የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች ወታደራዊ ሚስጥር እየሰረቁ መሆናቸውን አሜሪካ እና አጋሮቿ ገለጹ

የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች ወታደራዊ ሚስጥር እየሰረቁ መሆናቸውን አሜሪካ እና አጋሮቿ ገለጹ።

የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች እግድ ለተጣለበት የፒዮንግያንግ የኑክሌር ፕሮግራም ሊረዳ የሚችል መረጃ ለማግኘት ዓለምአቀፍ የስለላ ዘመቻ መክፈታቸውን አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ደቡብ ኮሪያ በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

በሳይበር ሴኩሪቲ ተመራማሪዎች ኤፒቲ 45 ተብለው የሚጠሩት መረጃ ጠላፊዎቹ፤ በአሜሪካ በፈረንጆቹ 2015 ማዕቀብ ከተጣለበት ሪኮኔሳንስ ጀነራል ቢሮ ከተባለው የሰሜን ኮሪያ የስለላ ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዳለው እንደሚታመን ተገልጿል።

ይህ የሳይበር ቡድን የታንክ ማምረቻዎችን፣ ባህር ሰርጓጆችን፣ የባህር ኃይል መርከቦችን፣ ተዋጊ ጀቶችን፣ ሚሳይሎችን እና የራዳር ሥርዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከያ እና የኢንጂነሪንግ ተቋማትን ኢላማ እያደረገ እና እየበረበረ እንደሚገኙ መግለጫው ጠቅሷል።

በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙት የናሽናል ኢሮኖቲክስ እና ስፔስ አስተዳደር (ናሳ)፣ በቴክሳስ የሚገኘው ራንዶልፍ ኤየር ፎርስ ቤዝ የመረጃ ጠለፋ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የፍትህ ሚኒስትር ከትናንት በስተያ አስታውቀዋል።

በፈረንጆቹ የካቲት 2022፣ ናሳን ኢላማ ያደረጉ የመረጃ ጠለፋዎች ማልዌር በመጠቀም የኮምፒውተር ሥርዓቱን ለሶስት ወራት ሳይበረብሩ እንዳልቀሩ የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ጥርጣሪ አለው።

መግለጫው “ቡድኑ እና የሳይበር ቴክኒኮች በመላው ዓለም በሚገኙ ተቋማት ላይ ስጋት ደቅነዋል” ብሏል።

በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መገለል ውስጥ ያለችው እና ቀደም ሲል ዴሞክራቲክ ፒፕልስ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮሪያ (ዲፒአርኬ) የመረጃ ጠላፊዎችን በመጠቀም ጥብቅ ወታደራዊ ሚስጥሮችን የመስረቅ ታሪክ አላት።

የመረጃ ጠላፊዎቹ ይህን ተግባራቸውን የሚረዳ ገንዘብ ለማግኘት የአሜሪካ ሆስፒታሎችን እና የጤና ተቋማትን የኮምፒውተር ሥርዓት በመስበር ገንዘብ በማጭበርበር መውሰዳቸውን ተገልጿል።

ኤፍቢአይ እና የፍትህ ሚኒስቴር 600 ሺህ ዶላር ቨርቹዋል ገንዘብ ያለውን አካውንት ጨምሮ የተወሰኑ የጠለፋ አካውንቶችን መያዛቸውን እና ለተጠቂዎቹ እንደሚመልሱ ተናግረዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You