በቤጂንግ የቻይና አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የተመድ ዋና ጸሀፊን አንቶኒዎ ጉቴሬዝን ጨምሮ ከ50 በላይ የሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ፒንግ ባደረጉት የጉባዔው መክፈቻ ንግግር ቻይና እና አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምርጥ ግንኙነታቸውን እያጣጣሙ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ቻይና በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ትሰጣለች ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ውስጥም 25 ቢሊዮን ዶላሩ በብድር መልኩ ለአፍሪካ ሀገራት ይሰጣል የተባለ ሲሆን 11 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ ርዳታ እንዲሁም 10 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ሄደው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚደረግ ድጋፍ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ ለአንድ ሚሊዮን አፍሪካውያን የሥራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ የዓለማችን ቁጥር ሁለት ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና ከአፍሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሲሆን ለዚህ ጉባዔ ወደ ቤጂንግ ያቀኑ ሀገራት አዳንድ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምነቶችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
እስካሁንም ዛምቢያ ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ኬንያ እና ናይጀሪያ በርካታ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ከቻይና ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ታንዛኒያና ዛምቢያ የሚያስተሳስራቸውን የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ከቻይና በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ለመገንባት ሲፈራረሙ፣ ዚምባብዌ አቭካዶ ምርቶቿን ወደ ቻይና ገበያዎች መላክ የሚያስችላትን የንግድ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡
ናይጀሪያ ደግሞ የወደብ ልማት፣ ነጻ የንግድ ቀጣና እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ተፈራርማለች፡፡ ዛምቢያ የታዳሽ ሃይል ኢንቨስትመንት ስትፈራረም ኬንያ ደግሞ የግብርና ምርቶቿን ወደ ቻይና አብዝታ መላክ የሚያስችላትን ከመፈራረሟ ባለፈ የባቡር መስመር ግንባታ ስምምነት እንደተፈራረመች ተገልጿል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም