ሩሲያ እና ቻይና የመከላከያ እና ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ ውይይት አደረጉ። ሁለቱ የእስያ ኃያላን ሩሲያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ የመከላከያ እና ውታደራዊ ንግግሮችን ማድረጋቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል።
“ወሰን የለሽ” ያሉትን ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ያሉት ሞስኮ እና ቤጂንግ አሜሪካ በእስያ ተፅዕኖዋን ለማስፋት እየሠራች ነው ሲሉ ተችተዋል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስትሩን አንድሬ ቤሎሶቭን ጠቅሶ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ” የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ክፍሎች አንድ አይነት ዓለምአቀፋዊ ግምገማ እና በአሁናዊ ሁኔታዎች ምን መደረግ አለበት? በሚለው ጉዳይም ተመሳሳይ አረዳድ ያላቸው ናቸው”
ብሏል።
ቤሎሶቭ ከቻይና ሴንትራል ሚሊታሪ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ጋር ተገናኝተው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል። ከስብሰባው በኋላ የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ እና እንደሚያስፋፉ እና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ያለውን የመረጃ ልውውጥ ባለበት እንደሚያስቀጥሉ ተስፋ እንዳለው ገልጿል።
ቤሎሶቮ በቤጂንግ ጉብኝት ያደረጉት ቻይና አስፈላጊ ከሆነ በታይዋን ላይ የኃይል እርምጃ እንደምትወስድ በዛተችበት ወቅት ነው። ቻይና በታይዋን ዙሪያ 125 የጦር አውሮፕላኖችን እና የጦር መርከብ በመጠቀም ግዙፍ የተባለ የጦርነት ልምምድም አድርጋለች።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በየካቲት 2022 በዩክሬን ልዩ ላሉት ወታደራዊ ዘመቻ ጦራቸውን ከማሰማራታቸው ከሦስት ሳምንታት ቀደም ብለው በቤጂንግ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነበር ቻይና እና ሩሲያ “ወሰን የለሽ” ግንኙነት ለማድረግ መወሰናቸውን ይፋ ያደረጉት።
እኤአ በዚህ ዓመት ባለፈው ግንቦት ወር ሁለቱ የአሜሪካ ተቀናቃኞች ፑቲን እና ሺ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመክፈት ቃል ገብተዋል። ፑቲን እና ሺ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን የገለጹት ቤሎሶቭ “ውጤታማ እና ከባድ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ” ብለዋል።
አሜሪካ ቻይና ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶችን እያቀረበች ነው የሚል ክስ እያቀረበች ነው። ቻይና የጦር መሣሪያ ለየትኛውም አካል አለመስጠቷን እና ከሩሲያ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ሊቆም ወይም ሊቋረጥ እንደማይገባ ገልጻለች ሲል የዘገበው አል ዐይን ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም