የእስራኤል ጦር ግብጽ ከፍልስጤም ከምትጋራው ድንበር እንደማይለቅ ኔታኒያሁ አረጋገጡ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የሀገራቸው ጦር ጋዛና ግብጽ ከሚጋሩት እና ስልታዊ ጠቀሜታ ካለው የፊላደልፊ ‘ኮሪደር’ እንደማይለቅ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእየሩሳሌም ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ወደፊት በሚኖር ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት ውስጥ በጋዛና ግብጽ ድንበር የእስራኤል ወታደሮችን ለማስፈር ሌላ አማራጭ ካለ “ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” ካሉ በኋላ “ግን ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ኔታኒያሁ በዚህ ነጻ የድንበር ቀጣና የመሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እና ታጋቾች ወደ ሌላ ሥፍራ እንዳይወሰዱ የእስራኤል ጦር ወታደሮች መቆየት ይኖርባቸዋል ሲሉ ተከራክረዋል።

እስራኤል ከፊላደልፊ ‘ኮሪደር’ ወታደሮቿን አላስወጣም ማለቷ የተጀመረውን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የማደናቀፍ ሙከራ ነው ሲል ሀማስ መቃወሙን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ጨምሮም እስራኤል ላይ ጫና የማሳደሪያ ጊዜው አሁን ነው ብሏል።

ያለፈው ረቡዕ መግለጫ የሰጡት ኔታኒያሁ ወደፊት ማንኛውም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚኖር ከሆነ በፊላደልፊ ኮሪደር በኩል “ምንም ዓይነት ክፍተት” የሚተው ሊሆን አይችልም ብለዋል።

“በጽሑፍ ወይም በቃል ሳይሆን መሬት ላይ በተግባር በዚያ ኮሪደር ላይ እየሆነ ያለውን ለመከላከል የሚያስችል ሌላ አማራጭ ካለ ለመቀበል ዝገጁ ነን” ያሉት ኔታኒያሁ “ይህ ሲሆን አይታየኝም። እሱ እስከሚሆን ደግሞ በዚያ እንቆያለን” ብለዋል።

ኔታኒያሁ ደጋግመው እያሳዩት ያለው ፍላጎት በደቡባዊ ጋዛ የሀገራቸው ጦር የመውጣት ‘ቅንጣት’ ፍላጎት እንደሌለው ማረጋገጫ የሰጠ ነው። በድንበሩ የእስራኤል ጦር መቆየትን አስፈላጊነት “ቀይ መስመር’ ሲሉ ገልጸውታል።

“ሰዎችን ይህ ውሳኔ (ከድንበሩ የእስራኤል ጦር መውጣት) ስምምነቱን ያኮላሸዋል ይላሉ። እኔ ደግሞ ይህ ከሆነ እኛን ያኮላሸናል እላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም

Recommended For You