የማጠናቀቂያ ቀሪ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የኦክስጅን ማምረቻ ሥርዓት የተዘረጋ ቢሆንም የሲቪል ሥራው አልተጠናቀቀም ብለዋል።
ቀሪዎቹ የሲቪል ሥራዎች ሲጠናቀቁም ለእያንዳንዱ የአገልግሎት ዘርፍ የሚያስፈልጉ ሁሉ ከወዲሁ ተገጥመዋል ሲሉ ተናግረዋል። ተጨማሪ የሕክምና እቃዎች በግዢና በእርዳታ መልክ መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ እስካሁን ከ550 በላይ አልጋ ሂውማን ብሪጅ ከተሰኘ የስዊድን ግብረሰናይ ድርጅት በክቡር ዶክተር አዳሙ አንለይ አስተባባሪነት በእርዳታ መገኘቱንም ያመለክታሉ። ከሕክምና እቃ ጋር ተያይዞ ብዙም ክፍተት እንደሌላ እና በርካታ ማሽነሪዎች መኖራቸውንም ነው ያስረዱት።
ዶክተር ብርሃኑ እንደገለፁት፤ አሁን በተወሰኑ ባለሙያዎች በተመላላሽ ሕክምና ሥራውን የጀመረው ሆስፒታሉ ፤ ተጨማሪ ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ በኢሜጂንግ እና ራዲዮሎጂ እንዲሁም በላቦራቶሪ የሚሰሩ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር ከ100 በላይ ስፔሻሊሰት ሐኪሞች እንዲሁም የአስተዳደርና ሌሎች ባለሙያዎችን ጨምሮም ከሁለት ሺ በላይ ሠራተኛ እንደሚኖሩት ይጠበቃል።
ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ሆስፒታሉ ዘመናዊ የሕክምና ማሽኖች በተለይ የራዲዮሎጂ ማሽን፣ ኤም አር አይ የሕክምና መሳሪያዎች መገጠም ሥራ መጠናቀቁን ጠቅሰው፣ ለእዚህ ሥራ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች ስልጠና መጀመሩንም ያመለክታሉ።
የሲቲ.ስካን አገልግሎት አሁን እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኤም.አር.አይ ሰርቪስም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት እንደሚጀምር ጠቁመዋል። ዘመኑን የዋጁ የጥርስና የዓይን ሕክምና መሳሪያዎችም እንዳሉም አመልክተው፣ ለላቦራቶሪ አገልግሎት ከሚውሉ መሳሪያዎች አንዳንዶቹ እየተገጠሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ እንደተናገሩት፤ ሆስፒታሉ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩ የጤና አገልግሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ያስችላል። በሆስፒታሉ ምረቃ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ “ይህ ሆስፒታል መጠነ ሰፊ ርዕይ ያላቸው የሕክምና አገልግሎቶች ለመስጠት የተገነባ ነው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። “ገና ብዙ እርምጃ መራመድ ቢጠበቅብንም በጤናው ዘርፍ በቂ የሕክምና አገልግሎት ለዜጎቻችን ለማቅረብ ሰፋፊ ሥራዎች እየሰራን ነው” ሲሉም ጠቅሰዋል።
ለዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በማቅረብ ሥራ ለሚተጉ የጤና ባለሞያዎች ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀገራችንን የጤና ጥበቃ ሥርዓት ለማዘመን መንግሥት በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ ሀገራቸው በመምጣት አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪም አቅርበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም