የዲጂታል ዘርፉ የለውጥ መንገዶችና ተጨባጭ ለውጦች

ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል። ይህንን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ዘርፉን በሰው ኃይል ልማት ለመደገፍ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተግባር ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ በከፍተኛ ትምህርት እና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት አማካይነት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲስፋፋ ተደርጓል። ይህን ተከትሎም አያሌ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በእዚህ ዘርፍ እየተመረቁ የሥራውን ዓለም ተቀላቅለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉን የሰው ኃይል ከማልማት ጎን ለጎን ጥናትና ምርምሮችን ያካሂዳሉ። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የሚተገበረው ስልት እንዳለ ሆኖ በልዩ ትኩረት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው በሰው ኃይል ልማትም ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ በኩል እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ዘርፉ ራሱን ችሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ እንዲቋቋም ተደርጓል። በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ባለውና ዘርፉ ይበልጥ እንዲጎልበት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ በሚገኘው በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም አጀንዳዎች ተቀርፀው በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። መንግሥት የዘርፉን እምቅ አቅም በማጤን የግሉ ዘርፍ በቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰማራ አድርጓል፤ ሌሎች እንዲቀላቀሉም እየሰራ ነው፡፡

መንግሥታዊ ሥራዎች በእዚህ ቴክኖሎጂ እንዲፈጸሙ ማድረግ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሥራዎችን የግዴታ በዲጂታል መንገድ መፈጸም እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ነው። ዓለም አቀፍ ሁኔታውም ከዚህ ውጭ ሥራዎችን ማከናወን የማይችል መሆኑን እያመላከተ እንደመሆኑ መንግሥታዊም ሆነ የግሉ ተቋማት ሥራዎች በዲጂታሉ ዘርፍ እንዲታገዙ ማድረግ የግድ ሆኗል። ይህን ተከትሎ እየተከናወኑ ባሉ ተግባሮች ውጤቶች እየታዩ ናቸው።

ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሀገሪቱ ወሳኝና ወቅታዊ አጀንዳ መደረጉን ተከትሎም በተለይ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በአስር ዓመቱ እቅድ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ በሚል ከተያዙት ከግብርና ፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ማዕድን እኩል ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትኩረት መሰጠቱ ይታወቃል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የሚል ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶችና ሕፃናት የሚማሩባቸው፣ የሚሰለጥኑባቸውና ፈጠራቸውን የሚያጎለብቱባቸው ተቋማት ተከፍተው እየሰሩ ናቸው። ይህንን የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበላይነት ይመራዋል። በክረምት ወቅት ጭምር ታዳጊዎችና ወጣቶች የአይሲቲ አቅማቸውን እንዲያገለብቱ፣ የፈጠራ ሃሳባቸውን የሚያወጡበት እድል፣ ክህሎታቸውንም እንዲያጎለብቱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በተለይ ከፈጠራ ጋር በተያያዘ ውድድሮች በስፋት እየተካሄዱ ይገኛሉ። በወጣቶችና በሌሎች የተለያዩ ክፍሎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተገኙ የፈጠራ ውጤቶችን ማሳየት እንዲሁም የፈጠራ ውጤቶቹን ማጎልበት የሚቻልባቸው ኢግዚቢሽኖችና የውይይት መድረኮች በስፋት እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህም አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች የሠሩ አካላት ሥራዎቻቸው እየታዩላቸው ከመሆኑም በላይ አብረዋቸው ሊሰሩ የሚችሉ አካላትን የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው። የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች /startup ideas/ ሃሳባቸው እየታየ የሚያጎለብቱበት ሥርዓት ተዘርግቷል፤ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታም እየተመቻቸ ነው።

ሀገሪቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰጠችው ትኩረት ሌላው መገለጫ በከፍተኛ ወጪ ገንብታ ወደ ሥራ ያስገባችው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ / አይሲቲ ፓርክ/ ነው። በዚህ ፓርክ መንግሥት ለዘርፉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት መሆን ችሏል። ተቋሙ ወደ ሥራ ከገባ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም በአሁኑ ወቅት ለሀገሪቱ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉና በዘርፉ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ግዙፍ የዳታ ተቋማትን ጭምር እያስተናገደ ይገኛል።

የአዲስ አበባው የሳይንስ ሙዚየም፣ የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሌሎች ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።

በግሉ ዘርፍ፣ በሌሎች ተቋማት፣ ግለሰቦች ድረ ገጾችን በመጠቀም የሚያካሂዷቸው ሥራዎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ወይም ለዲጂታል ዘርፉ አዎንታዊ ተግባሮችን እያከናወኑ ይገኛሉ። እነዚህ ተግባሮች ሀገሪቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደፊት እንድትራመድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡

መንግሥትን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ በስፋት በመሰማራትና በዘርፉ የተከፈቱ መልካም እድሎችን በመጠቀም እያከናወኑ ባሉት ተግባር ምንም እንኳ ገና ብዙ ሥራዎች ቢቀሩትም፣ ሀገሪቱ ዓለም በዘርፉ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባሮችን ለማከናወን የምትችልባቸውን ምህዳሮች ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፤ በዚህም ውጤቶች ታይተዋል።

ሀገሪቱ ክፍያዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲፈጸሙ ማድረግ በጀመረችበት በአጭር ጊዜ ውስጥ በትሪሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በእዚህ ቴክኖሎጂ ማንቀሳቀስ ተችሏል። የባንኮች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ፣ወዘተ. ሪፖርቶችም ይህንኑ እያረጋገጡ ይገኛሉ።

እንደ ውሃ ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም ፣ ግብር ዓይነት ክፍያዎችን፣ ወዘተ. በጥሬ ገንዘብ መፈጸም እየቀረ ነው። ባንኮች ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር እየወጡ ይገኛሉ፤፤ ግለሰቦች ጥሬ ገንዘብ ከመለዋወጥ ወጥተው በዲጂታል መንገድ እያስተላለፉ ናቸው። በሱፐር ማርኬቶች፣ በትላልቅ ሆቴል ቤቶች፣ በትላልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ ወዘተ ክፍያዎች ዲጂታል እየሆኑ መምጣታቸው፣ አገልግሎት ተጠቅሞ ጥሬ ገንዘብ መምዘዝ ጨርሶ ሊቀር እንደሚችል የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እየታዩ ይገኛሉ።

የገንዘብ ዝውውሩ ዲጂታል መሆኑ ሰዎች ያለምንም እንግልት ባሉበት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲፈጽሙ፣ ጥሬ ገንዘብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በሕገወጦች ሊደረስባቸው የሚችለው ጉዳት እንዲቀር አድርጓል። የትራንስፖርትና መሰል ወጪዎችንም አስቀርቶላቸዋል። የመንግሥት ግዥዎችም እንዲሁ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲካሄዱ ማድረግ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ሙሉ በዲጂታል እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ሶፍትዌር /መተግበሪያ/ ማበልጸግ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ ከተካኑ ቆይተዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች ፣ ከሀገርም አልፈው ለውጭ ኩባንያዎች ጭምር በሶፍት ዌር ማበልጸግ፣ በዘርፉ የሰው ኃይል ስልጠና በመስጠትና በመሳሰሉት ላይም እየሰሩ ስለመሆናቸው ይታወቃል። ለአርተፊሻል ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበትም ይገኛል።

እነዚህ በዲጂታል ኢኮኖሚው እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ሀገሪቱ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የሰጠችውን ትኩረት እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርጻ ወደ ሥራ ማስገባቷን ተከትሎ የመጡ ጉልህ ለውጦች ናቸው።

እነዚህ ሥራዎች ያስገኙት ለውጥ ከዚህም የተሻገረ ሆኗል። በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያም ሀገሪቱ በአይሲቲው ዘርፍ ውጤታማ እየሆነች እንደምትገኝ አመላክቷል።

በበጀት ዓመቱ የአይቲው ዘርፍ ከአምራች ዘርፉ ቀጥሎ ጥሩ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያሥላሴ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ፈቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት በማምረቻ ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው። በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል። በቤት ግንባታ እና በግብርና ዘርፎችም ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች አሉ።

ዘርፉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተገኘበት ይህ አፈጻጸም ትልቅ ስኬት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የአይሲቲው ዘርፍ በእዚህ ደረጃ ላይ መገኘቱ የዘርፉ ኢንቨስትመንት ምን ያህል እየተስፋፋ እንደመጣም ያመለክታል። ከተሰጠው ትኩረት፣ እየተከናወነ ካለው ተግባርና ዘርፉ ካለው እምቅ አቅም አኳያ በቀጣይም ጥሩ አፈጻጸም ሊመዘገብ እንደሚችል ከወዲሁ መግለጽ ይቻላል።

መንግሥት በዚህ ዘርፍ የሚያከናውን ተግባር አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል። የዘርፉን የሰው ኃይል ማልማት ላይ ትኩረት ሰጥቷል። በቅርቡ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ጋር ኢትዮጵያ ባደረገችው ስምምነት አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ዘርፉ በኮዲንግ ለማሰልጠን መታቀዱም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህ ምቹ ሁኔታ ወጣቱ ትውልድ በመተግበሪያ ማበልጸግና በመሳሰሉት ሰልጥኖና አቅሙን ይበልጥ አጎልብቶ ሀገሪቱ በዘርፉ የሚያስፈልጋትን እንድታገኝ፣ ከዚያም አልፎ የዲጂታል ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስገኘው ገቢ ሀገሪቱም የበለጠ ተቋዳሽ እንድትሆን እንደሚያስችል ታምኖበታል።

ይህ ለወጣቶቹ የተገኘው እድል መንግሥት ለዘርፉ ካለው ቁርጠኝነት ከተባበሩት አረብ ኤምሬት መንግሥት ጋር ባደረገው የወዳጅነት ግንኙነት ቱሩፋት ነው። ይህም መንግሥት ዘርፉን የላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል። ለዚህም ነው በዲጂታል ቴክኖሎጂውም ሆነ በጥቅሉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት አድማሱን አስፍቶ መቀጠል አለበት የምንለው።

እስመለአለም

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You