በሰሐራ በረሃ ለ50 ዓመታት ያልታየ ዶፍ ዝናብ ዘነበ

ደቡብ ምስራቅ ሞሮኮ በሚገኘው የሰሐራ በረሃ ላይ በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዶፍ ዝናብ መጣሉን የሳተላይት ምስሎች አስመለከቱ። ለሁለት ቀናት ተከታትሎ የዘነበው ከባድ ዝናብን ተከትሎ ነው በበረሃው ውሃ መከማቸት የጀመረው። የሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን አካልሎ የተዘረጋው የሰሐራ በረሃ በዓለማችን ረዥሙ እና ሞቃታማው በረሃ ነው።

“በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ዝናብ ከጣለ ቆይቷል። ምናልባትም ከ30 እና 50 ዓመታት በፊት ነው” ሲሉ የሞሮኮ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ሆሲን ዩዋቤብ ገልጸዋል። ደቡብ ምስራቅ ሞሮኮ በዓለማችን እጅግ ሞቃታማ ደረቅ ከሚባሉ ሥፍራዎች አንዱ ሲሆን ዝናብ የሚያጋጥመው በዓመታት አንድ ጊዜ ቢሆን ነው። ከሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ታፎናይት በ24 ሰዓታት ውስጥ 100 ሚሊ ሊትር ዝናብ ተመዝግቧል።

የአየር ትንበያ ሙያተኞች መሰል ዝናብን ‘ኤክስትራትሮፒካል ስቶርም’ ሲሉ ይጠሩታል። “አየሩ በርካታ እርጥበት ሲይዝ፤ ወደላይ መትነን ይጀምራል፤ ይህ ደግሞ ዝናብ ሊያስከትል ይችላል” ሲል የሞሮኮ አየር ትንበያ ኤጀንሲ ተናግሯል። የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ይፋ ያደረጋቸው ምስሎች እንደሚያሳዩት በኃይለኛው ዝናብ ምክንያት በዛጎራ እና ታታ ከተማዎች መካከል ያለው ሐይቅ ሞልቷል። ይህ ሐይቅ ላለፉት 50 ዓመታት ደርቆ ነበር የቆየው።

በዓለም ዙሪያ የዝናብ ጉዳይ እጅግ ተለዋዋጭ እየሆነ መጥቷል። “የሙቀት መጠን እየጨመረ ሲመጣ ሀይድሮሎጂካል ሳይክል የሚባለው ዑደት እየተፋጠነ ነው” ይላሉ የዓለም አየር ትንበያ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሴሌስት ሳውሎ። ጸሐፊዋ በሰጡት መግለጫ የዝናብ ነገር “በጣም ተለዋዋጭ እና መገመት የሚከብድ እየሆነ መጥቷል” ብለው “አሁን እየገጠመን ያለው ችግር ወይ ብዙ ዝናብ አሊያም በጣም ትንሽ እየሆነ መምጣቱ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

የዓለም ሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ አስከፊ የሚባሉ የአየር ፀባይ ለውጦች እየታዩ ነው። ሳይንቲስቶች በሚመጡት ዓመታት ተመሳሳይ ክስተት ሰሐራ በረሃ ላይ ልናይ እንችላለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You