ብሪታንያ ለእስራኤል ስትሸጣቸው ከነበሩ የጦር መሣሪያዎች መካከል የተወሰኑት ከሽያጭ ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ውሳኔ አሳልፋለች፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ለእስራኤል የምታቀርባቸው የጦር መሣሪያዎች የዓለም አቀፍ ሕግን ለመጣስ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ በሚል ነው፡፡
350 ከሚደርሱ የጦር መሣሪያ ዝርዝሮች ውስጥ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወይም እንዳይሸጡ የታገዱት የጦር መሳሪያዎች ቁጥር 30 እንደሚደርስ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ እንደተናገሩት የድሮን፣ የውጊያ ሄሊኮፕተሮች እና ጄቶች አካላት በክልከላው ውስጥ ተካተዋል፡፡
እስራኤል የጦር መሣሪያዎች ከምታስገባባቸው ሀገራት መካከል ከብሪታንያ የምታስገባው አንድ በመቶ ብቻ ቢሆንም በጋዛ ለምትፈጽማቸው የአየር ላይ ጥቃቶች ክልከላ የተላለፈባቸው የጦር መሣሪያዎች ወሳኝ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
እንግሊዝ የጦር መሣሪያዎቹ ዓለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን በማይጻረር መልኩ ጥቅም ላይ መዋላቸውን እስከምናረጋግጥ ድረስ ክለከላው ይጸናል ብላለች።
እ.አ.አ. ከ2019-2023 69 በመቶ የጦር መሣሪያ ግዢን የፈጸመችባት አሜሪካ ትልቋ የእስራኤል ጦር መሣሪያ አቅራቢ ናት፡፡ ብሪታንያ ከቴልአቪቭ በተጨማሪ ለቱርክ፣ ሳዑዲ ዐረቢያ እና ዩክሬን ጦር መሣሪያዎችን ትሸጣለች፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ብሪታንያ ለእሥራኤል ከምታቀርበው የጦር መሣሪያ ከ10 በመቶ ሽያጭ ያነሰ ክልከላ ማድረጓ “አስመሳይ የፖለቲካ ውሳኔ” ነው ብሎታል፡፡
የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ይህ ያልተጠና ውሳኔ ሃማስን ከማበረታት የዘለለ ሚና የሌለው “አሳፋሪ” ተግባር ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም እሥራኤል እገዳው ቢጣልባትም ሀማስን ማሸነፏ እና ጥቅሟን ማስከበሯ አይቀርም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም