በመላው ፈረንሳይ የባቡር ትራንስፖርት ተቋረጠ

በመላው ፈረንሳይ የባቡር ትራንስፖርት ተቋርጧል።

በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ተወዳጁ የኦሎምፒክ ውድድር ከ100 ዓመት በኋላ ወደ ፓሪስ ተመልሷል። ትናንትና አመሻሽ በጀመረው በዚህ ውድድር ላይ ከሰባት ሺህ 500 በላይ የዓለም አትሌቶችን ጨምሮ ሚሊዮኖች ይታደሙታል።

ይሁንና በመላው ፈረንሳይ በትናንትናው ዕለት አዳር በባቡር ሀዲዶች ላይ ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት የባቡር ትራንስፖርት ተቋርጧል። የሀገሪቱ ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት እንዳስታወቀው ሆን ተብሎ በባቡር ሀዲዶቹ ላይ በተፈጸመ ከባድ ጥቃት ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን ገልጿል።

ይህንን ተከትሎም በመላው ፈረንሳይ ፈጣን ባቡር ትራንስፖርት የተሰረዘ ሲሆን ጉዳዩ በሀገሪቱ ድንጋጤን ፈጥሯል ተብሏል። ጥቃቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ውድድርን ለማስተጓጎል ታስቦ የተፈጸመ እንደሆነም ተገልጿል።

ለኦሎምፒክ ውድድር ወደ መክፈቻ ቦታው ለመጓዝ ቲኬት የገዙ ሰዎች ጉዟቸውን እንዲያራዝሙ ተጠይቀዋል። አደጋው በተለይም ፓሪስን ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያስተሳስሩ የባቡር መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።

የፈረንሳይ ትራንስፖርት ሚኒስትር ፓትሪስ ቬርግሪት በኤክስ አካውንታቸው ላይ እንዳሉት ጥቃቱ የሀገሪቱ ባቡር ትራንስፖርትን ለቀጣዮቹ ቀናት ያስተጓጉላል ብለዋል።

ጥቃቱን ያወገዙት ሚኒስትሩ የባቡር ትራንስፖርት ሠራተኞች የተቋረጠውን ትራንስፖርት ለመመለስ እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You