በክብር ይቀበራል በሚል አንድ ዓመት የሞላው የታይዎ አስከሬን

የናይጄሪያን ሰንደቅ ዓላማ የቀረጸው ታይዎ አኪንኩንሚ ሕይወቱ ካለፈ አንድ ዓመት ቢሞላውም እስካሁን ሥርዓተ ቀብሩ አልተፈጸመም።

ታይዎ አኪንኩንሚ ሀገሪቱ አሁን ላይ እየተጠቀመችበት ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች በመምረጡ በመላው ሀገሪቱ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሰው በተወለደ በ87 ዓመቱ ከአንድ ዓመት በፊት ሕይወቱ ቢያልፍም የሀገሪቱ መንግሥት ተገቢውን ክብር በጠበቀ መልኩ በክብር ሥርዓተ ቀብሩ እንደሚፈጸም አሳውቆ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ቤተሰቦቹ የአኪንኩንሚን አስከሬን በቀን 2 ሺህ ኔይራ ወይም አንድ ዩሮ እየከፈሉ ካስቀመጡ አንድ ዓመት እንዳለፋቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

የሟች ልጅ የሆነው አኪንዉሚ አኪንኩንሚ የናይጄሪያ ባሕል ሚኒስቴር ደውለውልኝ ለአባቱ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በኢባዳን ግዛት እንደሚካሄድ ከነገሩት በኋላ ድጋሚ የትኛውም አካል አነጋግሮት እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡

የናይጄሪያ መንግሥት ግን ታይዎ አኪንኩንሚ በዚህ ሳምንት በኦዮ ግዛት ክብሩን በጠበቀ መልኩ ሥርዓተ ቀብሩ እንደሚፈጸም አስታውቋል፡፡

ታይዎ አኪንኩንሚ እ.አ.አ. በ1960 በእንግሊዝ ትምህርት ላይ እያለ ናይጄሪያ አዲስ ሰንደቅ ዓላማ ለመቅረጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቷን በጋዜጦች ለይ ካነበበ በኋላ ነበር የተወዳደረው፡፡

ናይጄሪያ በግብርና የታደለች ሀገር መሆኗን ለማሳየት አረንጓዴውን ቀለም እንዲሁም ነጩን ቀለም የናይጄሪያውያንን አንድነትና እኩልነት ለማንጸባረቅ በሚል እንዲሆን ለውድድር እንደላከውም አኪንኩንሚ በወቅቱ ተናግሮ ነበር፡፡

በወቅቱ ከመላው ዓለም ከሦስት ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች የሰንደቅ ዓላማ መወዳደሪያቸውን አስገብተው የነበረ ቢሆንም የአኪንኩንሚ አረንጓዴ እና ነጭ ቀለሞች ተወዳጅ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በናይጄሪያውያን ዘንድ “የሰንደቅ ዓላማው ሰው” የሚል ስያሜ ያለው ታይዎ ሀገሪቱ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበትን 50ኛ ዓመት ስታከብር ከምርጥ 50 የሀገሪቱ ዜጎች መካከል አንዱ ሆነው ብሔራዊ ጀግና ተብሎ ተመርጦ ነበር፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You